“ተወዳዳሪ የቴሌፎን ገበያ እንፈልጋለን!” የኢትዮ-ቴሌኮም ጥገትላሞች!

በ21ኛው ክ/ዘመን ለውጭ ገበያ እና ተወዳዳሪ “ገበያህን እና ድንበርህን ዝጋ!” የሚል ሰው ይኖራል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ቢመስልም በሌላም ሃገር ይሁን በኢትዮጵያ የዚያ ዓይነት ሰዎች አሉ። ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሃገር ከምትልከው ምርት የምትገዛው በብዙ እንደሚበልጥ የሚረዳ ሰው የኢትዮጵያን ገበያ ለውጭ ዝግ ይሁን ብሎ አፉን ሞልቶ አይናገርም።ምክንያቱም እነሱ እኛ ላይ ጥገኛ ከሆኑት በላይ የእኛ ህልውና በነሱ ገበያ ላይ የተመሰረተ ነው። ከባህል መድሃኒቶቻችን ውጭ ኢትዮጵያ ውስጥ በዘመናዊ መንገድ ተቀምሞ የሚሰራ አንድም መድሃኒት የለም። ከህንድና ከቻይና ፓራሲታሞልን እና አሞክሳሲሊን ወይም ለቅባት መስሪያ የሚውለው ንጥረ ነገር በዱቄት መልክ ወደሃገር ውስጥ ይገቡና እንደገና ከውጭ በተገዛ ማሽን በቅርጽና በመጠን እየተደረጉ ይታሸጋሉ።ኢትዮጵያዊያንም መድሃኒቶቹን ከገበያ ላይ ያገኟቸዋል ማለት ነው።ኢትዮጵያ ለነዚህ መድሃኒቶች መስሪያ የሚያገለግለውን  ጥሬ እቃ ከምትገዛባቸው ሃገራት ጋር መልካም የገበያ ትስስር ካልመሰረተች ወይም በኢትዮጵያ ገበያ ለመሳተፍ ሲፈልጉ ብትከለክላቸው እንደ መጨረሻ አማራጭ መድሃኒት አንሸጥም በማለት ሊቀጧት ይችላሉ።ኢትዮጵያ ወትሮም ቢሆን ከነዚህ ሃገራት መድሃኒት የምትገዛው በተመጣጣኝ ዋጋ ስላገኘች ስለሆነ ወደ ሌላ አማራጭ መሄድ ከዋጋ አንጻር አዋጭ አይሆንላትም። ሌላ ገበያ መፈለግም ሌላ ወጭ ነው።አንድ ነገር መታወቅ ያለበት ሙሉ ለሙሉ100 % ጥሬእቃውን ከራሳችን ሃገር አግኝተን በራሳችን የሰው ሃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ለኢትዮጵያ ገበያ የሚበቃ መድሃኒት ወይም ሌላ ምርት እስካላመረትን ድረስ በአንድም ሆነ በሌላ ነገር የሌሎች ጥገኛ ነን። ሌሎችም በተመሳሳይ ደረጃው ይለያይ እንጅ የእኛ ጥገኞች ናቸው። ሁልጊዜም የጥገኝነቱን መጠን ለመቀነስ መስራት ይኖርብናል።አለዚያ የሌሎች ቅጣት በመጣብን ጊዜ ይበልጥ ያመናል። አሜሪካ ሁልጊዜ በማዕቀብ ዱላ ሃገራትን ስትዠልጥ የምናየው ከሷ ይበልጥ ሌሎች ሃገራት በሷ ላይ ጥገኛ ስለሆኑ ነው።

