ነፃነት እና ምግባር፡-የራስ እና የማህበረሰብ ለውጥ ሂደት ቁልፎች

free

ነፃነት ተድላ ወይም ተወዳጅ ሐሳብ ብቻ አይደለም። የሰው ልጅ ያለ ነጻነት ከቶውንም ሙሉ ‘ሰው’ ነኝ ማለት አይችልም። ነጻነት ደስታን ከሚሰጥ ኹነት እና ጥብቅና ሊቆሙለት ከሚገባ ፅንሰ-ሐሳብ ሁሉ እጅግ ይልቃል። በነፃነት አለመኖር የሚያስገኘው መልካም ነገር ቢኖር መራራ ሕይወት ነው። በነፃነት አለመኖር የሚያስገኘው እጅግ መጥፎው ነገር ደግሞ ሰብዓዊ ክብርን መገፈፍ ነው። መራራ ሕይወት እና ሞት የባርነት ፍሬዎች ናቸው። አምባገነኖች ሁልጊዜ ሰዎች የነፃነት ፍላጎት እንዳይኖራቸው ታዛዥነትን እና ባርነትን ያለማምዳሉ። ነፃነትን የሚያጠፋ ወይም የማያጎለብት መንግስት ምግባርን ከሰዎች መሃል ለማጥፋት ይሰራል። ካስት ኤክስፕሎይቴሽን ቲወሪን በመጠቀም ለአምባገነናዊ ስርዓቱ ዘብ የሚቆሙ እና ከስርዓቱ ጋር በፍቅር የሚወድቁ ሰዎችን ከገባሩ ብዙሃን መሃል ይመለምላሉ። እነዚህ ሰዎች በህዝቡ መሃል ሆነው የስርዓቱን መልካምነት ከመስበክ በተጨማሪ ህዝቡ ውስጥ የቀሩትን ጥቂት ሞራላዊነት፣ የምግባር እሴቶች እና የነፃነት ፍላጎት ለማጥፋት ቀን ከሌት ይሰራሉ። በማህበረስብ ውስጥ የምግባረ ብልሹ ሰዎች መብዛት በአምባገነኖች መብቶቻቸው ሲረገጥ ፈቃደኛ የሚሆኑ ሰዎች መብዛት ምልክትም ነው። ሰዎች ውሸትን፣ ሙስናን፣ ማጭበርበርን፣ ማስመሰልን እና ስርቆትን የሚያበረታቱ ከሆነ እንዲያ ያለ ማህበረስብ ጉዞው ወደ ስርዓተ-አልበኝነት እንጅ ከቶውንም ወደ ነፃነት ሊሆን አይችልም። ምግባር ወደ ነፃነት የሚደረግ ጉዞ ርቀት መለኪያም ነው።

ነፃነት እና ምግባር አይነጣጠሉም። የግለሰብ ነፃነት ዕጣ -ፈንታ ሁሌም በምግባር ላይ የመመስረቱ ነገር የማይታበል ሐቅ ነው። ቁሳዊ ሐብት ፣ ማህበረሰባዊ ደረጃ እና ሕዝባዊ ዕውቅና የቱንም ያህል ልቆ ቢሔድ ነፃ ማህበረሰብ ማበብ የሚችለው ሰዎች የክብር፣ የታማኝነት እና የባለቤትነት ሞዴሎች የመሆን ፍላጎት በውስጣቸው ሲያድር ነው።የሠናይ ምግባር እና የዕኩይ ድርጊት ምንነት በሰዎች ተፈጥሮ ውስጥ የሚገኝ ነው። የሰው ልጅ ይህን ተፈጥሮአዊ ጥልቅ ስሜቱን ማድመጥ ትቶ ማፈንገጥ ሲጀምር የዚህ ጥልቅ ስሜት ተፈጥሮአዊ ቤት ከሆነው ህሊናችን ጋር ግብግብ እንገጥማለን። ምናልባት ይህን ግብግብ ለማሸነፍ እንዲረዳን አልኮል መጠጣትን እና አደንዛዥ ዕፅ መውሰድን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን ልንፈጥር እንችል ይሆናል። ሆኖም ግን ይህን ማድረጋችን ከህሊናችን ያፈነገጥንበትን ስራ ከውስጣችን ሊያወጣው አይችልም።

