ታታሪነት እና ስኬት

IMG_0970_editedፓትሪክ ፓስካል ይባላል፡፡በትውልድ አገሩ አየርላንድ ቢዝነስ የጀመረው ገና በአምስት አመቱ ሲሆን ከሎሚ የሚሰራ ጣፋጭ መጠጥ መንገድ ዳር ቆሞ ይሸጥ ነበር፡፡በ11 ዓመቱ ደግሞ ከተለያዩ ጋዜጣዎች ላይ ዜናዎችን እና እሱ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል የሚላቸውን መጣጥፎች በድጋሚ በእጁ ጽፎ ፎቶኮፒ በማድረግ እያባዛ ይቸበችብ ነበር።

“በልጅነትህ የምትቀርጸው ምናብ ሁሉ ላይሰራ ይችላል፡፡ይሄንን እኔ ላረጋግጥልህ እችላለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ዶሮ ማርባት ነበር ምኞቴ እናም ማርባት ጀመርኩ። ወደ ሁለት መቶ ሃያ ዶሮዎች የነበሩኝ ሲሆን እንቁላል በመሸጥ የሚታወቅም መጠነኛ ሱቅ ነበረኝ፡፡ የሚገርመው ድሮ የሎሚ ጭማቂ ስሸጥ እንዴት እንደሚሰራ እንኳ አላውቅም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እንቁላል ለመሸጥ ወሳኝ የሆኑትን የበዓል ቀናቶች ለምሳሌ ገና እና ፋሲካ መቼ እንደሚውሉ ማወቅ አቀበት ሆነብኝ፡፡ስለዚህ በነዚህ ቀናቶች ሣይቀር ባለማወቅ እረፍት እወስድ ነበር፡፡እናም የሚገባኝን አገኘሁ፡፡ከሰርኩ! በመቀጠልም በግና ፍየል ማርባት ጀመርኩ፡፡ ብዙም ሣልገፋበት በድጋሚ ከሰርኩ፡፡” የሚለው ፓትሪክ ይህን ሁሉ ሲያደርግ የነበረው ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ ነበር፡፡

“አንድ ቀን ጧት ቁርስ በልተን ከጨረስን በኃላ አባቴ ከፊቱ የተቀመጠውን የአክስዮኖችን ዝርዝር እና ስለ ድርጅቶቹ ሁኔታ የሚተነትን ጋዜጣ አንስቶ ማንበብ ጀመረ፡፡ከዚያም አክሲዮን ስለሚባል ነገር ምንነት፣የድርጅቶችን አመታዊ ሪፖርት እንዲሁም ትርፍና ኪሳራ እንዴት እንደሚነበብ በጋዜጣው ላይ ታትሞ ከወጣው ሰንጠረዥ አሳየኝ፡፡ የአባቴ ስጦታ ትልቅ ነበር፡፡በርግጥ አባቴ ከዚህም በላይ በራስ መተማመን እንዲኖረኝ እና ራሴን ማመን እንድችልም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡” የሚለው ፓትሪክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሳይጨርስ የአክስዮን ገበያዎችን የግብይት ሥርዓት ሂደት ጠንቅቆ ተረድቷል።

ፓትሪክ ስለ ኢንተርፕርነሮች እንዲህ ይላል “ይገርምሃል! ስለኢንተርፕርነሮች በማስብበት ጊዜ አሳ አስጋሪዎች ትዝ ይሉኛል።ታንኳቸዉ ላይ ተቀምጠው በውሃው ላይ እየሄዱ መጀመሪያ መረባቸዉን ምናልባት በስተቀኝ በኩል ይጥሉታል፡፡አሳ ካላገኙ ደግሞ መረባቸውን በስተግራ በኩል ይወረውራሉ፡፡ ኢንተርፕርነር ማለት ግን የእነዚህ አይነት ሰዎች ተቃራኒ ነው፡፡ ኢንተርፕርነር አሳ ለማጥመድ ታንኳው ላይ ከመውጣቱ በፊት አሳዎቹ በየትኛው አቅጣጫ እንዳሉ ለይቶ ካወቀ በኃላ ነው መረቡን ከታንኳው የሚጭነው፡፡ልማዳዊ አሰራር ኢንተርፕርነር በሆነ ሰዉ ዘንድ ቦታ የለዉም፡፡” በማለት “ኢንተርፕርነር መሆን ከፈለግህ እንዲህ ያሉ ልማዶችን ምናልባት ከልማድ በላይ ሆነው ተቀባይነት ያላቸው አሰራሮችን ጥሰህ እለፍ” ሲል ይመክራል።

ፓትሪክ የሁለተኛ ዓመት የኮሌጅ ትምህርቱን አቋርጦ ነበር የአክሲዮን ሽያጭ እና መገበያያ ማዕከል ውስጥ ረዳት ሰራተኛ ሆኖ የተቀጠረው። በመቀጠልም ዋና የአክሲዮን አገበያይ ስፔሻሊስት በመሆን ለአስር ያህል ዓመታት ሰርቷል፡፡በ1970 ዓ/ም የራሱን ፓትሪክ ፓስካል አሶሽየትስ የተባለ ኩባንያ የኢንቨስትመንት ኩባንያ ያቋቋመው ፓትሪክ በ1997 ዓ/ም የቼልሲ ማኔጅመንት ኩባንያ የኢንቨስትመንት ኮሚቴ አባል እንዲሆን ያደረገለትን ግብዣ ተቀብሎ እስከ 2002ዓ/ም ሲሰራ ቆይቶ በዚሁ ዓመት ድርጅቱን የፖርቲፎሊዮ ኢንቨስትመንት ከሚያስተዳድረው ግዙፉ የቼልሲ ማኔጅመንት ኩባንያ ጋር አዋህዶታል፡፡

