ወርቅ፣ዶላር እና አሜሪካ!

Screen Shot 2017-08-26 at 23.24.14.jpg

(©Kidus Mehalu) ወርቅ ድንበርና ዜግነት ሳይወስነው በመላው ዓለም ተፈላጊ መሆኑ፣ ፖለቲከኞች እንደ ወረቀት ገንዘብ በፈለጉ ጊዜ ስለማያጋሽቡት፣ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ቀላል እና በተፈለገው መጠን መስራት የሚቻል መሆኑ፣ ለብዙ ጊዜ ቢቀመጥ የማይበላሽ እና ዋጋውን ጠብቆ መቆየት የሚችል መሆኑ፣እንዲሁም በቀላሉ የሚተጣጠፍ፣ ጠንካራ እና እንደ ወረቀት ገንዘብ በማቃጠል ፈፅሞ ማጥፋት የማይቻል መሆኑ እውነተኛ ገንዘብ አሰኝቶታል። ለአንደኛውን የዓለም ጦርነት ዝግጅት አውሮፓዊያኑ መንግስታት እንዳሻቸው ማጋሸብ የማይችሉትን ወርቅን ከዓለም ገበያ ዋጋ ውጭ በከፍተኛ ሁኔታ ማራከሳቸው ሰዎች የያዙትን ወርቅ በገንዘብ እንዲለውጡ ከማድረጉም በላይ ወርቅ አውጭዎችም ቆፋሮ እንዲያቆሙ አስገደዳቸው። ይህም ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ዋጋ መለኪያ የሆነው ወርቅ በሌሎች ሃገራት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ከማድረጉም በላይ ሰዎች በወርቅ ላይ የነበራቸው እምነት መሳሳቱ እና ዓለማቀፍ የወርቅ አቅርቦት መገታቱ ከጦርነቱ በኋላ ዓለም ሲጠቀምበት የነበረው ወርቅን ማዕከል ያደረገው ግብይት ሙሉ ለሙሉ እንዲጠፋ ምክንያት ሆነ። ወርቅን ማዕከል ያደረገው ዓለማቀፍ የገንዘብ ዋጋ ስሌት መቅረቱ የዓለምን የንግድ ሚዛን ከማዛባቱም ጋር ተዳምሮ በአሜሪካ ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት መከሰት ዓለም ከገባችበት ምስቅልቅል ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት በማጨናገፉ ምክንያት አውሮፓ ላይ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት እሳት ሊነድ ግድ ሆነ።

አውሮፓዊያኑ በጀርመን አሳራቸውን በሚያዩበት ወቅት ዓለም አይታው በማታውቀም የኢኮኖሚ መቅሰፍት የተመቱት አሜሪካዊያን ከችግራቸው ለመላቀቅ ላይ ታች እያሉ ነው። እኤአ ታህሳስ 7ቀን 1941ዓ/ም የአሜሪካን ባህር ሃይል በጃፓን ጦር በድንገት መመታቷን ተከትሎ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ ህጋዊ ምክንያት አገኘች። አሜሪካ ከዳርእስከዳር “ጃፓንን እንበቀላለን!እንዋጋለን” በሚሉ ወዶዘማች አሜሪካዊያን ወጣቶች አመጽ ተናጠች።የአሜሪካ ኮንግረስ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የወጣውን እና አሜሪካ በሌላ ሃገር ጦርነት ውስጥ እንዳትሳተፍ የሚከለክለውን አዋጅ ተነሳ። ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት በጃፓን፣ ጀርመን እና ኢጣሊያ ላይ ልጓም ለማበጀት አሜሪካ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ መግባቷን በይፋ አወጁ።

