ቺሊን የታደጋት የቺካጎ ቦይስ ምክር ለኢትዮጵያ

በታህሳስ ወር 1976ዓ/ም የስዊድን መዲና ስቶክሆልም ጎዳናዎች፣ሻይ ቤቶች፣ምግብና መሸታ ቤቶች ሁሉ የአሜሪካዊያን እና የአሜሪካ ጉዳይ ጎልቶ ይወራ የነበረበት ወቅት ነው። በወቅቱ  ይህን የታዘቡ ሰዎች “ስቶክሆልም የአሜሪካን 200ኛ የነጻነት ዓመት በይፋ እያከበረች ትመስል ነበር።” ብለዋል። በዚያ ዓመት በሰባቱም ዘርፎች የኖቤል ሽልማት ያሸነፉት ሰባቱም ሰዎች አሜሪካዊያን ነበሩ። የስዊድን ሮያል አካዳሚ የኖቤል አሸናፊ አድርጎ ከመረጣቸው ሰዎች ውስጥ በተለይም በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ሽልማቱን ለሚልተን ፍሪድማን ለመስጠት መወሰኑ ሶሻሊስቶችን እጅግ አስቆጥቷል።ይህንኑ ተቃውሞ ለማሰማት በተለይም ቺሊያዊያን ኮምኒስቶችንና ሶሻሊስቶችን የቀደማቸው አልነበረም። ሚልተን ፍሪድማን የኖቤል ሽልማቱን ተቀብሎ ንግግር ማድረግ እንደጀመረ በአዳራሹ ውስጥ የሽልማቱን ስነስርዓት ይከታተሉ ከነበሩት ሰዎች ውስጥ መጮህ ጀመሩ። ፍሪድማን ንግግሩን አቋርጦ ተቃሚዎቹ ማን እና ለምን እንደሚቃዎሙት ተረዳ። በዚህን ጊዜ ፖሊስ የሚጮሁትን ሰዎች ከስፍራው ለማስዎጣት እየታገ ነው። ሚልተን ፍሪድማን ፖሊሶቹ ሰዎቹን እንዲተዋቸው ጥያቄ አቀረበ። ምክንያቱም አለ ፍሪድማን “ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በሃገራቸው መቃዎም ቀርቶ መናገር የማይችሉ ነበሩ። ይህም ብቻ ሳይሆን በሃገራቸው መኖርም ያልቻሉ ናቸው። የሚያሳዝነው እነዚህ ሰዎች እዚህ የሚኖሩትም ሆነ  የሚቃዎሙት በነሱ ሃገር የሌለው የሃብትና የነጻነት ምንጭ የሆነው ካፒታሊዝም ስላለ ነው። የሚቃወሙኝ ደግሞ ይህን ስርዓት ለነሱ ሃገር መንግስት አማክሯል ብለው ነው። የቺሊ መንግስት እንዳማክረው ጠይቆኝ “አላማክርም!” የሚል ምላሽ ሰጥቸዋለሁ ። ሆኖም ባማክረው እንኳ ለነሱ ሃገር እኔ ለምሰራው ስራ ምስጋና እንጅ ተቃውሞ እንደማይገባኝ ለመረዳት በነጻነት ተኮትኩቶ ያደገ አይምሮ እንደሚያስፈልግ እነዚህ ሰዎች ማሳያ ናቸው።” ከፍተኛ ጭብጨባ…..

ነገሩ እንዲህ ነው። በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ መጀመሪያ ላይ በቺሊ የነበረውን ሶሾሳሊስታዊ ስርዓት ተከትሎ የቺሊያዊያን ሕይወት ተናጋ። የቺሊ ዜጎች ኑሮ በድህነት እና በርሃብ ተመሳቀለ። ይህ ቀረሽ የማይባለው የዋጋ ቁጥጥር ከፍተኛ የሆነ የምርት አቅርቦት ችግር እንዲከሰት ምክንያት ሆነ። እጅግ የከፋ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ግሽበት የችሊያዊያንን ህልውና ተፈታተነ። ይህን ተከትሎ በመስከርም ወር 1973 ዓ/ም የኮምኒስቱ ሳልቫዶር አሌንዴ መንግስት በጄነራል ኦግስቶ ፒኖቼ በሚመሩ ወታደሮች ተገለበጠ።

