ነፃነት እና ምግባር፡-የራስ እና የማህበረሰብ ለውጥ ሂደት ቁልፎች 2

pezፋኒ ክሮዝቢን ላስተዋውቅዎ! በአሜሪካ ኮንግረስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ንግግር ያደረገች ሴት ናት። ስለዚች ሴት ብዙም ሰምታችሁ ላታውቁ ትችሉ ይሆናል። ይህች ሴት ታዋቂውን ‘ብሌስድ አሹራንስ’ ጨምሮ በርካታ ፈጣሪን የሚያመሰግኑ መዝሙሮችን እና ውዳሴዎችን በመጻፍ ተወዳዳሪ የላትም። የካቲት ሁለት ቀን አስራ ዘጠኝ አስራ አምስት ዓ/ም ዘጠና አምስተኛ ዓመት የልደት በዓሏን ለማክበር ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ሲቀሯት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው ፋኒ ክሮስቢ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ጋር በመገናኘት በህይዎት ካሉም ሆኑ ከሞቱ ሰዎች የሚስተካከላት የለም። ከጆን አዳምስ እስከ ውድሮው ዊልሰን ድረስ የነበሩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶችን በሙሉ በአካል ታውቃቸዋለች። አብራቸው ተጫውታለች። ሻይ ቡና ብላለች። ፋኒ ሰዎች ሁልጊዜ በምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ፣ለራሳቸው ክብር ቦታ እንዲሰጡ እና ለህሊናቸው ታማኝ እንዲሆኑ ትመክር ታስተምርም ነበር።ፋኒ ክሮዝቢ “ሰዎች ራሳቸውን መግዛት ካልቻሉ በሌላ መገዛታቸው እና የሌሎች ባሪያ መሆናቸው አይቀሬ ነው!” ትላለች።   ፋኒ ለዘጠና አምስት ዓመታት በምድር ላይ ስትኖር አንድም ቀን አካል ጉዳተኛ መሆኗ ትዝ ብሏት አያውቅም። እርሷ ግን በህክምና ስህተት በተፈጠረባት ኢንፌክሽን ምክንያት ሁለቱንም የዓይን ብርሃኗን ያጣችው ገና በስድስት ወር ዕድሜዋ ነበር። ፋኒ ክሮዝቢ እድሜዋን በሙሉ የአይን ብርሃን ባይኖራትም በዚያ ምክንያት ከአንድም ሰው እርዳታ እና ድጋፍ ጠይቃ አታውቅም። እንዲያውም በግንቦት ወር አስራ ዘጠኝ አስራ አንድ ዓ/ም በካርኒጌ አዳራሽ ለተሰበሰቡ ከአምስት ሽሕ በላይ አድናቂወቿ “እውነቱን ልንገራችሁ-ነገ ‘ዓይንሽን እናብራልሽ’ ብትሉኝ እሽ አልላችሁም። ምክንያቱም የዓይን ብርሃን ባይኖረኝም ፈጣሪ የልብ ብርሃን አልነፈገኝም። ዓይን ቢኖረኝ ምናልባትም በዙሪያየ በማየው ቆንጆ እና ማራኪ ነገሮች ምክንያት ፈጣሪየን ልዘነጋው እችል ይሆናል። ያ እንዲሆን አልፈልግም። ዛሬም፣ ነገም፣ ሁሌም ፈጣሪየ ከፍ ይበል እላለሁ። አወድስዋለሁም!” ብላለች።  ይህን ንግግርሯን ተከትሎ በአዳራሹ የተሰበሰበው ህዝብ ለሰላሳ ደቂቃ ያህል “ፈጣሪ ሁሌም ከፍ በል!” የሚለውን የሷን መዝሙር እየደጋገመ ዘምሯል።

