የፊስካል ፖሊሲው ክሽፈት፣መራራ ዋጋው እና መፍትሄዎቹ

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር የነበረው ጄምስ ካላኻን እኤአ በ1971ዓ/ም የመንግስታቸውን ፖሊሲ ክሽፈት ሲናዘዙ “ገንዘቡን እያጋሸብን የመንግስትን ወጭ በመጨመር የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የተገበርነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የኢኮኖሚክስ ተዋሪያን ቤተ ሙከራ አድርጎናል።ይህ ዓይነት ፖሊሲ እንደማይሰራ ለመረዳት 20ዓመታት ፈጀብን። ያሳዝናል። በውጤቱ ያተረፍነው ብዙ ስራ አጥነት መፍጠር ብቻ ነው።ኪሳራ!!።”ሲሉ ለእንግሊዝ ሕዝብ ሃገራቸው የተለየ መንገድ ካልተከተለች አደጋ እንደተጋረጠባት አስታወቁ። ይህን ዓይነት የፖሊሲ ውድቀት መፍትሄ ሳያገኝ የሚቆይበትን ምክንያት እኤአ በ1995ዓ/ም በኢኮኖሚክስ ሳይንስ  የኖቤል ሽልማት ያገኘው የራሽናል ኤክፔክቴሽን ቲወሪ ቀማሪ ሮበርት ሉካስ እንዲህ ይገልጸዋል። በቲወሪው መሰረት  መንግስት ትክክለኛ ባይሆንም ለፖለቲካ ድጋፍ ህዝቡ የሚፈልገውን ዓይነት(ለኢኮኖሚ ጎጅ እንደሆነም ቢታወቅ እንኳ) ግን መሬት ላይ ካለው የኢኮኖሚ ሃቅ ጋር የማይጣጣም የምኞት ፖሊሲ ትግበራ ውስጥ ይገባል። በዚያ ዓይነት መንገድ የሚተገበረውን የተሳሳተ ፖሊሲ ውጤት ህዝቡ ሳያውቅ እያማረረ ተስፋ ማድረጉን ይቀጥላል። ግን ተስፋው አሳ የሌለበት ውሃ ላይ እንደተጣለ መረብ መልካም ውጤት አያመጣም። በኢትዮጵያም አላመጣም። ለዚህም ማሳያ የኢትዮጵያን የግብር እና የመንግስት ወጭ ገዥ ፖሊሲ(ፊስካል ፖሊሲ) እና የገንዘብ ፍሰት እና አስተዳደር(ሞኔታሪ ፖሊሲ)  ክሽፈትን ለማሳያ እጠቀምበታለሁ። ግብር እና ሞት በሚል ርዕስ በ5 ተከታታይ ጽሁፍ የግብር ስርዓቱ እና ዜጎች የሚከፍሉት የግብር ተመን ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነባራዊ ሃቅ ጋር የማይጣጣም መሆኑን ለማስረዳት ሞክሪያለሁ።

የመንግስት ከአቅሙ በላይ(በግብር ከሚያገኘው ገንዘብ በላይ) ገንዘብ ማውጣት የበጀት ክፍተቱን ማስፋቱ እንዳለ ሆኖ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት/ቢዝነሶችን ያዳክማል፤የገንዘብ ግሽበትንም ያባብሳል።  የገንዘብ ግሽበት ሲባባስ የስራ አጥነት መጠን ይጨምራል።የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ግሪጎሪ ማንኪው ማክሮኢኮኖሚክስ በተባለ መጽሃፉ ላይ [1994፡62]” የበጀት ክፍተት ሲሰፋ የመንግስት የብድር ፍላጎት በዚያው ልክ ስለሚጨምር የሃገር ተቀማጭ ገንዘብ ሃብት ይመናመናል። ይህም በሃገር ኢኮኖሚ አጠቃላይ ምርት ላይ መመናመንን ይፈጥራል።የኢኮኖሚ ዕድገትንም ይገታል።” በማለት አስቀምጧል። የሆነ ሆኖ ፊስካል ፖሊሲ በዜጎች ገቢ፣በገንዘብ ግሽበት እና የቢዝነስ መዋዠቅ እና እንቅስቃሴ ወዘተ ላይ የሞኔታሪ ፖሊሲውን ያህል ተጽእኖ ባይኖረውም እንኳ የኢትዮጵያ የገንዘብ ግሽበት መጠን ሁለት ዲጅት ውስጥ መሆኑ ግን የፊስካል ፖሊሲውን ክሽፈት ያመላክታል። የፊስካል ፖሊስው (የግብር እና የመንግስት ወጭ አስተዳደር ገዥ መመሪያ) በጊዜ መፍትሄ እንዲበጅለት እና ጠቅላይ ሚንስትሩ በሪፎርም ጉዟቸው ምናልባት ካላካተቱት እንዲያካትቱት ‘የኔም ጉዳይ ነው’ ብለን ሁላችንም ጥረት ብናደርግ መልካም ነው። የፖሊሲ ውድቀትን በዝምታ የሚያልፍ ህዝብ በዶ/ር ሮበርት ሉካስ ጁኒየር ቲወሪ መሰረት የፖሊሲው ክሽፈት የሚያደርስበትን አሉታዊ ውጤት ለመቀበል ተስማምቷል ማለት ነው። ከኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ጋር የሚጣረስ ፖሊሲ አሉታዊ ውጤቶችም ድህነት፣ስራ አጥነት፣የኑሮ ውድነት እና ማህበራዊ ምስቅልቅል ናቸው። ይህን ዋጋ መክፈል እንደበቃን እና እንደነቃንም ጭምር  ብቻ ሳይሆን የሚሻለውን መፍትሄም በመናገር ሃሳባችን በተለያየ መንገድ መግለጽ ይገባል። የፊስካል ፖሊሲውን ግድፈት ለመክላት ከሚመከሩ መፍትሄዎች ውስጥ የመንግስት ወጭ ቅነሳ፣ የጀመረውን የፕራይቬታዤሽን ዕቅዱን እና የዱይንግ ቢዝነስ ሪፎርም በተግባር ማቀላጠፍ፣ የቀጥተኛ ግብር ተመን ቅነሳ(የደመወዝ፣የቢዝነስ ወዘተ) እና  ሃገሪቱን ድንበር ዘለል እና አጎራባች ሃገራት ጋር ያላትን የነጻ ንግድ አድማስ ለማስፋት የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠናን ሳይረፍድ መቀላቀል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የመንግስት ልክ የሌለው ኢ-ምርታማ ወጭ የኢትዮጵያዊያን ህይወት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ይፈጥራል። መንግስት በግብር፣በብድር፣እና በግሽበት(የብርን የመግዛት አቅም በማዳከም) ከሚሰበስበው የሕዝብ ገንዘብ ውጭ የራሱ የሆነ ምንም ዓይነት ገንዘብ የለውም። ሆኖም ይህን ገንዘብ ኢኮኖሚውን የሚያሳድግ ነገር ላይ በማዋል ፋንታ የመንግስትን ጡንቻ የሚለጥጡ( ስቴት አክሰሲብል ፕሮዳክት)  ዕሴት የማይፈጥሩ ፕሮጀክቶች ላይ ካፈሰሰው  ከእጅ ወዳፍ  ከሆነው የኢትዮጵያዊያን ጎሮሮ ላይ የዕለት ጉርሳቸውን መንጠቁን ይቀጥላል። የመንግስት  ወጭ በከፍተኛ ሁኔታ ካልቀነሰ በቀር የኢትዮጵያዊያን ኪሳራ ይቀጥላል። የመንግስት ወጭ ሁልጊዜም በእቅድ ወቅት ያልታሰቡ አሉታዊ ተጽእኖዎችን በሃገር እና በህዝብ ላይ እንደሚፈጥር የተረጋገጠ ኢኮኖሚያዊ መርህ ነው።በኢትዮጵያ የመንግስት ፕሮጀክቶች ከዕቅዳቸው በላይ ከ60 እስከ 600በመቶ ጭማሪ በጀት እንደሚጠይቁ ዶ/ር ፍጹም አስፋው የተባሉ በጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ የተሾሙ ባለስልጣን ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ይህም የመንግስት ፕሮጄክቶች በአምስት ዓመት ውስጥ 30ቢሊዮን ብር ያህል ለብክነት እንደሚዳርጉ ያሳያል። የዛሬ ሳምንት ሱር ኮንስትራክሽን በሚባል ድርጅት በ5ቢሊዮን ብር ሊሰሩ የታሰቡ የዛሬማ ሜይዴይ እና መገጭ የተባሉ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን የኦዲት ሪፖርት የገመገመው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ፕሮጀክቶቹ ለዓመታት ከመጓተታቸው በተጨማሪ 13ቢሊዮን ብር ያህል  ተጨማሪ ሕዝብ ብር ጨርሰውም እንኳ ባለመጠናቀቃቸው አልተቆጩም። ይልቁንስ “መንግስት ተጨማሪ በጀት መድቦ ፕሮጄክቶቹ እንዲያልቁ ማድረግ አለበት።” በማለት ለውሃ፣መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስቴር መመሪያ አሳለፉ። እዚህ ላይ ችግሩ መንግስት ለሚሰራው ፕሮጀክት የሕዝብ ገንዘብ ለብክነት ሲዳርግ እንደ ግል ድርጅቶች ከስሮ ከገበያ የሚወጣበት ወይም በሕግ አግባብ የሚጠየቅበት አሰራር አለመኖሩ ነው። መንግስት ከትላላቅ ፕሮጀክቶች እና ከገበያው ላይ እጁን ይሰብስብ የሚባለው ፕሮጀክቶቹ በትክክል ሊፈጸሙ ያለመቻላቸው ዕውነታ ሁሌም እንዳለ ሆኖ  የህዝብ ገንዘብ ለከፍተኛ ሙስና እና ብክነት ያለውን ተጋላጭነት መቀነሻው የተሻለ መንገድም ስለሆነ ነው። ይህ ካልሆነ ከላይ እንዳያችሁት በሚያሳዝን ሁኔታ በጊዜው ማጠናቀቀ ላልቻለው እና ላባከነው በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ብር በተጠያቂነት ፋንታ ተጨማሪ በጀት ይጠይቅበታል። በዚህ መንገድ የሚከስረው እና የሚራቆተው ግን ሕዝብ ነው። እንዲህ ያለ አሰራር ማብቃት ይኖርበታል። ሌላ ልጨምርላችሁ።

የኢትዮጵያ ስራ አመራር ተቋም የሚባለው መንግስታዊ ድርጅት ይፋ ባደረገው ጥናት የኢትዮጵያ መንግስት በዓመት 18 ቢሊዮን ብር ያህል ለመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ይከፍላል። ይሄው ጥናት አክሎም ከ18 ቢሊዮን ብር ውስጥ 6 ቢሊዮን ብር ያህሉ በአግባቡ ወይም በስራ ገበታቸው ላይ ለማይገኙ/ምናልባትም ለሌሉ/ ሰዎች የሚከፈል እንደሆን በመግለጽ መንግስት የሕዝብን ገንዘብ ከብክነት ለማዳን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይመክራል። እኔም የምለው ይሄንኑ ነው። የተዛባውን የፊስካል አስተዳደር ፖሊሲ ለማቃናት የሕዝብ ገንዘብን ከብክነት መታደግ እና የመንግስት ወጭዎችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ አማራጭ የሌለው ዋና መፍትሄ ነው። ሁለተኛው እና ከዚያ ጋር አብሮ የሚሄደው ተጨማሪ መፍትሄ ደግሞ ግብር ቅነሳ ነው። ተመጣጣኝ ግብር ለተሻለ ስራ ከማዘጋጀት በላይ የገንዘብ ቁጠባን ባህል ይፈጥራል፤ የቢዝነስ አደጋን ለመውሰድና ገንዘብን ኢንቨትስ ለማድርግ ይበልጥ ያነሳሳል። ሰዎች ከግብር ቀሪ የሚያገኙት ትርፍ ሲያድግ ገቢያቸው ይጨምራል።ይህም ለመንግስት የግብር ተመን መሰረቱን እንዲያሰፋ ስለሚረዳው ገቢው ይጨምራል። ስለዚህ የገቢዎች ባለስልጣን ትኩረቱን “ግብር መክፈል ካለበት 40በመቶው አይከፍልም!” ካላቸው ሰዎች ይልቅ ለሚከፍሉት 60በመቶዎቹ  የግብር ቅናሽ ቢያደርግ ያጣውን ከፍተኛ ገቢ በቀላሉ ሊያሳድግ/ሊያካክስ  እንደሚችል ለመጠቆም እወዳለሁ። በዚህም ግብር ስለበዛባቸው ገቢያቸውን የደበቁት ግብር ከፋዮች የሰወሩትን ገንዘብ ወደ ገበያው እንዲመልሱ ስለሚገፋፋቸው “ግብር አይከፍሉኝም” ካላቸው  40በመቶዎቹ ውስጥ (ከወንጀለኞቹ በስተቀር) ወደ ሕጋዊ ማዕቀፉ ተመልሰው ስለሚገቡ ገቢዎች እንደተለመደው ህዝብ ሳያማርር እና ሳያስለቅስ ተጨማሪ ገቢ ያገኛል ማለት ነው። ይህ ይሆን ዘንድ የመንግስት ፕሮጀክቶች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያባክኑ “ግዴለም በጀት ይጨመርና ፕሮጀክቶቹ ይፈጸሙ” የሚለው የኢትዮጵያ ፓርላማ የገንዘቡ ባለቤት ለሆነው ህዝብ የቀጥተኛ ግብር(የደመወዝ፣የቢዝነስ ወዘተ) ተመን ጣሪያውን ተቀባይነት ባለው ደረጃ ዝቅ በማድረግ ህጉን ማሻሻል የተፋለሰውን የግብር ስርዓት ለማስተካከል  ጊዜው [እና የጠቅላይ ሚንስትሩ የዱይንግ ቢዝነስ ሪፎርም] የሚጠይቀው አንዱ ምላሽ/ግብዓት ይህ የግብር ቅነሳ ጉዳይ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብኝ እንደሁ አላውቅም።  