የአማራ ክልል የጫት ቃሚወችን ቁጥር ለመቀነስ የያዘው ዕቅድ:- ከፍተኛ ቀረጥ መጣል!

v(ናይሮቢ) ሰዎች በግል የሚፈጽሙትን ጎጅ የሚባሉ ነገሮች እንዳይጎዳቸው ለማቆም ወይም ሰዎች ሌሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለማድረግ እና ድርጊቱን ለመቀነስ መንግስታት የክልከላ ሕግ ማውጣታቸው የተለመደ ነው። ይሁን እንጅ መንግስታት ጎጅ ድርጊቶችን ለመቀነስ ወይም ለማስቀረት የሚያወጧቸው ሕጎች ብዙ ጊዜ ውጤታቸው ተቃራኒ ሲሆን ይስተዋላል።ይህን ጽሁፍ የምጽፈው ሰሞኑን በአማራ ቴሌቪዥን ዜና ላይ የአማራ ክልል በክልሉ የሚገኙ ጫት ቃሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ በጫት ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ለመጣል ማሰቡን እና ይህንኑ የሚደግፉ አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎች ያላቸውን ሰወችም በዜናው ላይ ከተመለከትኩ በኋላ ነበር። ጽሁፉን ለመጻፍ በቂ የማሰቢያ እንጅ የመጻፊያ ጊዜ ባላገኝም እንደምንም ብየ የተባለው ‘ሕግ’ ከመውጣቱ በፊት የበኩሌን ሃሳብ ለመወርወር ወደድኩ።ይህ የኔ ሃሳብ የኢኮኖሚ ሳይንስ መርህ ላይ የቆመ ዕውነታ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ በመሆኑ በየትም ቦታ እና ሃገር የሚሰራ ነው።በግሌ የጫት ቃሚወች መበራከት ብዙ ግዴለሽ ዜጎችን እንዳይፈጥር ቢያስፈራኝም ሰዎች ጫት እንዳይቅሙ ለማድረግ ብየ ግን ኢሳይንሳዊ እና መሰረት የለሽ ማስፈራሪያወችን አልጽፍም። ይህኛው አካሄድ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከል ተብሎ በጭራቅ አምሳል የተሰሩ ማስታወቂያወች እና ማስተማሪያወች ያስከተሉትን ዓይነት ዓሉታዊ ውጤት ላይ እንዳያደርሱን እፈራለሁ።መልካም ንባብ!

ጫት እንደ ሲጃራ የሱስ ዕስረኛ የሚያደርግ ዕጽ ነው። ጫት ቃሚወች በሂደት ራሳቸውን ሲጥሉ ወይም ሲጀዝቡ ማየት የተለመደ ይመስለኛል። ለዚህም ነው ወላጆቻችን፣ጎረቤቶቻችን ወይም የሚያውቁን ሰወች “ልጆች እባካችሁ ይህ ጫት አይጠቅማችሁም።ጎጅ ነው። የእንትናን ልጅ አታዩትም። ያጀዘበው ጫት ነው።እንደሱ መሆን ትፈልጋላችሁ? የንትና ልጅ ያበደውም እኮ በጫት ነው።” እያሉ ምክራቸውን በሚታወቁና በየአካባቢው ሰወች ምክንያቱ ጫት ባይሆንም እንኳ የሱስ እስረኛ እንዳንሆን ያላቸውን መልካም ምኞት በሚገባን መንገድ ይነግሩናል። ይህን ምክር ሰምተው የሚመለሱ ብዙ ወጣቶች እንደሚኖሩ ባልጠራጠርም የጽሁፉ ዓላማ ግን ምናልባትም ይህን ዓይነት ምክር ያላገኙ ወይም ሰምተው ከምንም ባለመቁጠር እየተበራከቱ ነው የተባሉ ጫት ቃሚወችን እና እነሱን ለመቀነስ ይረዳል የተባለውን ከፍተኛ ቀረጥ ይመለከታል።