የአሜሪካ የምጣኔ ሃብት ጠበብቶች፣የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሊቃውንቶች እና ሃሳብ አመንጭዎች በበኩላቸው ወርቅን ማዕከል ያደረገው የዓለም የንግድ እና የገንዘብ ግብይት መቅረትን ተከትሎ የተዛባውን የዓለም ንግድ ሚዛን ወደነበረበት ለመመለስ የሚረዳ ውጥን ሲነድፉ፣ሲወያዩ፣ሲከራከሩ፣ሃሳብ ሲጨመሩ እና ሲቀነሱ ቆይተው በሐምሌ ወር 1944ዓ/ም አንድ ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ። በኒው ሃምሻየር ግዛት ውስጥ ብሪቶን ውድስ በሚባል አካባቢ ለመረጧቸው 44 ሃገራት ያስተዋወቁት ይህ ፕሮጀክት ዓላማው ሃገራት የአሜሪካ ገንዘብ የሆነውን ዶላር እንደወርቅ ቆጥረው ቢያከማቹ እና ቢገበያዩበት በፈለጉ ጊዜ ዶላሩን እየተቀበለች በወርቅ የመለወጥ ግዴታ ሲሆን ሂሳቡ በቋሚነት የሚሰላውም የአንድ ወቄት ወርቅ(28.67ግራም ወርቅ) ዋጋ 35 ዶላር ሆኖ ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ መጠነ ሰፊ የወርቅ እጥረት እንደሚያጋጥም ግልጽ ስለነበር በወቅቱ ዶላር እንደ አማራጭ መቅረቡ ሁሉም በደስታ ተቀበለው። ሆኖም ግን ያኔም ሆነ ዛሬ ዶላር ለማግኘት ብቸኛው መንገድ ንግድ እና የውጭ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት ስለሆነ አውሮፓዊያኑ ንግድን ማስፋፋት እና የውጭ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ ማበረታታት ተያያዙት። እኤአ እስከ 1950ዎቹ ድረስ ይህንን አጠናክረው በመቆየት የነበረባቸውን የዶላር ችግር ከማስወገዳቸውም በተጨማሪ የንግድና ኢንቨስትመንቱ መቀጠል የዶላር ክምችታቸው በጣም ከፍ እንዲልም ረድቷቸዋል። የአሜሪካ ዶላር ተቀባይነትም በመላው ዓለም በመስፋፋቱ  ዓለም ዓቀፍ ገንዘብ ሆኖ ሲሰራ የነበረውን ወርቅ ሙሉ ለሙሉ የአሜሪካ ዶላር ተካው። በ1960ዎቹ የአሜሪካ ዶላር ዓለምን አጥለቀለቀ።

ሆኖም ግን የብሪቶን ውድስ ስምምነት ዓለምን ወርቅን ማዕከል(ጎልድ ስታንዳርድ) ካደረገው የግብይት ስርዓት ዶላርን ማዕከል(ዶላር ስታንዳርድ) ወዳደረገው ስርዓት በይፋ ቢያሸጋግርም ከዚህ በኋላ ዶላርን ለሌሎች ሃገራት በወርቅ መለወጥ ‘ጅልነት’ መሆኑን የአሜሪካ ምሁራን መናገር ጀምሩ። ምክንያቱም የወረቀት ገንዘቦችን ለመስራት የሚያስፈልጉት ግብዓቶች እና የህትመት ወጭ አንድ ግራም ወርቅን ከመሬት ቆፍሮ ከማውጣት ጀምሮ ለገበያ እስከማቅረብ ድረስ ካለው ወጭ አንጻር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። ለምሳሌ ያህል እያንዳንዱን ባለ 1፣ ባለ 5፣ ባለ20፣ ባለ 50 እና ባለ 100 የአሜሪካ ዶላር ለመስራት 75% ጥጥ እና 25%ላይሎን ጥቅም ላይ ይውላል። የሁሉም ክብደት 1 ግራም አካባቢ ሲሆን እያንዳንዱን ዶላር ለማምረት የሚወጣው የገንዘብ ወጭ 4 የአሜሪካ ሳንቲም ብቻ ነው። እንግዲህ አስቡት በብሪቶን ውድስ ስምምነት መሰረት ሃገራት ያከማቹትን ዶላር ለአሜሪካ እየሰጡ በምትኩ ወርቅ ይቀበላሉ። ይህም ማለት ለምሳሌ 35 ዶላር ለሚያመጣ ሃገር 28.67 ግራም ወርቅ ትከፍላለች ማለት ነው። የምሁራኑ የጩኸት ምንጭም ይሄው ነው። 35የአሜሪካ ዶላር ለማተም ለምሳሌ (ባለ 1 ዶላር) ወጭው 1.4 ዶላር ነው።35ቱ ዶላር ባለ20፣10 እና 5 ዶላር ተደርጎ ቢከፈል ደግሞ ወጭው 0.12ዶላር ነው። ይህን ያክል ወጭ ለሚፈጅ ዶላር 28.67 ግራም ወርቅ መክፈል የእውነትም ዘላቂ ሊሆን አይችልም። እኤአ ነሃሴ 15 ቀን 1971 ዓ/ም ከገንዘብ ሚንስትራቸው ጆን ኮናሊ፣ የብሄራዊ ባንኩ ሊቀመንበር አርተር በርንስ እንዲሁም ከኢኮኖሚ እና ገንዘብ ጉዳዮች አማካሪዎቻቸው ሄርበርት ስቴይን እና ፖል ቮከር ጋር ሆነው ካምፕ ዴቪድ ውስጥ በጉዳዩ ላይ ሲመክሩ ዋሉ።  •••(ይቀጥላል)