የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረታዊ መሰረቶች ከተፈጥሮዊ ሕጎች ወይም ከኦሪት ዘመን ትዕዛዛት ይመነጫሉ። አትስረቅ ፣ የሰውን ንብረት አትመኝና በሐሰት አትመስክር ከሚሉት የወጣ ነው። “የሥርቆት” ጨዋታ የሌላን ሰው ሐብት መቀራመት ያመጣል።ሐብትን የማሳደግ ተስፋን ያጨልማል። የሌሎችን ንብረት መመኘት የሌላን ሰው ሐብትን አስገድዶ ለመከፋፈል ድርጊት ይጋብዛል። ይህ ደግሞ የነገውን ምርት የማምረት ተነሳሽነት አደጋ ውስጥ ይከታል። በሐሰት መመስከር የማህበረሰብን ሞራላዊ ዕሴት ዝቅ በማድረግ ለውርደት ይዳርጋል። ይህ ደግሞ የሰብአዊነት መገለጫዎችን ይበልጥ ያጎድፋል። በተጨማሪም የአስተዳደርን ተአማኒነት፣የኢንቨስተርን አመኔታ፣የረዥም ጊዜ የትርፋማነትን ዕቅድና በገበያ ላይ በነጻነት የሚደረጉ ልውውጦችን መጠን ዝቅ ያደርጋል።
ከተሞክሮዬ እንዳየሁት በጣም ብዙዎች ምናልባትም 90 በመቶ የሚያህሉ አለመግባባቶች መንስኤ የሚሆነው የሌላውን ወገን መረጃ አለማግኘት ነው። ሰዎች ከአንድ ባህል ወደ ሌላ ባህል ሲንቀሳቀሱ የሌላው ወገን መረጃ ያስፈልጋቸዋል። በባህል ጥበቃ ሰበብ በሚደረግ ተከላካይነት፣በብሔርተኝነት እና አንዱ ሌላውን መረዳት ባለመቻል ምክንያት ገዥዎቻችን ለረጅም ዘመናት ከአመክንዮ እና ሳይንሳዊ ሃቆች ጋር የሚጣረሱ ፖሊሲዎች ሲፈጽሙ እና ሲያስፈጽሙ ኖረዋል። ይህም ከላይ በመግቢያው የጠቀስኩትን እንደ ሃገር የአስተዳደርን ተአማኒነት እና የኢንቨስተርን አመኔታ ስላሳጣን ይህንኑ ለማካካስ በከተሞች አቅራቢያ በሚገነቡት፣በግል ጥበቃዎች የሚጠበቁት እና ሙሉ ምርታቸውን ከታሪፍ ነጻ ወደ ወጭ ሃገራት የሚያቀርቡት የኢንዱስትሪ ዞኖችን ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር ከተገነቡባት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያን አንዷ አድርጓታል። እነዚህ ነዋሪዎችን በውድም ሆነ በግድ ከሚኖሩበት በማስነሳት/በማፈናቀል የሚገነቡት የዓለም ባንክ ቻርተር ሲቲስ ብሎ የሚጠራቸው የኢንዱስትሪ ዞኖችን ለመገንባት ፈቃደኛ አለመሆን የምዕራብያዊያንን ዕርዳታ እና የዓለም ባንክ የገንዘብ ብድርን የሚያሳጣ ለአፍሪካ የተነደፈ አዲስ አሰራር ነው። ይህም አፍሪካ እና አፍሪካዊያን ወደ ዴሞክራሲዊ ስርዓት የሚወስዱ ተቋማትን እስኪያቋቋሙ ድረስ በአዲሱ የቅኝግዛት ቀመር መሰረት ከሃገሮቻቸቸው መሬት ላይ የተወሰነውን እነዚህን ቻርተር ሲቲስ/የኢንዱስትሪ መንደሮች እንዲያቋቋሙ ያደርጋል።
ይህን የኢንዱስትሪ መንደሮች ግንባታ ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የድሃ አገራት መንግስታት የ“ውጭ ኢንቨስተሮች”ን አመኔታ ለመሳብ በዓለም ባንክ የገንዘብ ብድር ያቋቋሟቸውን የኢንዱስትሪ ዞኖች በማስተዋወቅ ተጠምደዋል። ሆኖም የሃገራቱ ትኩረት “የውጭ ኢንቨስተሮችን” መሳብ ላይ እንጂ የገዛ ሕዝቦቻቸውን ወደ ንግዱ ዓለም እንዲገቡ ወይም በከፊልም እንኳ እነዚህን የኢንዱስትሪ ግንባታዎች እንዲጠቀሙባቸው አያበረታታም። የውጭ ኩባንያዎች በሃገራቱ በሚገነቡት የኢንዱስትሪ ዞኖች ተጠቅመው ምርቶቻቸውን ሙሉለሙሉ ወደውጭ ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ ለመሆን ሲሯሯጡ የየሀገሮቻቸው ሕዝቦች ግን ተጠቃሚ እንዲሆን አልተደረገም። ምክንያቱም “የኒዎ-ኮሎኒያል ቻርተር ሲቲስ” አስተዳደር ይህ እንዲሆን አይፈቅድም። ለምን ከተባለ የውጭ ልሂቃን ከራሳቸው መንግስታት ጋር በመነጋጋር በሚሰጡት ዕርዳታ አማካይነት የራሳቸውን ጥቅም የሚያስከበር ድርድር በማድረግ የአፍሪካን መንግስታት የውል እስራት ውስጥ ስለሚከቷቸው ነው።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ “ለውጭ ኢንቨስተሮች” ከሚሰጡት የሞኖፖል መብት በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነቶቹ መንግስታት የዘረጉት የኢኮኖሚ ስርዓት ወትሮም የኒዎ-ኮሎኒያል ቻርተር ሲቲስ የሚከተለውን አሰራር በብዙ ይመስለዋል።የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛ ተዋንያን በመሪዎች ፈቃድ የልዩ ጥቅማጥቅም ባለመብቶች እና ከነሱ ጋር በጥቅም ትስስር የተደራጁ የራሳቸው ቡድኖች ናቸው። ገዥዎቻችን በጥቅም የተሳሰሯቸው ቡድኖች ገበያውን እንዳሻቸው እንዲፈነጩበት እየፈቀዱ የገዛ ሕዝባቸውን ከገበያ ከሚገኘው ትሩፋት ተቋዳሽ በማድረግ ፋንታ የበይ ተመልካች እንዲሆን አስገድደውታል። ይህ ዓይነት አሰራር ድሆችን ይበልጥ ወደታች ይጫናል። የመንግስት ትስስር ወይም የጥቅም ተጋሪ ያልሆኑ ጥሮ አዳሪ ነጋዴዎች እና ባለሃብቶች በነጻነትና በሙሉ አቅማቸው እንዳይሰሩ ደግሞ በነርሱ ላይ ብቻ የሚተገበር ገዳቢ ህግና መመሪያ በማውጣት እንዳያንሰራሩ ይደረጋል። በተጨማሪም ይኽው የሕግ የበላይነት መክሸፍ አብዛኛውን የሃገር ቤት ነጋዴዎች እና ባለሃብቶች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ሽባ ያደርጋቸዋል። በነጻነት እና በህግ የበላይነት ላይ መህልቁን የማይጥል የንግድና የገበያ ስርዓት የሃገራችንን ውስን ሃብት ለብክነት ሲዳርግ ኖሯል።አሁንም በመዳረግ ላይ ነው። ይህም የሃገሪቱ ገቢ እና የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ ዝቅተኛ ሆኖ ከቀጠለበት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል። ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ ሃገራዊ መመሪያዎች እና የኒዎ-ኮሎኒያል ቻርተር ሲቲስ ውሎች የኢኮኖሚ ነጻነታችንን ከመግፈፋቸው በተጨማሪ ድካማችንን ሁሉ መና በማስቀረት ድህነታችንን ይበልጥ ያባብሳሉ።
ከመሪዎች ምን ይጠበቃል?
