የዜጎችን አስተሳሰብ መለወጥ የቻለ የዓላማ ጽናት እና ምግባር

 

ዊሊያም ዊልበርፎርስ (William Wilberforce)

ዊሊያም ዊልበርፎርስ (William Wilberforce)

በመላው የእንግሊዝ ግዛቶች ላይ የነበረውን የባርነት ስርዓት እንዲያከትም ከማንኛውም ግለሰብ በላይ  ያደረገውን የዬርክሻየሩን ሰውዬ ዊሊያም ዊልበርፎርስን ይተዋወቁት፡፡ “ተኣምራዊ ሞገስ”(The Amazing Grace) በሚል ርእስ ኤሪክ ሜታክሳል በጻፈው ድንቅ የግል ህይወት ታሪክ እና በተመሳሳይ ርዕስ በተሰራ ፊልም ታሪኩ ናኝቷል-ዊሊያም ዊልበርፎርስ!

እኤአ በ1759ዓ/ም የተወለደው ዊሊያም አጭር እና ቀጭን ተክለ ሰውነቱ በራዕዩ ሃያልነት ፣ በማራኪ አነጋገሩ እና በማይቀለበስ የዓላማ ጽናቱ ተኣምራዊ ሞገስን የተላበሰ ነው። ዊሊያም እኤአ በ1780ዓ/ም በሃያ አንድ ዓመት እድሜው ተመርጦ ለፓርላማ በመግባት ከአሜሪካ ጋር የሚደረገውን ጦርነት በማያሻሙ ቃላት ካኔያዊ፣ ደም አፍሳሽና ተገቢነት የሌለው” የሚል ስያሜ በመስጠት ተቃውሞውን በይፋ አሰማ፡፡ ዌልበርፎርስ የተሰበሰበ አትኩሮት ሳይኖረው ካንድ ሐሳብ ወደ ሌላ ሐሳብ ሲዘልል እና ሲባዝን ከቆየ በኋላ በስርዓት የለሹ ድብቅ እና ኋላም በይፋ ዓለም ላይ በሰፊው በተስፋፋው የባርያ ንግድ ላይ ማመጽ እንደሚገባው እና ይሄው የባሪያ ንግድ ሥርዓት እንዲወገድ ቁርጠኛ ሆኖ ለመስራት በወርሃ ጥቅምት እኤአ 1787 ዓ/ም ወሰነ፡፡

በ1700 ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ የባርያ ንግድን የማስወገድ  እንቅስቃሴ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የባሪያ ንግድ ለእንግሊዝ የባህር ኃይል እና የንግድ ስራ ስኬት በስፋት እንደዋነኛ አውታር የሚታይ ትልቅ ቢዝነስ ነበር፡፡ የባርያ ንግድ ለእንግሊዝ ሰፊ ፖሊቲካዊ ድጋፍ እንዲሁም በየስፍራው የተስፋፋን (በተለይም በዘረኝነት አራማጆች በኩል ያለውን) ምሁራዊ ተቀባይነት እንድታጣጥም አስችሏታል፡፡ ዊሊያም በበሮ ላይ የሚካሔደው የንግድ እና በመጨርሻም ራሱ ባርነት የሚያበቃበትን አጀንዳ ከመንደፉ በፊት ለሰባ አምስት ዓመታት ያህል እንግሊዝ የምትይዛቸውን አፍሪካውያኖች በአብዛኛው በስፔን ቅኝ ግዛቶች ውስጥ ስትሸጣቸው ኑራለች፡፡ ንግዱ ለእንግሊዝ የባርያ ነጋዴዎች የገቢ ምንጭ ነገር ግን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን ሰለባዎቹ እንደምህረት የለሽ የአውሬዎች ድርጊት የሚቆጠር ነበር።