በግሌ ሱስ የሚያሲዝ ነገር ሁሉ ጥቅም የለውም ብየ አላስብም። ለምሳሌ ቡና እጅግ በጣም ምናልባትም ከጫት በላይ ሱስ የሚያሲዝ ይመስለኛል።ግን ደግሞ ጥቅም አለው። የቡና መጠጫ ሰዓት ሲያልፍባቸው የሚነጫነጩ፣ ከፍተኛ ራስ ምታት የሚያማቸው እና መቆም አቅቷቸው የሚወድቁ እንዲሁም በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ደግሞ ቤት አንኳኩተው የቋጠሩትን ቡና እባካችሁ አፍሉልን ወይም ቡና አጠጡን የሚሉ ሰወች መኖራቸውን የማያውቅ ያለ አይመስለኝም። ቡና ሱሰኛ ስለሚያደግ ለጤና ጎጅ ነው ብሎ ማስታወቂያ መስራት ወይም ማስተማር ቡና ጠጭዎችን ከመጠጣት አያቆማቸውም።መንግስት በቡና ሱስ የተያዙ ሰወችን ቁጥር ለመቀነስ ቡና ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣልን እንደመፍትሄ ቢወስድ የቡና ጠጭዎች ቁጥር ይቀንሳልን? የቀረጥ ጭማሪ መፍትሄ የሚሆን ከሆነ የጫት፣የሲጃራ እና የአልኮል ሱሰኞችንም ለመታደግ ይጠቅም ይሆናል።

ጫት ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣል የጫት መሸጫ ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ይፈጥራል። ይህ ኢኮኖሚያዊ ሃቅ ነው። የዋጋ ጫናው በጫት ቃሚዎች ባህሪ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ይህም ኢኮኖሚያዊ ሃቅ ነው።የቡና ሱሰኞች ከአካባቢያቸው ርቀው መጓዛቸው በባህሪያቸው ላይ በሚፈጥረው ተጽዕኖ ምክንያት በየደረሱበት የማያውቁትን ቤት አንኳኩተው እባካችሁ ቡና አፍሉልን ወይም አጠጡን እንደሚሉ ሁላችንም የምናውቀው ኢትዮጵያዊ ሃቅ ነው። እነዚህ ሰወች የቡና ሱሰኞች እንጅ ለማኞች አይደሉም። ቀረጡን ተከትሎ በጫት ቃሚዎች ባህሪ ላይ የሚፈጠረው ተጽዕኖ በዕድሜ፣በዓይነት እና በይዘት ከቡና ሱሰኞቹ አንጻር ልዩነት ቢኖረውም መዳረሻው ግን ተመሳሳይ ነው። ይህም በየትኛውም መንገድ ሱሳቸውን ለማሟላት መሞከር ነው። የዋጋ ጫናው በቃሚዎች ባህሪ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ ጫት መግዛት የማይችሉ ምናልባት ሊያቆሙ ይችላሉ ወይም ደግሞ መንገድ ላይ ጫት መግዣ የሚለምኑ አሊያም ደግሞ ይህንኑ ሱሳቸውን ለማሟላት ወዳልተፈለገ ውንብድና እና ሌሎች አማራጭ የማህበራዊ ቀውስ ወጥመዶች ውስጥ የሚገቡም እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። ለምሳሌ ጤፍ ያመርቱ የነበሩ ገበሬወች ወደ ጫት አምራችነት የተሸጋገሩት በአዋጅ ሳይሆን የጫት ዋጋ ጤፍ አምርተው ከሚያገኙት ገቢ አንጻር እንደሚበልጥ ገበያው በባህሪያቸው ላይ ተጽዕኖ በመፍጠሩ ነው።የክልሉ መንግስት የጫት ጉዳይ ሊያሳስበው የሚገባው ያኔ ነበር።አሁን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ጫት ቃሚወችን ዋጋ በማስወደድ ለመቀነስ የሚደረገው ሙከራ ምናልባትም ክልሉን ጫትን ተከተው በቀላሉ ሊዘዋወሩ የሚችሉ የአደንዛዥ ዕጽ መናኽሪያ ሊያደርገው ይችላል። በተጨማሪም ከፍተኛ ቀረጥ በጫት አምራቹና ጫቱን ለተጠቃሚ በሚሸጠው ነጋዴ መሃል ህገወጥ ግን አዋጭ ስለሆነ ለመጋፈጥ የማያመነቱ ጫት በድብቅ ወደገበያው የሚያቀርቡ ወይም በድብቅ ጫት የሚሸጡ ሰወች እንዲፈጠሩ ያደርጋል።  