(By Redeat Bayleyegn) የመጀመሪያው መሬት ለአራሹ እና መዘዙ

(By Redeat Bayleyegn) የመጀመሪያው መሬት ለአራሹ እና መዘዙ

ደርግ ለአመታት የቆየውን የ”መሬት ለአራሹ” ጥያቄ በታህሳስ 1967 በአዋጅ “መፍትሄ” ሰጠሁበት አለ:: መፍትሄውም የኢትዮጵያ መሬትን ከግል እና መንግስታዊ ካልሆነ ባለቤትነት ወደ መንግስት ወይም በተለምዶ የህዝብ ባለቤትነት ለወጠው:: ኢትዮጵያ በዘመኗ (ሺዎች) አይታው የማታውቀው ይህ የመሬት ይዞታ 44 አመት ሊሆነው ነው:: በኔ አመለካከት ውጤቱም ኪሳራ ነው!

ያ አዋጅ በኢትዮጵያ ምድር ከወጡ አዋጆች በቀደምትነት ዛሬ ላለንበት ረሃብ እና ዘረፋ ትልቁን አስተዋፆ እያደረገ ነው:: የተወሰኑ ክፋቱን ላስቀምጥ:-

  1. ብዙ መሬት ካላቸው ግለሰቦች ላይ መንጠቅን እንጂ መሬት ለሌለው ገበሬ መሬት መስጠት ላይ አለማተኮሩ::
  2. “ፊውዳል ባላባት የከተማ ገበሬ” ተብለው ከተወነጀሉ የመሬት ባለቤቶችን ከይዞታ ማንሳት “ተጨቆኑ” ለሚባሉ ገበሬዎች እና ማህበረሰቦች “መፍትሄ” ለመስጠት እንጂ በዚህ ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር (ምርታማነት) ሊጎዳ ይችላል ብሎ አለማሰብ::
  3. ጭሰኛ (የግብርና ሙያ ያለው እና ለባለመሬት ተቀጥሮ የሚሰራ) ገበሬን እና ባለቤትን (one on one) ስምምነት አስወግዶ ገበሬው ያልተስማማበትን የመንግስት ጭሰኛ ማድረጉ:: ያ ማለት ተቀጣሪው ገበሬ በመሬት ለአራሹ አዋጅ ምክንያት ከአንድ ሰው ጋር ሳይሆን መንግስት ከሚያስቀምጣቸው ካድሬዎች እና ለሌሎች አዛዦች ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው::
  4. እየሰለጠነ እና እያደገ የሚሄድ ህብረተሰብ የገበሬ ቁጥሩን እያሳነሰ ነው የሚሄደው:: የሚታረሰው መሬት እየሰፋ አሰራሩ እየተሻሻለ ነው የሚሄደው:: መሬት ለአራሹ ግን የገበሬውን ቁጥር ጨምሮ የሚያርሳትን መሬት ግን ብዙ ምርት በማትሰጥ 5 ካሬ ሜትር ገደባት!
  5. መሬት ለአራሹ ለገበሬው “መሬት ሰጠሁህ” ቢለውም በተግባር ግን ባለቤትነት አልሰጠውም:: ስለዚህ ገበሬው ቋሚ ገበሬ ነው የተደረገው:: ምክንያቱም መሬቱ የመንግስት ስለሆነ መሬቱን ሊያከራየው ሊሸጠው አስይዞ ሊበደርበት ስለማይችል ገበሬው ያንን መሬት የራሴ ነው ብሎ አልተማመነበትም::
  6. መሬት የመንግስት ስለሆነ የቀድሞውም “ጭሰኛ” “መሬት ስለተሰጠው” እንደ ቋሚ ገበሬነቱም በአዋጁ ምክንያት “ሞያውን” ይዞ ለሚመቸው እና ለሚጠቅመው ባለመሬት ተቀጥሮ በሙያው እንዳይኖር ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቱንም ነፍጎታል:: ታስሯል!
  7. ገበሬው መሬት ተሰጥቶሃል ቢባልም የመንግስት መሬት ስለሆነ በተፈለገ ግዜ ከቦታው የመነቀል ስጋቱ ጨምሯል:: ሲነቀልም የግል መሬቱ ስለሆነ እውነተኛውን የመሬቱን የገበያ ዋጋ አያገኝም:: ይህ ስጋት ደግሞ በደርግ ዘመንም በተለይ ደግሞ በወያኔ ዘመን በየከተማው እና ገጠሩ አስተውለነዋል:: በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞች ውስጥ ባሉ “ባለቤቶች” ላይ በጋምቤላ እና ሌሎችም ቦታዎች የተደረጉ ገበሬውን (ነዋሪውን) የማፈናቀል “ህጋዊነት” መነሻው መሬትን የመንግስት ያደረገው የመሬት ለአራሹ አዋጅ ነው::

አዋጁ እንደወጣ ደርግ እና በእሱ ዙሪያ የነበሩ አብዮተኞች ህጉን ለማስፈፀም የተጠቀሙት የሁለተኛ ደረጃ እና ኮሌጅ ተማሪዎችን ነበር:: ይሄ እንግዲህ አዋጁ በምን ያህል ችኮላ እና ቸልተኝነት እንደወጣ ያሳያል:: አዋጁን መቃወም እስከ ሞት የሚያስቀጣ መዘዝ ነበረው:: በዚህ አዋጅ ምክንያት ኢትዮጵያ የእርሻ ሚኒስትሯን አጥታለች ዶክተር ዳኛቸው ወርቁ ከበአሉ ግርማ በፊት ከምድረ ገፅ እንዲጠፋ የተደረገ እውነተኛ የግብርና አዋቂ ሳይንቲስት ነበር::

ከአዋጁ በኃላ በገበሬው ላይ የተጫኑት የገበሬ የቀበሌ የአብዬት ጥበቃ ንቃት … የሚባሉ መዋቅሮች እና አሰራሮች በተለይ ገበሬው ምን መዝራት እንዳለበት እና በስንት ብር መሸጥ እንዳለበት የተበተነው ነገር የስራ ተነሳሽነትን አቀጭጮ የገበሬውን አምራችነት ቀንሶታል:: ያም ገበሬ ለራሱ ሳያልፍለት ከተሜን መጋቢ ሆነ:: ይህ አዋጅ ከአብዮት በፊት ከነበረበት ይልቅ እውነተኛ ተገዥ አድርጎታል:: ወያኔ የተወሰኑ ለውጦችን ቢያደርግም በዋናነት “መሬቱ የኔ አይደለም እና አልምቼው እንዳይወሰድብኝ” የሚለውን ስጋት ሊቀርፈው ስላልቻለ አገራችን ለራሱ እህል የሚሰፈርለት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገበሬ ያለባት አገር ሆናለች::

ስለዚህ በኢትዮጵያ አዲስ ገበሬውን እውነተኛ የመሬቱ ባለቤት የሚያደርግ “መሬት ለባለቤቱ” የሚል ህግ ያስፈልጋል!

Advertisement