አንድን ሰው ሌላው ሰው እንደእቃ በባለቤትነት መያዝ ኢሰብኣዊነት መሆኑን የሚያስተጋቡ ድርጅቶች ከመፍጠር እስከ ድጋፍ ማሰባሰብ ዘልቆ የገባው ዊሊያም በዘረኛ እንግሊዛዊያን እንደ ከሓዲ የመንጋ አመጸኞች መሪ ተወገዘ ፤ ተፌዘበትም፡፡ የተያያዘው ዓለማም ለሕይወቱ ስጋት ውስጥ መግባት ምክንያት ሆነው፡፡ይደርስበት የነበረው ተስፋ አስቆራጭ ድርጊትን አስመልክቶ በአንድ ወቅት ለተከታዮቹ ሲናገር “ትግላችን የጸና ይሆን ዘንድ ጩኸታችንን መቀጠል አለብን ብሏል፡፡

የባርያ ንግድ ራሱ በሕግ እንዲታገድ ከመደርጉ በፊት ተጨማሪ አስራ ስምንት ዓመታትን እንደሚወስድ ሳያውቅ ዊልበርፎርስ በ እንግሊዝ ፓርላማ የመጀመሪያውን ‘የባርነት ይወገድ’ ንግግሩን ለማሰማት ተነሳ፡፡ በየዓመቱ ባርነትን ለማስወገድ መፍትሔ ይሆናል ያለውን እቅድም ማቅረብ ተያያዘ፡፡ ነገር ግን በየዓመቱ አንዲትም ለውጥ ሊከሰት አልቻለም፡፡ የእርሱን ዓላማ የሚቃወሙ ቡድኖች ወሳኝ በሆነ የድምጽ መስጫ ጊዜ ድምጽ ሰጭዎች ቲያትር እንዲመለከቱ የነጻ የመግቢያ ቲኬቶችን ያድላሉ።ይህ ደግሞ የቅርብ አጋሮቹ የሆኑ ሰዎችን ሳይቀር እንዲሸሹት ምክንያት ሆኗል።

የእሱ ደጋፊዎች በነጻ ቲያትር በሚያዩበት ወቅት ተቃዋሚዎቹ ፓርላማ ውስጥ የእሱን ሃሳብ በመቃወም ድምጽ ይሰጣሉ።ከሽንፈቱም በኋላ እኤአ በ1805ዓ/ም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዊሊያም ትግሉን ያቆም ዘንድ በፓርላማው ጸሐፊ ተመከረ፡፡ በማይሞት እና ተስፋን በሰነቀ ንግግሩ ምላሽ ሲሰጥም “ዓላማዬን ከግብ እንደሚደርስ ተስፋ አደረጋለሁበማለት የቆመለትን ዓላማ በድንበር የማይገደብ እንዲሁም በጥቅም የማይበገር የምግባር ጉዳይ መሆኑን አሳየ።

በእርግጥም በአንድ ወቅት ከቶውንም የማይቻል ሕልም መስሎ ይታይ የነበረው ጉዳይ እኤአ በ 1807ዓ/ም እውን ሆነ፡፡ በበላይነት የፓርላማውን ተቀባይነት በማግኘት ‘የባሪያ ንግድ ይወገድ!’  የሚለው የዊሊያም ትግል ድል ተቀናጀ፡፡ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ዴቪድ ሾጋን ይህንን ክስተት ሲዘግብ “የሕግ ጉዳዮች ዋና ሹም ሰር ሳሙኤል ሮሚሊ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው የዊሊያምን የትግል ጽናት ሲያወድሱ ምክር ቤቱ በደስታ ጩኸት ተናወጠ፡፡ ዊሊያም ዊልበርፎርስ በስሜት ከመዋጡ የተነሳ በተቀመጠበት እጆቹን በጭንቅላቱ ላይ አድርጎ  ዕንባውን በጉንጩ ላይ ቁልቁል አፈሰሰ፡፡” ብሏል፡፡