ለሕዝባቸው አክብሮት ያላቸው መሪዎች ህዝብን የሚያደህይ ሃገራዊ መመሪያ/ፖሊሲ ተግባራዊ አያደርጉም።ለሕዝባቸው አክብሮት ያላቸው መሪዎች የሀገር ውስጥንና የውጭን የገበያ ተወዳዳሪዎች የማያካትት የሞኖፖሊ መብቶችን ለአንድ ወገን በመስጠት የኢኮኖሚ ነፃነታችንን አይገፉም። በገበያ ላይ ያለንን የምርጫ ነፃነት አይገድቡም።በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የጥራት ጉድለት የሚታይባቸውን ሽቀጣ ሸቀጦችና አገልግሎቶች እንድንገዛ አያስገድዱንም። አዋጭ ያልሆነ ዋጋ የመክፈል ግዴታ ውስጥም አይከቱንም። የንግድ ስርዓትን ጤናማ ሂደት የሚያፋልስ አድሏዊ መመሪያ እና ግልጽነት የጎደለው የግብር ስርዓት አይተገብሩም።
ለሕዝባቸው አክብሮት ያላቸው መሪዎች ገበያውን ለውድድር ክፍት የሚያደርግ መመሪያ ስራ ላይ ለማዋል በአጀንዳዎቻቸው ላይ በማስፈር ለተግባራዊነቱ ጠንክረው ይሰራሉ። ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በመሪዎች ፈቃድ የልዩ ጥቅማ ጥቅም መብት የሚያገኙበት አካሔድ “ነፃ ገበያ” ሳይሆን አግላይ ገበያ መሆኑን ይረዳሉ።የሀገር ውስጥ ተቋማት በገዛ መሪዎቻቸው ከገበያ (ንግድ ስራ) የሚወገዱበት ስርዓት “ነፃ ገበያ” ሳይሆን አዳይ ገበያ መሆኑን አይስቱትም።ከኢኮኖሚው አቅም በላይ ወይም በኢኮኖሚው ጤናማ አካሄድ ያልተገኘ ገንዘብ እያተሙ ወደኢኮኖሚው ውስጥ ማስገባት አገርና ህዝብን ዋጋ እንደሚያስከፍል ይረዳሉ።
ለሕዝባቸው አክብሮት ያላቸው መሪዎች የ“ውጭ ኢንቨስተሮች”ን ለመሳብ “ልዩ የኢንዱስትሪ ዞኖች”ን ማዘጋጀታቸው ጥሩ ሐሳብ ከሆነ “ለምንድንስ ነው ሰፊው ሕዝባችን ከእነርሱ ተጠቃሚ መሆን የማይችለው?” ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። የልዩ ጥቅማጥቅም መስጫ የኢንዱስትሪ ዞኖችን ለ“ውጭ ኢንቨስተሮች” ከመገንባትና አገሬውን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ስርዓት አዘጋጅቶ ከመተግበር የሚሻለውን በሳይንሳዊ ሃቆች እና አመክንዮ መሰረት ላይ ቆመው ለመረዳት ይሞክራሉ። ለሕዝባቸው አክብሮት ያላቸው መሪዎች ለ“ውጭ ኢንቨስተሮች” ልዩ እድል በመስጠት የራስን ዜጎች መግፋትና ከውድድር ማስወጣት ህዝባቸውን ወደ ድህነት ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጂ አማራጮችንና መሠረተ ልማቶችን በመንፈግ ወደ ኋላቀርነት ላለመግፋት ይጠነቀቃሉ። ለምሳሌ እንደ ቴሌ፣ውኃና የሃይል አቅርቦት ያሉ አገልግሎቶችን የመስጠት ስራ ላይ የሀገር ውስጥ ተወዳዳሪዎች እንዳይሳተፉ መደረጉ ወይም ለመሳተፍ የሚችሉበት አቅም እንዳያገኙ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ስርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ሕዝባችን ቴክኖሎጂን፣አማራጮችንና መሠረተ ልማትን የተመለከቱ ሀገራዊ እውቀቱንና ችሎታዎቹን እንዳይጠቀም ትኩረት ይነፍጉታል።