የንብረት ባለቤትነት መብት

የንብረት ባለቤትነት መብት እንደ ንብረቱ ዓይነትና ባህሪ በግለሰቦች፣በድርጅቶች፣በመንግስት ወይም በሌላ ነገር ስያሜ ወይም በአካባቢ ስም ሊያዝ ይችላል። በግለሰብ በባለቤትነት ከሚያዙ ንብረቶች መካከል ቤት፣መሬት፣መኪና፣የአይምሮ የፈጠራ ውጤቶች ወዘተ ይገኙበታል።በድርጅት ከሚያዙት ውስጥ አክሲዮን ማህበሮችና ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ።ለምሳሌ አዋሽ ባንክ የአዋሽ ባንክ አክሲዮን ማህበር ባለንብረት ነው።በመንግስት በባለቤትነት ሊይዛቸው ከሚችሉት ንብረቶች መካከል ብሄራዊ ፓርኮች የሚገኙበት መሬት፣የህዝብ ትምህርት ቤቶች የተገነቡበት መሬት ለአብነት ይጠቀሳሉ። መሬቱ እንጅ ብሄራዊ ፓርኩም ሆነ የህዝብ ት/ቤቱ የመንግስት ንብረት አይደሉም። በሆነ ነገር ስያሜ ወይም በአካባቢ ስም  በባለቤትነት ከሚያዙ ንብረቶች መካከል ዓለም ዓቀፍ የውሃ ክልሎች፣ ዓለም ዓቀፍ የአየር ክልሎች፣ዓለም ዓቀፍ የህዋ ጣቢያ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።

እንደሚታወቀው ንብረትን ማሻሻል፣መጠበቅ እና መንከባከብ ጊዜ እና ገንዘብ ይጠይቃል።ሰዎች የንብረቶቻቸው ባለቤት መሆናቸው ካልተረጋገጠ በቀር መሬታቸውን፣አካባቢያቸውን፣መኪናቸውን ወዘተ ከጉዳት ለመጠበቅ እና በእንክብካቤ ለመያዝ ገንዘባቸውን እና ጊዜያቸውን የሚያጠፉበት ምክንያት የላቸውም። እነዚህን ንብረቶች ለመንከባከብ የእኔ ማለት የሚችሉበት ስርዓት እና ከዚያ የሚመነጨው ተነሳሽነት የግድ ያስፈልጋል።አንድ ሰው የመኪናውን ዘይት በወቅቱ የሚቀይረው እና በየጊዜው መኪናውን ለባለሙያ የሚያስመረምረው የመኪናው ደረጃ  በተሻለ ይዘት ለማቆየት እና ምናልባትም ወደፊት መሸጥ ቢፈልግ ጥሩ ዋጋ እንዲያወጣለት በማሰብ ነው። ይህን የሚያደርገው ማንም አስገድዶት ሳይሆን ንብረቱን በመንከባከቡ ተጠቃሚው ራሱ ስለሆነ ነው።ንብረቱን ባይንከባከብም የሚጎዳው ራሱ ነው። የባለቤትነት መብት የት ድረስ እንደሆነ ይበልጥ ለማሳየት አንድ መዶሻ ያለው ሰው ስለሚኖረው መብት እና መውሰድ ስለሚገባው ሃላፊነት እንዲህ ልግለጥ።በህግ የባለቤትነት መብት በተከበረበት ሃገር ይህ ባለ መዶሻ ሰው መዶሻውን መጠቀም አለመጠቀም መብቱ ነው።ለሌሎች ማከራየት፣መሸጥ ፣መስጠት ወይም ማውረስ የሚከለክለው የለም።መዶሻውን ከሌባ ወይም ያለፍቃዱ ሊወስዱበት ከሚቃጡ ሰዎችም መከላከል ህጉ ይፈቅድለታል። ይህ ሰው መዶሻውን በፈለገው መንገድ ጥቅም ላይ የማዋል መብት አለው። ይህ መብቱ ግን የሌሎችን መብት ያለመንካት ሃላፊነትን ይጨምራል። ለምሳሌ መዶሻውን ወደ ኮምፒውተሬ ቢወረውር እኔ ለኮምፒውተሬ ያለኝን የባለቤትነት መብት ተዳፈረ ማለት ነው። የሰው መብት የሚጥስ በህግ ይቀጣል። ከላይ ለማብራራት የሞከርኩት የመዶሻ የባለቤትነት መብት ለሌሎች የንብረት ዓይነቶች ሁሉ የሚሰራ ነው።

የንብረት ባለቤትነት መብት አንዱ እና ዋናው የኢኮኖሚ ነጻነት ምሰሶ ሲሆን ማህበረሰብን በማስተሳሰር ረገድ እንደ ሙጫ ሆኖ ያገለግላል። ለምሳሌ የአንድ የአምልኮ ስፍራ የባለቤትነት መብት የአማኞቹ ካልሆነ፣የአምልኮ ነጻነታቸው በሌላ አካል ቁጥጥር ስር ይወድቃል።ፕሬስ በግል ባለቤትነት ካልተያዘ በቀር ስለፕሬስ ነጻነት ማውራት ‘ወሬ’ ብቻ ይሆናል።መንግስት የንብረት ሁሉ ተቆጣጣሪ ከሆነ የመናገር፣የመጻፍ ወዘተ ነጻነት የግለሰብ መብቶች መሆናቸው ይቀርና የመንግስት ንብረቶች ይሆናሉ።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.