ይህ ደግሞ ቀደም ሲል በህጋዊ መንገድ ግብር ከፍሎ ጫት የሚሸጠውን ነጋዴ ትኩረት ይስባል። ጫት ከህጋዊው ገበያ ቀስ በቀስ በመውጣት የጥቁር ገበያ ሸቀጥ ይሆናል ማለት ነው። እንግዲህ የአማራ ክልል መንግስት ከፍተኛ ቀረጥ በመጣል አሳካዋለሁ ብሎ ያሰበው ግብ ሃዲዱን መሳት የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው። አንደኛ ድሮ ከጫት ላይ ያገኝ የነበረውን ገቢ ያጣል። ሁለተኛ የጫት ሱሰኞችን ወደባሰ አደገኛ አቅጣጫዎች ይመራል።ክልሉ ትምህርት ቤቶች ወይም ጤና ጣቢያዎችን ወዘተ የሚሰራበትን ገንዘብ ቀደም ሲል ወንጀል ያልነበረውን የጫት ሽያጭ ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት፣ሕገወጥ የጫት ነጋዴወቹን ለማሳደድ፣ለመያዝ እና ለፍርድ ለማቅረብ ወጭ ለማድረግ ይገደዳል። አንድ ትምህርት ቤት ወይም አንድ ጤና ጣቢያ ቢሰራ በክልሉ ከሚገለገልበት ህዝብ ቁጥር አንጻር ምክር የመስማት ዕድሜ ላይ የደረሱ የጫት ቃሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ ከሚደረግ ሙከራ ጋር አይወዳደርም። ከዚህ በተጨማሪም ጫት ቃሚወች በሱሰኝነት “ራሳቸውን እንዳይጎዱ”ተብሎ በሚጣለው ከፍተኛ ቀረጥ ምክንያት የሚከሰተው የዋጋ ጭነት በባህሪያቸው ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ራሳቸውን ከመጉዳት ሌሎችን ወደ መጉዳት በማሸጋገር በክልሉ ባለው የወንጀል እንቅስቃሴ እንዲሁም የኤችአይቪ ስርጭት ላይ ተጨማሪ ነዳጅ እንዳይሆን መጠንቀቅ ወይም ይህ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። የአማራ ክልል ፖሊሲ አውጭዎች የያዙትን ቀረጥ የመጨመር ዕቅድ ትተው ከጫት ላይ ክልሉ ከሚያገኘው ገቢ ላይ የተወሰነውን ቀንሶ የጫትን እና ሌሎች አደንዛዥ ዕጾች ጎጅነት ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ በትምህርት ላይ የሚካተትበትን መንገድ መፈለግ የተሻለ ይመስለኛል። በዚህ መንገድ የጫት ቃሚዎችን ቁጥር ወይም ወደ ጫት ቃሚነት የገቡ ሰወችን ሳይሆን ወደዚያ የሚወስዳቸውን መንገድ መዝጋት ወይም ማጥበብ ይቻላል።ይህ ካልሆነ አተርፍ ባይ አጉዳይ እንዲሉ የክልሉ መንግስት ተጨማሪ ወጭ ለማውጣት ይገደዳል። ሌላ ተጨማሪ ወጭ ለማውጣት በግብር ከፋዩ ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠሩ የማይቀር ስለሆነ የክልሉ ህዝብ ከድህነት አዙሪት ውስጥ ለመወጣት የሚያደርገውን መፍጨርጨር እንደገና ያጨነግፈዋል።