ከህሊናችን ጋር ግብግብ የፈጠርን ሁሉ እርቅ በመፈጸም ወደ ቀልባችን እንመለስ። ምክንያቱም ከህሊናቸው ጋር የተጣሉ ሰዎች ጨለምተኞች ናቸው። ጨለምተኛ ሰዎች ሌሎች ነፃነት ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ለማጨናገፍ ይሰራሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች ውሸታም፣ አጭበርባሪ እና ሆድ-አደር ናቸው። በተሾሙበትም ሆነ ተመርጠው በያዙት ስልጣን ላይም ዋሾዎች እና አጭበርባሪዎች ይሆናሉ። ኃላፊነትን የማይወጡ ሰዎች እና ምግባር የጎደላቸው የመንግስት ባለስልጣናት የራሳቸው ደካማ ውሳኔዎቻቸው ለሚፈጥሯቸው ችግሮች ሁሉ ሌሎችን ጥፋተኛ ያደርጋሉ። ትሁትነት የጎደላቸው ሰዎች ከስልጣናቸው በላይ ራሳቸውን በመቆለል ይኮፈሳሉ። የሌሎችን ደረጃ ዝቅ በማድረግ እና ጥበባቸውንም በማጣጣል የራሳቸውን ‘ታላቅነት’ ለማሳየት ይጥራሉ። ምግባረ ቢስ መሆናቸው በግብዝነታቸው ይገለጣል። እንዲህ ያሉ ግብዞች ከታሪክ  እና ከሰው ልጅ ድርጊቶች አይማሩም። ከአፍንጫቸው አርቀው ስለማያስቡ ውሳኔዎቻቸውም ሁሉ ለወዲያው እና ለይምሰል የሚደረጉ ናቸው።

ምግባር የሌላቸው ሰዎች በራስ መተማመን የሌላቸው ስለሆኑ በተቀፅላነት በተጠጓቸው ሰዎች በቀላሉ ይጠመዘዛሉ። ራሳቸውን በስርዓት የማያንፁ እንዲህ ያሉ ሰዎች እጣ ፈንታቸው በማይመለከታቸው ሰዎች ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ መንገድ ይከፍታሉ። ምግባረ ብልሹ ሰዎች በገዛ ጥረታቸው ሰርቶ ከመብላት ይልቅ የሌሎችን ላብ እና የድካም ውጤት ለማግኘት ይሯሯጣሉ። እነዚህ ሰዎች ቢጤዎቻቸው በሆኑት የመንግስት ባለስልጣናት ላይ በመንጠላጠል ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ በሕዝብ ሃብት ላይ ይወሰልታሉ። ነፃነታቸውን አሳልፈው በመስጠት በልዋጩ ፍርፋሪ ለመልቀም ይራወጣሉ። ይህን በምሳሌ ለማብራራት ይጠቅመኝ ዘንድ ባንድ ወቅት ያነበብኩትን ታሪክ ላካፍላችሁ።

