ወርቅ፣ዶላር እና አሜሪካ!  (ክፍል 2 እና የመጨረሻ ክፍል) 

ወዶአ.jpg

(©Kidus Mehalu) እኤአ ነሃሴ 15 ቀን 1971 ዓ/ም ከገንዘብ ሚንስትራቸው ጆን ኮናሊ፣ የብሄራዊ ባንኩ ሊቀመንበር አርተር በርንስ እንዲሁም ከኢኮኖሚ እና ገንዘብ ጉዳዮች አማካሪዎቻቸው ሄርበርት ስቴይን እና ፖል ቮከር ጋር ሆነው በጉዳዩ ላይ በካምፕ ዴቪድ ሲመክሩ የዋሉት ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ምሽቱን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ዓለም ለአጭር ደቂቃ ጆሮ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ንግግራቸውን ቀጠሉ። እንዲህም አሉ። “የአሜሪካን ዶላር ያከማቻችሁ ሃገራት ሆይ ከንግዲህ ዶላርን በወርቅ ለውጡን ብላችሁ ወደኛ እንዳትመጡ። ከዛሬ ጀምሮ የብሪቶን ውድስ ስምምነት አይሰራም። ስለዚህም ዶላርን በወርቅ አንቀይርም።ንግግሬን ጨርሻለሁ፤ አመሰግናለሁ።” በማለት ከቴሌቪዥኑ መስኮት ተሰወሩ።

ዶላር ሲያከማቹ የነበሩ ሃገራት ሁሉ ግን የሰሙትን ለማመን ተቸግረው ከቴሌቪዥኑ መስኮት ላይ ዞር ለማለት ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። አውሮፓዊያኑ በዶላር ላይ ፊታቸውን በማዞር በፍጥነት የራሳቸውን ገንዘብ በአነስተኛ የምንዛሬ መወዛወዣ (ፍሎቲንግ ሬት) ክፍተት ዋጋውን እየተመኑ ለመስራት “ዩሮፒያን ስኔክ” የሚባል ፕሮጀክት ጀመሩ። የአውሮፓዊያኑን ፕሮጀክት ለማምከን አሜሪካ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዶላርን ዋጋ ዝቅ (ዲቫሉየት) በማድረግ እና ዓለም ከአውሮፓዊያኑ ገንዘብ የበለጠ ዶላርን እንዲጠቀሙ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መወዛወዣ ክፍተቱንም አሰፋችው። ይህ የአሜሪካ ስትራቴጅ “የአውሮፓዊያኑ እባብ” ብዙ ርቀት እንዳይሄድ ያደረገ ዘንዶ ነበር። አውሮፓዊያኑ አንድ ዓመት ያህል እንደተጓዙ እንግሊዝ መሃል መንገድ ላይ ዘንዶው ማድፈጡን ተመለከተችና ቶሎ እራሷን አገለለች። ጣሊያን ተከተለቻት። የአውሮፓዊያኑ ስኔክ ፕሮጀክት ፈረሰ። የዓለም ኢኮኖሚ በከፍተኛ ግሽበት፣ የስራ አጥ ቁጥር እና የዋጋ ንረት በድጋሚ ተናጋ።

በታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደቀቀችው አውሮፓ ግን ሌላ የኢኮኖሚ ቀውስ መቋቋም የሚያስችል አቅም አልነበራትም። ስለዚህም በወርቅ ይቀየርልናል ብለው እንደ ገንዘብ ሲገበያዩበት እና ሲያከማቹት የነበረውን የአሜሪካ ዶላር አለመቀበል ማለት ሲገነቡት የኖረውን ኢኮኖሚ በመናድ ለዳግም የኢኮኖሚ ውድቀት መዳረግ መሆኑን ተረዱ። ለወትሮውም በዓለም ንግድ እና ኢኮኖሚ ላይ እዚህ ግባ የማይባል ድርሻ የነበረው የተቀረው የዓለም ክፍልም ፊቱን ወደ ዶላር ከመመለስ በቀር ምንም ምርጫ እንደሌለው ተረዳ። አሜሪካ አንድም ወታደር ሳትጠቀም ዓለምን እንዲህ አስራ ያዘች። ይህም ብቻ አይደለም።

