የሞኔታሪ ፖሊሲው:-የገንዘብ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንት ምንነት፣ጥቅም እና ጉዳት!


የብሄራዊ ባንክ የሚተገብረው የገንዘብ አስተዳደር ስርዓት ዜጎች ላይ የሚጫወተው አወንታዊ ሚና የኢኮኖሚ ዕድገት እና የዜጎች ብልጽግና ላይ ቀጥተኛ ውጤት የሚኖረውን ያህል አሉታዊ ተጽእኖው ደግሞ ዜጎችን በማደህየት እና በመንግስት ላይ ያላቸውን ዕምነት እንዲያጡ ምክንያት ይሆናል። የገንዘብ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንት ለሃገር ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ከሚባሉት የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። የገንዘብ ቁጠባ ከዛሬ ይልቅ ገንዘብ በማስቀመጤ ነገ እጠቀማለሁ በማለት የዛሬ ፍላጎትን በማቀብ ገንዘብ ማጠራቀም ማለት ነው። ኢንቨስትመንት ማለት ደግሞ የራስን ወይም የሰወችን ገንዘብ በብድር ከባንክ ቤት ወስዶ ነገ እጠቀማለሁ በማለት ዛሬ ላይ የተለያዩ ቢዝነሶችን ለመክፈት ወይም ፋብሪካ ለመገንባት ወዘተ ጥቅም ላይ ማዋል ማለት ነው። የገንዘብ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንት የማይነጣጠሉ እና የተቆራኙ የኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፎች ናቸው። ገንዘብ የሚቆጥበው ግለሰብ እና ገንዘቡን ስራ ላይ የሚያውለው ኢንቨስተር ጥቅም የሚያገኙት ጊዜን ተንተርሰው ነው።ሁለቱም ጥቅማቸው ‘ዌቲንግ ፋክተር’ ላይ የተመሰረተ ነው።

በአንድ ሃገር ዜጎች በርከት ያለ ገንዘብ ሲያስቀምጡ በባንክ ቤቶች ውስጥ ለኢንቨስትመንት የሚሆን በቂ ገንዘብ ይኖራል ማለት ነው። ይህ ይሆን ዘንድ ዜጎች ገንዘብ እንዲቆጥቡ የሚያነሳሳ የገንዘብ አስተዳደር ፖሊሲ ያስፈልጋል። ይሁን እንጅ ይህ ሂደት በመንግስት ጣልቃ ገብነት ሊጨናገፍ ይችላል። ለምሳሌ የብሄራዊ ባንክ የኢኮኖሚ እድገት ሳይኖር ወይም ኢኮኖሚው ከሚያድግበት ፍጥነት በላይ ብር እያተመ ወደ ገበያው በሚያስገባበት ወቅት ጤናማውን የኢኮኖሚ ሂደት ስለሚያዛባ ውጤቱ የገንዘብ ግሽበት ይሆናል። ይህም የብር የመግዛት አቅም መዳከም ማለት ነው። ለዜጎች የሚያሽቆለቁለው የብር የመግዛት አቅም ለመንግስት ‘ኢንፍሌሽናሪ ታክስ’ የሚባል የገቢ ምንጭ ነው። ይህም ዜጎችን ለኑሮ ውድነት ሰለባ ያደርጋቸዋል። ይህ ግሽበት ዜጎች ገንዘብ እንዳይቆጥቡ የሚያደርግ ጋሬጣ ነው። በሜስስ ሪግረሽን ቴረም መሰረት ይህ ችግር የሚከሰተው ብር የምርት ሂደትን ወጭ ተመርኩዞ ለገበያ የማይቀርብ እና ምርቱ አላግባብ ሲጨምርም ጉዳቱ በዚያው ልክ የሚጨምር ብቸኛ ምርት ስለሆነ ነው። ይህ ማለትም የህትመት ወጭው 2ብር የማይሞላው መቶ ብር በላዩ ላይ በሚጻፈው ሕጋዊ ትዕዛዝ ብቻ ‘መቶ ብር ነው’ ብለን ከመቀበላችን ውጭ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እስካለ ድረስ የመቶ ብሩ ዋጋ/የመግዛት አቅሙ/በህግ ከተጻፈውም በታች ስለሚሆን ነው። ይህን ከኢትዮጵያ ነባራዊ የግሽበት መጠን አንጻር በምሳሌ ለማሳየት እሞክራለሁ።

የፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት ሊቅ የነበረው ፕሮፌሰር ፍራንክ ፌተር ሰዎች ከዛሬ ይልቅ የወደፊቱን የሚመርጡበትን ምክንያት አስመልክቶ ስነልቦና(ሳይኮሎጅ) የሚያጠናውን ሳይንስ ከኢኮኖሚክስ ጋር በማቆራኘት ‘የታይም ፕሪፈረንስ ቲወሪ ኦፍ ኢንተረስት’ን ለዓለም አበርክቷል። ይህ ቲወሪ ከስነልቦና ጋር የተቆራኘ ሲሆን ለምሳሌ ግለሰቦች ዛሬ ከምትሰጣቸው 10ሽህ ብር እና ከአንድ አመት በኋላ ከምትሰጣቸው 10ሽህ ብር ብታስመርጣቸው አብዛኛው ወይም ሁሉም ብሩን ዛሬ መቀበል ይመርጣሉ።ነገር ግን ዛሬ 10ሽህ ከምትሰጣቸው እና ከአንድ ዓመት በኋላ 20ሽህ ከምትሰጣቸው ምርጫ ብትሰጣቸው ውሳኔያቸው ምርኩዝ የሚያደርገው ዛሬ ገንዘቡን የሚፈልጉበት ጉዳይ/ያለባቸው ጊዜያዊ ችግር/ወይም ከነገ 20ሽህ ብር የሚበልጥ ጥቅም ዛሬ በ10ሽህ ብር የሚያገኙት እሴት ያለ እንደሁ ብቻ ነው። ይህ ቲወሪ ግለሰቦች ጊዜን ተመስርተው የሚያደርጉት ጥቅም ላይ የሚወስኑት ምርጫ ማለት ነው። ስለዚህ ዛሬን ከመጠቀም ታቅበው ገንዘባቸውን ባንክ ቤት በማስቀመጥ በሚመጣው ዓመት ወይም ወደፊት ለመጠቀም ለወሰኑት ግለሰቦች ባንኮች የሚሰጡት የጊዜ ማካካሻ ወለድ ይባላል። የሆነ ሆኖ በተጠቀሱት የምጣኔ ሃብት መርሆዎች እና ቲወሪዎች መሰረት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ምናልባት ከሌባ ለመጠበቅ ካልሆነ በቀር በባንክ ቤት ገንዘብ ለመቆጠብ የሚያነሳሳ ሳይንሳዊ ምክንያት የለም። እንዲያውም የገንዘብ ግሽበቱ መጠን 10በመቶ/የብራቸው የመግዛት አቅም እያደር የሚዳከምበት ፍጥነት/ በወለድ ከሚያገኙት 7በመቶ ስለሚበልጥ ብር በማስቀመጣቸው ተጨማሪ ኪሳራ እና ድህነትን ይገበያሉ። የዚህ ምክንያት በሂሳብ ሲሰላ ዜጎች ብር ሲያስቀምጡ ከሚያገኙት ዓመታዊ የ7በመቶ ወለድ ይልቅ ዓመታዊ የግሽበት መጠኑ በ3በመቶ መብለጡ ነው። የግሽበቱ መጠን ሁለት ዲጂት ውስጥ መሆኑ ብቻ የገንዘብ አስተዳደር ፖሊሲውን ክሽፈት አመላካች ከመሆኑም በላይ ዜጎች ባንክ ቤት ሲያስቀምጡ በማትረፍ ፋንታ በዓመቱ መጨረሻ ወለዱም ተጨምሮ መጀመሪያ ያስቀመጡት ገንዘባቸው ይገዛው የነበረውን ያህል እንኳ መግዛት የማይችል ገንዘብ ይኖራቸዋል ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ገቢያቸው እየጨመረም እንኳ በኑሯቸው ላይ ለውጥ የማያዩት በዚህ ምክንያት ነው።

የገንዘብ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንት የተቆራኙ እና የማይነጣጠሉ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች ቢሆኑም የገንዘብ ግሽበት ግን ሁለቱንም ያዳክማቸዋል። ለምሳሌ ግሽበት ሰዎች ገንዘብ የማጠራቀም ፍላጎታቸውን ይጠፋል። ኢንቨስተሮችም ቢሆን እንደ ዜጎች የረዥም ጊዜ እቅድ ለማውጣት ስለሚቸገሩ ገንዘባቸው በግሽበት ዋጋውን ከማጣቱ በፊት ወደ ሌሎች ሃገራት ገንዘብ በመመንዘር ወደ ውጭ ሃገር ለማሸሽ ይሯሯጣሉ። ባለሃብቶች ከስራ ይልቅ ገንዘባቸውን ቢያንስ ባለበት ለማቆየት እንደ ቤት፣ወርቅ፣መሬት ወዘተ ዓይነት ዋጋቸው በጊዜ ሂደት በቀላሉ የማይወድቅ ጥሪቶች ላይ ለማዋል ይገደዳሉ። በተጨማሪም በርከት ያለ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ብዙ ሚሊዮኖችን በግሽበት ከማጣት በፍጥነት መኪናና ቤት እንዲሁም የተለያዩ እቃዎችን በመግዛት የገበያ አድማሳቸውን ለማስፋት እና ደንበኞቻቸውን ለማብዛት በሎተሪ መልክ በመሸለም በአንድ ዲንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት ሲጥሩ የምናየውም ለዚህ ይመስለኛል። ኢንቨስተሮች ከባንክ ቤት ሲበደሩ የሚጠየቁት የወለድ ተመን የሃገሪቱ ህዝብ ገንዘብ ሲያስቀምጥ በሚከፈለው የወለድ ተመን ከዛሬ ይልቅ ነገን ይመርጥ እንደሆን የሚያንጸባርቅ እውነታ ነው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ያለው የዘንድሮ ዓመታዊ የግሽበት መጠን 10በመቶ (አምና 12በመቶ ነበር) ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ ይቆጥቡ ዘንድ የማያነሳሳ ማለትም ከዛሬ ይልቅ ገንዘባቸው ነገ ዋጋውን ስለሚያጣ ለመቆጠብ የሚያስችል ተፈጥሮአዊ እና ሳይንሳዊ ምክንያት የለም። ልብ በሉ! ዛሬ ባንክ ቤት 100ብር በ7በመቶ ወለድ የሚያስቀምጥ ሰው በዓመቱ መጨረሻ ከነወለዱ 107ብር ይኖርዋል። የዘንድሮ ዓመታዊ የብር ግሽበት መጠን ግን 10በመቶ ነው። የብር የመግዛት አቅም 10በመቶ ነው ማለት ባንክ ቤት የተቀመጠው መቶ ብር ዋጋውን/የመግዛት አቅሙን በ10ብር ያህል ያጣል ማለት ነው። ዘንድሮ 100ብር ይገዛ የነበረ ነገር በዓመቱ መጨረሻ ዋጋው 110ብር ይሆናል ማለት ነው። አንድ ዓመት ያህል 100ብር በማስቀመጥ ከነወለዱ የሚገኘው ግን 107 ብር ነው።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ብዙ ገንዘብ የሚያስቀምጥ ሰው በዚህ መንገድ ብዙ ገንዘቡን ያጣል። ለምሳሌ ሙስሊሞች ወለድ የማይቀበሉት ተጨማሪ የሌላ ሰው ገንዘብ ወይም ትርፍ ላለመውሰድ ይመስለኛል። ሆኖም በዚህ ስሌት መሰረት ወለድ የሚባለው ተጨምሮ እንኳ የራሳቸውን እውነተኛ ገንዘብ ስለማያገኙ ይህንንም አለመቀበላቸው ይበልጥ ኪሳራ ያደርስባቸዋል። ይህ ነባራዊ ሃቅ ላይ ብቻ የተመሰረተ የእኔ ኢኮኖሚያዊ ምልከታ ነው።እንደ ግለሰቦች ሁሉ ባለሃብቶች ሃገንዘባቸው ይዘው ወደ ስራ የሚገቡት ለምሳሌ ፋብሪካ የሚገነቡት መጭው ጊዜ ላይ በመተማመን ነው። የአብስቲነንስ ቲወሪ ኦፍ ኢንተረስት ይህንኑ ይነግረናል። ኢንቨስተሩ ለወደፊት ጥቅም አገኝበታለሁ ብሎ በሚያወጣው ገንዘብ ዛሬ ላይ ትልቅ ሪስክ ይወስዳል። ፋብሪካው እስኪጠናቀቀ ለሰራተኞቹ ደመዎዝ መክፈሉን አያቆምም። ከተጠናቀቀ በኋላ ምናልባት ምርቱ በተጠቃሚ ፈላጊ ካጣ ወይም በገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን ካልቻለ የሚከስረው ባለሃብቱ ብቻ ነው።