ይህን ሁሉ ስኬታማ ስራ መስራት የቻለዉ ፓትሪክ ጊዜው መጣና ለብዙ ጊዜ አቋርጦት የነበረውን ትምህርቱን ለመቀጠል በመወሰኑ በ1996ዓ/ም ወደቀድሞው ት/ቤቱ አመራ፡፡ በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ስር የሚገኘው የማርሻል ቢዝነስ ት/ቤት የፓትሪክን ማመልከቻ የተቀበለው በስራ ላይ ያገኘውን ስኬት አብራርቶ ካስረዳ በኋላ ነዉ፡፡ለአስር ተከታታይ ዓመታት በትርፍ ሰዓቱ እየተማረ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ፓትሪክ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ የቼልሲ ማኔጅመንት ኩባንያ ፕሬዚዳንት ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

“ኢንተርፕነር ለመሆን ተነሳሽነት ሊኖርህ ይገባል።” የሚለው ፓትሪክ “ከዚህ በተጨማሪ መጥፎ አጋጣሚዎችን ለመጋፈጥ እንድትችል በራስ መተማመን ሊኖርህ ይገባል፡፡ እወድቃለሁ ብለህ እንዳትፈራ! መንገዱ አልጋ ባልጋ ባይሆንም የምሄድበት እደርሳለሁ። በዚህ ዉስጥ ውድቀት ይኖራል፡፡ግን ምንም ቢከሰት ወደፊት መሄዴን አላቋርጥም ብለህ ለራስህ  ንገረው፡፡” በማለት ይመክራል፡፡

የሁለተኛ ዓመት የኮሌጅ ትምህርቱን አቋርጦ የአክሲዮን መገበያያ ተቋም ዉስጥ ሲሰራ በነበረበት ወቅት አንድ የስራ ባልደረባዉ ጠርቶ “ይህ ስራ ለአንተ አይሆንም” እንዳለው የሚያስታውሰው ፓትሪክ “በርግጥ በሰዓቱ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላወቅሁም፤ ቢሆንም ግን የጓደኛየን ምክር ለመቀበል ዝግጁ አልነበርኩም” ብሏል።  “ኢንተርፕርነሮች ሰውን ሲመክሩ እንደኔ ጓደኛ በሰዉ ሞራል እየተጫወቱ እንዳልሆነም እርግጠኛ ነኝ፡፡” ሲልም ተናግሯል።

“በስራ ላይ የሚገጥም እክልና አንዳንድ አስቸጋሪ ስራዎች ሰዎችን ከህልማቸዉ ሲያርቁ ልታይ ትችላለህ። አንተ ግን ሁሌም ለራስህ ከፊቴ እንቅፋት ቢገጥመኝም ወደፊት ለመሄድ ጥረት ማድረጌን አላቋርጥም ማለት ይኖርብሃል፡፡ካንተ ዉጭ ባሉ ሰዎች ሃሳብ እና አስተያየት ከአላማህ አትዘናጋ። ወላዋይ አትሁን፡፡ ህልምህን ሳትጥል ወደፊት ለመራመድ ሞክር፡፡ጊዜ የጣለህ ነጋዴ ብትሆንም እንኳ ለውድቀትህ ዋጋ ስጠዉ፡፡ጊዜ ለምን እንደጣለህ በጥሞና ማሰብ ከቻልክ ወደፊት ሊያራምድህ የሚችለውን መንገድ ትለያለህ፡፡ አየህ! ውድቀት ከት/ቤት እና ከኮሌጆች ቅጥር ግቢ ውጭ ብዙ ዋጋ ያለው የስኬት ቁልፍ ነው፡፡” የሚለው ፓትሪክ ገንዘብን ስለመግራት እና የማዘዝ ጥበብ ደግሞ እንዲህ ሲል አክሏል። “ገንዘብ ካለህ ቀጣዩ ስራህ ይሄን ገንዘብ እንዴት ስራ ላይ ማዋል እንዳለብህ ማወቅ ነዉ፡፡ይሔን ማወቅ ደግሞ ወደ ስኬት የሚወስድህን መንገድ መጥረግ ማለት ነዉ፡፡”

ሁሌም ነገሮችን አመጣጥነህ መጓዝ ይኖርብሃል የሚለው ፓትሪክ “አርቆ አሳቢነት፣ የፈጠራ ችሎታ እና ጥረት” ራስን ለማነሳሳት ብሎም ነፍስያ የተመኘችው ቦታ ለመድረስ ወሳኝ ግብዓቶች መሆናቸውን በመግለጽ “ለነገሮች ጊዜ ሰጥተህ ማሰብ ጀምር፡፡የፈጠራ ችሎታህን ለመጠቀምም ጥረት አድርግ!” በማለት በማለት ምክሩን ቋጭቷል።

[በጽሁፉ የተጠቀሱት ዘመኖች በሙሉ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር (እኤአ) ነው።]

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.