የዶላር ምንዛሬ ዋጋ መጨመር እና የብር ዋጋ ማጣት-ትርጉም እና ምንነት (2) 

2(By Kidus Mehalu/በቅዱስ መሐሉ©2017) የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም ይበልጥ ተዳከመ ማለት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ሃገር ዕዳ እንዳለባት ጠቋሚ ምልክት ብቻ ሳይሆን ይሄንንቱ ዕዳ ለመክፈል የምታደርገው ጥረት መንግስትን ተፈታትኖታል ማለት ነው። ምክንያቱም  የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በጀርመን ሃገር ለብድር ማስያዣ ካደረገው በዩሮ የሚከፈል የ1 ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ሽያጭ ውጭ ባብዛኛው የውጭ ሃገር እዳው የሚከፈለው እና የሚሰላው በዶላር ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያን ብር ዋጋ አሳንሶ ዶላርን ከፍ ማድረጉ የሚፈጠረውን የምንዛሬ ልዩነት ያህል ከኢትዮጵያዊያን ላይ ብር ያገኛል። ይህም መንግስት የገባበትን የዕዳ ክፍያ አጣብቂኝ ያቃልለታል። ይህ በራሱ ሌላ ትልቅ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ችግር ያሳያል።ይሄውን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የንግድ ሚዛን ክፍተት እና የበጀት ጉድለት እንዳለባት ነው። የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የንግድ ሚዛን ክፍተት መንግስት የኢኮኖሚውን  መዋቅር ለማሻሻል ፍላጎት ስለሌለው እና ኢኮኖሚውን ሙሉ ለሙሉ በብቸኝነት ለመቆጣጠር በሚያደርገው  ጥረት የተከሰተ ነው። የዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ይሄ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ችግር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት ወደኋላ እየጎተተው መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

      ⦿ እውን የብር ዋጋ መውደቅ የውጭ ሃገር ባለሃብቶችን ይስባል? 

የብር ዋጋ መውደቅ ማለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በአንጻራዊ መልኩ ከጎረቤት ሃገራት አንጻር ወደኋላ እየተጎተተ መሆኑንም ጠቋሚ ነው። ምክንያቱም የብርን ዋጋ ከሚወስኑት ነገሮች አንዱ በጎረቤት ሃገራት የሚደረግ ኢንቨስትመንት እና ኢንቨስትመንቱ የሚደረግበት የገንዘብ ዓይነት(ለምሳሌ ዶላር፣ዮሮ፣ፓውንድ ወዘተ) እና እንቅስቃሴ የሚፈጥረው ጫና ነው። ስለዚህ የብር ዋጋ ሲወድቅ ኢንቨስተሮች  የዶላ ምንዛሬ ጨመረ ብለው ወደ ኢትዮጵያ ዝም ብለው የሚጓዙ የዋሆች አይደሉም። እንዲያውም በተቃራኒው የብር ዋጋ ሲወድቅ የውጭ ሃገር ኢንቨስተሮች የሚመለከቱት ዋነኛ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑ ሃገራትን የቢዝነስና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሁኔታ ነው። ሌሎች ከግምት ውስጥ የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ሳይዘነጉ በዚህ ረግድ ግን ለኢንቨስተሮች እና ለውጭ ሃገር ባለሃብቶች ደግሞ ከኢትዮጵያ ይልቅ በጎረቤት ሃገራት  ገንዘባቸውን ኢንቨስት ቢያደርጉ አዋጭ መሆኑን ምልክት ይሰጣቸዋል። ምን ይሄ ብቻ በረጅም ጊዜ ሂደት ኢትዮጵያ ያለባትን ግሽበት ለመቆጣጠር ብሄራዊ ባንክ በባንኮች ላይ የሚጥለው ወለድ ኢኮኖሚውን ሊያናጋው ስለሚችል የውጭ ባለሃብቶች/ኢንቨስተሮች ከኢትዮጵያ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ያደርጋል። ይህ ደግሞ የንግድ ሚዛን ክፍተቱን፣የበጀት ጉድለቱን፣ግሽበቱን ወዘተ ይበልጥ በማባባስ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዲናጋ ያደርገዋል።

3

          ⦿ ታዲያ መፍትሄው ምንድ ነው?

