ተማሪዎቹ ዛሬም የገቡበት አልታወቀም!

የዚህ ጽሁፍ ቅጅ ቀደም ሲል በአርሂቡ መጽሄት ላይ ታትሞ ወጥቷል/This articled was originally Published on February 29,2020 in the Bi-weekly Arhibu Magazine in Ethiopia

በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ የተነሳውን ሁከት ሽሽት ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ታግተው ደብዛቸው የጠፉት የአማራ ተማሪዎች የገቡበት ሳይታወቅ እና ፈላጊ አስታዋሽ መንግስት ካጡ ሶስት ወድ አለፋቸው። የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች በናፍቆት፣በእንባ እና በሲቃ ሁነው ተስፋቸውን ፈጣሪ ላይ ጥለው ልጆቻቸውን ዛሬ ነገ ይመጡ ይሆን እያሉ ነው። ተስፋ የቆረጡም አሉ። ለወላጅ እና ዘመድ አዝማድ ሁኔታው ከመርዶም በላይ የከበደ ሃዘን እንዲጫናቸው አድርጓቸዋል። ምክንያቱም ይህኛው ማለቂያ የሌለው ፍራቻ እና ሃዘን ይፈራረቅበታል። እየተፈራረቀባቸውም ነው። ሃዘኑ የከፋ ነው። እንኳን ለወላጅ ለማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ምንም በማያውቁ ተማሪዎች ላይ የተቃጣው ማንነት ተኮር ጥቃት የሚያም ነው። የሰውን ልጅ ሰብዓዊ ክብርን በሚገፍ ሁኔታ ስር በሰቆቃ ስር ስላሉት ተማሪዎች የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ አንዳች ተጨባጭ ነገር አልተናገረም። አንዳንድ ወላጆችም ቢሆኑ በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት የተነገረን ባዶ ተስፋ ብቻ ነው ብለዋል። መንግስት ተማሪዎቹ የት ናቸው? ለሚለው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም። ማን እንዳገታቸውም ደፍሮ መናገር አልወደደም። ተማሪዎቹ ወዴት ናቸው? የመንግስት ዋና ስራ ምንድ ነው? መንግስት ከዜጎች ላይ ግብር የሚሰበስብበት ዋነኛ ምክንያት የዜጎችን ደህንነት በህግ በተሰጠው ስልጣን በብቸኝነት የያዘውን ሃይል ተጠቅሞ ማረጋገጥ ነው። አንድ መንግስት ይህን ማድረግ ካልቻለ ተማሪዎቹ ወዴት አሉ? ከሚለው ጥያቄ ከፍ ብለን መንግስት ስለመኖሩም እንጠይቃለን። 

የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተካሄደውን አፈና ለዓለም ለማሳወቅ የመቶ ሃገራት ዜጎች ከሰላሳ ሁለት ሽህ አምስት መቶ በላይ ሰዎች የተሳተፉበት የፊርማ ማሰባሰብ እና ፒቲሽን ተካሂዷል። በዚህ ፒቲሽን የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሴ ሃላፊዎች፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወኪሎች ፊርማቸውን ከማኖራቸው በላይ ልጆቹን ለማስለቀቅ በሚደረግ ጥረት ውስጥ መንግስት ላይ ጫና በመፍጠር ጭምር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለጹም አሉ።  በዚህም የመጀምሪያው ደረጃ የሚባለው ጉዳዩን ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መስሪያ ቤት ማሳወቅ ነው። ይሄም ተደርጎ ድርጅቱ ጉዳዩን እንደሚመረምረው ገልጿል። ይሁን እንጅ ድርጊቱን በፎርማል መንገድ ለድርጅቱ ለማሳወቅ እና ፋይል ለማያያዝ እስካሁን ከ7ቱ ተማሪዎች በቀር የተሟላ መረጃ ማግኘት አልተቻለም። የዚህን መረጃ መሰራጨት እና የማሰባሰብ ስራ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም መንግስት ጣልቃ በመግባት የተማሪዎቹን ቤተሰቦች ማስፈራራት እና ማዋከብን ጨምሮ “ለምን መረጃ ትሰጣላችሁ?” በማለት እስራት እየፈጸመባቸው መሆኑም ታውቋል። ይህም መረጃ የማግኘት ሂደቱን በተወሰነ ደረጃ ከማወሳሰቡም በላይ በተማሪዎች ደብዛ መጥፋት ላይ የመንግስት እጅ ሳይኖርበት አይቀርም የሚለውን ጥርጣሬ ከፍ አድርጎታል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የጠፉት ተማሪዎች ሳያንስ የጠፉት ተማሪዎች ነን ብለው ዶክመንታሪ እንዲሰሩ ከባህርዳር አባብሎ የወሰዳቸውን ሁለት ወጣት ሴቶችንም ሊሰራው ያሰበው ፕሮፖጋንዳ ከከሸፈ በኋላ ወንጅሎ አስሯቸዋል።

