ዘረኞች የፈነጠዙበት፤ዴሞክራቶች የተሸማቀቁበት የጀርመን ምርጫ! 

የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራቲክ ሕብረት ፓርቲ የዕሁድለቱን ምርጫ 33በመቶ በሆነ ድምጽ አሸንፏል። ይህም የሃገሪቱን ቻንስለር አንጌላ መርክልን ለአራተኛ ጊዜ ጀርመንን እንዲመሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ጠንካራ ሆኖ የቀጠለው የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምርጫውን ቢያሸንፍም ያገኘው ውጤት ግን ከአራት ዓመታት በፊት ካገኘው 8በመቶ ያነሰ ነው። እስከዛሬ ጀርመንን ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ጋር  በጥምረት ሲመራ የቆየው የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲም 20.5 በመቶ በሆነ ውጤት የፓርላማውን ወንበር በሁለተኛነት  ደረጃ መቆጣጠር ቢችልም ይህ ግን ፓርቲው ከ1949ዓ/ም ወዲህ ያገኘው ዝቅተኛ ውጤት ነው ተብሏል። በዚህ የተበሳጩት ሶሻል ዴሞክራቶች ከእንግዲህ ጠንካራ ጥምር መሪ ሳይሆን ጠንካራ ተቃዋሚ ሆነው እንደሚቀጥሉተናግረዋል።በዚህም ምክንያት ምርጫውን ያሽነፈው የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ መንግስት ለመመስረት እና አንጌላ ሜርክልን በስልጣን ለማቆየት ከነጻ ዴሞክራቶች(10.7) እና አረንጓዴ ፓርቲ(8.9) ጋር ከመስራት ውጭ አማራጭ ያለው አይመስልም። ይህ ይሆን ዘንድ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ ከራሱ ፖሊሲ ጋር የማይጣጣሙ እና የሚጋጩ የሁለቱን ፓርቲ ፖሊሲዎች ለማስታረቅ መደራደር ይኖርበታል። ከነዚህ ፖሊሲዎች ውስጥ በመንግስት ተቋማት እና በቢዝነስ ስራዎች ሁሉ ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጅ የመጠቀም ግዴታ እና በቴክኖሎጂ መተካት የሚችሉ ስራዎችን  ከሰዎች የመቀማት ሃላፊነት መውሰድ፣የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የጀርመንን ኢንዱስትሪዎች ግዴታ ላይ የሚጥሉ አሰራሮችን መተግበር እና ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የመላክ ግዴታ ሳይኖርባቸው በየቤታቸው የፈለጉትን ትምህርት የማስተማር መብትን መስጠት እና እነዚህን ተማሪዎች መደበኛ ተማሪዎች የሚወስዱትን ፈተና እና ምዘና በትምህርት ተቋማት እየሄዱ በየሴሚስተሩ እንዲወስዱ ማድረግ የሚያስችል አሰራሮችን በሙሉ ወይም በከፊል የመቀበል ግዴታ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነስ?

