የበርሊን ግምብ ለምን እና በማን ተሰራ? እንዴትስ ፈረሰ?

(By Kidus Mehalu) እኤአ 1980ዎቹ መጨረሻ እና 1990ዎቹ መጀመሪያ ለሾሻሊስት አብዮተኞች እና ኮምዩኒስቶች መጥፎ ጊዜያት ነበሩ። በካርል ማርክስ ፍልስፍና ሰክረው ገነትን በምድር ላይ ለመገንባት በምኞት ይዳክሩ የነበሩት ሶሻሊስት ተስፈኞች በየሃገሩ ህዝቡን ሰንገው ይዘው በራብ ይቆሉት ነበር። ምዕራብ ጀርመናዊያን የመርሴዲስ ሞዴል እያማረጡ ሲነዱ የተሻለ ኑሮ የነበራቸው የምስራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ደግሞ ሳይክል ለመንዳት የመንግስትን ፈቃድ ፍለጋ ተሰልፈው ይውሉ ነበር። በቁጥር የሚበዛው ደሃው ደግሞ ዳቦ ፍለጋ የበርሊን ግምብ ስር ተኮራምቶ ቢውልም ከምዕራብ በኩል ዳቦ ሲወረወር መጀመሪያ ዳቦ የሚበሉት ግምቡን የሚጠብቁት የምስራቅ ጀርመን ወታደሮች ነበሩ። ከተረፋቸው እነሱም ከታች በራበ ሆዱ አፍጥጦ ለሚመለከታቸው ወገናቸው ይወረውሩለታል። ታዲያ በዚያ ወቅት የምስራቅ ጀርመንን ቴሌቪዥን የሚከታተል የሚያደምጠው ፕሮፖጋንዳ እንዲህ የሚል ነው። “ምስራቅ ጀርመን ይሄን ያህል ቶን እህል አምርታ (ከህዝቡ ስለተረፈ) ለወዳጅ ሃገሮች ልትረዳ እየተዘጋጀች ነው።” ወዘተ ሚዲያው ምስራቅ ጀርመንን የሚያወዳድረው ከገነት/ጀነት ጋር እንጅ ከሌላ ሃገር ጋር አልነበረም። 

በምስራቅ ጀርመን ብቻ ሳይሆን የኮምዩኒዝም ስርዓት ከሰውነት ተራ አስወጥቶ ባሃገራቸው ባይተዋር ያደረጋቸው የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ዜጎች እዚህም እዚያም በመንግስቶቻቸው ላይ ተነሱ። በወቅቱ ሩሲያ “አንድ ሃገር አንዴ ኮምዩኒስት ከሆነ በኋላ ተመልሶ ሌላ መሆን አይችልም። የሩሲያ ታንኮች ኮምዩኒዝምን የትም ሄደው መጠበቅ አለባቸው።” የሚል ፖሊሲ ነበራት። በዚህም መሰረት በኮምዩኒስት ስርዓት ላይ በየሃገራቸው ያመፁትን የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ዜጎች ለመምታት የሩሲያ ታንኮች ድንበር እየሰበሩ መጀመሪያ ወደ ሃንጋሪ እና ቼኮዝላቫኪያ ገቡ። የሃንጋሪ እና የቼኮዝላቫኪያ ዜጎች ሩሲያን እንደ ኮምዩኒስት ወዳጅ ሳይሆን እንደ ወራሪ ጠላት ተመለከቷት። ትግሉ ቀጠለ። የሩሲያ ታንኮችም መጨፍጨፋቸውን ቀጠሉ።…ሩሲያ ቀጠለችና አፍጋኒስታን ገባች። አፍጋኒስታን ደም ለጠማው የሩሲያ ቀይ ጦር ምቹ አልሆነችም። የሩሲያ ልዩ ሃይል ተተካ። አፍጋኒስታን ለልዩ ሃይሉም ልዩ ፈተና ሆነችበት። ሩሲያ ከምስራቅ አውሮፓ ሰራዊቱን ወደ አፍጋኒስታን ያጓጉዝ ጀመር። አፍጋኒስታን ከየትም ውሰድለት መሬቱ ላይ ከሆነ “መዠንገር” ማለት ነው። አትችለውም።ሩሲያ ሃፍረቷን ተከናንባ በሽንፈት አፍጋኒስታንን ለቃ ወጣች። ሚካኤል ጎርባቾቭ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ሆኖ ብቅ አለና ከእሱ በፊት የነበረውን የፕሬዝዳንት ብሬዥኔቭ “ኮምዩኒዝምን የትም ቢሆን በሩሲያ ታንክ መጠበቅ” የሚል ፖሊሲ ውድቅ አደረገው። “ሁልህም እራስህን አውጣ!” አለ ጎርባቾቭ።(ይህንን ነው እንግዲህ ጓድ መንግስቱ ሃይለማሪያም ጎርባቾቭም ባለቀ ሰዓት ከዳኝ የሚሉት።) ጎርባቾቭ ወደ ስልጣን የመጣው ሩሲያ በኢኮኖሚም ጭምር በተዳከመችበት ወቅት ነው። ሩሲያ እንኳን የሌላ ሃገራት ኮምዩኒስቶችን ልታድን ከፊቷ የተደቀነውን የገዛ ህዝቧን ቁጣ እንዴት እንደምታልፈው ማጣፊያው አጥሯታል። ምስራቅ አውሮፓ ላይ የኮምዩኒስት ስርዓቶች በመጡበት አይነት መንገድ በህዝባዊ አመጽ ይገረሰሱ ይዘዋል። ሃንጋሪ ድንበሮቿን እኤአ በ1989ዓ/ም ክፍት ማድረጓን ለዓለም ይፋ አደረገች።ድንበሩ በተከፈተ የመጀመሪያው ቀን ብቻ 13ሽህ የምስራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ወደ ኦስትሪያ መሻገር ቻሉ።