የመንግስትን ድርጊት በመኮነን የአማራ ክልል ህዝብ መሬት ላይ የተቀረው ደግሞ በማህበራዊ ድረገጾች ድምጻቸው አሰምተዋል። ወላጆችቻቸው በማያልቅ ተስፋ ውስጥ ልጆቻቸውን ዛሬም መጠበቅ አላቆሙም። ወገኖቻቸው ስለ ሰብዓዊ አጋርነት እና ስለራሳቸው ልጆች የነግ እጣ በመጨነቅ የታገቱትን ተማሪዎች አድራሻ ዛሬም ይጠይቃሉ። መንግስት ተማሪዎቹን እንዲመልስ ወይም እንዲያስመለስ መወትወታቸውን አላቆሙም። ተማሪዎቹ የት ገቡ? 

የኦሮሞ ተገንጣይ ታጣቂዎች ሰርገው መዋቅሩን እንደተቆጣጠሩት በሚታመነው የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ውስጥ  ህግ እና ስርዓት ከፈረሰ የቆየ ቢሆንም በተማሪዎቹ እገታ ላይ በርግጠኛነት መናገር ባይቻልም ከዚያ ይበልጥ የሚከብደው ግን የታጣቂዎች እና የክልሉ መንግስት በእገታው ላይ የነበራቸውን ድርሻ ለይቶ ማስቀመጥ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ በጉዳዩ ላይ አግቻለሁ ያለ አካል የለም።ስለዚህ እከሌ ነው ማለት አይቻልም።” ያሉበት ምክንያትም አገታው እከሌ ነኝ ማለት በማይቻልበት ጥምረት እና እቅድ ስለተፈጸመ የሚመጣው ተጠያቂነት ከመንግስት እንደማያልፍ ተረድተው ለማዳፈን እየሞከሩ ካልሆነ በቀር አንድ መንግስትን ከሚመራ ሰው ወንጀል ተፈጽሞ ሃላፊነት የሚወስድ ከሌለ ተጠያቂ የለም ማለት እብደት ነው። ሌላው እቅድ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከላይ ከላይ የሚያብድ መሆኑን ስለተገነዘቡ እና አሻግሮ የሚመለክት የለም ብለው “ተማሪ ይፈታ!” እያልን ስንውል ከጀርባው ያለውን ትልቁን ወንጀል እንዳናይ ለመደበቅም እየሞከሩ ነው። በተማሪዎቹ ላይ የተፈጸመው ወንጀል በክልሉ ህግና ስርዓት እንዲፈርስ ያደረጉትን እና በአደባባይ ከፋፋይ እና ዘረኛ ንግግር በማድረግ የሚታወቁትን የክልሉን ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በቀጥታ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያዊያን መተባበር ከቻልን የተማሪዎቹን እገታ ጨምሮ አቶ ሽመልስ አብዲሳን በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍ/ቤት ማቅረብ የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ መቅረብ ይችላል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ሃላፊነት የወሰደ ወንጀለኛ የለም ያሉት ማን ሊወነጀል እንደሚችል ስለሚያውቁ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ በአማራ ክልል ለሚፈጸም ድርጊት ራሳቸው አክቲቪስት ሁነው በሚተውኑበት መድረክ ላይ በኦሮሚያ ክልል ለ87 ቀናት ታግተው በተወሰዱት ተማሪዎች ላይ ግን “ወንጀለኛው ሃላፊነት ስላልወሰደ ወንጀለኛው እከሌ ነው ማለት አይቻልም።” በማለት ተሳልቀዋል። ሊዮናርዶ ዳቪንች በገዛ እጁ በሳላት የሞናሊዛ ስዕል በፍቅር  እንደወደቀው ሰላም እና ፍቅር የሚሉት ቃላት ካንደበቱ የማይጠፋው ጠቅላይ ሚንስትርም በገዛ ራስ ፍቅር ወድቀው ህግ ማስከበር፣ ወንጀል እና ሰብዓዊነትን መለኪያ ባሮሜትራቸውን ብሄርተኮር አድርገውት አንዴ ሳይሆን ደጋግመው ሲወድቁ ታዝበናል። ብዙውን ፈተና የሚወድቁት ደግሞ በራሳቸው የትናንት ንግግር እየተጠለፉ እና እየተጠላለፉ ነው። በማንነታቸው ምክንያት ታፍነው ደብዛቸው የጠፋው ተማሪዎች ዋነኛ ተጠያቂ እሳቸው በሚመሩት የመንግስት ሰንሰለት ውስጥ ያለው የኦሮሞ ክልል መንግስት ነው። ቀጣይ ተጣይቂው ደግሞ ራሳቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ናቸው።