ሰዎች ህሊናቸው የሚሰጠውን ፍርድ ሲጥሱ ምግባራቸውን እያጓደሉ ይሔዳሉ። ሕጋዊነትን ባልተከተለ መንገድ በአቋራጭ ለመክበር ሲንቀሳቀሱም ከምግባር ደረጃቸው ይወርዳሉ። ምናልባት አቋራጭ መንገዱን የሚመርጡት ብዙ የማያደክምና የማያስጨንቅ ስለሆነ አሊያም ድርጊቱን ሲፈፅሙ ሌላ ሰው ላያስተውለው ስለሚችል ሊሆን ይችላል። ሆኖም እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ከህሊና ጋር የሚያጋጩ እና የምግባር ደረጃን ዝቅ የሚያደርጉ አዳላጭ ቁልቁለት መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። የሰው ልጅ ምግባር ሰው በማያየው ጊዜ በሚሰራው ስራ ይገለፃል የሚባለው ለዚህ ነው። የመንግስት ሹመኞች ተገቢ የሆነ ውሳኔ በመስጠት ፋንታ በሙስና እና በጥቅም ውሳኔዎችን የሚያዛቡ ከሆነ ከምግባር እያፈነገጡ ይሄዳሉ። ምግባር ማለት ነገሮች የቱንም ያህል ተራ መስለው ቢታዩንም እንኳ ሳይንቁ ተገቢ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ማለት ነው። ለዚህ ምሳሌ ይሆነኝ ዘንድ አንድ ሰው ላስተዋውቅዎ!

በአስራ ስምንት ሰማኒያ አራት ዓ/ም ባንድኛው ቀን የአሜሪካ ኮንግረስ(የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) በአንድ የሕግ ረቂቅ ላይ መምከር ይዟል። የሕግ ረቂቁ ስመ-ጥር የአሜሪካ ባህር ሃይል የነበረ ሰው መሞቱን ተከትሎ ለቤተሰቡ መደገፊያ የሚሆን ገንዘብ መስጠትን ይመለከታል። በርካታ የኮንግረስ አባላት ረቂቁን ደግፈው ስለ አስፈላጊነቱም ጭምር በየተራ ንግግር አደረጉ። በዚሁ መሰረት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ የሕግ ረቂቁ ላይ ድምፅ ለማሰጠት ሲሉ ድንገት አንድ የኮንግረስ አባል እጁን አወጣ። ዴቪድ ክሮኬት ነበር።

“ሚስተር አፈ ጉባዔ! እኔ እንደናንተ ሁሉ ለተሰዋው ጀግና ትልቅ ክብር አለኝ። የቤተሰቡ ሀዘንም ቢሆን ጠልቆ ይሰማኛል። ነገር ግን ይህን የሚሰማኝን ክብር እና ሃዘን ወደ ኢ-ፍትሃዊነት በሚወስድ የሕግ ረቂቅ መግለፅ አልፈልግም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዳችን ከኪሳችን የወደድነውን ያህል ገንዘብ አዋጥተን ለጀግናው ቤተሰብ ብንሰጥ ይሻላል። አይ! ብላችሁ ወደ ድምፅ መስጠት የምትገቡ ከሆነ ደግሞ የተቃውሞ ድምፄን እሰጣለሁ።አመሰግናለሁ!” በማለት ሃሳብ ሰጠ።  ይህን ንግግር ተከትሎ ሌላ የኮንግረስ አባል የዴቪድን አቋም የሚቃረን ሃሳብ እንዲህ ሲል አቀረበ።  “ይህ ገንዘብ እንደ ስጦታ የሚቆጠር አይደለም። ይህ ጀግና እኮ አሜሪካን ሲያገለግል የኖረ ነው። የዚህ ሰው እዳ አለብን። መክፈል ይኖርብናል። አስር ሽሕ ዶላር ደግሞ ብዙ ገንዘብ አይደለም።” በማለት ንግግሩን ቋጨ።  ዴቪድ ክሮኬትም ምላሹን  እንዲህ  በማለት አቀረበ።