የቲወሪው ቀማሪ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሊቅ ፕሮፌሰር ናሳው ሲኒየ “ቢዝነስ ባለሃብቶችን ሁልጊዜም በተሰማሩበት መስክ እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ፣ደንበኞችን በትህትና እንዲያገለግሉ እና ስነ ምግባር እንዲላበሱ ያስገድዳቸዋል።” በማለት ይህን የሚያሟሉ ባለባለሃብቶቹ ዛሬ የሚያወጡት ገንዘብ ከትርፍ ጋር ተመላሽ የሚሆነው ፋብሪካው በወራቶች ወይም በአመታት ውስጥ ተገንብቶ አልቆ ወደ ምርት ሂደት ከገባ በኋላ ለተጠቃሚዎች ወደ ገበያ የሚያስገቡት ምርት መሸጥ ሲጀምር እና በገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን ሲችል እንደሆን ያስረዳል።ይህ ሁሉ ይሆን ዘንድ ግን “የተረጋጋ ገንዘብ(ዋጋው ቶሎ ቶሎ የማይዳከም ብር) እና የሕግ የበላይነት መኖር የግድ አስፈላጊ ነው።” ሲል ያሰምርበታል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አቢይ መንግስት የጀመረው የቢዝነስ እና ኢንቨትመት መዋቅራዊ ማሻሻያ(ዱይንግ ቢዝነስ ሪፎርም) ውስጥ ይህን የከሸፈ እና ያልተረጋጋ የገንዘብ አስተዳደር ፖሊሲ ካላቃና ዜጎች በገዛ ገንዘባቸው ድህነት አምራች በሆነው የተሳሳተ ፖሊሲ ውጤት ምክንያት መራራ ዋጋ መክፈላቸውን ይቀጥላሉ። የገንዘብ ግሽበት ዜጎች ባንክ ቤት ብር ሲያስቀምጡ ከሚያገኙት ወለድ ሲበልጥ መንግስት ከሃገር ቤት ተቀማጭ ገንዘብ አብዛኛውን ገንዘብ እንደሚጠቀምበት ስለሚጠቁም በዚህ ረገድ ሪፎርሙ መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ወጭዎቹን በመቀነስ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል። በተጨማሪም የተጠቀሰውን የፖሊሲ ክሽፈት ለማቃናት ሪፎርሙ በሃገር ውስጥ የሚደረግ ሕጋዊ የገንዘብ ዝውውር ነጻነት እና የወለድ ተመን ምጣኔን ከግሽበት መጠን ጋር የተቆራኘ እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል። የለውጥ ተስፋ የሆነው የኢኮኖሚ ሪፎርም ደጋፊ እንደመሆኔ የሪፎርሙ ሂደት እስኪጠናቀቅ በትዕግስት መጠበቅ እንዳለብን ባምንም ዜጎች ገንዘብ ሲያስቀምጡ የሚያገኙት የወለድ መጠን ግን ዛሬ ነገ ሳይል ቢያንስ ቢያንስ የሃቅ ገንዘባቸውን ያገኙ ዘንድ ከግሽበቱ መጠን እኩል 10በመቶ ሊደረግ ይገባል። ዜጎች ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ባንክ ቤት እንዲያስቀምጡ እና የሃገር ተጨማሪ ሃብት እንዲያድግ ደግሞ ከዛሬ ብራቸው ይልቅ ነገ የሚያገኙትን ማካካሻ ወይም ወለድ ያገኙ ዘንድ የግድ ነው። አለዚያ ገንዘብ ቆጥቤ ተጨማሪ ጥቅም ባይሆን እንኳ ገንዘቤ መጀመሪያ የነበረውን የመግዛት አቅም ካላገኘ ለምን ነገን እጠብቃለሁ? የብሬ የመግዛት አቅም ሳይዳከም ዛሬውኑ የምፈልገውን ለምን አልገዛበትም? በመቆጠቤ ምን አገኛለሁ? መንግስት ይህን ትኩረት ሰጥቶ በአስቸኳይ ሊያስብበት ይገባል። ምክንያቱም በባንክ ቤት የሚቆጥቡ ሰዎች ቁጥር ካሽቆለቆለ፣ የባንኮች መሰረት ይናጋል። ለኢንቨስትመንት የሚውል ብድር ይጠፋል። አዳዲስ ስራዎችም አይፈጠሩም። ይህም የድህነትን መጠን ይጨምራል። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሃገር ኢኮኖሚ ዕድገትን ሃዲድ ያስታል።

Advertisement

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.