አንስታይን፣አሜሪካ እና ጃፓን:-የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ!

(By Kidus Mehalu) እኤአ ከ1894ዓ/ም እስከ 1895ዓ/ም በጃፓን እና በቻይና በተደረገው ጦርነት በአውሮፓዊያን ይሰለጥን የነበረው የቻይና ሰራዊት ክፉኛ ተመቶ ጃፓን በቢጫ ባህር እና በኮሪያ ላይ ከመንገሷም ታይዋንን ተቆጣጠረች። ይህም አልበቃ ብሏት በቻይና እና ራሽያ መሃል የሚገኘውን ስትራቴጅክ ቦታን በእጇ አደረገች። ይህ ቦታ ማንቹሪያ ይባላል። ሩሲያ “ማንቹሪያ የቻይና ነው” በማለት በ1904 ከጃፓን ጋር ጦርነት ውስጥ ገባች። በራሽያ ድንገተኛ ጥቃት ማንቹሪያን የለቀቀችው ጃፓን በባህር ኋይሏ አማካይነት በአጭር ጊዜ የራሽያ ወታደሮች ዋና መተላለፊያ የባቡር መስመር እና የአርተር ወደብን በመቆጣጠር ለውጊያ ወደ ስፍራው ያቀኑ የነበሩትን የራሽያ የጦር መርከቦች በሙሉ ሳያስቡት አወደመችባቸው። ራሽያ ለቻይና አግዛ ገብታ የራሷ ግዛት የነበረውን የአርተር ወደብን በይፋ የጃፓን ነው ብላ ከማወጅ በተጨማሪ ኮሪያም የጃፓን መሆኑን ዕውቅና እንድትሰጥ ተገደደች። ከአምስት ዓመታት በኋላ እኤአ በ1910ዓ/ም ጃፓን ከቻይና ጋር ባደረገችው ጦርነት ያወጣችውን ወጭ እንድትከፍል ከማስገደዷም በላይ የቻይና ግዛት የነበረችውን ኮሪያን በራሷ አንደበት “ኮሪያ የጃፓን ግዛት ናት!” አስባለቻት። ይህ ሽንፈት እና ውርደት ያንገበገባት ቻይና ከ21ዓመት በኋላ ጃፓንን ለመበቀል ጦርነት ከፈተች። በዚህኛው ጦርነት 20ሚሊዮን ቻይናዊያን ካለቁ በኋላ ጃፓን የቻይናን ዋና ከተማ ተቆጣጥራ የራሷን አሻንጉሊት መንግስት አቋቋመች። ቻይናዊያን በገዛ አገራቸው ጎዳናወች እና መተላለፊያዎች ላይ“ቻይና እና ውሻ በዚህ ማለፍ አይችልም” በሚሉ የጃፓናዊያንን ጽሁፎች አንገታቸውን ደፉ። የቻይና ሴቶችም በሕግ የጃፓን ወታደሮች መጫወቻ እንዲሆኑ ተደረገ።ታዲያ ቻይናዊያንን ከጃፓን ማን ነጻ አወጣቸው?