ተማሪዎቹ እስካልተመለሱ ድረስ እንቅልፍ አንተኛም። ተማሪዎቹን እንዲታገቱ ያደረጉት እና በክልሉ ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ በአደባባይ የጥላቻ ንግግር በማድረግ በር የከፈቱ ባለስልጣናት ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍ/ቤት እንዲቀርቡ ጥረት ማድረግ ይገባናል። እኤአ የ2007ቱን ምርጫ ተከትሎ በኬንያ በነበረው ግጭት ውስጥ  የአሁኑ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት የያኔውን ሞየ ኪባኪ ደግፈው በጎሳ እና በሃይማኖት ለተደራጀ ሙንጊኪ ለሚባል የኪኩዩ መንጋ ቡድን የያኔውን ተፎካካሪ ራይላ ኦዲንጋን ደጋፊዎችን በተለይም የሉዎ ጎሳ አባላትን እንዲጨፈጭፍ በገንዘብ በመደገፍ ተከሰው ነበር። ጆሞ ኬንያታ ያኔ ፕሬዝዳንት አልነበሩም። ሆኖም ኬንያዊያን ተረባርበው ለዓለም ባሰሙት ጩኸት የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍ/ቤት አቤቱታቸውን ተቀብሎ መርምሮታል። ጆሞ ኬንያታም ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ኔዘርላንድ ዘ ሄግ በሚገኘው የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ችሎት በመገኘት ጥፋተኛ ከሆኑ ለመቀጣት ዝግጁ ሆነው የያዙትን ስልጣን ለምክትላቸው አስረክበው አቅንተው ነበር። ለህግ እና ለሞራል እንዲሁም ትንሽ ለፍትህ ርትዕ ቦታ የሚሰጥ አይምሮ ያለው ማንኛውም ሰው ይህን ያደርጋል። ፍትህን አይሸሻትም። ኬንያ እና ኬንያዊያን ለዚያ በኋላ ምርጫ አካሂደዋል። ጆሞ ኬንያ እና ራይላ ኦዲንጋ በምርጫ በቀጥታ ተፋጠዋል። ግን የ2007ቱ የጎሳ እልቂት ዳግም አልታየም። ምክንያቱም ኬንያዊያን አቅማቸውን አሳይተዋል። ፖለቲከኞቹ ከቴሌቪዥን ፕሮፖጋንዳ ባለፈ ዓለማቀፍ ህግ ጥሰው የጥላቻ እና የጎሳ ምስቅልቅል የሚቀሰቅሱ ጠብ አጫሪ ንግግሮችን እንደ ኢትዮጵያ ባለስልጣናት በአደባባይ አይናገሩም። እንደ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ እና የኦሮሞ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመለስ አብዲሳ ህዝብ በጎሳው እየተፈናቀለ፣በሃይማኖቱ ምክንያት እየታረደ እና የሚያምንበት የአምልኮ ስፍራው እየነደደ በየቀኑ በሃገሩ ላይ ስደተኛ እና ባይተዋር የተደረገ ህዝብ ባለበት ስፍራ በአደባባይ ሰበርነው እና አደቀቅነው ብሎ መናገር ከሞራል እና ከሰብዓዊነት ሃዲድ ላይ መንሽራተት ነው። እነዚህን ሰዎች ወደ ሃዲዱ የምንመልሳቸው እኛ ከአንድ ሰሞን ጩኸት ወጥተን እንደኬንያዊያን ከሚቆጣጠሩት እና ከሚጫወቱበት የፍትህ ተቋም ሌላ እነሱን ሊጠይቅም የሚችል ዓለም አቀፍ አካል እንዳለ ለማሳየት ቆርጠን