ወደ ነገሬ ልመለስ። በአጭሩ ሌሎች ሃገራት ላይ የኢትዮጵያን ገበያ ዝጉ የሚሉንን ሰዎች ምክር ብንከተል በማግስቱ  በቀላል  ቋንቋ እነሱም ገበያቸውን ይዘጉብናል። ለምሳሌ የኬንያ አየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይበር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገበያ እንዳይሻማ መንግስት የሚከለክል ከሆነ የኬንያም መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኬንያ እንዳይበር በማገድ ተመሳሳይ ውሳኔ ያሳልፋል። ሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ በቀር የጋራ የተንቀሳቃሽ ስልክ ታሪፍ ስምምነት አላቸው። ማለትም አንድ ኬንያዊ ወደ ሩዋንዳ ቢሄድ ሌላ የሩዋንዳን ስልክ ሲም ካርድ/መስመር መግዛት ሳያስፈልገው ኬንያ በሚከፍለው ዋጋ በሩዋንዳ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ከነዚህ ሃገራት ጋር ያልተስማማችው ኢትዮቴሌኮም ለስልክና ኢንተርኔት የሚያስከፍለው ክፍያ በዓለም ውድ ስለሆነ እና አገልግሎቱም ኋላቀር በመሆኑ እንዲሁም ይህ ኋላቀር ድርጅት በጎረቤት ሃገራት እጅግ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት በጣም ርካሽ በሆነ ዋጋ ከሚሰጡት አቻዎቹ ጋር መወዳደር ስለማይችል እና ስምምነቱ ውስጥ ከገባ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥገት ላሙ አድርጎ ገንዘብ ማለቡን ላለማቆም የጋራ የስልክ አገልግሎት ቀጠናው ውስጥ አልገባም።

ለመሆኑ በኢትዮቴሌኮም ቢሮዎች ላይ “በምስራቅ አፍሪካ ዝቅተኛ የስልክ ክፍያ ታሪፍ!” የሚል ማስታወቂያ አስተውለው ያውቃሉ?  ኢትዮቴሌኮም ህዝብ ማለብ ብቻ ሳይሆን ህዝብ ላይ መቀለድ ተክኖበታል። እስኪ ማስታወቂያውን ወደ ሂሳብ ቀይረን ለመረዳት እንሞክር። ሂሳቡ ውስብስብ አይደለም። ስለዚህ እርሳስና ወረቀት አያስፈልግዎትም። የሂሳብ ስሌቱ ይህ ነው። በሞባይል ስልክዎ ከኬንያ ወደ አሜሪካ ደውለው ለ17ደቂቃ ከ30ሰከንድ ያህል ሲያወሩ 10ብር ገደማ ሂሳብ ይከፍላሉ። ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ስልክ ደውለው ለ1 ደቂቃ ያህል ሲያወሩ ኢትዮቴሌኮም ወዲያውኑ 12ብር ይዘርፍዎታል።ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮ ቴሌኮም ለደምበኞቹ “ከሌሊቱ 5ሰዓት ሌት 11ሰዓት ይህን ያክል ደቂቃ በነጻ ስልክ ደውሉ፤ ይህን ያክል አጭር የስልክ መልክት ተለዋወጡ” ወዘተ እያለ ያለተፎካካሪ በደምበኞቹ ያላግጣል።በጎረቤት ኬንያ ግን የቴሌፎን ኩባንያዎች  ደምበኛ ለማፍራት ህዝብን ይለማመጣሉ፤ በአገልግሎታቸው ለመሳብ ይፍጨረጨራሉ፤ደምበኛ የሆንክ ሰሞንማ ትንበሸበሻለህ።ስልክ እያወራህ ድንገት ገንዘብ አልቆብህ ቢቋረጥ ይህን ያህል ገንዘብ የሚያወጣ ካርድ ስጦታ ከኤርቴል፣ይህን ያህል ሜጋ ባይት ኢንተርኔት ስጦታ፣ ካርድ ሳትሞላ ከቆየህ ደግሞ ምናልባትም ወደ ሌላኛው የቴሌፎን ኩባንያ ሳፋሪኮም ሊሄድብን ይሆን እንዴ ብለው “ውድ ደምበኛችን ይህን ያህል የኢንተርኔት ፓኬጅ በነጻ ይጠቀሙ!” እያለ ደምበኛውን እያባበለ ያገለግላል። የኬንያዎቹ የቴሌፎን ኩባንያዎች የግል ስለሆኑ ትርፍ የሚያገኙት ደምበኞቻቸውን እያባበሉ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ነው። የኢትዮጵያው ኢትዮቴሌኮም የመንግስት ስለሆነ ትርፍ የሚያገኘው ያለተወዳዳሪ እና እዚህ ግባ የማይባል ኋላቀር አገልግሎት በመስጠት ነው። ይህንንም ታዲያ በፈለገው ጊዜ እንዳሻው ያቋርጠዋል።ኢትዮቴሌኮምን ተማምነው ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የኢትዮጵያ ባንኮች እና ሌሎች ድርጅቶችም “ሲስተም አይሰራም” እያሉ በተደጋጋሚ ደምበኞቻቸውን የሚያማሩት በዚሁ ድርጅት የተነሳ ነው።ደምበኞቹን በጥገት ላሞች የሰየመው የኢትዮቴሌኮም ሌላ አማራጭ በማጣት ደምበኞቹ ለሆኑት ድርጅቶች እና ደምበኞቻቸው እንዴት ሊጨነቅ ይችላል? ይህ በመሆኑ ኢትዮቴሌኮም የሌሎች ድርጅቶችን በቴክኖሎጅ የመዘመን እና የእድገት ፍላጎታቸውን ወደኋላ የጎተተ እና እየጎተተ ያለ ድርጅት ነው።ይህ ብቻም አይደለም። ኢትዮቴሌኮም እነዚህን ድርጅቶች ወደፊት ተመሳሳይ የውጭ አቻዎቻቸው ወደሃገር ቤት ገብተው በገበያው ላይ ባለድርሻ የሚሆኑበት ስርዓት ሲፈጠር(ይህ መሆኑ የማይቀር ነው) በቴክኖሎጅው ረገድ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ትልቅ እንቅፋት ጋርጦባቸዋል። በርግጥ የኢትዮቴሌኮም ኋላቀርነት በአንድ ጽሁፍ የሚቋጭ አይደለም። ሆኖም ለምሳሌ ብቻ ያህል አንዳንዶቹን በወፍበረር መቃኘት እንቀጥል።ኬንያ እና ሩዋንዳ 4G ኔትዎርክ ከዋና ከተማዎቻቸው ውጭ ለማዳረስ እየሰሩ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮቴሌኮም የቤት ስልክ ለሚያስገባ የስልክ ቀፎ በነጻ እያለ ማስታወቂያ እየሰራ ነው። ሌሎቹ ከዘመን ጋር ወደፊት ሲጓዙ እሱ ወደ ኋላ ሄዶ የተውነውን እንድናነሳ ይወተውታል።

