ግብር እና ሞት

መንግስት የዜጎችን ሰላማዊ ህይዎት፣ ነጻነት፣ እና ንብረት የመጠበቅ ግዴታውን ይወጣ ዘንድ ግብር መሰብሰብ ይኖርበታል። ይህ የማይታበል ሃቅ ነው። በግብር መልክ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለተለያዩ የጤና፣ የትምህርት፣ የመከላከያ እና ሌሎች ለህዝብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የመንግስት ወጭዎችን ለመሸፈን ይውላል። በተጨማሪም ግብር ነጋዴው በገበያ ላይ ለማዋል የማይችላቸውን ወይም ለገበያ ለማቅረብ አዳጋች የሆኑ ህዝባዊ እቃዎችን እና አገልግሎቶችን (ፐብሊክ ጉድስ) ለዜጎች ለማቅረብ ይጠቀምበታል። ሆኖም ግን ግብር መንግስት ገቢ ስለፈለገ ብቻ ‘ይህን ያህል ክፈሉ’ የሚባል የገቢ ምንጭ አይደለም። አንድ ግብር ከፋይ ከሚያገኘው ትርፍ ወይም መንግስታዊ አገልግሎት አንጻር በላይ ግብር የመክፈል ግዴታ የለበትም።

ይህ ማለት ግብር የሚሰበሰበው የግብር ከፋዩን ገቢ እንጅ መንግስት ሊሰራ ያሰበውን መንግስታዊ ፕሮጀክት ከግምት ውስጥ በማስገባት አtይደለም ማለት ነው። የትም ሃገር ቢሆን ግብር ከፋዮች ከአቅማቸው በላይ ግብር የሚጫንባቸው ከሆነ ወይ ሽያጭ በመደበቅ መንግስት የጣለባቸውን ግብር ለማቅለል ይሞክራሉ፤ አሊያም ደግሞ ድርጅታቸውን ዘግተው ወደ ሕገወጥ(አየርባየር፣ኮንትሮባንድ ወዘተ) ዓይነትንግድ ይገባሉ፤ምናልባትም ደግሞ ጭራሹኑ ንግድ ፈቃዳቸውን መልሰው ስራቸውን ያቆማሉ።ሁሉም ያለአግባብ እና ያላቅማቸው ከፍተኛ ግብር በመጫን “ተጨማሪ ገቢ አገኛለሁ” ያለውን መንግስት ‘ጽድቁ ቀርቶብኝ•••’ እንዲሉ ቀደም ሲል ያገኝ የነበረውንም ገቢ ያሳጣዋል። ይህ የሚሆነው የተጣለው ግብር በከፋዩ ላይ በሚፈጥረው አይቀሬ የባህሪ ለውጥ ምክንያት ነው። የ50ሽህ ብር ሸቀጥ የያዘ ባለ ሱቅን 30ሽህ ብር ግብር ክፈል ካልከው ውጤቱ ይሄው ነው። ይህ እውነታ ‘ለሃገሬ’ በሚል በጎ ምኞት አይቀየርም። ምክንያቱም ሃብትና ገንዘብ እንደ በጎ ምኞት ገደብ አልባ አይደሉም። ልክ እና ገደብ አላቸው። ይህ “ግብር እና ሞት ሁለት አይቀሬ የመኖር ዕዳ ናቸው።” በሚሉት እንግሊዛዊያን ዘንድም የሚታይ ዕውነታ ነው። ለዚህ ነው ግብር ጊዜውን፣ የሕዝቡን ኑሮ እና የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል የሚባለው! ከዚህ አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ ትናንት ያወጀችው የግብር ዘመቻ ከነባራዊ የሃገሪቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕውነታ ጋር የሚጣረስ ነው።