ይህ ደግሞ ወጣቱ በፈጠራም ይሁን ከቴክኖሎጅ ጋር ሊኖረው ከሚገባው ቁርኝት እና ዘመኑ የሚጠይቀውን ዕውቀት ይዞ ከመገኘት አንጻር በዓለም የስራ ገበያዎች ተወዳዳሪ እንዳይሆን ያደርጉታል። ይህ ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሰራበት ኢትዮጵያ ከቤት ሰራተኛ ውጭ ለውጭ ሃገር የምታቀርበው የሰው ሃይል ለወደፊትም ሊኖራት አይችልም።ይህኛውም ቢሆን አማራጭ በሌለበት ሁኔታ አማራጭ የሚሆነው ለሴቶች ሲሆን “ወንዶችስ ምን አማራጭ ይኖራቸዋል?” ብለን ለዘላቂው መፍትሄ ማሰብ ይኖርብናል። ለጊዜው በሃገራቸው የመኖር ተስፋ ያጡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተስፋ ወደሰነቁበት የሰው ሃገር ለመግባት ሲሉ ውድ ህይወታቸውን መገበር ቀጥለዋል። ግን እስከመቼ?
እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ብልፅግናችን በውጭ ዕርዳታ ወይም በቀላል መንገድ በሚገኝ ገንዘብ የሚመጣ አይደለም። እሱን ብዙ አግኝተናል። ግና በድሆች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ አላመጣም። የዚህ ዓይነት ዕርዳታ ሙስናን ይፈጥራል፤ ፈጥሯልም። የሕግ የበላይነትን ይሸረሽራል፤ሸርሽሯልም። ይህ የነጻ ንግድ እና ገበያ መርሆች ጋር ይጣረሳል። ከምንም በላይ ደግሞ “ዕርዳታ” መሪዎችን ከሕዝብ ይነጥላል።
የሚያስፈልገንስ ምንድ ነው?
እኛ የሚያስፈልገን መረጃ ነው።መሬት ላይ የሚያሰራ ሀገሬው እውቀቱንና ችሎታዎቹን እንዲጠቀም የሚያበረታታ ስርዓት እንፈልጋለን። ይህ ዓይነት ተመሳሳይ ስርዓት የት እንደሚገኝ ሃቁን በማስረጃ ማረጋገጥ እንሻለን። አብዛኞቹ ምስጢራት እይደሉም። እንዲያውም ሚስጢር የሚመስሉት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። የነፃ ገበያ ስርዓት የንግድ ነጻነትና የሕግ የበላይነት መከበር ላይ ተመስርቶ የሚሰራ የብልጽግና ቁልፍ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ነፃ ገበያ የሕግ የበላይነት መኖርንና በተፈጥሮኣዊ አካሔዶች ሁሉም በቻለው እና አቅሙ በፈቀደው መጠን – በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ በንግድ ስራው (በማንኛውም ልውውጥና ግብይት) እንዲሳተፍ ማድረግ የሚያስችለን ስርዓት ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይኖርብናል። ነጻ ገበያ በህግ የበላይነት መህልቅ ላይ ሲቆም ሥራን የመፍጠር እድሎችና በገበያው ላይ ስራ የሚፈጥሩ ውድድሮች ይበራከታሉ። ከነዚህ ዓይነት ውድድሮች የሚፈጠሩ የንግድና የስራ አጋጣሚዎች ተጠቃሚ ለመሆን ደግሞ አይምሮአችንን ይበልጥ ለመጠቀም እንሞክራለን። ይህ ደግሞ እምቅ ኃይላችንና እውቀታችን መክኖ እንዳይቀር ይረዳናል። በሌላ ጎንም የተከላካይነትና የልዩ ጥቅማ ጥቅም መብቶች መኖር የሚደግፍን ስርዓት አሰራር