ይህ ታሪክ ባንድ ወቅት ለያዥ ለገራዥ ባስቸገሩ ከርከሮዎ ላይ የሚያጠነጥን ነው። የጎርፍ አደጋ፣ የሰደድ እሳት፣ የበረዶ ቅዝቃዜ እና ድርቅ ሊያጠፋቸው ያልቻለው እነዚህን ከርከሮዎች ከሚያሳድዳቸው ተኩላ  እና ከሚያድናቸው የሰው ልጅም ራሳቸውን ይጠብቁ ነበር። ከርከሮዎቹ ይህን ሁሉ መከራ ተቋቁመው የመዝለቃቸው ነገር በሁሉ ዘንድ ዝነኛ እንዲሆኑ እና ከዳር ዳር እንዲነገርላቸው አደረገ። በዚህ ጊዜ ይሄን ዝናቸውን የሰማ አንድ ወጣት “እንዴት አይያዙም? እኔ እይዛቸዋለሁ!” በማለት ከርከሮዎቹ ይኖሩበታል ወደ ተባለው መንደር አመራ። በመንደሩ እንደደረሰም በመንገድ ዳር ከሚገኙ ሱቆች ወደ አንዱ ጎራ ብሎ ከርከሮዎቹን ሊይዝ እንደመጣ በመንገር በትክክል የትኛው ጫካ ውስጥ እንደሚኖሩ መረጃ ጠየቀ። ባለ ሱቁ  ወጣቱ ለማንም ያልተበገሩ ከርከሮዎችን ለመያዝ መወሰኑን “የልጅ ውሳኔ” ብሎ ካጣጣለ በኋላ  “እዚያ ጫካ ውስጥ አሉልህ!” በማለት የከርከሮዎቹን መኖሪያ አመላከተው። ወጣቱም ቀለቡን እና መኖሪያ አነስተኛ ድንኳን፣ በበቆሎ የተሞሉ ከረጢቶች፣ ገመድ እና መጥረቢያውን  በጋሪ እየገፋ ከርከሮዎቹን ፍለጋ ወደ ጫካው ውስጥ ገባ። ከሁለት ወር በኋላ የጫካውን አቅጣጫ ወዳመለከተው ሰውዬ ሱቅ ተመልሶ ከርከሮዎቹን ከጫካው ውስጥ ለማውጣት እንዲረዳው ይጠይቀዋል። ባለ ሱቁም የሰማውን ማመን አቃተው። ይህን ወሬ የሰሙ የአካባቢው ሰዎች ወጣቱ ያደረገውን ሊያምኑ ባለመቻላቸው በዓይናቸው ለማየት ወደ ጫካው መጉረፍ ጀመሩ። ሰዎቹ እነዚያን አስቸጋሪ ባህሪ የነበራቸውን ከርከሮዎች እንዴት ሊይዛቸው እንደቻለ እንዲነግራቸው ጠየቁት።

ወጣቱ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት ጀመረ። “መጀመሪያ ላይ ከርከሮዎቹ መኖሪያ አቅራቢያ የሚገኙ ጥቂት ዛፎችን በመጥረቢያ ቆረጥኩና ክፍት ቦታ እንዲኖር አደረግሁ። ከዚያ በክፍት ቦታው ላይ የተወሰነ በቆሎ አስቀመጥኩ። ከርከሮዎቹ በመጀመሪያ ወደ ክፍት ቦታው መጠጋት ፈርተው ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ወጣቶቹ እና ትናንሾቹ ከርከሮዎች ወደ ክፍት ቦታው መግባት ጀመሩ። በክፍት ቦታው ላይ ያስቀመጥኩን በቆሎም ቀመሱት። እሱን በልተው እንደጨረሱ እየሮጡ ወደ ደኑ ይገባሉ። እኔ በተመሳሳይ መንገድ በቆሎ እያስቀመጥኩ ዞር እላለሁ። እነሱ እየገቡ በቆሎዋን እየበሉ መሮጥ ስራቸው አደረጉት። ትልልቆቹ ከርከሮዎችም ቀስ በቀስ ወደ ክፍት ቦታው መግባት እና የማስቀምጠውን በቆሎ እየበሉ መሄድ ጀመሩ። ባዘጋጀሁት ክፍት ቦታ ላይ የሚገቡት ከርከሮዎች ቁጥር እየጨመረ ስለሄደ የማስቀምጠውን የበቆሎ መጠንም በዚው ልክ ጨመርኩ። በጫካው የሚገኙ ከርከሮዎች ሁሉ በራሳቸው ጥረት ቅጠላ ቅጠላቸውን ማሰስ እና ምግብ ፈልጎ መብላት ረሱት። ክፍቱን ቦታ ዙሪያውን በየቀኑ ትንሽ ትንሽ እየጨመርኩ ማጠር ጀመርኩ። አጥሩን ለማጠር የሚያገለግል እንጨት መጀመሪያ ክፍት ቦታውን ለመስራት ከቆረጥኳቸው ዛፎች ተጠቀሚያለሁ። በየቀኑ በቆሎ ማስቀመጤን ሳልረሳ የእንጨት አጥሬን ከርከሮዎቹ እንዳያስተውሉ አድርጌ ከዕለት ዕለት ትንሽ ትንሽ እየጨመርኩ በመጨረሻም መዝጊያውን አበጀሁና የመጨረሻው ከርከሮ ሲገባ ዘጋሁት። ይህ ወጥመዴ አሁን ትልቅ በረት ሆኗል። ከርከሮዎቹ እኔን ሲያዩ በበረቱ ውስጥ ሆነው ይጮሃሉ፤ይደነብራሉ። ግን ከእንግዲህ የኔ ናቸው። ነፃነት የላቸውም።” በማለት እንዴት ሊይዛቸው እንደቻለ አብራራላቸው።