ሩሲያዊያን በሃገራቸው የለኮሱት የማይበርድ የነጻነት እሳት ሚካኤል ጎርባቾቭን የሚይዘውን አሳጥቶታል። ምስራቅ ጀርመን በህዝባዊ አመጽ ቋፍ ላይ ናት።… የምስራቅ ጀርመን ህዝብ ድንገት ወደ በርሊን ግምብ ተመመ። ህዝቡ በእጁ የያዘው መሮ፣መዶሻ፣ ዶማ፣ ብቻ ግምብ ለማፍረስ የሚረዳ ነገር ይዞ ገሰገሰ። መጀመሪያ ላይ በግምቡ ጠባቂ ወታደሮች ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ተገደሉ። ሆኖም ህዝቡ የሚመለስ አልሆነም። ግምቡ ላይ የቆሙት ወታደሮች አሻግረው ህዝቡን ሲመለከቱ አጠገባቸው ካለው ህዝብ የሚልቅ ህዝብ ከኋላ እየተግተለተለ እየመጣባቸው መሆኑን ተመለከቱ። ይሄኔ ነው እንግዲህ ያነገቡትን መሳሪያ ወደ ህዝቡ እየወረወሩ ወደ ምእራብ ጀርመን መዝለል የጀመሩት-የምስራቅ ጀርመን ወታደሮች። እኤአ ህዳር 9 ቀን 1989ዓ/ም የመለያየት፣ የድንቁርና፣የሰቆቃ፣የኋላ ቀርነት፣የረሃብና የጠኔ ተምሳሌት ተደርጎ ሲቆጠር የነበረው የበርሊን ግምብ ፈረሰ። በቀድሞዋ ኮምዩኒስት ሩሲያ የተገነባው ይህ አጥር የምስራቅ ጀርመን ነዋሪዎች የምእራብ ጀርመን ነዋሪዎችን የተድላና የፍስሃ ኑሮ እንዳያዩ እና “የእኛ ህይዎት ለምን እንደነሱ አይሻሻልም?” ብለው እንዳይጠይቁ ለማድረግ የቆመ ደንቀራ ነበር። የበርሊን ግምብ በፈረሰበት ወቅት የሶሻሊስት ስርዓት አራማጅ በነበረችው ምስራቅ ጀርመን ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ የለም ነበር። በአንጻሩ ካፒታሊስቷ ምእራብ ጀርመን በኢኮኖሚ አቅሟ ከአሜሪካ ቀጥላ ከዓለም ሁለተኛ ነበረች።

ምዕራብ ጀርመን ምስራቅ ጀርመንን ከወደቀችበት አንስታ ለምስራቅ ጀርመን ህዝብ የምግብ እና የመጠለያ ድጎማን ጭምሮ ቅጣምባሩ የጠፋበትን የኮምኒስት አስተዳደር ወደሰውኛ ስርዓት ለመመለስ እና ዛሬ የምናውቃትን የተዋሃደች ጀርመንን ለመፍጠር ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አውጥታለች።

Advertisement