(By Redeat Bayleyegn)ኢትዮጵያ እና የመንግስት ግዝፈት!
ጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ ከአራት ወራት በፊት ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርገው ነበር:: ስልጠና ቢባል በሚሻለው ስብሰባ ላይ የሚከተለውን ገልፀው ነበር:: እንደ ጠቅላይ ሚንስቴር የመጀመሪያ የስራ ቀናቸው ዕለት ጠረጴዛቸው ላይ የ120 ሰዎች ውጭ ሃገር ሄዶ ለመታከም ማመልከቻ ጠብቋቸዋል:: የመጏጏዣ ቲኬትን አያጠቃልልም:: የነዚህ 120 ሰዎች ጥያቄ ብቻ ሂሳቡ ወደ 6 ሚሊዮን ብር እንደሚጠጋ አስልተውታል:: የኢትዮጵያ መንግስት በአመት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለውጭ አገር ህክምና እንደሚያወጣም ተናግረዋል:: 1 ቢሊዮን ዶላር! በስራ እያሳበቡ በአመት 10 ግዜ ከአገር የሚወጡ ግለሰቦችም እንዳሉ ነግረውናል::
እስቲ አስቡት!
ኢትዮጵያ አብዮት በሚባል መከረኛ መንገድ መሄድ ከጀመረችበት ከ1966 ጀምሮ መንግስት እንደ ሐረር ሰንጋ በሬ እየፋፋ አሁን ያለበትን ቅርፅ ይዟል:: እንደው ለይስሙላ ካልሆነ በቀር የመንግስትን ግዝፈት እንደ ትልቅ ችግር ቆጭቶት የሚናገር ፖለቲከኛም ሆነ ፓርቲ እስከ አሁን አይስተዋልም:: መንግስትን ስለመቀየር እንጂ እንደዚህ አይነቱን የመንግስት ወጪ እና ብክነት እንደ ቁምነገርም የሚያሳስበው ወደ አጀንዳነት ሊያመጣው ይገባል:: ይሄ ብክነት እና የመንግስት ወጪ ደግሞ በሁሉም የአገሪቷ አወቃቀር ውስጥ ስላለ አገር መሸከም ከምትችለው በላይ ይሆንና አገር ያፈርሳል:: የመንግስት ልክ ያጣ ወጪ ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየውን የኢኮኖሚ ግሽበት (inflation) እና የኑሮ ውድነትን አምጥቷል:: ለለውጥም እንቅፋት ይፈጥራል:: ትንሽ ምሳሌ ልስጥ!
በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሳይቀሩ የሚኖሩት በግል ቤታቸው ነበር:: በክፍለሃገር ለስራ እና ከከተማ ውጭ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት የሚያርፉባቸው የተወሰኑ ቤቶች ካልሆኑ በስተቀር “የመንግስት ቤት” የሚባል የበጀት ፀር አልነበረም:: አብዮተኞቹ ግን ባለፉት 44 አመታት ከግለሰብ በወረሱት ቤት እና ቤተ መንግስት ነው የሚኖሩት:: ከገጠር እስከ ከተማ ከቀበሌ ሊቀመንበር እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በወያኔ ዘመን ደግሞ ምንም ጥቅም በማይሰጥ ፕሬዚዳንት በሚባል ስልጣን የተቀመጠው ሁሉ የሚኖረው በ”መንግስት” ቤት ነው:: ከመንግስት የወጣውም ለምሳሌ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በወር 400,000 ብር ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት:: ሌሎችን እናንተ ጨምሩ:: እነዚህ መኖሪያዎችን ለማስተዳደር (maintenance) እና ከገበያ ዋጋ በታች ለማከራየት (ወይም በነፃ) ለማስተዳደር ኢትዮጵያ የምታጣውን ገቢ አስቡት::
አብዮተኞች “ፈላጭ ቆራጭ” ያሏቸው ንጉሠ ነገሥት በመጨረሻው ዘመናቸው ያውም የኤርትራ አማፅያን እና ሶማልያ እያስፈራሯቸው አገሪቷን በ40 ሺህ ጦር ነበር የሚያስተዳድሯት (እነ ጥላሁን ገሠሠን ጨምሮ):: የደርግን ዘመን ትተን በወያኔ ዘመን የመከላከያ ሰራዊቱ እስከ 250 ሺህ እንደሚደርስ ይነገራል:: ይሄ ጦር ከደሞዙ እስከ ጥይቱ ይህች ደሃ አገር ላይ ያለውን የበጀት ሸክም አስሉት እስቲ!