ዶላር ዓለማቀፍ ገንዘብ መሆኑ አሜሪካ የትም ሃገር አንዲት ሳንቲም ሳታወጣ የፈለገችውን መግዛት አስችሏታል። በቃ! እዳ እንዳለባት የሚገልፅ ህጋዊ ወረቀት ትሰጣለች። ሃገራት ያን ወረቀት እንደ ገንዘብ ያዘዋውሩታል። ምክንያቱም የአሜሪካ ዶላር ሁሉም የሚቀበለው ዓለም ዓቀፍ ገንዘብ ነው። በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር እዳ ያለባት ሃገር በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እርዳታ ስትሰጥ የምናያትም በዚሁ ምክንያት ነው።ይህንኑ ዶላር ያስቀየማትን ለመቅጫም ትጠቀምበታለች። ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ ገንዘብ ባተመች ቁጥር ሁሉም የዓለም ሃገራት የግሽበቱን ፅዋ አብረው ለመቋደስ ይገደዳሉ። ሌላስ? ሌላው ደግሞ ዶላር ዓለም አቀፍ ገንዘብ እና የዋጋ ማንጸሪያ መሆኑ በዓለም ላይ አሜሪካን የውጭ ምንዛሬ ክምችት የማያስፈልጋት ብቸኛ ሃገር አድርጓታል።ይሁን እንጅ በወርቅ ክምችትም ቢሆን አሜሪካ ያላትን ግማሽ ያህል እንኳ ያለው ሌላ ሃገር የለም። ከአሜሪካ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ጀርመን 3374 ቶን ወርቅ ክምችት ያላት ሲሆን ይኸውም የሃገሪቱን 70በመቶ ያህል የውጭ ምንዛሬ ክምችት ይሸፍናል። ጣሊያን፣ፈረንሳይ እና ቻይናም በብሄራዊ ባንኮቻቸው አማካይነት በተከታታይ እስከ አምስተኛ ደረጃ ያለውን የዓለምን የወርቅ ክምችት ይዘዋል። አብዛኛው የእነዚህ ሃገራት የወርቅ ክምችት የሚገኘውም በኒውዮርክ/ፌደራል ሪዘርቭ/ ውስጥ ከፊሉ ደግሞ የዓለም የገንዘብ እና የወርቅ ግብይት በሚካሄድባቸው እንደ ለንደን እና ፓሪስ ወዘተ ባሉ ስፍራዎች ነው። ለምሳሌ የጀርመን 37በመቶ የወርቅ ክምችት በኒውዮርክ ሲገኝ 13 በመቶ ደግሞ በለንደን ይገኛል። ሃገራቱ ይህን  የሚያደርጉት የውጭ ምንዛሬ ችግር ሲገጥማቸው የወርቅ ክምችታቸውን በፍጥነት ወደ ዓለም አቀፍ የወርቅ ገበያ በማቅረብ እንዲሸጡ እና የውጭ ምንዛሬ(ዶላር) እንዲያገኙ ስለሚረዳቸው ነው። ለማብራራት ያህል 3374 ቶን የወርቅ ክምችት ያላት ጀርመን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢገጥማት እና ይህን የወርቅ ክምችቷን አሁን ወርቅ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ባለው ዋጋ ብትሸጠው ለሃገሪቱ በቀጥታ 132 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር(ሃርድ ከረንሲ) ያስገኝላታል ማለት ነው።

አሜሪካ ዶላርን በወርቅ እየቀየረች ዓለምን አጓጉታ በወጥመዷ ውስጥ ካስገባች እና ገንዘቧ ዓለማቀፍ ተቀባይነት አግኝቶ ሃገራት ሊተውት በማይቻል መጠን በብዛት ካከማቹት በኋላ ፊቷን በማዞሯ ምክንያት ለአጭር ጊዜ ጥቅም በዘላቂነት ጥገኛ ለመሆን ተገደዱ። አሜሪካ በብሪቶን ውድስ ስምምነት መሰረት ዶላር እየመለሱላት  ወርቅ ሲቀበሏት የነበሩትን ሃገራት ሁሉ እስከዛሬ ድረስ በተቃራኒው ለዶላር ወርቅ እንድትከፍላቸው ማድረግ ችላለች። ይህ የሆነበት ምክንያትም ሃገራት የውጭ ምንዛሬ ክምችት የሚያስቀምጡት በዶላር አሊያም ደግሞ በወርቅ በመሆኑ ነው። ሃገራቱ ወርቃቸውን የሚሸጡበት ወይም በዶላር የሚቀይሩበት ዋጋ የሚተመነው በኒውዮርክ፣ለንደን እና ፓሪስ በሚገኙ ዓለማቀፍ የወርቅ ገበያዎች ነው። የዓለም  ሃገራት የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ክምችት 69በመቶው በአሜሪካ ዶላር የተቀመጠ ነው። ይህ ጽሁፍ በአጠቃላይ በአንድ ሃገር ላይ የሚደማመጡ ምሁራን፣ፖሊሲ አውጭዎች፣ሃሳብ አፍላቂዎች እና የፖለቲከኞች ጥምረት ሊታመን የማይችል ተዓምር መስራት እንደሚችል ማሳያ ይሆናል ባይ ነኝ።