የአሜሪካ ምስረታ የነጻነት ሰነድ ላይ “መንግስት ለዜጎች የሚሰጠው መብት የለም፤የተቋቋመው ቀድሞውኑ የነበራቸውን መብት ለመጠበቅ ነው።” ይላል። ከዚህ መግቢያ ተነስቼ በቀጥታ ወደ ጥንት ልውሰዳችሁማ። አይ! መግቢያ አያሻኝም የሚል ደግሞ ችግር የለውም ወደፊት እንጅ ወደኋላ ለመሄድ የመግቢያ ክፍያ ስለሌለ የጊዜ ፈረስን በጋራ የኋሊት እንጋልብ። ድሮ….ድሮ…..ድሮ…… እንዲህ ሆነ።አዎ! አሁን እየደረስን ስለሆነ ልጓምዎን ጠበቅ አድርገው ይያዙ። እና ያኔ ጥንት የተወለዱትን ሁለት ነገሮች እዚህ ግድም ለማየት መቃኘት እንጀምር። ሁለቱም ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። እነዚህ ሁለት ቡድኖች ሁለት ዓይነት የመኖሪያ/የእንጀራ ገመድ ዘርግተዋል። አንደኛው የኢኮኖሚ ገመድ ሲሆን ሁለተኛው በፖለቲካ የሚገኝ እንጀራ ነው። የኢኮኖሚው ገመድ በግልጽ አነጋገር በስራ የሚገኝ ሲሆን ፖለቲካው ደግሞ የንጥቂያና የዘረፋው መንገድ ነው። የንጥቂያና የዘረፋው መንገድ የወንበዴዎቹ የገቢ ምንጭ ነው።እነዚህ ወንበዴዎች ተዘዋዋሪ ናቸው። ስራ ጋር ስለማይተዋወቁ ያገኙትን ይዘርፋሉ። ይነጥቃሉ። ከነሱ የተረፈውን እና መንጠቅ ያልቻሉትን በእሳት ለኩሰውት ይጠፋሉ። ደግሞ ሌላ ቦታ ይሄዳሉ። ተመሳሳይ ድርጊት ይፈጽማሉ። የገበሬወችን ምርት እና ነጋዴወችን ገንዘብ በተለያየ መንገድ እና በተለያየ ጊዜ በየጊዜው ድንገት እየተከሰቱ ጥሪቱን ያራቁታሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ በየጊዜው የሚሰሩት እና የሚዘረፉት ሰወች የስራ ተነሳሽነት እየጠፋ ሲሄድ የሚያፈሩት ሃብት እየተመናመነ ሄደ። በዚህ ጊዜ የሚዘረፈው ሃብትም እያነሰ በመሄዱ በዘራፊዎቹ ወንበዴዎች መሃል የጥቅም ግጭት የማይቀር ሆነ። ይህ ሂደት በጉልበት የበለጠውን የውንብድና ቡድን ሌሎች ወንበዴወችን ካልተከላከለ ህልውናው አደጋ ላይ መውደቁን አስተዋለ። ስለዚህ ጉልበቱን ተጠቅሞ ውንብድናውን ለብቻው ለማድረግ ሌሎች ወንበዴዎችን በመምታት በሃብት ካራቆቷቸው ሰዎች ላይ በትንሽ በትንሹ ዝርፊያውን ቀጠለ። ይህ ከቀድሞው የሚሻል ዓይነት ዘረፋ ስለሆነ በድንገት እየመጡ ከሚያራቁቱት ዘራፊወች የተገላገለው ሰራተኛም አልተቃወመውም።
እንግዲህ የግብር እና የመንግስት አመጣጥ ታሪክ ይሄው ነው። ከሚሰሩ ሰወች ላይ በትንሽ በትንሹ የሚደረገው ንጥቂያ በዘመናዊ አጠራሩ ግብር ሲባል ጉልበተኛው ወንበዴም ዛሬ ላይ መንግስት ብለን የምንጠራው ተቋም ነው። እንግዲህ መንግስት ሀ ብሎ ሲጀመር የዜጋውን የዕለት ተዕለት ሰላማዊ እንቅስቃሴ፣የሰራተኛውን የላብ ውጤት፣ሃብትና ንብረት በብቸኝነት የያዘውን ሃይል በመጠቀም ከወንበዴወች ለመጠበቅ የተቋቋመ ተቋም ነው።ለዚህ አገልግሎቱ የሚከፈለው ክፍያም ግብር ይባላል። ሁላችንም መረዳት ያለብን ሃቅ በፖለቲካ መስመር ገቢ የሚያገኘው መንግስት በእግሩ ይቆም ዘንድ ዜጎችን በነጻነት የሚያሰራ ምቹ የኢኮኖሚ ሁኔታ መፍጠር ግዴታው መሆኑን ነው። ለአንድ ሃገር እጅግ የከፋ የሚሆነው ከላይ እንዳነበብነው ከጥፋታቸው ተምረው በትንሽ በትንሹ በሚዘርፉት ቋሚ ወንበዴዎች ፋንታ መጥፋት ያለባቸው ተዘዋዋሪ ሽፍቶች በጉልበት በልጠው ሲገኙ ነው። ሽፍቶች የመንግስት ስልጣን ድንገት ካልሆነ በቀር ሊይዙ አይችሉም። ስልጣን ሲይዙ የሚፈጽሙት እኩይ ድርጊቶች ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ ተፈጽሟል። ተዘዋዋሪ ሽፍቶች የኔ የማይሉት ማህበረሰብ ላይ በዘላቂነት እንደማይኖሩ ስለሚያውቁ ግብር ከፋዩን ከአቅሙ በላይ ግብር ይጭኑበታል። በተጨማሪም ፖለቲካን የግል የገቢ ምንጫቸው ያደርጉታል። በሁለት የፖለቲካ የገቢ ምንጭ ማለትም በከፍተኛ ግብር እና የጥንቱን ንጥቂያ በሚያስመኝ ዓይን ያወጣ ዘረፋ ፍዳውን ያየው ህዝብም ወደ ድህነት አዘቅት ይወርዳል።