የእንስሳትንም ሆነ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ማዛባት ከተቻለ ማንም እንደፈለገው አድርጎ  ባሻው መንገድ ሊጋልባቸው ይችላል። ከርከሮዎቹ በተፈጥሮ ያገኙትን ተሯሩጦ ቅጠል በጥሶ የመብላት ተግባር አቁመው ሳይሰሩ መብላት ጀመሩ። በመጨረሻም በጠላት እጅ ላይ ወደቁ። የሰው ልጅም ሳይሰራ ለመብላት፣ እና ሳይደክም ሌሎች የለፉበትን ለማግኘት ሲሞክር ሰብዓዊ ክብሩን በማጉደፍ ነፃነቱን አሳልፎ ይሰጣል። ከዚያ በኋላ ወጥመድ ውስጥ ገብቷል። ለጥቂት ፍርፋሪ ብለው ነፃነታቸውን ያጡ ሰዎች ነፃነታቸውን ማጣታቸውን በተገነዘቡ ጊዜ ከገቡበት ወጥመድ በቀላሉ መውጣት አይችሉም። በወጥመዱ ውስጥ የገቡት ሰዎች እጣፈንታ የሚወሰነው እንደ ከርከሮዎቹ ሁሉ ፍርፋሪ እየጣሉ ባጠመዷቸው ሰዎች ይሆናል።

ስለዚህ የምግባር ደረጃዎን ከፍ በማድረግ የሌሎች ወጥመድ ሲሳይ ከመሆን ራስዎን ይጠብቁ። ጠንካራ ምግባርን ከሚገልፁ ዋነኛ ባሕርያት መካከል ታማኝነት፣ ትሁትነት፣ ታጋሽነት፣ኃላፊነትን መወጣት ፣ ራስን በስርዓት ማነፅ ፣ ቀናነት ፣ ደፋርነት ፣ የረጅም ጊዜ ግብ ላይ ትኩረት እና ዘወትር ለመማር ዝግጁ መሆን ይገኙበታል። መልካም ምግባር ያላቸው ሰዎች ራስን ለመቻል ባላቸው ፅኑ ፍላጎታቸው፣ የሰው የሆነን ነገር ከመንጠቅ ቁጥብ መሆናቸው፣በጥንካሬያቸው፣ በንግግራቸው፣ በፅናታቸው፣ በቆራጥነታቸው፣ በጠንካራ ሰራተኛነታቸው የሚታወቁ ሲሆን እነዚህም የሰው ልጆች መልካም ባህሪያት መገለጫዎች ናቸው። ነፃነትን የሚሹ ሰዎች ሁልጊዜ አመለካከቶቻቸውን፣ የአሰራር ባህርያቶቻቸውን እና ግለሰባዊ ምግባሮቻቸውን ማሻሻል እና በወጉ ቅርፅ ማስያዝ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የሰው ልጅ አሁን አለኝ የሚለው ነፃነት የቆመበት ከሌለው ደግሞ የሚፈልገው ዓይነት ነፃነት፣ፍቅር፣ እና ሰላም የሚቆሙበት ምሶሶ ጥንካሬ የሚለካው በደረሰበት የሞራል እና የምግባር ደረጃ ልክ ነውና ነው!

 

Advertisement