የባሮች ሽያጭ በእንዲህ ሁኔታ በህግ ቢከለከልም ባርነት ራሱ እንዲያከትም ማድረግ ግን ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍል ጉዳይ ሆኖ ቆየ፡፡ ዊሊያም የሩብ ክፍሉ ዘመን ከሚሆነው የፓርላማ አገልግሎቱ በእኤአ 1825ዓ/ም ከተሰናበተ በኋላም ዓላማውን ከግብ ለማድረግ ለተጨማሪ ሃያ ስድስት ዓመታት ሰራ፡፡ እንግሊዝ ባሮችን በባለቤትነት ለያዙ ባለሐብቶች ማካካሻ በመስጠት በሰላማዊ አካሔድ ባሮችን ነፃ የማውጣት ውሳኔ በሕግ በማጽደቅ  የባሮችን ሰንሰለት በመፍታት ከዓለም ቀዳሚ እና ዋነኛ አገር ሆነች-እኤአ ሐምሌ 26 ቀን 1833ዓ/ም፡፡ ዊሊያም ለ51 ዓመታት ያህል የጤና ወታወክን ፣ ከባልደረቦቹ የደረሰበትን ተስፋ አስቆራጭ የለበጣ ሳቅን እና ለመቁጠር አታካች የሆኑ ሸንፈቶችን ጨምሮ ያጋጠሙትን ሌሎች ዕንቅፋቶችን ሁሉ አንድ በአንድ በማለፍ በጽናት ዘለቆ የትግሉን ፍሬ ለማየት በቃ፡፡  ምንኛ ድንቅ የጽናት ሞዴል ማለት ይህ ነው! ዊሊያም በየትኛውም የክብር መመዘኛ ፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነውን የምግባር ደረጃ ጠብቋል፡፡ የላቀ ምግባር ባለቤት መሆኑ ለቆመለት ዓላማ እንደ ጠንካራ መግነጢሳዊ ኃይል ሊጠቀምበት ችሏል። በውጣውረድ በተሞላ የ51 ዓመታት ትግል ህልሙን ዕውን ማድረግ በመቻሉም በመላው እንግሊዝ ‘ጀግና!’ ተባለ።ለስራው ምስክር ይሆኑ ዘንድም በበርካታ የእንግሊዝ ግዛቶች ሃውልት ቆሞለታል፤መንገድ በስሙ ተሰይሞለታል እንዲሁም በርካታ መታሰቢያዎች ተሰርተውለታል።  እኤአ ሐምሌ 26 ቀን 1833ዓ/ም  ባሮች ከሰንሰለታቸው ተፈተው ሲለቀቁ  በአይኑ ለማየት የቻለው ዊሊያም ዊልበርፎርስ ይህ በሆነ ከሶስት ቀናት በኋላ ይህችን ዓላም በሞት ተሰናበታት፡፡ እርሱና ሐቀኛ አጋሮቹም የእንግሊዝ ሕዝብን በተለይም ጥቁርን እንደ ሰው የማያዩትን ዘረኛ ዜጎችን  ሕሊና መለወጥ ቻሉ።

ከዊሊያም ዊልበርፎርስ ሕይወት ያገኘናቸውን  ትምህርቶች በአጭሩ መግለጽ ቢያስፈልገን እነሆ ይህን እናገኛለን፡፡ የተቀደሰ ዓላማ ሁሌም መንፈስ እንደሚያበረታ እና  ኃይል እንደሚሰጥ ያስተምራል። ከነደፉት የትኛውም ዓላማ ወደ ኋላ ማፈግፈግን መፍቀድ እንደማይገባ ያስረዳል። ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ወደፊት ማሄድ እንደሚገባን ይናገራል፡፡ ሁሉንም ምግባር በተሞላው አካሄድ እና በተገቢው መንገድ እንድንፈጽም ይመክራል። ሌሎችም ለዓላማችን መሳካት ከጎናችን እንዲቆሙ መቀስቀስ እና ማግባባት እንዳለብን ያብራራል።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.