የሰዎች ተፈጥሮ፣ጤናማ ኢኮኖሚ እና መንግስት

(Kidus Mehalu) የኢኮኖሚ ጤናማነት ማሳያ ግለሰቦች በነጻ የኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ያላቸው ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። በተፈጥሮ ተሰጥኦዎቻችን እና ችሎታዎቻችን የተለያየን ነን። አንዳንዶች ከሌሎች የላቀ ተሰጥኦ አላቸው። የአንዳንዶች ተሰጥኦ ትልቅ እሴትን የሚፈጥር ነው። አንዳንዶች ያላቸውን እጅግ የላቀ ተሰጥኦ ሳያውቁት ዕድሜያቸው ይሄዳል። ከነጭራሹ ተሰጥኦዎቻቸውን ሳያውቁ የሚያልፉም ሞልተዋል። ሰዎች በአይምሯቸው፣ በጥንካሬያቸው፣ በጉልበታቸው እና በመጠናቸው ሁሉ የተለያዩ ናቸው። ሰዎች ለነገሮች የሚኖራቸውም ተነሳሽነት እና ጽናት እንዲሁ የተለያዩ ናቸው። በትምህርት ጎበዝ የሆኑ ሰዎች በሙዚቃ ደካማ ሊሆኑ ይችላሉ። ጎበዝ ሙዚቀኞች ትወና ላይ ደካማ ሊሆኑ ይችላሉ። በአንድ ሙያ የተካነ ሰው በሌላ ሙያ ላይ ደካማ ምናልባትም ጎበዝ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ። የሰው ልጅ ከዘመነ አዝማናት በፊት ጀምሮ ርስበርሱ ይፎካከራል። ምግብ ለማግኘት በአደን ይፎካከራል። ማደን የማይችል ለአደን የሚሆን መሳሪያ በመስራት ከአዳኙ ላይ በምግብ ይለዋወጣል። ታዲያ የሰው ልጅ አስተሳሰብ እና የኑሮ ዘይቤ እያደገ ሲሄድ የሚተዳደርበትን የተለያዩ የኢኮኖሚ፣ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተቋም ወደመመስረት ተሸጋገረ። ይህም ተቋም “መንግስት” ይጠራል። ስራውም ዜጎች በገበያው ውስጥ የሚያካሂዱትን የንግድ እና የቢዝነስ እንቅስቃሴ የጨዋታ ህግ በማስቀመጥ በተዋናዮቹ መሃል ለሚደረግ ውል ተፈጻሚነት እንዲሁም በአንደኛው ወገን ክህደት ቢፈጸም ደግሞ ውሉን በህግ አግባብ እንዲቋጭ ያደርጋል። ያለ ጠንካራ የህግ ስርዓት እና መዋቅር ኢንቨስትመንት አይኖርም። ንግድ እና ቢዝነሶች ይቀጭጫሉ። እንዲሁም ለውጥ ፈጣሪ አዳዲስ ሃሳቦችም ይመክናሉ።

ለአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ከሆኑ ተቋማት መካከል ጠንካራ የህግ ስርዓት አንዱ እና አማራጭ የሌለው ግብዓት ነው። ይህም የንግድ እና የቢዝነስ ተቋማት በልበ ሙሉነት እንዲንቀሳቀሱ እና ሃብታቸውን እያስፋፉ ራሳቸውን በመጠቀም ዜጎችንም ወደ ስራው ዓለም ማምጣት ያስችላቸዋል። ይህ ይሆን ዘንድ ገበያ ከመንግስት ተፅእኖ የተላቀቀ ጠንካራ የጨዋታ ህግ ይፈልጋል። መንግስት ሥራ ለመፍጠር ወይም ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት በሚል ወጭ የሚያደርገው ገንዘብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል።