ይህ ካልሆነ ታላላቆቹን የክርስቲያን እና የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ተጋፍቶ ሳይጠበቅ የጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ቀላል የማይባል ድርሻ መያዝ ከቻለው ዘረኛው፣ጸረ እስላም ፣ጸረ ስደተኛ፣ጸረ አሜሪካ እና አክራሪ ብሄርተኛው የጀርመን አማራጭ ፓርቲ ጋር ለመጋፈጥ ይገደዳሉ። የጀርመን አማራጭ ፓርቲ ከተቋቋመ ገና አራት አመት ያህል ቢሆነውም አሁን ግን የጀርመንን ፓርላማ ወንበር 13 በመቶ በመቆጣጠር በሶስተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ይህ ውጤት ያስደነገጣቸው የተቀሩት የሁሉም ፓርቲ ደጋፊዎች የቀኝ አክራሪውን ዘረኛ ፓርቲ ድል እና ስር መስደድ በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል። የጀርመን አማራጭ ፓርቲ ሊቀመንበር አሌክሳንደር ጉላንድ ግን “ገና ምን አይታችሁ!” እያለ ነው። አሌክሳንደር እንዳለው “እኔ እና ጓደኞቼ ጀርመንን እና ህዝቧን ከወራሪ ስደተኞች መልሰን እስክንነጥቅ ድረስ እንቅልፍ የለንም።አንጌላ ሜርክልንም ማጥቃታችንን አናቆምም።” ብሏል። ከዚህ በፊት በጀርመን ፖለቲካ እና ምርጫ ውስጥ ተሳትፈው የማያውቁ ከ1.5 ሚሊዮን ዘረኛ ደጋፊዎችን በማቀናጀት ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ የተሳተፈው የዘረኞች ፓርቲ ከሌሎቹ ሁሉ የተሻለ ድምጽ ማግኘት ችሏል። የቀኝ አክራሪ ብሄርተኛው፣ዘረኛው እና ጸረ ስደተኛው የጀርመን አማራጭ ፓርቲ ያገኘው ውጤት አንጌላ ሜርክልንም ሳያስደነግጣት አልቀረም። እናም ጀርመንን ለ12 ዓመታት የመራችው ቻንስለር አንጌላ መርክል ከምርጫው “የኤኤፍዲን(የአማራጭ ፓርቲውን) ደጋፊዎች ስጋታቸውን በማስዎገድ እና ፍርሃታቸውንም በመጋራት ከጥላቻ በራቀ ፖለቲካ ወደ እኛ እናመጣቸዋለን።”ስትል ደስታ ከራቀው ፊቷ ጋር በቴሌቪን መስኮት ታይታለች። የዘረኛው ፓርቲ ሊቀመንበር እና አርክቴክት ለንግግሯ ምላሽ እንዲህ አለ። “ለአንጌላ ሜርክል እና ጀርመንን ለጀርመናዊያን ብቻ እንዳትሆን ለሚሰሩ እንዲሁም በስደተኞች ለሚያስወርሩን ፓርቲዎች ሁሉ የጭቃ ላይ እሾህ ሆነን እንቀጥላለን።አናስተኛቸውም።” የሆነ ሆኖ በለየለት የምስራቅ ጀርመን አምባገነን ሥርዓት  ውስጥ ተወልዳ ያደገችውን አንጌላ መርክል የፖለቲካ ሕይወት ጅማሮ እጇን ይዞ እየመራ ያስገባት የቀድሞው ቻንስለር ሄልሙት ኮህል ዛሬ ለደረሰችበት ስኬቷ ትልቅ ሚና መጫወቱ አሌ የማይባል ሃቅ ነው። “የኔ ውድ!” እያለ የሚያቀናጣትን ይህችን ሴት አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ ደርሳ ማየቱ ጀርመንን ለ16 ዓመት ያህል የመራትን ቻንስለር ሄልሙት ኮህል እጅግ ያስደስተው እንደነበር በቅርቡ ሕልፈቱን ተከትሎ የወጣው የህይወት ታሪኩን የሚዳስስ መጽሃፍ ላይ ሰፍሯል። ሌላው ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት የወጣው የጀርመን ቻንስለር ደግሞ ኮንራድ አዴናውር ሲሆን ሃገሪቱን ለ14 ዓመታት ያህል አገልግሏል። አንጌላ መርክልም እንቅፋት ሳይገጥማት ማለትም ፓርቲዋ ከግሪን እና ነጻ ዴሞክራቶች ጋር ተስማምቶ መጣመር ከቻለ ጀርመንን ለ16 ዓመታት ያህል በቻንስለርነት/በጠቅላይ ሚንስትርነት የማገልገል ዕድሉ ይፈጠርላታል። ይህ ብቻም አይደል። እንደ ዶናልድ ትራምፕ፣ኤርዶጋን፣ ፑቲን እና ኪም ለመንገስ በሚሯሯጡበት ዓለም ውስጥ ለዓለም ሰላም ጠበቃ በመሆን የነጻው ዓለም ትልቅ ድምጽ የመሆን ሃላፊነት ተጥሎባታል።ይህን ሃላፊነት ሊጋራት የሚችል ሌላ አንድ ሰው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑየል ማክሮን ነው።  በአጠቃላይ ሲታይ ግን የትናንቱ(የእሁዱ) የጀርመን ምርጫ ዘረኞችን ያስፈነጠዘ ፤ዴሞክራቶችን ደግሞ ያሸማቀቀ ነበር ማለት ይቻላል።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.