የመንግስት ወጭ እና የኢትዮጵያዊያን ኪሳራ

0229የአንድ ሃገር መንግስት የገቢ ምንጭ ከሃገር ውስጥ የሚሰበስበው ግብር ነው። ሆኖም መንግስት በሚሰበስበው ግብር ልክ ዕቅዶችን አውጥቶ ተፈጻሚ ማድረግ ካልቻለ ልክ አንድ ግለሰብ ከገቢው በላይ የሚፈልገውን ወይም የሚያምረውን ነገር ለማድረግ ሲሞክር ችግር እንደሚደርስበት ሁሉ ችግር ይገጥመዋል። ይህን ጊዜ መንግስት ሌላ ገንዘብ ማግኛ ዘዴ ይፈልጋል። በዚህም መሰረት ወደ አበዳሪዎች ይሄዳል ማለት ነው። መንግስት ብድር ከሃገር ውስጥ እና ከውጭ ሃገር ሊያገኝ ይችላል። በሃገር ውስጥ ለባለሃብቶች ቦንድ በመሸጥ ገንዘብ ሊያገኝ ይችላል። የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች የመንግስትን ብድሩን የመክፈል አቅም ከተጠራጠሩ ወይም መግዛት ካልፈለጉ አይገዙትም። በዚህ ረገድ መንግስት እንደ ግለሰብ ተበዳሪዎች ያን ያህል ችግር አይገጥመውም። ምክንያቱም ለመንግስት ለሚያበድሩ ባለሃብቶች መተማመኛ ሰነድ (ቦንድ) የሚሰጠው ብሄራዊ ባንክ ራሱ ለመንግስት የፈለገውን ገንዘብ ያበድረዋልና ነው። መንግስት ከሃገር ውስጥ በተለያየ መንገድ የሚበደረውን ገንዘብ ከነ ወለዱ የመክፈል አቅም አለው። ይህ አቅሙ የሚመነጨው ደግሞ በዜጎች ላይ ግብር መጣል እና የገንዘብን የመግዛት አቅም ማጋሸብ ከሚያስችለው ስልጣኑ ነው። ብዙ ጊዜ መንግስት እንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ የሚገባው በሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ከሃገሪቱ አቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ሲፈጠርም (ለምሳሌ ጦርነት እና የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት) ብድር ውስጥ የመግባት አጋጣሚ ይኖራል። በዚህ እና በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያ ከውጭ ሃገር አበዳሪ መንግስታት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ወደ 30ቢሊዮን ዶላር ገደማ ዕዳ አለባት።

በዶ/ አቢይ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ዕዳ ለመክፈል የኢትዮጵያን አየር መንገድን እና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትን በሙሉ እና በከፊል ፕራይቬታይዝ  ለማድረግ መወሰኑ ትልቅ እርምጃ ነው።መንግስት ለሰራተኞቹ ደመወዝ ለመጨመር የነበረውን ፍላጎት መግታቱም ይበል የሚያሰኝ ውሳኔ ነው። ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን መንግስት ወጭዎቹን ልብ ብሎ መፈተሽ እና ማጤን ይኖርበታል። ምክንያቱም የመንግስት ወጭ እየበዛ በሄደ ቁጥር የዜጎች ኢኮኖሚያዊ አቅም በዚያው ልክ መፈታተኑ አይቀሬ ስለሆነ ነው። 

የመንግስት ምላሽችግር የለውም ወጭየን ብጨምርም የግብር ተመን በመጨመር አካክሰዋለሁ።የሚል ከሆነ ውጤቱ የባሰ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በአማካኝ 3በመቶ ያህል ግብር ለመጨመር እንዳሰበ እና ይሄም በጥናት ላይ እንደሆነ ከኢቢሲ ዜና የሰማሁ ይመስለኛል። ይህ ግን ለኢትዮጵያዊያን እና ለኢትዮጵያ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደማለት ነው። ምክንያቱም እንደ ዕውቁ የኢኮኖሚ እና የልማት ተቋም OECD ላለፉት 20ዓመታት በተለያዩ ሃገራት ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በአንድ ሃገር ላይ የሚደረግ የአንድ በመቶ (1%) የግብር ጭማሬ ወይም ግብር ከፋዮች ላይ የሚጣል የአንድ በመቶ (1%) ግብር የሚፈጥረው ግፊት ሃገራዊ ምርትን 0. 3 በመቶ በቀጥታ እንደሚቀንስ ያሳያል።በቀጥታም ባይሆን ደግሞ በኢንቨስትመንት ላይ 0.6–0.7 በመቶ አሉታዊ ተፅእኖ ይፈጥራል።ይህኛው መንገድ መንግስትን ሁልጊዜም ቢሆን ኪሱ እንዳይሞላ በማድረግ በመጨረሻም ሽባ ያደርገዋል። ምክንያቱም የኢኮኖሚ እድገት ሲገታ የበጀት ክፍተቱ ይበልጥ ይባባሳል። ይህም መንግስትን አጣዳፊ የሆነ የገንዘብ እጥረት ውስጥ ስለሚከተው ሌላ ብድር ፍለጋ ወደ መሄድ ይገባል። ይህ ደግሞ በአንጻሩ ጥሮ አዳሪውን ህብረተሰብ፣ነጋዴውንና ባለሃብቶችን ከሃገር ውስጥ ባንኮች ለኢንቨስትመንት የሚሆን ገንዘብ ማግኘት አዳጋች ስለሚያደርግባቸው ቢዝነሶች አይስፋፉም። ስለዚህም አዳዲስ ስራዎች አይፈጠሩም። የሃገሪቱ ዋነኛ ችግር የሆነው ስራ አጥነት ከተባባሰ ደግሞ ኢትዮጵያ ሌላ ምስቅልቅል ውስጥ እንደምትገባ አያጠራጥርም። ይህም ብቻም አይደለም፤እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን የተመቻቸች የኑሮ ደረጃ ላይ ለማድረስም ሆነ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያደርገው ጥረት ይጨናገፋል ማለት ነው። ይህ እንዳይሆን ቢያንስ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን 400ሽህ ያህል ስራ በኢትዮጵያ መፈጠር አለበት። እነዚህን ተያያዥ እና የማይነጣጠሉ ችግሮች ለማቃለል መንግስት ሊወስዳቸው ከሚችለው ዘላቂ የመፍትሄ መንገዶች ውስጥ ዋነኛው መንግስት ከአቅሙ በላይ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች ፕራይቬታይዝ በማድረግ መሸጥ ሲሆን ያልተጀመሩትን ደግሞ ፈጽሞ መተው ነው። ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት እቅዱን ድጋሚ በመከለስ ወጭዎቹን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ መንግስት ቢያንስ ቢያንስ በአንድ በመቶ(1%) ወጭውን ቢቀንስ  እንኳ በኢኮኖሚው ጅዲፒ ላይ 0.16በመቶ ጭማሪ የመፍጠር ያህል ኢንቨስትመንት እንደማለት መሆኑን ልብ ይሏል።

በአጠቃላይ መንግስት የጀመራቸው የለውጥ ጉዞ/የሪፎርም መንገዶች ማለትም የገለልተኛ የፍትህ ሥርዓት መፍጠር፣ በብዙ ሸቀጦች ላይ የተደረገ እና ለመደረግ የታሰበው የቀረጥ ቅነሳ፣ለንግድ እንቅስቃሴ እንቅፋት የሚሆኑ ህጎችን ማንሳቱ እና ለማንሳት ማሰቡ እንዲሁም በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ውስን ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ ለአንድ ሃገር ዘላቂና አስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ስለሆኑ የሚበረታታ ነው።

Advertisement

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.