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ራሽያ ከጀርመን፤ቻይናም ከጃፓን ነጻ የወጡበት መንገድ ተመሳሳይ ነው። ታህሳስ 7 ቀን 1941 ዓ/ም ጃፓን በሃዋይ ግዛት ‘ፐርል ሃርበር’ የሚገኘውን ትልቁን የአሜሪካ ባህር ሃይል እና የሂካም አየር ሃይል ጣቢያ ማውደሟን ተከትሎ አሜሪካ በጀርመን፣በጃፓን እና በጣሊያን ላይ ጦርነት አወጀች። አሜሪካ በሌላ ሃገር ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ የሚከለክላትን የ “ኒውትራሊቲ አክት” እንዲሻር ተደርጎ በሶስቱ ሃገራት የተጠቁ እና የተወረሩ ሃገራት ራሳቸውን ነጻ ማውጣት ይችሉ ዘንድ የጦር ተሽከርካሪዎች፣የተዋጊ አውሮፕላኖች እና ካሚዮኖች እንዲሁም ስንቅና የጦር መሳሪያ እርዳታ እንዲደረግላቸው ተወሰነ። ስታሊን ጀርመንን ለማሸነፍ ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ጋር መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን በመቀበል የአሜሪካ ‘ሌንድ ሊዝ’ ስምምነት ተጠቃሚ ሆኗል። በስፋት በዓለም ትልቋ ሃገር የሆነችውን ሩሲያ ከጀርመን ወረራ ለመታደግ ከ1941ዓ/ም ጀምሮ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስካበቃበት 1945ዓ/ም ድረስ ሶቬት ህብረት 11.3 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ አገኘች።ከዚህ በተጨማሪ  ሶቬት ህብረት 427 ሽህ 284 ስንቅ የሚያቀርቡ ካሚዮኖች፣ ከ11ሽህ በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ 35ሽህ 170 ሞተር ሳይክሎች፣ ከ4ሚሊዮን ቶን በላይ የሚመዝን ስኳር፣ ስጋ፣ ጨው እና ዱቄትን ጨምሮ 120 ታንኮች እና 18ሽህ700 የጦር አውሮፕላኖች በእርዳታ አግኝታለች።በዚሁ ስምምነት መሰረት እንግሊዝ 31.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ፈረንሳይ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ሲያገኙ ቻይና ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሎጅስቲክስ ድጋፍ ከአሜሪካ ማግኘት ችለዋል። አግኝተዋል። ከእርዳታው በቀር ሩሲያ ከጀርመን ጋር እንዲሁም ቻይና ከጃፓን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት ግን በአብዛኛው ለራሳቸው የተተወ ነበር።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አውድማን በሰሜን አፍሪካ፣ምዕራብ አውሮፓ እና አውስትራሊያን ከጃፓን ወረራ ለመታደግ በተደረገው ትንቅንቅ ውስጥ አሃዱ ብላ የተቀላቀለችው አሜሪካ ጀርመን እንጅ ጃፓን ያን ያህል ታስቸግራለች ብላ የገመተች አትመስልም። ይህንኑ የጀርመን ፍራቻ በተለይም አልበርት አይንስታይን “ናዚ የአቶም ቦምብ ሊሰራ ይችላል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ አሜሪካንም ቢሆን ከናዚ የሚታደጋት አታገኝም።” በማለት ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልትን በማሳመናቸው የማንሃተን ፕሮጀክት እንዲጀመር ተደረገ። ከሁለት ዓመት በኋላ የፕሮጀክቱን ሂደት እና ስኬታማነት