ወተት  የሚጡት ዝሆኖች — የንብረት ባለቤትነት መብት እና የአካባቢ ጥበቃ!

(By Kidus Mehalu)

የንብረት ባለቤትነት መብት መረጋገጥ ለአካባቢ እንክብካቤ እና የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ ረገድ ወሳኝ እና የማይተካ ሚና ይጫወታል። እንዴት የሚለውን በዝርዝር እንመልከት። እስከ አስራ ዘጠኝ ዘጠና ዓ/ም ናሚቢያ የምትገዛው ደቡብ አፍሪካን ጠፍንጎ በያዘው በዘረኛው የአፓርታይድ ስርዓት ነበር። የናሚቢያ ዜጎች የኔ የሚሉት ነገር አልነበራቸውም። ህይዎታቸው፣ ንብረታቸው፣የዱር አራዊቱ ሁሉ የአፓርታይድ አርክቴክቶች (የዘረኞቹ ነጮች) ነበሩ። የናሚቢያ ዜጋ በልቶ ከመተኛት ውጭ ምንም የተፈቀደለት ነገር አልነበረም። የሚዘሩት እህል በዝንጀሮ ሲበላ፣ ሰብሎቻቸው የዱር አራዊት መፈንጠዣ ሲሆን እና የቤት እንስሳቶቻቸው በአውሬ ሲበሉባቸው መከላከል አይችሉም ነበር። ምክንያቱም ዘረኛው ስርዓት (አፓርታይድ) ከሰዎቹ የበለጠ ለዱር አራዊቱ መብት በመስጠቱ ነው። የግፍ ጽዋ ሞልቶ ፈሰሰና እኤአ በአስራ ዘጠኝ ዘጠና ዓ/ም ናሚቢያዊያን ከዘረኛው ስርዓት ነጻ መውጣት ቻሉ። ከዚህ ጊዜ በኋላ የናሚቢያ ዜጎች ሰብሎቻቸው በአራዊት እንዳይጠፋባቸው መከላከል ጀመሩ። ናሚቢያዊያን አራዊቱን እያሳደዱ መግደል ተያያዙት። የዱር አራዊቱ ቁጥር ክፉኛ ተመናመነ። ይህም የናሚቢያን መንግስት ይበልጥ ስላሳሰበው እኤአ በአስራ ዘጠኝ ዘጠና ሰባት ዓ/ም የዱር አራዊቱን ማስተዳደርን የሚመለከት አዲስ አሰራር ይፋ አደረገ። አዲሱ አሰራር የዱር አራዊት በሚበዙበት አካባቢዎች የሚገኙ ሃምሳ ማህበረሰቦች የዱር አራዊቱን በመንከባከብ እና በመጠበቅ የሚገኘውን ገቢ ለራሳቸው እንዲዎስዱ ይፈቅዳል። በውጤቱም የሚደንቅ ለውጥ መጣ። የናሚቢያ ሰው የዱር አራዊቱን በመግደል ፋንታ እንደ ፍየል እና ላም ይጠብቅ ገባ። ይሄም አልበቃቸው። የዱር አራዊቱ ወደ ሌላ ስፍራ እንዳይሄዱባቸው አካባቢውን በአጥር አጠሩ። ናሚቢያዊያን ለሌሎች ማህበረሰቦች የዱር እንስሳቱን በመሸጥ እና ከጎብኝዎች ላይ ገቢ ማግኘት ጀመሩ። ለወጣቶቻቸው ስራ መፍጠር ቻሉ።

ናሚቢያዊያን ቀደም ሲል የዱር አራዊቱን ሲገድሏቸው የነበረው የህዝብ ንብረት እና የአገር ሃብት መሆናቸው ጠፍቷው ሳይሆን ናሚቢያዊያኑ የኔ የሚሏቸው ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ገንዘባቸውን ያፈሰሱባቸውን የእርሻ ሰብል እና የቤት እንስሳት መሆኑ ነው። ምክንያቱም በዱር አራዊቱ ላይ የባለቤትነት መብት ስለሌላቸው ግዴለሾች ናቸው። የእኔ የማይሏቸው እንስሳት ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ገንዘባቸውን ያፈሰሱባቸውን የእኔ የሚሉት ንብረታቸውን ሲያጠፉት ዝም ብለው ማየት አይሹም። ስለዚህም ንብረቶቻቸውን ከዱር አራዊት ይከላከላሉ። እስከመቼ? የዱር አራዊቱ የእነሱ ንብረት መሆናቸውን በህግ እስኪያረጋግጡ ድረስ ማለት ነው። የዱር አራዊቱን በባለቤትነት መያዛቸው በሚከተሉት ሶስት ነጥቦች ይረጋገጣል።