ኢትዮጵያ የካድሬ እና የፖለቲካ ጥገቶች አገር መሆኗን ደግሞ አትርሱ:: በ2010 የኢሕአዴግ ፓርቲዎች ለየግላቸው እና በጋራ ያደረጏቸውን ስብሰባዎች መለስ ብላችሁ አስታውሱ:: የስብሰባዎቻቸው እርዝመት የሚገርም ነው:: የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ (45 ሰው) ለ38 ቀን ተሰበሰበ የሚለውን አንብበህ ሳትጨርስ ኦህዴድ ለ20 ቀን የደቡብ ህዝብ ፓርቲ ለ15 ቀን …. አማራው ለእንደዚህ ያህል ቀን በተከታታይ ተሰብስቦ … የሚል ዜና ትሰማለህ:: እነዚህ ስብሰባዎች በአገሪቷ ስራ ክንውን ላይ የሚኖራቸውን ችግር እንኳን ብንተወው ለነዚህ ስብሰባውች የሚወጣውን ወጪ ሲያስቡት ያደክማል:: በያዝነው 2011 ደግሞ ልክ ካቆሙበት ቀጥልዋል:: መስከረም ወርን በሙሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን እንደምንከታተለው መሰብስብ መሰብሰብ ነው! የአዋሳውን የኢሕአዴግን ስብሰባ አጀማመር ማየት ብቻ ያቺ ሃገር በስብሰባ እና በተያያዥ የፓርቲዎች ጉዳይ የምታወጣውን በጀት ማሰብ ይቻላል:: የአሁኑ ኦሮሞ ዴሞራቲክ ፓርቲ ለብቻው 4 ሚሊዮን አብላት አሉት:: ይሄ ሁሉ አባል ደግሞ ከክልሉም ከፌዴራል መንግስትም በአበል እና በሌላ መልኩ የሚንጠባጠብ የጥቅም ተጋሪ ነው! ይሄንን በአራቱ “እህት” ፓርቲዎች እና አጋር በሚባሉ በጀት መጣጮች አስሉት!
ብክነት በብክነት ለመሆናችን አንድ ተጨማሪ ምስሌ ልስጣችሁ እና ልጨርስ :-
የቀዳሚው ኃይለሥላሴ መንግስት ቀበሌም መታወቂያ ወረቀት የሚባልም ነገር የሌለበት መንግስት ነበር:: መንግስት እና ህዝብ እርቀታቸውን ጠብቀው ነበር የተዋቀሩት::
በኢትዮጵያ ዛሬ የቀበሌ እና የወረዳ ብቻ 3.5 ሚሊዮን ተመራጭ አለ! በ44 አመት ውስጥ መንግስት የሚባለው ዝሆን ምን ያህል እንደገዘፈ እና ይሄ የሚያመጣውን የበጀት እብጠት ማሰብ ያስፈልጋል:: 3.5 ሚልዮን ደግሞ በከተማ ክልል እና ፌዴራል ያለውን ሳይጨምር ነው! በመላው አሜሪካ ከትንሹ ከተማ እስከ ሴኔት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ ወደ 510 ሺህ ተመራጭ ነው ያለው (የህዝብ ብዛቱ ከእኛ ሶስት እጥፍ ስፋቱንም የምታቁት ነው):: አንዳንዶቹ የከተማ ተመራጮች ደግሞ ደሞዝተኞች አይደሉም:: ባለፈው ግዜ የሆነች መርጦ ለማርያም የምትባል ትንሽ ሺህ ህዝብ ያለባት የምስራቅ ጎጃም ከተማ 44 የወረዳ ተመራጮች እንዳሏት አንብቤ ገርሞኝ ነበር:: እንደው እውነት ለመናገር አዲስ አበባ ራሷ 44 ተመራጭ ያስፈልጋታል?
የመንግስት ግዝፈት ለሌላ ቁምነገር ሊውል የሚገባውን በጀት መምጠጡ ብቻ ሳይሆን የመንግስትን የማይጠረቃ ሆድ ለመሙላት ህዝብ እና ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን የቀረጥ እና የግብር ሸክም ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል:: መንግስትን ለማንቀሳቀስ ቢዝነሶች ላይ የሚጣለውን የቀረጥ እና የግብር ሸክም የውጭ ብድር እና የበጀት ልመና መቀነስ ተገቢ ነው:: የግብር ሸክም ደግሞ ነጋዴው ስራውን እንዳያስፋፋ ተጨማሪ ሰው ቀጥሮ ስራ አጥነትን እንዳይቀንስ ይባስ ብሎ ደግሞ ስራቸውን በጥቁር ገበያ ከግብር እይታ ዞር አርጎ ለመንቀሳቀስ ይገፋፋል::
እንደ ዜጋ ንግግራችንን እንደዚህ ባሉ የአገሪቷ እውነተኛ ችግሮች ላይ ማዋል ያስፈልጋል:: ብዙ ዝርዝር ውስጥ መግባት ይቻላል:: እንደው ጭብጡን ለማስያዝ ያክል ነው::
You must be logged in to post a comment.