ለዚህ ችግር ምላሽ የሚሆን አንድ ወጥ የሆነ መፍትሄ የለም። ሆኖም ግን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ባንክ እንደ  የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሲስተም(ECBS) እና የአሜሪካ ብሄራዊ ባንክ (ፌደራል ሪዘርቭ ባንክ) በግል ኩባንያ መዋቅራዊ ይዘት እንዲዋቀር ማድረግ አንዱ መፍትሄ ይመስለኛል። ሌላው ደግሞ የባንኩ መሪዎች በፋይናንስ እና ኢኮኖሚክስ በዓለምአቀፍ ደረጃ እጅግ ተወዳድሪ የሆኑ እና የበቁ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ሃገራትን እና የዓለምን የገንዘብና ፋይንስ ግብይት አሰራር ጠንቅቀው የሚያውቁ ምሁራን መሆን ይኖርባቸዋል። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ታጋይ አቦይ ፀሃየ መሆናቸው ይታወቃል። በተጨማሪ በኢኮኖሚው ውስጥ መንግስት እና ገዥ ፓርቲዎች ያላቸው ትልቅ ድርሻ የተቻለውን ያህል መቀነስ ሌላ መፍትሄ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ያላቸውን የፖለቲካ ስልጣን በመጠቀም የነሱን ወይም ከነሱ ጋር የሚሰሩ ባለሃብቶችን ለመጥቀም ወደፊትም የዚህ ዓይነት ውሳኔዎችን ማሳለፉ አይቀሬ ነው።  ይህን ጽሁፍ በዓለም ላይ ምርጥ የሚባሉትን የብሄራዊ ባንኮች የሚከተሉትን አሰራር ምን እንደሚመስል በመግለጽ ጽሁፌን ልቋጭ።

በመጀመሪያ በፍራንክፈርት ከተማ ጀርመን ውስጥ የሚገኘው የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሲስተም(ECBS) የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክን(ECB)እና ባንኩን ያቋቋሙትን 15 ሃገራት ብሄራዊ ባንኮች ላይ የፖለቲካ ባለስልጣናት ጣልቃ እንዳይገቡ ገለልተኛነታቸውን ያስጠብቃል። የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር የባንኩን አሰራር እና ፖሊሲ በአውሮፓ ህብረት የገንዘብና የፋይናንስ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቀርቦ የማስረዳት ግዴታ ቢኖርበትም ባንኩ የመረጠውን አካሄድ የማረምም ሆነ የማሻሻል ስልጣን ግን የለውም። ከላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ታጋይ አቦይ ጸሃየ መሆናቸውን ጠቁሚያችኋለሁ። ይህ ማለት በብሄራዊ ባንኩ አሰራር ላይ ትልቁ ስልጣን ያላቸው ሰው የፖለቲካ ባለስልጣን ናቸው ማለት ነው። ይህ አሰራር ከላይ ካያችሁት የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሲስተም አሰራር ሙሉ ለሙሉ ይቃረናል።

