1776፡ አዳም ስሚዝ እና አሜሪካ!

hahahእኤአ መጋቢት 9 ቀን 1776ዓ/ም አዳም ስሚዝ ለዘመናዊ የኢኮኖሚ ሳይንስ መሰረት የጣለውን መፅሃፍ ሲያሳትም መፅሃፉን አንብበው ካንቆለጳጰሱት መሃል ቶማስ ጀፈርስን አንዱ ነው። የአሜሪካ መስራች እና ኋላም ፕሬዝዳንት የነበረው ጀፈርሰን ለአዲሲቷ ሃገር የሚሆኑ አዳዲስ እና ጥሩ ጥሩ ሃሳቦችን ይሰበስብ ነበር። እነዚህን ሃሳቦችም እራሱ ባረቀቀው የአሜሪካ ህገመንግስት ውስጥ አካቷቸዋል። ከነዚህ መሃል የአሜሪካ መሰረቶች ተብለው የሚታወቁት “ላይፍ፣ሊበርቲ እና ዘ ፐርሱይት ኦፍ ሃፒነስ” የአሜሪካ ህገመንግስት የማዕዘን ዲንጋይ ናቸው።

በዚያው ዓመት ሃምሌ 4 ቀን 1776ዓ/ም አሜሪካዊያን ከእንግሊዝ ጋር ያደረጉትን መራራ የነፃነት ትግል ድል አድርገው ነፃነታቸውን ያወጁበት ቀን ነበር። በ1776ዓ/ም ስኮቲሾች ከፍ ዝቅ የሚሉለትን ታላቁ ፈላስፋቸውን ዴቪድ ሂዩም በሞት ቢነጠቁም ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ መፅሃፉን ያነበበለትን አዳም ስሚዝ “እጅግ ድንቅ ተፈጥሮ፣ልዩ ስራ” ብሎ ስላወደሰው እሱን ተክቶ በቀላሉ በስኮትላንዳዊያን ልብ ነገሰ። ጆርጅ ዋሽንግተን የአዲሲቷ ሃገር አሜሪካ አባት ሲባል አዳም ስሚዝም ወዲህ የአዲስ ሳይንስ አባት ተባለ።

የአዳም ስሚዝ ሃሳቦች የፈጠሩት የአስተሳሰብ ለውጥ እንግሊዝ በነገስታቷ  እና ከነገስታቷ ጋር በተቆራኘችው ቤተክርስቲያን ላይ የሕግ ልጓም ታበጅ ዘንድ አስገደዳት። በአሜሪካ ሕገመንግስት ውስጥ እስከመካተት የደረሱት የአዳም ስሚዝ ሃሳቦች ለወትሮው ከእንግሊዝ ጋር በማይስማሙት በፈረንሳይ ሊቃውንቶችም ዘንድ ተቀባይነትን አገኙና እጅግ ተስፋፉ። በ1800ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ምግብ፣ልብስ እና መጠለያ ቤት በግል ጥረታቸው ማግኘት እንደሚችሉ በተግባር መታየት ጀመረ። ከዚያ በፊት በነገስታት ፍቃድ እንጅ በጥረት ወደፊት መራመድ ክልክል ነበር።ሻይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቅንጦት እና ከመኳንንት መጠጥነት ወጣችና የሰራተኛ ወግ ማፍኪያ ተራ መጠጥ ሆነች።

የአዳም ስሚዝ ሃሳቦችን የተገበሩት ሃገራት አጀብ ድንቅ በሚያሰኝ ሁኔታ የአዳዲስ ፈጠራዎች እና ቴክኖሎጅ ባለቤቶች መሆን ጀመሩ። ይህም ከቻይናዊያን  እና ከአረቦች ኋላ ሲንቀረፈፉ የነበሩትን ምዕራባዊያንን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀድመው እንዲታዩ በሩን ከፈተላቸው። በእንፋሎት የሚሰራ ሞተር፣ አውቶማቲክ የጨርቅ መስሪያ ማሽን ፣ የመገጣጠሚያ ማሽኖት ፣ ሲምፎኒ ኦርኬስትራ፣ በእንፋሎት የሚሰራ የሕትመት ማሽን ፣ በዝቅተኛ ዋጋ ሊገኝ የሚችል ወረቀት ፣ ብረትና መስታወት ፣ የመፃፍና የማንበብ ዕውቀት መስፋፋት ፣ የዘመናዊ ዩኒቨርስቲ መስፋፋት … ወዘተርፈ።

በ1860ዓ/ም እንግሊዝ የአለምን ንግድ 23በመቶ ያህል ብቻወን ታሾር ነበር። ሁለተኛዋ ፈረንሳይ ደግሞ 11በመቶ የዓለም ንግድን ስታጋብስ የነበር ሲሆን አሜሪካ ሶስተኛ ሆና 9በመቶውን ተቋድሳለች። በ1870ዓ/ም እንግሊዝ በፋብሪካ ውጤቶች እና ምርት 31.8 በመቶ የነበረ ሲሆን ሁለተኛ የነበረችው አሜሪካ ደግሞ 23.3በመቶ፣ ጀርመን 13.2በመቶ እንዲሁም ፈረንሳይ 10.3በመቶ ድርሻ ነበራቸው። በ1880 እንግሊዝ 6.5ሚሊዮን ቶን ሸቀጦችን እና ምርቶችን ለዓለም ገበያ ያቀረበች ሲሆን በወቅቱ ተቀራራቢ ተፎካካሪዋ አሜሪካ ደግሞ1.2 ሚሊዮን ቶን ሸቀጥ ለገበያ አቅርባለች። ከእንግሊዝ ነፃ ከወጡ በኋላ የሚሲሲፒ ሸለቆን ምርታማ ያደረጉት፣በትራስፖርት በኩል ሰፊዋን ሃገር በባቡር ሃዲድ ግንባታ ከዳድ እዳር ያገናኙት፣ ዜጎች በሰላማዊ ኑሮአቸው በህግ አግባብ እና በፍቃዳቸው በሚያደርጉት ግንኙነት ውስጥ መንግስት ጣልቃ እንዳይገባ በሕግ ልጓም ያበጁለት፣ በዘመናዊ ጥበብ ባሸበረቁ ህንፃዎቿ እና ነፃነት ባላቸው ሰዎች በሚፈለፈሉ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች  ብዛት ለእንግሊዛዊያኑ ሳይቀር ትንግርት የሆኑት አሜሪካዊያን በ20ኛው ክ/ዘመን መግቢያ ላይ ሃያልነቱን ከእንግሊዝ ተረከቡ።እንግሊዛዊያን አዝማናት ረግጠው የገዟት ሃገር ከመቶ ዓመታት ባነሰ የነፃነት ጊዜ የዓለም ልዕለ ሃያል መሆኑ ማመን ቢያቅታቸውም የሚታይ የሚዳሰስ ሃቅ በመሆኑ ሊክዱት አልተቻላቸውም።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.