የአምበጣ መንጋ እና የግብርና ባለሙያዎቻችን!

ኢኮኖሚስቶቹ አፍሪካን የምጣኔ ሃብት ኮንሰፕት ግሬቭያርድ ይሏታል። በምዕራቡ ዓለም ውጤታማ የሆነ እና የተጨበጨበለት እና በተግባር ተሞክሮ የተዋጣለት የኢኮኖሚ ቀመር አፍሪካ ላይ ሲሞከር ጥሩ ነገር ማምጣቱ ቀርቶ ራሳቸው “ለመሆኑ ይሄ ነው ለእኛ እድገት አስተዋጾ ያደረገው ነው?” እስኪሉ ድረስ ኮንሰፕቱ ወደ መቃብር ሲወርድ ይታዘባሉ። አፍሪካ የኢኮኖሚ ሊቀ ቃውንት የነደፏቸውን የተዋጣላቸው የኢኮኖሚክስ መርሆዎች እርሷ ዘንድ ሲሄዱ ህላዌነት አጥተው ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ። የአለም ባንክም አፍሪካ እራሷ እድገት ታመጣ ዘንድ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቢቆይም አፍሪካ እና ድህነት እጅና ጓንት ሆነው ቅርርባቸውን እየጨመሩ ጉዟቸውን ቀጥለዋል። በአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ ቢሆንም የህዝብ እድገት ምጣኔው ከእድገቱ ብልጫ ስላለው በእድገት የተገኘውን ውጤት ወደ ኔጋቲቭ ይዞት ይወርዳል። ነገሩ ውሃ ቢወቅጡት••• ሆኗል። ጣሊያናዊው የኢኮኖሚክስ ኖቤል ሎሬት ሮበርት ሶሎው ካፒታል እና የሰው ሃይል መሳ ለመሳ በጥምረት ስራ ላይ ከዋሉ ጥሩ የሚባል የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል በኤክስፕሪመንት አሳይቷል። ለምሳሌ አፍሪካ የሰው ሃይል እጥረት ስለሌባት ይሄንን አቅሟን በገንዘብ በማጣመር ራሷ ግድቦችን፣መንገዶችን፣ ፋብሪካዎችን እና ማሽኖችን እንድትገነባ ቢደረግ ውጤት ልታመጣ ትችላለች ተብሎ ታምኖበት ይህንኑ እውን ታደርግ ዘንድ አፍሪካ የሌላትን ገንዘብ በብድር መልክ በቀላሉ እንዲሰጣት ተደረገ። ከአመታት በኋላ የአፍሪካ እድገት እና ለውጥ ሲፈለግ በእዳ ክምር ተጋርዶ አልታይ አለ። በተገነቡት ፋብሪካዎች ውስጥ የተተከሉት ማሽኖች ሲቆሙ መጠገን የሚችል ስለሌለ ፋብሪካዎቹን የሚጠግን ባለሙያ ከውጭ እስኪመጣ በከፊል ስራቸውን ይቆማሉ ወይም ተዘግተው ይጠብቃሉ። ይሄኛው ስትራቴጅ ጥቂት ለውጥ ቢያመጣም የተፈለገውን ያህል ሊሄድ ስላልቻለ አፍሪካዊያንን እናስተምር ብለው ሌላ እቅድ አወጡ። 