የቀድሞው ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ “ቴሌ ማለት ጥገት ላማችን ነው” ያሉት ሃቅ ኢትዮቴሌኮም  ለሃገር ቤትና ለውጭ ባለሃብት እስኪሸጥ እና ሌሎች የውጭ ሃገር የቴሌፎን ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው መወዳደር እስካልጀመሩ ድረስ ጥገት ላም ሆነን እንቀጥላለን። ኢትዮቴሌኮም ይሸጥ ሲባል ቁልፉ ያለው መሸጡ ላይ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ የቴሌፎን ኩባንያዎች ወደሃገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀድ ላይ ነው። ከዚህ ውጭ ኢትዮቴሌኮም ይሸጥ ሲባል “አይሆንም” የሚሉ ጥቂቶች ካሉ ምናልባትም ጥገት ላም መሆን ያልሰለቻቸው አሊያም ደግሞ ከሚታለበው ህዝብ ኪስ ተቀናሽ ተደርጎ በነጻ አገልግሎቱን የሚጠቀሙት የቴሌ ሰራተኞች መሆን አለባቸው።በጥቅሉ ሲታይ የኢትዮጵያን ገበያ ከውጭ ሃገር ተወዳዳሪዎች መጠበቅ የሚቻለው ምናልባት ኢትዮጵያን በአማዞን ጫካዎች ውስጥ መደበቅ ከቻልን ወይም ከውጭ ሃገር ጋር ያለንን ማናቸውንም የንግድ ልውውጦች በማቋረጥ ራሳችንን ችለን ስንገኝ ብቻ ይሆናል።ይህን ማድረግ አንችልም። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እኔ እርሳስ የሚል ጽሁፍ ላይ እንዳስነበብኳችሁ አሜሪካ እንኳ ከሌሎች ሃገራት የጥሬ ዕቃ ግብይት ሳታደርግ ብቻዋን ራሷን ችላ እርሳስ መስራት አትችልም። ይህን ዕውነታ ለመካድ አንድም ለለውጥ ፈጽሞ ዝግጁ አለመሆን  ወይም በዙሪያችንና በአካባቢያችን ያለውን የለውጥ ሂደት መገንዘብ ያቃተን መሆን አለብን። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ለለውጥ ዝግጁ አለመሆናችን ለውጥን ማስቀረት እንደማይችል ነው።

A project of NFS & EPO

 

Advertisement

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.