እርግጠኛ እየሆኑ ሲመጡ አልበርት አይንስታይን እና ሊዮ ዚላርድ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት “አቶሚክ ቦምቡ የአሜሪካን ጠላቶች በጦር ሜዳ ላይ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ እጅ እንዲሰጡ ማድረጊያ ለማስፈራሪያ ብቻ የሚውል ነው።” በማለት ዕቅዳቸውን ተናገሩ። ይሄውም የሚደረገው ሰው በማይኖርበት ቦታ ላይ በመጣል “እንደዚህ ከምናረጋችሁ እጅ ስጡ!” በማለት ሊሆን እንደሚችል ዝርዝር ሃሳብ አቀረቡ። ይህን ዝርዝር ሃሳብ በቅጡ ማንበብ እንኳ ሳይችሉ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ሞት ቀደማቸው። ፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማን ስልጣኑን ተረከቡ።

ጃፓን ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በኤዥያ ተረጋግተው ተቀምጠው ለነበሩ አውሮፓዊያን ቅኝ ገዥዎች ራስ ምታት መሆኗን ቀጥላለች። በአውሮፓ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀርመን ሽንፈት ሲቋጭ ከማንሃተን ፕሮጀት ተሳታፊ ሳይንቲስቶች ውስጥ ኤድዋርድ ቴለር የአቶም ቦምብ መስራት የሚያስችለውን ቀመር ከአንስታይን E=MCውስጥ ለይቶ ማግኘት ቻለ። በዚሁም መሰረት የተቀመረው የአቶም ቦምብም በኒው ሜክሲኮ ስኬታማ ሙከራውን አደረገ። የጀርመንን ሽንፈት ተከትሎ ከራሽያ፣ከቻይና፣ከፈረንሳይ እና ከእንግሊዝ መሪዎች ጋር በበርሊን የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ስለ አቶም ቦምቡ ስኬታማ ሙከራ በስልክ ተነገራቸው። በዜናው በጣም የተደሰቱት ሃሪ ትሩማን አብረዋቸው ለነበሩት መሪዎች “ጃፓንን ከዚህ በፊት እናንተም ሆነ ዓለም ዓይቶት በማያውቀው መሳሪያ ልንቀጣት ነው?ምን ትላላችሁ?” ሁሉም በአንድ ድምጽ በተለይም በተለያየ ጊዜ በጃፓን ሽንፈት እና ውርደትን የተከናነቡት ቻይና እና ሩሲያ “ዛሬውኑ አድርጉት!ትመታ” ሲሉ ሙሉ ድጋፋቸውን ሰጡ።

“የአቶም ቦምቡ ሰዎች በማይኖርበት ቦታ በመጣል ጃፓንን እጅ እንድትሰጥ መጠየቅ ይሻላል” የሚለውን የአልበርት አይንስታይን እና የጓደኞቹን ሃሳብ ፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማን አልተቀበሉትም። ፕሬዝዳንቱ እና የጦር አዛዦቹ የአሜሪካን ሃያልነት ለዓለም ለማሳየት እና ጠላቶቿን ለማሸማቀቅ የተሻለ አማራጭ ባሉት እና  ቦምቡን በቀጥታ ጃፓናዊያን ላይ መጣል በሚለው ሃሳብ ተስማሙ። እኤአ ነሃሴ 6 ቀን 1945 ዓ/ም በጃፓን ሄሮሽማ ውስጥ የመጀመሪያውን የአቶሚክ ቦምብ ጣለች። ጃፓኖች ብቻ ሳይሆኑ የተቀረው ዓለም ሁሉ ደነገጠ። በአንድ ጊዜ ከመቶ ሽህ በላይ ሰዎች አለቁ። ጃፓናዊያን “የተኛውን ትልቅ አውሬ የቀሰቀስነው በገዛ እጃችን ነው።” አሉ። ጃፓን በይፋ በጦርነቱ መሸነፏን አምና እጅ እንድትሰጥ አሜሪካ ጠየቀች። ጃፓን ግን አሻፈረኝ አለች። እኤአ ነሃሴ 9 ቀን 1945 ዓ/ም ማለትም የመጀመሪያው አቶሚክ ቦምብ ከተጣለ ከሶስት ቀናት በኋላ ናጋሳኪ ተደገመች። ይህኛው የአቶም ቦምብ የመቶ ሽህ ህዝብ ህይዎት ቀጠፈ። ከስድስት ቀናት በኋላ ኦገስት 15 ቀን ጃፓን እጅ እንደምትሰጥ በማስታወቅ ልክ የዛሬ 72ዓመት በዛሬው ቀን ማለትም ሴፕቴምቤር 2 ቀን 1945ዓ/ም ይህንኑ ሽንፈቷን በኦፊሴል በፊርማዋ አረጋገጠች።