⦿የዶላር ምንዛሬ ዋጋ መጨመር እና የብር ዋጋ ማጣት-ትርጉም እና ምንነት 1 

1(By Kidus Mehalu/በቅዱስ መሐሉ ©2017)

የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብር ከዶላር አንፃር ያለው የምንዛሬ ዋጋ በይፋ እንዲቀንስ ማድረጉ ይታወቃል።ይህን ያደረገበት ምክንያት ደግሞ ምርታቸውን ወደ ውጭ ሃገር የሚልኩ ነጋዴዎች/ኤክስፖርተሮች/ በውጭ ሃገር ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እና ምርታቸውን በቅናሽ ዋጋ ለማቅረብ እንዲችሉ ማስቻል የሚል ነው።ሆኖም ግን የኢትዮጵያን ኤክስፖርተሮችን ለማበረታታት በሚል ምክንያት የብር ዋጋ ከዶላር አንፃር ዝቅ ከመደረጉ በስተጀርባ ሌሎች ሊታለፉ የማይችሉ ኢኮኖሚያዊ ሃቆች አሉ። አንዱ የገንዘብ ዋጋ ዝቅ እንዲል መደረጉ የብሄራዊ ባንክ ሞኔታሪ ፖሊሲ(በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ፍሰት ቁጥጥር) አይረቤነትን/ክሽፈትን ያሳያል። ሁለተኛው ከውጭ ሃገራት የሚመጡ ምርቶች እና ሸቀጦች ለኢትዮጵያዊያን ውድ እንዲሆኑባቸው በማድረግ እና አማራጭም በማሳጣት የሃገር ውስጥ ምርቶችን በግድ በውድ ዋጋ እንዲገዙ እጅ መጠምዘዝ ማለት ነው። የብር ዋጋ ዝቅ ሲል የሃገር ውስጥ ፋብሪካዎችም ከውጭ የሚገዙት የምርት ግብዓቶች ስለሚወደዱ ኢትዮጵያዊያኑ የሃገር ውስጥ ምርትንም ቢሆን እንኳ ተገደው የሚገዙት በርካሽ ሳይሆን ድሮ ሲገበዩበት በነበረው ዋጋ ላይ የዶላ ጭማሪው የሚፈጥረውን ክፍተት ከኪሳቸው በመጨመር ይሆናል ማለት ነው። ይሄንን ግልጽ ለማድረግ በምሳሌ እንዲህ ለማሳየት ልሞክር። ሂሳቡን ለማቅለል እና በደንብ ለመረዳት እንዲረዳ አንድ የአሜሪካ ዶላር በአንድ የኢትዮጵያ ብር ይመነዘራል ብለን እናስብ። ይሄ ማለት አጠቃላይ የምርት ወጭው 80ብር የሆነ ምርትን ወደ አሜሪካ የሚልክ የኢትዮጵያ ነጋዴ/ኤክስፖርተር/ በአሜሪካ በ100ዶላር ቢሸጥ ይሄንኑ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲቀረው ያው መቶ ብር ያገኛል ማለት ነው።

ነገር ግን መንግስት ኤክስፖርትን እና ኤክስፖርት የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ለማበረታት በሚል የብር ዋጋ ከዶላር አንፃር ያለውን ምንዛሬ ዝቅ አድርጎ አንድ ዶላርን በ1 ብር ከ50 ሳንቲም እንዲመነዘር መመሪያ/አዋጅ አወጣ። ይሄን ተከትሎ በአሜሪካ በ100ዶላር ምርቱን ሲያቀርብ የነበረው ነጋዴ ምርቱን በ66.66 ዶላር ለገበያ ያቀርባል ማለት ነው። የብርን የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ዝቅ በማድረግ የኢትዮጵያ ነጋዴዎችን በውጭ ሃገር ገበያዎች ከውጭ ተፎካካሪዎች ይበልጥ በርካሽ ምርቱን እንዲያቀርብ ይረዳዋል ማለትም ይሄው ነው። ሆኖም ግን ይህ ዓይነት የኢኮኖሚክስ አተያይ ከአመክንዮ ጋር የተጣላ እና ሸውራራ መሆኑን በሌላ ምሳሌ ልግለጸው።