“ሃገሬ እንዲህ ያሉ ጀግኖቿ የዋሉላትን ውለታ አትረሳም። ይህን በገንዘብ ሊተመን የማይችል የጀግኖች ውለታ በገንዘብ ለመክፈል መሞከር በጀግኖቹ መስዋዕትነት የተጎናፀፍነውን ክብር ማዋረድ ነው። ገንዘቡ ትንሽ ነው ተብሎ ዛሬ ይህ ረቂቅ ከፀደቀ ነገ ብዙ የህዝብ ገንዘብ በዚሁ መንገድ እንዲባክን በር ይከፍታል። እኔ የምቃወመው ገንዘቡ አነሰ ወይም በዛ ብዬ ሳይሆን ከመርህ አንፃር ነው። ከሁሉም በላይ ያቀረባችሁት የሕግ ረቂቅ የብዙ አባቶቻችን መስዋዕትነት ውጤት እና የታላቅነታችን መገለጫ ከሆነው ሕገ- መንግስታችን ጋር አብሮ አይሄድም። ሕገ መንግስቱ ይህ ኮንግረስ ለማንም ይሁን በምንም ምክንያት የህዝብ ገንዘብ ለግለሰብ የመስጠት ስልጣን እንደሌለው በማያሻማ ቋንቋ ደንግጓል። ቅድም እንዳልኩት እንደ ግለሰብ የወደድነውን ያህል ለጀግናው ቤተሰቦች ማዋጣት እንችላለን። በዚህ ምክር ቤት ውስጥ የመጨረሻው ድሃ እኔ ነኝ። እኔ የአንድ ሳምንት ደሞዜን ለማዋጣት ወስኛለሁ። በርግጥ በረቂቁ ልታፀድቁት ያላችሁት የገንዘብ መጠን ለአንዳንዶቻችሁ የኮንግረስ አባላት ለእራት ግብዣ ወይም ለቅንጦት በአንድ ጊዜ የምታወጡት ገንዘብ እንደሆነ አውቃለሁ። ስለዚህ ሁላችሁም እንደኔ ብታደርጉ የሕጎቻችን መሰረት የሆነውን ሕገ መንግስት ሳንጥስ በረቂቁ ከገለፃችሁት የገንዘብ መጠን በላይ ማዋጣት እንችላለን። አመሰግናለሁ!”

ዴቪድ ክሮኬት ንግግሩን በምስጋና ከቋጨ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ረቂቁን ድምፅ እንዲሰጥበት ቢያደርግም ንግግሩ ብዙዎቹን የኮንግረስ አባላት በማሳመኑ አብዛኞቹ የኮንግረስ አባላት ቀደም ብለው ሲደግፉት ለነበረው የሕግ ረቂቅ ድምፃቸውን ነፈጉት። እናም ረቂቁ ሕግ ሆኖ ሳይፀድቅ ቀረ። ለጀግናው ቤተሰብም ዴቭድ ባቀረበው ሃሳብ መሰረት ከኪሳቸው በማዋጣት አስራ ሶሽት ሽህ ዶላር ተሰብስቦ ተሰጠ። ነጻነት ሃላፊነትን ይጠይቃል። የሕዝብ ገንዘብን ተራ በሚመስል ግን በሂደት ለትልቅ ብክነት የሚዳርግ አሰራር በር መክፈት መልካም ምግባርን ይሽረሽራል። በምግባር የታነጹ ሰዎች አርቀው የሚያስቡ ናቸው። ለጊዜያዊ ችግር መፍትሔ ሲሉ ሕግ እንዲጣስ አይፈቅዱም። አፍንጫቸው ስር ብቻ ያለውን እየተመለከቱ ከህሊናቸው ጋር የሚያጋጭ ድርጊት ውስጥም አይገቡም።

ሰዎች ኃላፊነትን ከመወጣት ሲሸሹ፣ በፈተና ሲሸነፉ ፣ችግሮቻቸውን በተጭበረበረ መንገድ ለመፍታት ሲሞክሩ፣ ጥፋቶቻቸውን በሌሎች ላይ ሲለድፉ መልካም ምግባሮቻቸው ይጓደላሉ። የምግባር ጉድለት ተገቢን ነገር የመፈፀም ዕውቀቱ ያለው ሰው ዘወትር ተገቢውን ነገር አለመፈፀሙን ወይም ለተገቢ ነገር አለመቆሙን ያሳያል። ነፃ መሆን እና በነፃ ማህበረሰብ ውስጥ መኖር የሚሹ ከሆነ የምግባር ደረጃዎን ማሳደግ እና በመልካም ምግባራቸው ከሚታወቁ የምግባር ሰዎች ለመማር ጊዜ አያጥፉ።ይቀጥላል።

Advertisement