ጄነራል ፒኖቼ ስልጣን እንደያዘ በወቅቱ በዓለም ላይ ስማቸው እጅግ ገናና ከሆኑት ኢኮኖሚስቶች ውስጥ ሚልተን ፍሪድማንን ችሊን ለመታደግ የሚያስችል ምክር እንዲሰጣቸው ይጠይቁታል።ለዚህም የሚጠይቃቸውን ክፍያ እንደሚከፍሉ ይነግሩታል። ፍሪድማንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስትን በጉልበት የገለበጡ ወታደሮችን አላማክርም በማለት ምላሽ ይሰጣል።ይህን ቢልም በወቅቱ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ቺካጎ የፍሪድማን ተማሪዎች የነበሩ አራት ቺሊያዊያን ኢኮኖሚስቶች ግን እሱ በቀጥታ የቺሊን ወታደራዊ መንግስት መርዳት ባይፈልግ እንኳ ለነሱ ያን ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ እንዲያሳያቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሏቸዋል።እነዚህ አራት ቺሊያዊያን ከመምህራቸው ሚልተን ፍሪድማን ጋር ሆነው ለችሊ የሚበጀውን የኢኮኖሚ አቅጣጫ እና የአተገባበር ስልት ነድፈው ጨርሱ። ዘ ቺካጎ ቦይስ በመባል የሚታወቁት አራቱ ቺሊያዊያን ኢኮኖሚስቶች ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ለሃገራቸው የነደፉትን ዕቅድ ድረሱልኝ ላለው ወታደራዊ መንግስት እንዲተገብረው ወደ ቺሊ በረሩ።  ቺካጎ ቦይስ ቺሊን ከገባችበት አዘቅት ይታደጋታል በማለት ያቀረቡት መፍትሄ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሲሆኑ  ከተጠቀሱት መፍትሄዎች ጋር ተያያዥ ለሆኑት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮችም  እንደዋና መፍትሄ ተደርገው የሚቀርቡ ናቸው።

✲  መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ወጭዎቹን እንዲቀንስ፣

✲  የግብር ስርዓቱ ግልጽነት የተሞላበት እንዲሆን እና የተመን፣የክፍያ እና የአሰባሰብ ዘዴው ማሻሻያ እንዲደረግ፣

✲ መንግስት እንዳሻው ገንዘብ እያተመ እንዳያጋሽብ (ብሩን የመግዛት አቅም እንዳያሳጣው) ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት አሰራር እንዲዘረጋ ፣

✲ መንግስት ከኢኮኖሚው ውስጥ እጁን እንዲያወጣ እና የመንግስት የሆኑ ተቋማትን ሁሉ ለግለሰብ ነጋዴዎች እንዲሸጥ የሚሉ ነበሩ።

የቺሊ መንግስት ይህን  ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ በኋላ የነበረው ግሽበት በከፍተኛ ሁኔታ ከመቀነሱም በላይ ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ ሃገሪቱ ተአምራዊ የኢኮኖሚ እድገት አስመዘገበች። የቺሊ ስኬት ቀጠለ። በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ችሊ ለዓለም አዲስ የሆነ የሰራተኞችን ጡረታ በግል ኩባንያዎች ማስተዳደር የሚቻልበትን ስርዓት ተገበረች። ይህ ስርዓት ተግባራዊ በሆነ ሁለት ዓመታት ውስጥ የሃገሪቱ የካፒታል ገበያ እና የቁጠባ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋቱ የቺሊ ኢኮኖሚ ይበልጥ ተመነደገ። በአሁኑ ሰዓት 93% የሚሆነው የችሊ ጡረተኛ አገልግሎቱን የሚያገኘው ወደ ሃያ ከሚጠጉ የተለያዩ የግል የጡረታ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ነው። የበርካታ ሃገራት የጡረታ መስሪያ ቤት ሃላፊዎች የቺሊን ከችሊ ስኬት ለመማር በተደጋጋሚ ወደዚያው ያቀኑ ሲሆን እስካሁን በደቡብ አሜሪካ፣በአውሮፓ እና በኤዥያ የሚገኙ 31 ያህል ሃገራት የቺሊን የግል የጡረታ ስርዓት በሃገራቸው ዘርግተዋል።