በዚያው ልክ የማህበረሰቡ ዕድገት ይጨነግፋል። የነገ ተስፋው ይጨልማል። ለተዘዋዋሪ ወንበዴወች ይህ ጌጣቸው ነው። ሌሎች ኢሞራላዊ ድርጊቶችን ጨምሮ ዘረፋን እንደ ስራ ይሰብካሉ። ምክንያቱም ተዘዋዋሪ ናቸውና በነሱ ዘንድ የሞራል ቅንጣት፡ይሉኝታና ሃፍረት ቦታ የለውም። ይህን ህዝብ ነገ በማናቸውም ጊዜ ይከዱታል። ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ሕወሃት የተዘዋዋሪ ሽፍቶች ህያው ምሳሌ ነው።
“የአፍሪካ ሃገራት በአማካይ ከአጠቃላይ ምርታቸው 17በመቶ ያህል በግብር መልክ ስለሚሰበስቡ ኢትዮጵያም ያን ማድረግ አለባት።” የሚለው ከሕወሃት ኢኮኖሚያዊ ድንቁርና የመነጨ የምኞት ነጋሪት ነበር። ዶ/ር አቢይ ይህን ነጋሪት መጎሰም አልነበረባቸውም። ምክንያቱም የሳቸው ዘመቻ በመጨረሻው ውጤት ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይታየኝም። የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የምትሄድበት ጎዳና ትክክል ካልሆነ በላይም ሆነ ተክላይ የሚፈጥሩት ልዩነት የለም። የፖለቲካ ጉዞ ላይ ግን በተመሳሳይ ጎዳና የተጓዙ ሁሉ መዳረሻ ውጤታቸው ላይ ሁሌም ልዩነት የሚጠበቅ ነው።
እንደ ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት መረጃ ከሆነ በያዝነው ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2.7 በመቶ ቁልቁል ይወርዳል። ይህ ማለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት አምና ከነበረው የ10.2 በመቶ ወደ 7.5 በመቶ ያሽቆለቁላል ማለት ነው። በቀላል ቋንቋ በግብር ከፋዩ ላይ ካምናው የበለጠ የኑሮ ውድነት፣ የገንዘብ ግሽበት እና የመንግስት በጀት ጉድለት እንደሚሰፋም የሚጠበቅ ነው ማለት ነው።የዕድገቱ መገታት ነጋዴው እና የግል ቢዝነሶችን ስለሚፈትን የሚያስፋፉት ቢዝነስ እና የሚፈጥሩት ስራ አናሳ ነው። የነሱ መዳከም የሃገር ኢኮኖሚ እድገትን ይበልጥ ወደ ኋላ ይጎትተዋል። መንግስት ለዚህ ምላሽ መስጠት ያለበት በዋናነት ሁለት ነገሮችን በማድረግ ነው። አንደኛ ወጭዎቹን እጅግ በጣም በመቀነስ ማለትም ለፖለቲካዊ ድግሶች የሚያወጣውን ወጭ ማቆም፣ ከሃገር ውስጥ ብድር መበደሩን ማቆም፣ የጀመራቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ማቆም እና ለባለሃብቶች መሸጥ(ፕራይቬታይዝ ማድረግ)፣ ከጥቅማቸው ወጭያቸው የሚያመዝኑ ሁሉንም የመንግስት ተቋማትን እና ኮሚሽኖችን በሕግ ማፍረስ ወዘተ ይጠበቅበታል። ሁለተኛ ደግሞ እያሽቆለቆለ ያለውን የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በፍጥነት ስራ ማዋል ይኖርበታል።
የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሃቅ ጋር የሚጣረስ መንግስታዊ ዕቅዶችን ለማስፈጸም በፈለገ ጊዜ ቴምኔታዊ ዕቅዱን በማሻሻል ወይም ጨርሶ በመተው ፈንታ ግብር ከፋዩን ሕዝብ “ይህን ያሕል አምጣ” እያለ እንዳያስጨንቅም ራሱ መንግስት ላይ ልጓም ማበጀት (ገዳቢ ሕግ ማውጣት) ያስፈልጋል። ግብር ለመንግስት ሕልውና ነው ማለት የሚጠበቅበት ግዴታም አለ ማለት ነው። ግብርና ሞት የሚያያዙትም በዚሁ መልኩ ነው።