ልብ አድርጉ! በ2010ዓ/ም  የገቢዎች ባለስልጣን 230 ቢሊዮን ብር  ለመሰብሰብ አቅዶ 190 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል።በዚህ ስሌት መሰረት 50ቢሊዮን ብር ያህል ገንዘብ አልተሰበሰበም ማለት ነው። ከዚያ ቀደም ባለው የ2009ዓ/ም ደግሞ 190 ቢሊዮን ብር  ለመሰብሰብ ያቀደው የገቢዎች ባለስልጣን 160 ቢሊዮን ብር  ገቢ አግኝቷል። በዚህኛውም የ30ቢሊዮን ብር ያህል ክፍተት አለ። የገቢዎች ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት 12በመቶ (የሲኣይኤ መረጃ13.9 በመቶ ይላል)  ያህል በግብር መልክ ይሰበሰባል።

የገቢዎች ባለስልጣን ይሄንን የ12 በመቶ ገቢ በያዝነው ዓመት 17በመቶ ለማድረስ አቅዷል። ለዚህም መሳካት የግብር ከፋዩን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችል ዘመቻ ከፍቷል። የግብር አምባሳደሮችንም ሹሟል። ከላይ ያለው መረጃ በግልጽ የሚያሳየው ግን ግብር ሰብሳቢው አካል የመንግስትን ገቢ ለማሳደግ በግምት ላይ የተመሰረተ ጫና በግብር ከፋዮች ላይ እንደሚጭንና ስለ ግብር ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ነው።

መንግስት ከአጠቃላይ አመታዊ ምርት 17በመቶ ያህሉን ገቢውን ከግብር ለማግኘት ያቀደው “የአፍሪካ ሃገራት በአማካይ ከአጠቃላይ ምርታቸው 17በመቶ ያህል በግብር  መልክ ይሰበስባሉ።ስለዚህ ኢትዮጵያም ያን ማድረግ አለባት።” በሚል ከጅምሩ የከሸፈ መርህ አልባ የግብር አሰባሰብ ‘ዘዴ’ ነው። በምስራቅ አፍሪካ ትልቁን  ኢኮኖሚ የገነባቸው ኬንያ ባላት ከፍተኛ የገበያ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምክንያት ከጠቅላላ ሃገራዊ ምርቷ 17.6በመቶ ግብር ትሰበስባለች። መንግስት ስለፈለገ ግብር ከፋዩን እንደ ኬንያ ‘ይህን ያክል ግብር ክፈል’ ማለት የሚችልበት ሕጋዊ መሰረት የለም። እንዲሁም ግብር የሚጣለው በሃገሪቱ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ነጋዴውና ኢንተርፕርነሩ ከሚያገኘው ገቢ አንጻር ተሰልቶ እንጅ የሌሎች ሃገራት ገቢ ይሄን ያህል ስለሆነ የኛም እንዲህ ቢሆን በሚል ከንቱ ምኞት አይደለም።

ይሄን የችኮላ ዕቅድ ከምኞት በላይ  ቅዠት የሚያደርገው ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት አምና ከነበረው የ10.2 በመቶ ወደ 7.5 በመቶ ባሽቆለቆለበት ወቅት መምጣቱ ነው። እንደ ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት መረጃ ከሆነ በያዝነው ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2.7 በመቶ ቁልቁል ይወርዳል። ይህ ጥሩ ዜና አይደለም።ከድህነት ብዛት የልጆቹን ጠኔ እንኳ ማስታገስ ያቃተው ከግማሽ በላይ የሃገሪቱ ሕዝብ ሰው ሊኖርበት የማይገባውን ሕይወት የሚገፋው መጀመሪያውኑ ጥሪቱን በግብር መልክ መንግስት ስለገፈፈው ነው። ሕዝቡ በሚከፍለው ግብር ምትክ ከመንግስት  ያገኘው የተሻለ አገልግሎት እና አስተዳደር ቢኖር ኖሮ የድህነት አድማሳችን አሁን ባለንበት ደረጃ አይሰፋም ነበር። ግብር እና ሞት አይቀሬ የመኖር ዕዳ ቢሆኑም የግብር ተመን አቅምንና ገቢን መሰረት ከማድረግ ይልቅ በግምትና በጉልበት የሚጫን ከሆነ እንደ ታላቋ ሮማ መውደቅ እንዳለም ከታሪክ መረዳት ይኖርብናል።

Advertisement

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.