ሌላው ለጽሁፌ የመረጥኩት የአሜሪካ ብሄራዊ ባንክን ነው። የአሜሪካ ብሄራዊ ባንክ (ፌደራል ሪዘርቭ ባንክ) የቦርድ ሊቀመንበር የባንኩን የገንዘብ አስተዳደር ፖሊሲ እና አሰራር በኮንግረስ ፊት ለፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ቀርቦ የማብራራት ሃላፊነት አለበት። በዚህኛው አሰራር ከአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሲስተም በተለየ የአሜሪካ ኮንግረስ የባንኩን አካሄድ የማሻሻል መብት አለው። ይህም ማለት ፖለቲከኞች በባንኩ አሰራር ጣልቃ እንዲገቡ የተከፈተ በር አለ ማለት ነው። ይሄም ሆኖ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የአንድ ፓርቲ አባል ቢሆኑም እንኳ ሳይከራከሩ እና ሳይተማመኑ ዝም ብሎ እጅ በማውጣት ረቂቅ ህግን አዋጅ አድርገው የሚያጸድቁ ወይም የሚቃወሙ ዓይነት ሰዎች አይደሉም። በተጨማሪም ምናልባት በጥንቃቄ ሳይታይ ቢያልፍ እንኳ ከኮንግረሱ በላይ ህጉን መጨረሻ ላይ የሚያፀድቀው የአሜሪካ ሴኔት(የህግ መወሰኛው ምክር ቤት) ተጨማሪ ክርክር ሳያደርግ ረቂቁን ሕግ አድርጎ ስለማያፀድቀው ፖለቲከኞች በባንኩ አሰራር ላይ በቀላሉ መፍጠር የሚችሉት ተፅእኖ አይኖርም። ይህን ሁሉ አልፎ ሕጉ ስራ ላይ የሚውለው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በፊርማው ሲያፀድቀው ብቻ እንደሆነም ልብ ይሏል።ለምሳሌ ያህል በቅርቡ የአሜሪካ ብሄራዊ ባንክ ያደረገውን የወለድ መጠን ማስተካከያ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና አንዳንድ ደጋፊዎቻቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሲቃወሙት ነበር። ሆኖም ባንኩ ለአሜሪካ ይጠቅማል ያለውን ውሳኔ ከመወሰን ግን ያገደው ምንም አልነበረም።ይህን የባኩን ውሳኔ ለመቀልበስ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ምንም ስልጣን የለውም። ባንኩ ያደረገውን ውሳኔ ፖለቲከኞች ለመቀልበስ ቢፈልጉ የባንኩን ባለስልጣናት ጠርተው በአሜሪካ ኮንግረስ የፋይንስ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ማድረግ ይችላሉ። ሆኖም የባንኩን ውሳኔ ካላመነበት ወይም ማሻሻያ ያስፈልገዋል ከተባለ ፖለቲከኞቹ አሳማኝ የሕግ ረቂቅ አቅርበው ከላይ በገለጽኩት መንገድ ሁሉ ለመጓዝ ይገደዳሉ እንጅ በዚህ ምክንያት ‘እንዲህ ካላደረግ’ ተብሎ ፖለቲካዊ ጫና የሚደርስባበት የብሄራዊ ባንክ ባለስልጣን አይኖርም። ምናልባት ግን ከዶናልድ ትራምፕ የትዊተር ዶፍ ላያመልጡ ይችላሉ። ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለት የብሄራዊ ባንክ አሰራሮች ውስጥ ፖለቲከኞች እንዳሻቸው እንዳይፈነጩበት የተደረገው እነዚህ ፖለቲከኞች በአብዛኛው በሕዝብ ከመመረጣቸው ውጭ እንዲህ ያለ አገራዊ የኢኮኖሚ እንድምታ የሚኖራቸውን ውሳኔዎች ለማሳለፍ ሙያው  የሚጠይቀው እጅግ ከፍተኛ የሆነ ልምድ፣ትምህርት፣ልዩ ዕውቀት እና አስተዋይነት ስለሌላቸው ብቻ ሳይሆን ይህ ዓይነት ችሎታ ያለው ቢኖር እንኳ የፖለቲከኞች ውሳኔ በድምጽ ብልጫ እንጅ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ስለማይሆን ነው። እናም ይህን ዕውን ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የአሜሪካ ብሄራዊ ባንክ እና ሁለት አስርት ዓመታት ያልደፈነው የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሲስተም(ECBS) እንዲዋቀሩ የተደረገው በግል ኩባንያ መዋቅራዊ ይዘት ነው።ልክ እንደ ግል ድርጅት!!!!