ፓት ሃደን-የደቡባዊ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲው ሁለገብ ኢንተርፕርነር

የ Rhodes Scholar የሆነው ፓት የእንዲህ አይነት ሙያ ባለቤት ነው ብሎ ፓትን ባጭሩ መገላገል አይቻልም፡፡የሚሻለው ሙያውን አንድ ሁለት ብሎ መዘርዘር ነው፡፡እንዲያ ካላደረግን ፓትን በትክክል አንገልጸውም፡፡ስለዚህ እንዘርዝር፡፡

  1. ጠበቃ/ነገረ      ፈጅ
  2. ፕሮፌሽናል      የእግር ኳስ ተጨዋች
  3. ነጋዴ
  4. ጋዜጠኛ
  5. በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የአትሌቲክስ ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር ነው፡፡

አየርላንዳዊያን ቤተሰቦቹ ካፈሯቸው አምስት ልጆች አራተኛ ልጅ ሆኖ ኒውዮርክ አሜሪካ ውስጥ የተወለደው ፓት ለተለመው ግብ መሳካት የማይጋልበው የውጥን ሰረገላ እንደሌለ ሥራውን አይተው አጀብ ያሉ ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡

ፓት ለበርካታ ዓመታት ጋዜጣ አዟሪ የነበረ ሲሆን አስራ ስድስት አመት ሲሆነው በጫማ መሸጫ መደብር ውስጥ የሽያጭ ሰራተኛ ሆኖ ተቀጥሯል፡፡በኮሚሽን በሚሰራበት የጫማ መደብር ውስጥ ውጤታማ ስለነበር በአንድ ክረምት የሽያጭ ሰራኞች ቡድን መሪ ሆኖ ለመሥራት ችሏል፡፡

ያን ጊዜ በግርምት በማስታወስ ‘በዚያን ጊዜ አብረውኝ ይሰሩ የነበሩት ሰወች ሁሉ ከሃያ ዓመት በላይ በሆነ እድሜ ነበር የሚበልጡኝ፡፡ስለዚህ ከነዚህ የብዙ ዓመታት ልምድ ካላቸው ሰዎች ልቆ መገኘት ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር::’ ይላል ፓት ሃደን፡፡

ፓት የአበባ እቅፍ በመሥራት ለመሸጥ መሞከሩም አልቀረ፡፡እና በአንድ በዓል ላይ ለመሸጥ የሰራው የአበባ እቅፍ በገዥዎች ተቀባይነት በማጣቱ የተበሳጨው እልኸኛው ፓት ለመሸጥ ይዞ የነበረውን የአበባ እቅፍ ታቅፎ ወደ ሱቁ ለመመለስ ተገዷል፡፡

ፓት ወደ ሱቁ ተመልሶ ምን አደረገ?

‘ያ አጋጣሚ ነገሮችን ቀለል አድርጌ እንዳይ አደረገኝ፡፡አበቦቹንም እንደገና ይበልጥ በሚማርክ ሁናቴ አሰባጠርኳቸው፡፡ከዚያ በድጋሚ ወደ ገበያ ተሄደ፡፡’ ኢንተርፕርነር ማለት ስለሚጓዝበት መንገድና ዓላማ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው እንደሆነ በመግለጥ ለስኬታማነት ግን ውስጣዊ ተነሳሽነት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል፡፡ ‘ይሄ ተነሳሽነት ከሌለህ ሊገጥምህ የሚችለውን የሕይዎት ፈተና ማለፍ አትችልም፡፡ላንተ ስኬት ደግሞ ካንተ በላይ የሚያገባው ሰው እንደሌለ ተረዳ፡፡የሌሎችን ጣልቃ ገብነትና ድጋፍ ስትሻ በዓይነህሊናህ የሳልከው ህልም ከቁጥጥርህ ውጭ ሆኖ ከእጅህ ሊያመልጥ ይችላል፡፡እናም ህልምህን ራስህ ጠብቀው፡፡አለዚያ መሆን የማትፈልገውና ልትሆን የማትችለው ዓለም ውስጥ ስትዳክር ትኖራለህ፡፡’

ፓት ይሄን ቀስቃሽ የመለወጥ ኃይል የተጎናጸፈው ከእናቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡’በሕይዎት ሳለ የምታበረክተው አስተዋጽዖ መቃብርህ ላይ ቋሚ ምስክር ሃውልት ይሆንልሃል፡፡የሚለውን የእናቴን አባባል የሕይዎቴ መመሪያ አድርጌዋለሁ፡፡ከእናቴ የወረስኩት ጽናት ባይኖር ኖሮ ፈጽሞ ጎበዝ አትሌት አልሆንም ነበር፡፡በትምህርቴም ጎበዝ ባልሆንኩ ነበር፡፡በራስ ተነሳሽነት መሥራት ለውጥ እንደሚያስገኝ የተማርኩትም ከእናቴ ነው፡፡እናቴ ሁሌም አንደኛ እንድወጣ ትፈልግ ነበር፡፡በትምህርቴ፣በአትሌቲክስ ውድድር፣እንዲሁም የገና ስጦታ ካርዶችና ከረሚላዎችንም በመሸጥ ጭምር አንደኛ እንድሆን ትፈልግ ነበር፡፡’

የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ሳለ በየጊዜው እግር ኳስ የሚጫወተው ፓት ኋላ ላይ ኮሌጅ ከገባ በኋላ የኮሌጁ ኳስ ተጨዋች ለመሆን የተሰጠውን ከባድ ፈተና በከፍተኛ ውጤት ማለፍ በመቻሉ እግር ኳስ ተጨዋች የመሆን ህልሙ ሰምሮለታል፡፡  

‘መጀመሪያ ስትጀምረው ደስ ይላል፡፡ከዚያ መዝናኛህ ይሆናል፡፡ትቀጥልና በኳስ ፍቅር ትለከፍና ሱሰኛ ትሆናለህ፡፡ስኬት ይከተላል፡፡ሌላ ስኬት ያምርሃል፡፡ለእሱ ደግሞ ሌላ ጥረት’ ይልና በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሳለ ውጤታማ ውድድሮች ፊቱ ላይ የደስታ ስሜት እየተነበበ ትረካውን ይቀጥላል፡፡’ያኔ በእግር ኳሱ ለሁለት ጊዜያት ያህል ብሔራዊ ሻምፒዮና ለመሆን ችለናል፡፡ከዚያ በተጨማሪ በትምህርቴም ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቤ የአካዳሚክ ኦል አሜሪካን/Academic All-American ሽልማት ሁለቴ በማግኘት በ1975ዓ/ም መመረቅ ችያለሁ፡፡’

ለዓለም እግርኳስ ሊግ ለአንድ ዓመት ያህል ሲጫወት የቆየው ፓት ለሦስት ጊዜያት ያህል የምርጦች ምርጥ የሚባል ውድድር ውስጥ ተሳታፊ በመሆንም ግንባር ቀደም ነው፡፡በ1976 ዓ/ም ሎስ አንጀለስ ራምስ የተባለውን ቡድን የተቀላቀለ ሲሆን የሮድስ ስኮላርም ሆኖ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በመግባት በክረምትና በማታ ክፍለ ጊዜ ለአራት ዓመታት ተኩል ያህል ትምህርቱን ተከታትሎ ጠበቃ የመሆን ህልሙን ከግብ አድርሷል፡፡

በሎስ አንጀለስ ራምስ ውስጥ በሚጫወትበት ጊዜ ብዙ ቅስም የሚሰብሩ አጋጣሚዎችን በጽናት ያሳለፈው ፓት በተደጋጋሚ ጉዳት ደርሶበት ለሆስፒታል አልጋ ተዳርጓል፡፡ለመጨረሻ ጊዜ ሆስፒታል የገባው በ1981ዓ/ም ጉልበቱ ላይ የቀዶ ህክምና ለማድረግ ነበር፡፡እዚያ እያለ ዴንቨር ብሮንኮስ የተባለ ቡድንን በሽያጭ ለመቀላቀል እያሰበ ሳለ አንድ ስልክ ይደወላል፡፡ስልኩ የተደወለው የ ሲቢኤስ ደቀመዝሙር ከነበረ አንድ ሰው ሲሆን የኮሌጅ ውድድሮች ዘጋቢ ጋዜጠኛ ይሆን እንደሁ ለመጠየቅ ነበር-ፓትን፡፡ፈጣኑ ፓት ይሄን ለምን አዲሱ ግቤ አላደርገውም በማለት ጥያቄውን ይቀበልና ሥራውን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ይጀምራል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ፓት በዩኒቨርስቲ ተጫዋች በነበረበት ጊዜ በደንብ ለሚያውቀው የኖትሪ ዳም እግር ኳስ ቡድን ዘጋቢ ጋዜጠኛ ሆኖ ለሃያ ስድስት ዓመታት አብሮት የዘለቀው፡፡

‘እናቴ ኖትሪ ዳምን እንድቀላቀል አጥብቃ ትሻ ነበር፡፡ለእኔ፣ ለኖትሪ ዳም ቡድን መሥራት ማለት ለእናቴ መታሰቢያ ግብር በየቀኑ ያበላሁ ያኽል ይሰማኛል፡፡በካምፓስ ሳለሁ እንኳ ግሮቶ እየሄድኩ ዘወትር ሻማ አበራላት ነበር’ የሚለው ፓት ከዚህ ሥራው በተጨማሪ በአንድ የግል ተቋም ውስጥ ለኢንትርፕርነሮች ስልጠና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን በ2010 ዓ/ም የደቡባዊ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በሰጠው ከፍተኛ የኃላፊነት ሥራ ተጠምዶ ስላለ ለጊዜው ያን ተወት አርጎታል፡፡ፓት የተሰጠውን ኃላፊነት ዩኒቨርስቲው  በአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ የነበረውን ስም ለመመለስ በማለም ቀን ተሌት እየሰራ  ሲሆን በብሔራዊ የኮሌጆች ስፖርት ማህበር የተጣለበትን በርካታ ማዕቀብም አንድባንድ ለማስነሳት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ‘ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ እንፈልጋለን፡፡ያን ታሪካችንንም በድጋሚ ለማስመለስ አንተኛም፡፡’ ፓት በቁጭት ነው ይሄን የሚለው፡፡

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.