ከተነሳን ብቻ ነው። ያን ማድረግ እስክንችል ድረስ ለቅሷችን ይቀጥላል። ያን ማድረግ እስክንችል ድረስ እንደ ኬንያው ሙንጊኪ ቡድን ጎሳ እና ሃይማኖትን መሰረት አድርገው ባዋቀሩት ቄሮ በሚባለው የኦሮሞ መንጋ የሚደርሰው ጥቃት አይቆምም። ሙንጊኪ እንደ ቄሮ ሁሉ የፖሊስ እና የደህንነት ድጋፍ ነበረው። ኋላም ግጭቱ ሲባባስ መረጃ እየጠለፈ ፖሊስን እና ደህንነቶችን ሳይቀር ይመታ ነበር። ምክናያቱም የተዋቀረው በመንግስት ሲሆን የሚደገፈውም ከባለስልጣንቱ ጀርባ በነበሩት ባለሃብቶች ነው። የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍ/ቤት የኬንያ ባለሃብቶች፣ ባለስልጣናት እና ሙንጊኪ ላይ ምርመራ በማድረግ ዋነኛ የተባሉ ሰዎቹን ለምርመራ እንዲቀርቡ አድርጎ ነበር። ኢትዮጵያዊያንም ቄሮ ማለት ወጣት ማለት ነው እያልን እነሱ የነገሩንን እንደ ገደል ማሚቶ ከማስተጋባት ባለፈ ቡድኑን ያደራጁትን እና በገንዘብ የሚደግፉትን ባለስልጣናት በተለይም ቡድኑ መዋቅሩን በሰፊው በዘረጋበት የኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዲደራጅ ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠሩለትን ዋነኛ የክክሉን ባለስልጣናት ተጠያቂ እንዲሆኑ የተደራጀ ስራ መስራት ይጠበቅብናል። የቄሮ አደረጃጀት የሙንጊኪ መዋቅር ነው። ቄሮ የተደራጀው በሁለት ስለት የዘር ምንጠራ ወንጀልን ለመፈጸም ነው። አንድም በጎሳ አንድም በሃይማኖት! ቄሮ በኢትዮጵያ ህጋዊ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ክልል ባለስልጣናት ጋሻም ነው። ይህ የሆነው እና በአደባባይ ደፍረው ስንቶችን በቁም ካረደ እና ሰቅሎ ያቃጠለን ቡድን የሚያሞካሹት በእኛ ደካማነት ነው። ትናንት ሽዎችን ስለ ጨፈጨው ሙንጊኪ አፉ አድጦት እንኳ የሚያወራ የኬንያ ባለስልጣት የሉም። ተማሪዎቹ የት ናቸው? ብለን መጠየቃችንን አናቆምም። ግን ደግሞ መንግስት ምላሽ ይሰጣል ብለን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም። ብዙ አማራጮች አሉን። ሁሉንም እንዴት እና መቼ መጠቀም እንዳለብን ማወቅ የእኛ ፋንታ ነው።አለዚያ ከዚህ የከፋ መራራ እና አስቸጋሪ ወቅቶች ከፊት ይጠብቁናል። እንተባበር። 

ይህም ከላይኛው ጽሁፍ የቀጠለ በአርሂቡ መጽሄት ላይ ቀደም ሲል የታተመ የጽሁፉ አካል ነው።

በዚህ ረገድ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር መስሪያ ቤት በግዳጅ ታፍነው የጠፉ ሰዎችን ለማፋለግ እና በኦፊሴል ፋይል ለማያያዝ የተማሪዎቹ መሰረታዊ መረጃ ስለሚፈለግ ከላይ እንዳነሳሁት የ17 ታጋች ተማሪዎች ሙሉ አድራሻን ጨምሮ በፎርሙ በጥያቄ ምልክት ላይ የሚታዩት ያልተሟሉ መረጃዎች በአርሂቡ ቢሮ በኩል ወይም በኢሜል kidnappedstudents@outlook.com በመላክ የድርሻወን እንዲወጡ እንጠይቃለን። ተፈላጊ መረጃዎቹ የታጋች ተማሪዎች የትውልድ ቀን፣የትውልድ ቦታ፣የእናት ስም እና የመኖሪያ አድራሻ(ቀበሌ እና የቤት ቁጥር) ይጨምራል። ቸር ያሰማን!

Thank you for your comments

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.