በጥቅሉ ጫት መቃም፣ ሲጃራ ማጨስ፣ የሚረጋ ዘይት፣ስብ የበዛበት ምግብ መመገብ፣ የህጻናት ልጆቻችን በተንቀሳቃሽ  ስልኮች እና ኮምፒውተሮች ላይ በሚገኙ ጌሞች ላይ ለብዙ ሰዓታት ማሳለፍ ወዘተ ጥሩ እንዳልሆኑ ይታወቃል። አብዛኛው ሰው ይህን የሚረዳ ይመስለኛል። ሆኖም ሰወችን እንዲህ አታድርጉ ብሎ ማስተማር የሚጠቅመውን ያህል እንዲህ አታድርጉ ብሎ በተለይም ወጣቶችን ለማቀብ መሞከር ውጤቱ ተቃራኒ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ታይቷል። ለምሳሌ ያህል በአብዛኛው የአውሮፓ ህብረት ሃገራት ሴተኛ አዳሪነት በህግ ሲከለከል ኢንተርፕርነሮች ማሳጅ ቤቶችን ይዘው ከተፍ ብለዋል። ክልከላውን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለክልከላ በማይመች መንገድ ጥቅም ላይ አዋሉት። በአሜሪካ ወጣት ሲጃራ አጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ ሲጃራ ሻጮች 17 ዓመት ላልሞላው እንዳይሸጡ የሚከለክለው ህግ በተተገበረባቸው ግዛቶች ውስጥ የአጫሾች ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ በመገኘቱ ሕጐ እንዲሻር ተደርጓል። የአልኮል ጠጭ ታዳጊወችን ቁጥር ለመቀነስ የወጣው ህግም በተመሳሳይ መንገድ ከሽፏል። ይህ ሰወች ሲከለከሉ ለማድረግ የሚገፋፋቸው ወይም በተቃራኒ አቅጣጫ የሚገፋቸው ምክንያት ከሰዋዊ ባህሪያቸው ወይም ከዚያች የተከለከለች ዕጽ የወረሷት ሳይሆን አይቀርም ይህን ክስተት ፖለቲካል ኢኮኖሚስቶች ‘ዘ ፎርቢድን ፍሩት ኢፌክት’ ይሉታል። ይህ እንዳይደርስብን መጠንቀቅ ደግሞ እንደየ ሃላፊነታችን ቢለያይም የሁሉላችንም ግዴታ ስለሆነ በግሌ የመጀመሪያውን ግዴታየን በዚህ ጽሁፍ ተወጣሁ።

*** አንባቢያን ልብ እንድትሉ የምፈልገው ነገር በጫት ላይ የሚጣለው ከፍተኛ ቀረጥ የሚያመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ በሌሎች ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ በሚጣል ከፍተኛ ቀረጥ ወይም ግብር ምክንያት ከሚፈጠረው ተጽዕኖ የተለየ አለመሆኑ ነው። ለምሳሌ መንግስት ከነጋዴ ላይ የሚሰበስበውን ገቢ ለማሳደግ ብሎ ግብር እጥፍ ቢጨምር ውጤቱ ቀደም ሲል እንደተገመተው እጥፍ ገቢ አይሆንም። ምክንያቱም ከፍተኛ ግብር በነጋዴው ባህሪ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ከህጋዊው የንግድ ስርዓት  በግድ ተገፍቶ እንዲወጣ ይደረጋል። መንግስት ድሮ ያገኝ የነበረውን ግብር ካለማግኘቱም በላይ ከህጋዊው የንግድ ስርዓት የወጡ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ተጨማሪ ወጭ እንዲያወጣ ይገደዳል። በዚህ ዙሪያ “ግብር እና ሞት” የሚለውን ቀጣይ ጽሁፌን በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ላይ አቀርባለሁ።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.