ይህን ማድረግ በከፍተኛ ግብር ምክንያት ከኢኮኖሚው ተገፍተው የበይ ተመልካች የተደረጉ ወይም በዚያ ምክንያት ወደ ቢዝነስ ለመግባት የሚያመነቱ ዜጎችንም ለስራ ያነሳሳል፤መንግስት ጋርም ያቀራርባቸዋል።እስቲ ሻይ ቡና እያላችሁ፤በጎደለ እየሞላችሁ ሁላችሁም ተወያዩበት።

በመጨረሻም ድንበር ዘለል ንግድ የሃገር ኢኮኖሚን ስለሚደግፍ፣ከፍተኛ የስራ ፈጠራ ምንጭም ስለሚሆን እና የዜጎችን አማራጭ ተወዳዳሪ ገበያ የማግኘት መብት ስለሚያረጋግጥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና የምትገባበትን ስምምነት የጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አቢይ መንግስት ተቀብሎ በማጽደቅ የተጀመረውን የሪፎም ሂደት ተዓማኒነት ከፍ እንዲያደርገው እንደ ዜጋ ጥሪየን አቀርባለሁ። ይህን አፍሪካዊ የነጻ ንግድ ቀጠና ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ደቡብ አፍሪካ፣ ቻድ፣ ኮንጎ፣ ኮትዲቫር፣ ጋና ወዘተ 18 ሃገራት ሲያጸድቁት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ናይጀሪያ ግን ቀጠናውን ይቀላቀላሉ ተብሎ እየተጠበቁ ነው። ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ቴሌኮም ህብረት ውስጥ አለመግባቷ የጎዳው ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ነው። ኬንያዊያንም ሆነ ሌሎቹ ሃገራት በምስራቅ አፍሪካ ሲንቀሳቀሱ አዲስ ሲም ካርድ መግዛት ሳያስፈልጋቸው በተመሳሳይ ታሪፍ ስልካቸውን በሃገራቱ ይጠቀማሉ። ኢትዮጵያዊያን  ግን ያን ማድረግ አይችሉም። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የእነዚህ ሃገራት ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሃገራቸውን ስልኮች መጠቀም አይችሉም ነበር። ሆኖም ግን መንግስት ላይ ባሳደሩት ከፍተኛ ተጽእኖ ዛሬ ላይ የሃገራቱ ዜጎች የኢትዮጵያ ሲምካርድ ሳያስፈልጋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሃገራቸውን ስልክ  በነጻነት ይጠቀማሉ። አንድ ኢትዮጵያዊ ግን ወደነሱ ሃገር ሲሄድ የነሱን ሃገር ሲምካርድ ሳይገዛ ሊጠቀም አይችልም።የመንግስት ስህተት ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ገለልተኛ እና ተጎጅ ከማድረጉ ውጭ ምንም ያተረፈለት ነገር የለም። ይህን ዓይነት ስህተት ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ከሚመሩት መንግስት ስለማልጠብቅ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠናን መቀላቀል የሚያስችላትን ስምምነት የሚያጸድቁበት ቀን የለውጡ ጉዞ አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ መግቢያ ይሆናል።

Advertisement

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.