ይህን ተከትሎ ቻይና፣ኮሪያ እና ራሽያን ጨምሮ የደቡብ ምስራቅ ኤዥያ ሃገራት በሙሉ በጃፓን የተነጠቁትን ሉዓላዊ ግዛታቸውን መልሰው ማግኘት ቻሉ።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲገባደድ አሜሪካ ለሩሲያ ከሰጠችው የገንዘብ ብድር ውስጥ 1.3 ቢሊዮን ዶላሩን እንድትከፍል ጠይቃታለች። ሆኖም በግንቦት 1942ዓ/ም በመርከብ ለክፍያ ወደ አሜሪካ የላከችው 45ሽህ ኪሎ ግራም ወርቅ፣ ጦርነቱ እስኪገባደድ ድረስ በበርካታ መርከቦች እየተጫነ ወደ አሜሪካ የሄደው የሩሲያ ውድ ማዕድን እና ጥሬ ሃብት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሩሲያ 722ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጥራጥሬ በተለያየ ጊዜ ወደ አሜሪካ ለመላክ ተስማምታ የተቀረው ዕዳዋ እንዲሰረዝላት አድርጋለች። ከጦርነቱ የተረፉት የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎች በሙሉ ሶቬት ህብረትን ጨምሮ ለ44 ሃገራት እንዲከፋፈል ተደርጓል። ብዙም ሳይቆይ ግን አሜሪካ እና ሶቬት ሕብረት እርስ በርስ እንደ ጠላት መተያየት ጀመሩ።

የሆኖ ሆኖ አሜሪካንን ከፕሮፖጋንዳ ባለፈ ፊትለፊት ጦርነት ገጥማ አቅሟን የተፈታተነች የምድራችን ብቸኛ ሃገር ጃፓን ናት። በዚህም ምክንያት የኑክሌር ጦር መሳሪያ አረር የነደደባት ብቸኛ ሃገርም መሆን ችላለች።  የጃፓንን እና የጃፓናዊያንን ያህል የኑክሌር ጦር መሳሪያን አደገኛነት በተግባር የሚያውቅ የለም። ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ውድድር ወቅት አድናቂዎቹ እና ደጋፊዎቹ “የሃሪ ትሩማንን ወኔ የታጠቀ ጀግና”  እያሉ ሲያቀማጥሉት ነበር። የሃሪ ትሩማን ወኔ የአቶም ቦምብን በንጹሃን ላይ የማዝነብ ድፍረት ነው። ትራምፕ ይህ ድፍረት ካለው በማን ላይ እና በምን ምክንያት ሊጠቀመው እንደሚችል ለጊዜው ከብዥታ የጠራ መልስ የለም። ለማጠቃለል ያህል ከቀናት በፊት በአንድ ታዋቂ የጀርመን ሚዲያ ላይ ቃለመጠይቅ ያደረገችው የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ስለ ትራምፕ እና አሜሪካ ይሄን ብላለች። “ከ12 የራሱ ፓርቲ ዕጩዎች ውስጥ   በብቸኝነት በመውጣት እና ድፍን ዓለም የተቃውሞ ድምጽ እያሰማበት የምርጫ ውድድሩን በአሸናፊነት የተወጣ ሰው ማክበር ግዴታየ ነው። ከትራምፕ ጋር የሃሳብ ልዩነት ቢኖረኝም ከሱ ጋር የሚኖረኝ ግንኙነት እንደ አንጌላ መርክል ሳይሆን እንደ ጀርመን ጠቅላይ ሚንስትር ነው። ስለዚህ የጀርመንን ፍላጎት ለማስጠበቅ እሰራለሁ። ከሰሜን ኮሪያ ጋር የሚደረግ ጦርነት በዓለም ትልቅ የሆነውን የንግድ መስመር ስለሚያውክ ከማንም አውሮፓዊ አገር በላይ ጀርመንን ይጎዳል።ስለዚህ አሜሪካ ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ከማጠናከር ውጭ አማራጭ የለንም።በአሁኑ ወቅት ለእኔ አሜሪካ ከቆሰለ አውሬ ጋር ትመሳሰልብኛለች።ሁሉም ነገር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው።ጀርመን ግን ሁሉም ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ትጥራለች።”