ዛሬ ላይ አስራ ሰባት ሚሊዮን ህዝብ ያላት ቺሊ ዜጎቿ ከደቡብ አሜሪካ ሃገራት ሁሉ የተሻለ የኢኮኖሚ እና የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የዜጎቿ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢም ከአስራ ስምንት ሽህ አራት መቶ ዶላር በላይ ሆኖል። በደቡብ አሜሪካ በኢኮኖሚ ነፃነቷ ተወዳዳሪ የሌላት ቺሊ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የተሸጋገረችው ገና እኤአበ1990ዎቹ መጀመሪያ ግድም ነበር። ይህን ጽሁፍ እስከምጽፍ ድረስ እጄ ላይ ባለው መረጃ መሰረት የፊታችን መስከረም ይፋ ሆኖ በሚወጣው የዘንድሮ(2018ዓ/ም) የዓለም የኢኮኖሚ ነፃነት ሪፖርት ላይም ቺሊ ከደቡብ አሜሪካ ሃገራት አንደኛ ስትሆን በሪፖርቱ ከተካተቱ መቶ ስልሳ ሶስት ሃገራት ውስጥም የ15ኛ ደረጃን ይዛለች። ይህ ደረጃ ምናልባት የመጨረሻው ሪፖርት ተጠናቅሮ ሲያልቅ ምናልባትም መጠነኛ ከፍና ዝቅ ሊኖር እንደሚችል ከወዲሁ ላሳስብ እወዳለሁ።

ከላይ በጥቂቱ ለማሳየት እንደተሞከረው መንግስት ለዕውነተኛ ለውጥ ዝግጁ ሆኖ የምሁራንን ዕገዛ ከጠየቀ ከሁሉም ባይሆንም እንኳ እገዛ በተጠየቀበት መስክ የተሰማሩ የጥቂት የበቁ ምሁራን እገዛ ካገኘ ሀገርን እና ህዝብን ወደተሻለ አቅጣጫ መውሰድ እንደሚቻል ማሳያ ይሆናል። በዚህ ጽሁፍ ለዕውነተኛ ለውጥ ዝግጁ  የሆነ መንግስት ማለት የምሁራንን ምክር በፖለቲካ አጀንዳው ሳይዋጅ ወደተግባር ለመቀየር ሲወስን ሲሆን “የበቃ ምሁር” ማለት ደግሞ በግል ከመረጡት ወይም ከሚከተሉት የፖለቲካ ጽንሰሃሳብ ይልቅ ሳይንሳዊ፣ታሪካዊ እና ሎጅካዊ አካሄድን ተከትለው ለሃገር ችግር መፍትሄ የሚፈልጉትን ለማለት ነው። ለምሳሌ ያህል አብዛኛው ሰው ከለበሰው ልብስ እስከተጫማው ጫማ ድረስ ከውጭ ሃገር የገባ መሆኑን እያወቀ እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጽፍበት ብዕር እና ወረቀት 100በመቶ ከውጭ ሃገራት ተገዝቶ መግባቱን እያወቀ ወይም ማወቅ እያለበት “አገራችንን ለውጭ ሃገር ገበያ ዝግ ማድረግ አለብን!” የሚል ምሁር ይህን ደፍሮ ከመናገሩ በፊት የተመኘው ዕውነት ከመሆኑ በፊት የሚጽፍባቸውን ቀለሞች ከቅጠላ ቅጠል መቀመምን ጨምሮ የቀለም ቀንድ እና የሚጽፍበትን ቆዳ ፍቆ ማዘጋጀት መቻሉን ማረጋገጥ አለበት።ይህንን በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ተማሪዎች እንዴት ማዳረስ እንደሚቻልም ማሰብ አለበት። ራሱን ከእንዲህ ዓይነት ያፈጠጠ እውነታ ጋር ማሟገትም ሆነ ለክርክር መዘጋጀት ትርፉ ጊዜ ማጥፋት ብቻ ነው። ስለዚህ ለውጥ ፈላጊው እነደነዚህ ዓይነት ምሁራን የእቅዱ እንቅፋቶች ሊሆኑ ከሚችሉ ዝርዝሮች ውስጥ በማስፈር የነሱን ተምኔታዊ ትርክት በኢኮኖሚያዊ እና ሳይንሳዊ ሃቆች ተመስርቶ ፉርሽ ማድረግ ይኖርበታል።