አንደኛ ❒ በዱር አራዊቱ በብቸኝነት መጠቀም ሲችሉ፣
ሁለተኛ ❒ የዱር አራዊቱን ከወንበዴ እና ከነጣቂ የሚጠብቅ ጠንካራ ህግ መኖሩ፣እና
ሶስተኛ ❒ የዱር አራዊቱን ለሌላ ማስተላለፍ፣ መሸጥ ወይም መለወጥ ሲችሉ ነው።

ናሚቢያዊያን ሶስቱንም ማድረግ ችለዋል። ከዚህ በተረፈ ከፓርክ የሚገኝ ገቢን ወደ ማህበረስቡ የሚደርስበት መንገድ ከሌለ አንድን የዱር እንስሳት ፓርክ ‘የህዝብ ንብረት ነው።’ በማለት ብቻ የቱሪዝም ገቢውን ማሳደግም ሆነ ከፓርኩ ተገቢውን ያህል ሃብት ማመንጨት አይቻልም። ይሄን ለመረዳት ስንቅዎን ይዘው በመንግስት በሚተዳደሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ፓርኮች ይሂዱና ጉብኝት ያድርጉ። ከዚያም ላም፣ ፍየል፣ በሬ፣ ግመል፣ በርካታ የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት፣ ማህበረሰቦቹ በፓርኩ ውስጥ የገነቧቸውን ጎጆዎች እና በእነዚህ የማህበረሰብ አባላት የተገደሉ ብዙ የዱር እንስሳትን ይመለከታሉ። ይህም ብቻ አይደለም፤ራሱ መንግስት አንዳንዶቹ ፓርኮች “የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል” ሲል እየሰማን ነው። የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያዊያኑ የአካባቢው ሰዎች እንደ ናሚቢያዊያኑ ሁሉ የዱር አራዊቱ የህዝብ እና የሃገር ንብረት መሆናቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ። የዱር እንስሳት መግደልም በህግ የተደነገገ ወንጀል መሆኑንን ብዙዎቹ ይረዳሉ። ሆኖም ግን የሰው ልጅ በተፈጥሮው ለራሱ እና ለኔ ለሚለው ነገር ቅድሚያ ይሰጣል። ስለዚህም ይህን ተፈጥሮአዊ ባህሪውን በሕግ እና በአዋጅ ማፋለስ ስለማይቻል ተፈጥሮአዊ የሆነው የንብረት ባለቤትነት መብቱ በጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ድጋፍ ሊሰጠው እና ሊከበርለት ይገባል።

በአጠቃላይ ከናሚቢያ ውጭ ባሉ አካባቢዎች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በመንግስት ከሚተዳደሩ ብሄራዊ ፓርኮች ይልቅ በግል የሚተዳደሩ የእንስሳት ጥበቃ መጠለያዎች እና ፓርኮች ሁሌም የተሻሉ ናቸው። በደቡብ አፍሪካም ስኬታማ እና ውጤታማ የሚባሉት ፓርኮች በሙሉ የግል መሆናቸው ይታወቃል። ለምሳሌ በፎቶው ላይ ወተት ሲጠጡ የምትመለከቷቸው ዝሆኖች በኬንያ መንግስት ከሚተዳደሩት ፓርኮች ውስጥ የዝሆን ጥርስ በሚያድኑ ሰዎች በመገደላቸው እና ተገቢውን ጥበቃ ባለማግኘታቸው ምክንያት ናይሮቢ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የግል መለስተኛ የዝሆኖች መጠለያ እና ፓርክ ውስጥ የተዛወሩ ናቸው።ይህን  ልምድ“10ቢሊዮን ብር ለወጣቶች ስራ ፈጠራ መድቢያለሁ” ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ከተጠቀመበት በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፎችን መምታት የሚችልበት ዕድል ይመስለኛል። አንደኛ እኩል ተነሳሽነት፣ብቃት፣ችሎታ እና ዝግጅት የሌላቸውን ወጣቶች በማደራጀት ብዙ ገንዘብ በመስጠት አስተማማኝ እና ዘላቂ ያልሆነ ኢንቨስትመንት ላይ የህዝብ ገንዘብ እንዳያባክን ይረዳል። ሁለተኛ መንግስት ራሱ ለአደጋ ተጋልጠዋል ያላቸውን ፓርኮች መታደግ ከማስቻሉ በተጨማሪ በእነዚህ ፓርኮች ላይ መንግስት የሚያወጣውን ወጭም ማስቀረት ይቻላል። ሶስተኛ ደግሞ ለወጣቶቹ አስተማማኝ ስራ እና ዘላቂ ገቢ ከማስገኘት አልፎ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለሃገር ማመንጨት እንደሚቻል መገመት አያዳግትም። እርሶ ይህን ሃሳብ እንዴት ያዩታል?

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.