በዚህም አፍሪካዊያን በብዛት አውሮፓ እና አሜሪካ እውቀት እንዲገበዩ በሩ ተከፈተላቸው። በመንግስት ለመንግስት የሙያ ድጋፍ ልውውጥ እና ለአፍሪካዊያን በሚሰጥ ስኮላርሽፕ ተጠቃሚ ሆነው በተለያየ የእውቀት መስክ ትምህርት እንዲያገኙ እና ወዳገራቸው ተመልሰው የተማሩትን እውቀት እንዲያጋሩ ተደረገ። ይሁን እንጅ አፍሪካዊያኑ በዋጋ የማይተመን እውቀት ቢገበዩም ያገኙትን እውቀት ኢኮኖሚውን ወደሚያሽጋግር እሴት ቀይረው አፍሪካን ከድህነት የማላቀቁን ትልም እውን ማድረግ አልቻሉም። እኤአ በ1970ዎቹ አስር በመቶ የነበረው የአፍሪካ የድህነት ምጣኔ (ፖቨርቲ ሬት) በ1990ዎቹ ወደ አምሳ በመቶ አሻቀበ። ድህነት ጨመረ ማለት ነው። በ1970ዎቹ ዓ/ም ሰባ በመቶ ያህሉ አፍሪካዊያን ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉ ነበሩ። ዛሬ ይህ ቁጥር ተሻሽሎ ቁጥሩ ወደ ሰላሳ በመቶ ዝቅ ብሏል። ነገር ግን አፍሪካዊያን በብድር በሚሰሩ ዘመናዊ ህንጻዎች ውስጥ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጠው ቢሮክራሲ ከመፍተል ውጭ እውቀታቸውን በተግባር ወደ ኢኮኖሚ ፐር ካፒታ ሲያሸጋግሩት ማየት አሁንም ቅዥት እንደሆነ ቀጥሏል። የተማሩት የሚሰሩት እንዳልተማሩት ነው። ኢትዮጵያን ማየት ይቻላል። በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ፣በጀርመን፣ በሆላንድ እና በሌሎች የአውሮፓ ሃገራት በተለያየ የግብርና ሳይንስ ትምህርት ዘርፎች በዶክትሬት እና በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀው አብዛኞቹም ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል። በርካቶቹም የመንግስት ቢሮ ሃላፊዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እና በግብርና ተኮር ምርምሮች ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች የተወጣጡ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ምሁራን ህብረተሰቡ በገጠመው ችግር የተማሩትን እውቀት በተግባር መንዝረው የሚጠበቀውን ሲያደርጉ አይስተዋልም። ከዚያ ይልቅ ዛሬ ያልተማረውን ገበሬ አሰራር ማሻሻል ይቅርና ገበሬው በሚያውቀ መንገድ እንኳ ችግሩን ለመፍታት የሚያመነቱ ናቸው። 

ይህን ዓይነት ሰው በተግባር ለመጥቀስ ሰሞኑን አንድ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ባልደረባ የሆኑ በቢቢሲ የተናገሩትን ዋቢ ማድረግ እችላለሁ። እኝህ ሰው ሰሞኑን በተከሰተው እና ህዝብን ባስጨነቀው የበረሃ አምበጣ መንጋ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ ቀድሞ ህዝቡን ማስተባበር እና የስጋቱን መጠን በማሳወቅ ይበልጥ ተነሳሽነት መፍጠር ሲገባቸው ህዝቡ ገበሬው ያመረተው እህል በአምበጣ ተበልቶ እንዳያልቅ ተጨንቆ አምበጣ ለማባረር ሲሮጥ እየዋለ እሳቸው “አምበጣው እስካሁን ጉዳት አላደረሰም።” ብለው ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህ በራሱ አምበጣነት ነው። በባህር ዳር የጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማጥፋት ገበሬው ድሮም እንደሚያውቀው እምቦጩን በእጁ ሲነቅል ህዝቡ አብሮ ሲነቅል በዘርፉ የተማሩት ምሁራን የተማሩትን በተግባር ሲጠቀሙበት አልታየም። እምቦጭን በተለያየ መንገድ በተግባር እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል ትምህርት አልወሰዱምን? የአምበጣ መንጋ ሲመጣ ጥንት ጀምሮ ገበሬው ባዳበረው እውቀት በተለያየ መንገድ ሲያባርር ነበር። ከነዚህ በውጭ አገር የተሻለ ትምህርት ቀሰሙ ከሚባሉት “ምሁራን” በተጨማሪ ኢትዮጵያ ብዙ ሽህ የግብርና ባለሙያዎች ከየትኛውም የትምህርት መስክ በላይ በየዓመቱ ስታስመርቅ ቆይታለች። ታዲያ ይህ ሁሉ የግብርና ባለሙያ ግብርና የማያውቀው ህዝብ ጭራሮ ይዞ አምበጣ ለማባረር ደፋ ቀና ሲል እንዴት የተሻለ መፍትሄ አያመጡም? ወይስ የአምበጣ መንጋን ለማባረር መፍትሄው ማሯሯጥ ነው? በዘርፉ የሰለጠናችሁ የግብርና ምሁራን ሰው በርሃብ ሳያልቅ የምታውቁትን መፍትሄ ቶሎ ገበሬው በሚገባው ቋንቋ ተናገሩ እንጅ!! ካልሆነ ጭራሮ ይዞ ለመሄድማ በናንተ በተማራችሁት እና ባልተማረው ገበሬ መካከል ልዩነቱ ገበሬው ላይ ተጨማሪ ቢሮክራሲ መፍጠራችሁ ካልሆነ ሌላ ምንድ ነው? ይህን ብትናገሩ እንደኢኮኖሚ ኮንሰፕት ከፖለቲካ አስተዳደር ጋር በቀጥታ የተጣመረ ስላልሆነ ህዝቡ ለመተግበር አይቸገረም። አይከብደውምም!

 

Advertisement