ፍሪድማን ለተቃዋሚዎቹ ያደረገውን ንግግር በመግቢያየ ላይ እንዳሰፈርኩት እዚህም ልድገመው። ፍሪድማን የኖቤል ሽልማት ሲቀበል የተቃወሙትን ቺሊያዊያን “…ለነሱ ሃገር እኔ ለምሰራው ስራ ምስጋና እንጅ ተቃውሞ እንደማይገባኝ ለመረዳት በነጻነት ተኮትኩቶ ያደገ አይምሮ እንደሚያስፈልግ እነዚህ ሰዎች ማሳያ ናቸው።” ነበር ያለው። አዎ! ነጻነትን ከሚያሳጣ ስርዓት በላይ ነጻነትን የሚገፍ አይዲዮሎጅ አራማጅ እና ተከታይ ሆኖ የወጣትነት ጊዜን ማሳለፍ የኋላ ኋላ የቱንም ያህል ቢማሩ ወይም በስደት ነጻነትን ማጣጣም ቢችሉም እንኳ አይምሮቸውን ለለውጥ ዝግጁ እንዳይሆን ያደርጋቸዋል። ይህን ሲያደርጋቸውም ይስተዋላል። ምክንያቱም ጥቂት የማይባሉት በዚህ መስመር ያለፉት ሰዎች/ምሁራን አስተሳሰባቸውን ከመቀየርም ሆነ ለሃገርና ህዝብ ከሚጠቅመው መንገድ ይልቅ ከከሸፈው የፖለቲካ አይዲዮሎጃቸው ጋር በትዝታ ሰመመን ውስጥ ተደብቆ መኖርን ምርጫቸው ስለሚያደርጉ ነው። ለማስረዳት ያህል የህወሃትን መሪዎች በአማራ ህዝብ ላይ ያወጁትን ጠላትነት ልጥቀስ። እነዚህ ሰዎች በጫካ ያደጉት በኮምኒዝም አስተምህሮ ነው።ኮምኒስቶቹ ወያኔዎች በዚያው በጫካ ሳሉ ስለመስፋፋትና ስለሚሰርቁት መሬት እያለሙ ከመሬቱ ላይ ሊያፈናቅሉት የከጀሉትን ህዝብ በጠላታትነት ፈረጁት።ይህንኑ ጥላቻ በማኔፌስቷቸው ላይ ጻፉት። ለነዚህ ሰዎች የአማራ ህዝብ ጠላታቸው የነበረው ጫካ እያሉ ነበር።ስልጣን ሲይዙና ያን ድሮ የተመኙትን መሬት ሲያስፋፉም ጠላት ነበር። ህወሃት ጠላታችን በሚለው ህዝብ ሜዳ ላይ እንዳሻው አዛዥናዛዥ መሆን ባቃተው በዚህ ሰዓትም የአማራ ህዝብ ጠላቱ ነው።ይህ ጠላቱን ድሮ እንደተመኘው ማጥፋት ያልቻለ ቡድን  ዕውን መሆን ያልቻለውን እና የማይችለውን ተምኔቱን በትዝታ ሰመመን ውስጥ ተደብቆ ሲያንጎላጅ ይኖራል እንጅ “የያዝኩት መንገድ አያዋጣም!” ብሎ በሁለት ዓመት እድሜው የፀነሰውን ጥላቻ በ42ዓመቱ ፈጽሞ አይተወውም። ሰዎችም በአፍላነታቸው ባንድ ነገር ላይ እምነት አድሮባቸው ለዚያ ተፈጻሚነት ከልባቸው ከሰሩ የተመኙት ተሳካም አልተሳካ በዚያ ነገር ያላቸው እምነት እና ፍቅር ወይም ያን ምኞታቸውን እውን ለማድረግ በሌላ አካል ወይም እነሱን በሚጻረር አስተምህሮ የሚጸንሱት ጥላቻ የእድሜ ልክ ነው። አበው “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም!” የሚሉት ለዚህም አይደል? አበቃ!!

Written by Kidus Mehalu | for EPO & NFS

Advertisement