ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የድህነት እና የረሃብ ልዩነት ወይም ደረጃ እንዳለው የተረዳው ለረሃብተኞች በተካሄደ ‘የላይቭ ኤድ’ የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ነበር። በወቅቱ ለመላው ዓለም በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ስርጭት የሰውን ልጅ አንጀት ለማራራት በችጋር የተጎሳቆሉ የተለያዩ ሃገር ሰዎችን ምስል በቴሌቪዥን ያሳያሉ። ቢሆንም ግን እንደ ኢትዮጵያዊቷ ሕጻን ብርሃን ወልዱ ዓለምን ስለርሃብ የሚያይበትን መነጽር የቀየረ አልነበረም። ይህ የሆነው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ሐምሌ 13 ቀን 1985ዓ/ም ነበር። በኮንሰርቱ ላይ ከተሰበሰበው ገቢ ከግማሽ በላይ የተገኘውም በርሃብ እና በጠኔ የደቀቀው የኢትዮጵያዊቷ ሕጻን ምስል ከታየ በኋላ ነበር። የሕጻን ብርሃን ወልዱ ምስል የኮንሰርቱን ገቢ ከመጨመሩ ባሻገር አዲስ የድህነት ወለል መግለጫ ቃል ይፈጠር ዘንድ ምክንያት ሆነ። ዓለም ለመጀምሪያ ጊዜ ‘ኤክስትሪም ፖቨሪቲ’ የሚለውን ቃል ጥቅም ላይ አዋለ። ይህ የመጨረሻው የድህነት ጥግ መግለጫ ቃል ነው። በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብ 62በመቶ በዚህ የድህነት አዘቅት ውስጥ ይኖራል። ከ ‘ኤክስትሪም ፖቨሪቲ’ ሻል ያለው የድህነት ደረጃ ደግሞ ‘ዘርፈ ብዙ ድሃነት’ ይባላል።ይህኛው የድህነት አረንቋ የአንድ ሰው ንጽህና መጠበቂያ ማግኘት መቻል ወይም አለመቻል፣መማር እና ማስተማር መቻል እንዲሁም በትምህርት የመዝለቅና የማቋረጥ ሁኔታ፣ንጹህ ውሃ ማግኘትና ያለማግኘት ሁኔታ፣ሃብት ንብረት ማፍራት የመቻልና ያለመቻል፣የኤሌክትሪክ ብርሃን ማግኘትና ያለማግኘት፣መጠለያ የማግኘት ወይም ያለማግኘት፣ የሕጻናት ሞት መጠን፣የምግብ ማብሰያ/ነዳጅ ማግኘት ወይም አለማግኘት፣ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ወይም ያለማግኘትን ወዘተ የሚያካትት ነው። ከነዚህ መገለጫዎች ሶስቱን ማሟላት ወይም ማድረግ የማይቻል ‘ዘርፈ ብዙ ድሃ’ ነው። የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በሚያወጣው ዓመታዊ የመጠነ ሰፊ ድህነት መመዘኛ ሪፖርት ላይ (2018 OPHI) ኢትዮጵያ በዚህ የድህነት አዘቅት ውስጥ ባሉት 85ሚሊዮን ዜጎቿ ከሕንድ እና ከናይጀሪያ ቀጥላ ከዓለም ሶስተኛ ናት። ከ105 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ 9 በመቶ የሚያህለው ህዝቧ ደግሞ ወደ ድህነት አዘቅት ለመውረድ አፋፍ ላይ የቆመ ነው። ለምሳሌ ተጨማሪ የግብር ጫና ቢያርፍበት ወይም ከሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ አቅም ጋር የማይሄድ የመንግስት ግዝፈት እየጨመረ ሲሄድ ወይም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በማናቸውም ምክንያት ሲገታ ወይም ደግሞ የገንዘብ ግሽበት ሲባባስ በቀላሉ ‘ከድህነት ወደ ለየለት ድህነት’ የሚወርድ 9በመቶ ህዝብ አለ ማለት ነው።
ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ ደግሞ አንዱ ሳይሆን ሁሉም በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖሩም ከሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ አቅም ጋር የሚጣረስ የመንግስት የመግዘፍ ፍላጎትና ወጭን ለመሸፈን የታሰበውን የ12 በመቶ ግብር(ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርት ላይ የሚሰበሰብ) ከ17በመቶ በላይ የማሳደግ ፍላጎትን ብቻ እንመልከት። የገቢዎች ባለስልጣን ከሃገሪቱ የሚሰበስበውን የግብር መጠን ለማሳደግ ያቀደው መንግስት በግልጽ ወትሮውንም ከአቅሙ በላይ ግብር ለሚከፍለው ሕዝብ ቀጥተኛ የግብር ተመን ላይ ቅናሽ ማድረግ ባለበት ወቅት ነው። የዚህ አጭር ምክንያት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ ስለሆነ ነው። የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ሲያሽቆለቁል የዜጎች ገቢ ይቀንሳል ስለዚህ በግልጽ ቋንቋ ገቢው ከሚቀንስ ዜጋ ላይ መንግስት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ማሰቡ በኢኮኖሚክስ ብቻ ሳይሆን ከሞራልና ከምክንያታዊነት አንጻርም ሚዛን አይደፋም። ገቢያቸው የሚቀንስ ዜጎችን ከላይ የጠቀስነውን የባሰውን የድህነት ጎራ እንዳይቀላቀሉ እና መስራት ያለባቸውን ስራ ያለጭንቀት በማከናወን ምርታማነት እንዲጨምሩ እንዲሁም ገንዘብ በማውጣት ገበያውን እንዲያነቃቁ እና በዚህም አምራቾች ሰራተኞቻቸውን በመቀነስ ወይም ስራ በማቆም ፈንታ የምርት ሂደታቸውን እንዲቀጥሉ ግብር መቀነስ ይኖርበታል።የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ቢያደርግ ዜጎቹን ከባሰ የድህነት አዘቅት ይታደጋቸዋል እንጅ የሚያጣው አንዳች ነገር አይኖርም። ለምን ቢባል ወትሮም ቢሆን በግብር ስም የሚወስደው ገንዘብ እንደሃገር መንግስት መውሰድ ካለበት ግብር 2 እጥፍ የሚበልጥ ነውና! ይህ የሆነውና እየሆነ ያለው ደግሞ “ይህን ያህል አምጣ” የሚል ደመነፍሳዊ ግምት እና ጉልበት ላይ ብቻ በተመሰረተ የግብር አሰባሰብ ዘዴ አማካይነት ነው። ግብር ከሰማይ የሚወርድ መና አይደለም። ይህን ሃቅ መንግስትና የገቢዎች ባለስልጣን መረዳት አለባቸው።

ራሱ የገቢዎች ባለስልጣን አደረኩት ባለው ጥናት መሰረት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ በአማካይ 12በመቶ ያህሉን በግብር መልክ ይሰበስባል።በጣም ጥሩ! ይህ በተግባር ተሞክሮ ገቢዎች ከኢኮኖሚው ላይ በግብር መልክ የሰበሰበው ገንዘብ ልክ ነው። የገቢዎች ባለስልጣን ‘በአማካይ’ ስላለ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ካምናው በ2.7 በመቶ ቢቀዛቀዝም ይህንን ለእኛም አማካይ አርገን ዕድገቱ አምና እንደነበረው አድርገን ቆጥረን ወደፊት እንሂድ።
ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት 12በመቶ ያህሉን በግብር የሚሰበስበው የገቢዎች ባለስልጣን የዚህ ቁጥር(12%) ኢኮኖሚ ነጸብራቅን ፈጽሞ በሚጻረር መልኩ በግለሰቦች ላይ እስከ 35በመቶ ግብር ይጥላል። በቁጥሮቹ መሃል ያለው ልዩነትን ያህል የግብር ጫና በግብር ከፋዩ ላይ ያርፋል። በቀጥታ ኑሮውን ይፈትናል ማለት ነው። የገቢዎች ባለስልጣን ከዓመታዊ ምርት 12 በመቶ ከሰበሰበ የሃገራችን ኢኮኖሚ እና ግብር ከፋዩ ህዝብ ጋር የሚጣጣመው የቀጥተኛ ግብር (ዳይሬክት ታክሴሽን ማለትም የደመወዝ ግብር፣የኪራይ፣የቢዝነስ ወዘተ) ከፍተኛ የግብር ጣሪያ 12 በመቶ መሆን ይኖርበታል። ቀጥተኛ ያልሆነውን የግብር ተመን ጣሪያም እንደ ሃገሪቱ የኢኮኖሚና የገበያ እንቅስቃሴ የሚተመን ሆኖ የግብር ምንጩን በማስፋት ገቢውን ልያሳድግ ይችላል።
ከዚህ ውጭ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሳይቀየሩ መንግስት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ስለፈለገ ብቻ ሊያገኝ አይችልም። ምክንያቱም መንግስት ስለፈለገ ከሰማይ እንደ መና ገንዘብ ማውረድ የሚችል ግብር ከፋይ የለምና!! ሆኖም ግን ሃገሪቱ በድንገተኛ ግጭት እና አለመረጋጋት እንዲሁም ውጫዊ ጫና ያለባት ከሆነ ወይም የጦርነት አደጋ ከተጋረጠባት በግምት ሳይሆን ከፍተኛ የግብር ጥሪያ መሆን የሚገባውን 12በመቶ በእጥፍ በመጨመር ወደ24በመቶ ማሳደግ ይቻላል። ይሁንና ይህ ተጨማሪ የ12በመቶ ግብር የተባለው አደጋ በሚወገድበት ጊዜ መነሳት ይኖርበታል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግብር ተመን መሰብሰብ ካለበት 12በመቶ እና ድንገተኛ አጋጣዊዎችን አስታኮ ሊደረግ ከሚችል የግብር ጭማሪ(12በመቶ) ድምር ውጤት ይበልጣል። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ በድህነት አረንቋ ተዘፍቆ የሚኖረውና የመንግስት ግዝፈት በየጊዜው እየጨመረ የሄደበት አንዱ ምክንያት ሕዝቡ ከአቅሙ በላይ ግብር ስለሚከፍል ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በላይ ሊወርድበት የሚችለው የድህነት አዘቅት የለም። ከድህነት ብዛት የልጆቹን ጠኔ እንኳ ማስታገስ ያቃተው ከግማሽ በላይ የሃገሪቱ ሕዝብ ሰው ሊኖርበት የማይገባውን ሕይወት የሚገፋው መጀመሪያውኑ ጥሪቱን በግብር መልክ ሲገፈፍ ስለኖረና እየተገፈፈም ስለሆነ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎቱን በመግታት በባዶ እግሩ እየሄደ ለባለስልጣናት ዘመናዊ መኪና ለሚቀያይረው እና ልጆቹን ለማስተማርም ሆነ ለማሳደግ አቅም ከከዳው ድሃ ህዝብ ጫንቃ ላይ የግብር ጫናውን እንዲያነሳ እንደዜጋ ጥሪየን አቀርባለሁ። ከዚህ ተቃራኒ መሄድ ደንን ቆርጦ ደኑን ከመቁረጥ ባነሰ ወጭ ምርት በማምረት ፋንታ ደኑን ጨርሶ በእሳት አውድሞ አመድ እንደማፈስ ነው። ይታሰብበት።