አሁንም በቀላሉ ለመረዳት እንዲረዳችሁ ይህችን እውነታ አንዴ ያዙልኝማ! የዓለማችንን ግዙፍ ኢኮኖሚ ዘዋሪዋ ትልቋ ሃገር አሜሪካ ትንሿን እርሳስ ለማምረት የሚያስችላትን የምርት ግብዓቶች ሁሉ ከሌላ ሃገር ካልገዛች በቀር እርሳስ እንኳ ማምረት እንደማትችል ልብ በሉልኝ። ይህ ማለት ምርቱን ወደውጭ የሚልክ በኢትዮጵያ የሚገኝ አንድ ፋብሪካም ለምርቱ የሚያስፈልገውን ግብዓት ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር ሊያገኝ እንደማይችል ምንም የማያጠራጥር ፋክት ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ የሚገኘው ፋብሪካ ለምርቱ የሚያስፈልገውን ግብዓቶች ከውጭ ሃገራት ይገዛል ማለት ነው። ቀደም ሲል ለምርት ግብአቶች 80ብር የሚያወጣው ነጋዴ በውጭ ሃገር ተወዳዳሪ እንዲሆን ተብሎ የብር ምንዛሬ ዋጋ ከዶላር አንፃር ወደ 1ብር ከ50 ዝቅ ሲልበት ይህ ፋብሪካ ለምርቱ ግብዓት ግዥ የሚያወጣው ወጭ ከ80ብር ወደ 120ብር ከፍ አለ ማለት ነው። በዚህ መሰረት በ80ብር ያመረተውን ምርት በ100ብር ለገበያ ያቀርብ የነበረው ነጋዴ የምርት ወጭው 120ብር ሲሆንበት መሸጫ ዋጋውን መጨመሩ የማይቀር ስለሆነ መንግስት በግርድፉ የ100ዶላሩን እቃ በርካሽ 66.66ዶላር እንዲሸጡ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማለት የብርን ዋጋ ዝቅ ማድረጉ የማያዛልቅ ስሌት ይሆናል ማለት ነው። ይሄው ምርት በኢትዮጵያ ሲቀርብም ኢትዮጵያዊያን ቀደም ሲል በ100ብር ይገዙት የነበረው በ120ብር ለመግዛት መገደዳቸው የማይቀር የገበያ ላይ ዚቅ ይሆናል። ይሄ ከሆነ ታዲያ ኤክስፖርተሮቹ ወይም ነጋዴዎቹ እንዴት ሊጠቀሙ ይችላሉ? በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው።

ኤክስፖርተሮቹ የሚጠቀሙት ደሞዝ ከሚከፍሏቸው ሰራተኞቻቸው ጉልበት ነው። ምክንያቱም የብር ዋጋ ዝቅ ቢደረግም ለሰራተኞቻቸው የሚከፍሉት ዋጋ/ደሞዝ ስለማይጨመርላቸው መንግስት ዝቅ ያደረገውን የምንዛሬ መጠን ያህል ከሚከፍሏቸው ሰራተኞች ላይ ያገኛሉ ማለት ነው። ለምሳሌ 120ብር ይከፈለው የነበረ ሰራተኛ በእጁ ድሮ የሚያውቀው 120ብር ቢሰጠውም የሚቀበለው ገንዘብ በገበያ ላይ ያለው ዋጋ(ወይም የመግዛት አቅም) ግን የ80ብር ያህል ብቻ ነው። ፋብሪካው ከያንዳንዱ ሰራተኛ 40ብር ያገኛል ማለት ነው። ሰራተኛው ደግሞ “እረ ምንጉድ ነው! ኑሮ ተወደደ። ትናንት በእንዲህ ዋጋ የገዛነው እንዴት እንዲህ ይሆናል?” እያለ መጠየቅ ይጀምራል። የብር ዋጋ ዝቅ በተደረገ ማግስት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የብር የመግዛት አቅም ቢዳከምም ፋብሪካው ግን የሚጠቀመው ከቀጠራቸው ሰራተኞቹ ብቻ ነው። ሰራተኞቹ ነቅተው ደሞዛቸው የብር ዋጋ ዝቅ ከመደረጉ በፊት በነበረው የመግዛት አቅም እንዲስተካከል ካስደረጉ ፋብሪካው በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ  እንዲሆን በሚል ሽፋን የሚያገኘው ጥቅም ሙሉ ለሙሉ አከተመ ማለት ነው። አሁን ተግባባን መሰለኝ። ይህ ማለት የብርን የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በማሳነስ ይበረታታሉ የሚባሉት ወደ ውጭ ሃገር ምርታቸውን የሚልኩ ነጋዴዎች ዋነኛ ትርፍ የሚገኘው በሃገር ቤት ከቀጠሯቸውን ሰራተኞች ጉልበት ነው ማለት ነው። (ክፍል ሁለት ይቀጥላል)