መመርመር ይኖርብናል። ይህ ዓይነት ስርዓት አሁን በኢትዮጵያ የሚተገበረው ማለት ነው። በእኔ አረዳድ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅር የኢኮኖሚ ውድቀት እና የህዝብ ማደህያ ሁነኛ መንገድ ማሳያ ሲሆን በኢኮኖሚው ላይ ለሚፈነጩ ባለልዩ መብት ተጠቃሚዎች ደግሞ ከልክ ያለፈ የማይገባቸውን ሃብት መቀራመቻ መንገድ ነው። የማይገባቸውን ሃብት በማይገባ መንገድ በሚያከማቹበት ስርዓት ውስጥ የሚያልፉ ጥቂት የማይባሉ የማህበረሰብ አባላት የነዚህን የጥቅም ተጋሪዎች ድርጊት በማየት ከጥረት ይልቅ ፖለቲካው በኢኮኖሚው መዋቀር ላይ ባቆራኘው የጥቅም ሰንሰለት ለመንጠላጠል ሲወጡና ሲወርዱ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ ማየት የስርዓቱ ሌላው አሳዛኝ ገጽ ነው።በአንጻሩ ይህ ደግሞ የእውቅትን፣ራስን የመቻልን፣የሥነምግባርን፣ የቁርጠኝነትንና በራስ የመተማመን ችሎታ አስፈላጊነትን ያደበዝዘዋል። ይህ እየቀጠለ እና እየተስፋፋ ሲሄድ በህዝብ ላይ የሚፈጸም ታላቅ ወንጀል ይሆናል።
ታዲያ ምን ይሻላል?
ፔሩያዊው ኢኮኖሚስት ሔርናንዶ ዲ ሶቶ እንዳለው ሰዎች ኑሯቸውን ለማሻሻል “ሙት ካፒታልን” ወደ “ሕያው ካፒታል” መቀየር የሚያስችል አቅም የሚያገኙት እና ያን አቅም ተጠቅመው ኑሯቸውን ማሻሻል የሚችሉት በሕግ ፊት እኩል የሚያደርጋቸው ስርዓት ሲተክሉ ብቻ ነው።ለዚህም ኢትዮጵያን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። አዎ!ኢትዮጵያ ሙት ካፒታል የተትረፈረፈባት ሃገር ብትሆንም ህዝቡ ከድህነት ለመውጣት ያለውን እምቅ ፍላጎቱን እና አቅሙን ተጠቅሞ ይህን የተትረፈረፈ ሙት ካፒታል ሕይወቱን ማሻሻል ወደሚችል “ሕያው ካፒታል” ለመቀየር እንዳይችል ያደረጉት እና የሚያደርጉት በርካታ የፍትህ እና የኢኮኖሚ ነጻነት እንቅፋቶች የሰፈኑባት ሃገር ናት።ይህ ዓይነት ስርዓት ሳይሻሻል የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት የሚወጣው “ከእባብ እንቁላል እርግብ ይፈለፈላል” የተባለ እንደሁ ብቻ ነው። ከተገቢው የኢኮኖሚና የፍትህ ስርዓት ለውጥ ጋር ተያይዞ ህያው ሊሆን የሚችል ብዙ ሙት ካፒታል አለን። ስለዚህ ይህኛው ስርዓት ከተሻሻለ ኢትዮጵያዊያንን የካፒታል አጥረት ወይም እጦት የሚገታን አይሆንም ማለት ነው። ይሁን እንጅ እንዳለመታደል ሆኖ ይህ ዓይነት ወደ መሰረታዊ ለውጥ የሚወስድ ሽግግር ከኢኮኖሚው እና ከፍትህ ስርዓቱ ልዩ ባመብቶች እና ተጠቃሚዎች ቀላል የማይባል ፈተና እንደሚጋረጥበት የታወቀ ነው።ሆኖም ግን ይህን ፈተና ተጋፍጠን በስኬት ካላለፍን የለውጡን ጣፋጭ ፍሬ ማጣጣም አንችልም። ለውጥ በእርግጠኝነትም በፈተና የተሞላ መሆኑን አውቀን ለዚያም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል።
Written by Kidus Mehalu | EPO & NFS
You must be logged in to post a comment.