ይህን የከፋ የሚያደርገው መንግስት የራሱ የሆነ ምንም ዓይነት ገንዘብ ስለሌለው ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም መንግስት ከኢኮኖሚያዊ ትርፍ በላይ ለፖለቲካዊ ትርፍ ቅድሚያ መስጠቱ ነው። ይህም የሁሉም መንግስታት ባህሪ ስለሆነም ነው መንግስት እና ገበያ መነጣጠል ያለባቸው። ብዙውን ጊዜ መንግስት ለስራ ፈጠራ በሚል ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ ነገር ግን ምርታማነታቸው እስከዚህም ወደሆነ ፕሮጀክቶች ውስጥ የህዝብ ገንዘብ ሲያፈስ ይታያል። ይህን የሚያደርገውም በግብር እና በብድር የሚያገኘውን ገንዘብ በመጠቀም ነው። የዚህ ደግሞ ግለሰቦች፣ሥራ ፈጣሪዎች እና ነጋዴዎች ሥራቸውን ለማስፋፋት የሚያስችል ገንዘብ ከባንክ ቤት እንዳያገኙ ስለሚያደርጋቸው ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ያላቸውን ሥራቸውን ለማስፋፋት እና ተጨማሪ ሥራ መፍጠር እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል። የነዚህ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ያላቸው ስራዎች መቀጨጭ ደግሞ የሃገር ኢኮኖሚን ወደ ኋላ ከመጎተቱም በላይ መንግስትንም ጭምር ያዳክመዋል። በተጨማሪም የመንግስት ወጭ እየበዛ በሄደ ቁጥር የዜጎች ኪሳራም በዚያው ልክ መጨመሩ አይቀሬ የመሆኑ ጉዳይ ነው።ይህም ብቻ አይደለም። ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር መንግስት በርካታ የህዝብ ገንዘብ እያፈሰሰ ዘላቂ ያልሆነ እና  ፖለቲካዊ ስራ ፈጠርኩ ባለ ቁጥር የሆነ ቦታ በሆነ ሰዓት ዘላቂ እና ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ያለው ስራ የሚሰሩ የግል ሰራተኞች ወይም የግል ድርጅት ተቀጣሪዎች ስራቸውን ያጣሉ። ይህን ሂደት ኢኮኖሚስቶች ዘ አን ኢንተንድድ ኮንሲኩዌንሲስ ኦፍ ሰከንዳሪ ኢፌክትስ ይሉታል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ እና በክክል ከተሞች እየተገነቡ ያሉትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለዜጎች በርካታ የስራ ዕድል ፈጥረዋል ይባላል። ምን ዓይነት የስራ ዕድል የሚለውን ለማሳየት ያህል አንድ አሜሪካዊ ኢንጅነር ለማማከር ስራ ወደ ቻይና ሄዶ ያጋጠመውን ታሪክ እነሆ!

ይህ ኢንጂነር ቻይና ሄዶ ብዙ ሰራተኞች አካፋ እና ዶማን የመሳሰሉ ባህላዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም ግድብ ሲሰሩ ይመለከታል። ኢንጂነሩም ይህን በተመለከተበት ጊዜ ስራውን ይቆጣጠር ለነበረው ሃላፊ ግድቡን ለመስራት፣ ስራውንም ለማቃለል እና  በፍጥነት ግድቡን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ዘመናዊ የቁፋሮ እና የኮንስትራክሽን መኪኖች እንደሚያስፈልግ ይነግረዋል። የሥራው ሃላፊ በበኩሉ “አንተ ያልከውን ዘመናዊ ማሽነሪዎች ከተጠቀምን የብዙ ሠራተኞቻችንን የስራ እድል ይዘጋብናል።” ሲል ይመልስለታል። ኢንጂነሩም “አሃ! እኔ እኮ ያሰብኩት ግድብ የመስራት ፍላጎት አላችሁ ብዬ ነው። ፍላጎታችሁ ብዙ የስራ እድል መፍጠር ከሆነ ለምን ሠራኞቹ አካፋና ዶማውን ጥለው በማንኪያና በሹካ እንዲጠቀሙ አታደርጉም” ብሎ መለሰለት። እዚህ ላይ ትልቁ ቁም ነገር ይህ ዓይነት የስራ ዕድል ከላይ እንዳልኳችሁ ዘላቂ ያልሆነ ፖለቲካዊ ትርፍ ላይ ያተኮረ ሲሆን የህዝብን ገንዘብ በማባከን የሃገርን ኢኮኖሚ እንዲዋዥቅ ያደርጋል።

ይህ በሚሆንበት ጊዜ መንግስት እንደ መፍትሄ በርካታ ወጭዎቹን በመቀነስ(ለምሳሌ የተለያየ ስም ያላቸው ግን አንድ ዓይነት ስራ የሚሰሩ መስሪያ ቤቶችን፣እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዓይነት መንግስታዊ የሆኑ ግን መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሊሰሩ የሚችሉ ድርጅቶችን፣በበርካታ የመግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የተለያዩ አላስፈላጊ የስራ ዘርፎችን ወዘተ) ማፍረስ  ይኖርበታል።ከዚያ ውጭ ለሁሉም የመንግስት ተቋማት እና ሰራተኞች ጭምር ግብር በመክፈል እስትንፋስ የሆናቸው ነጋዴ ላይ ግብር መጨመር ማለት ለሃገር ኢኮኖሚ ደንቀራ መፍጠር ነው። በዚህ ምክንያት የሚመጣው ችግር ደግሞ መዘዙ ብዙ ነው። ምክንያቱም ይህን ዓይነት ደንቀራ ለማስዎገድ በሕግ ስልጣን የተሰጠው መንግስት ራሱ እንቅፋት ሆኖ መገኘቱ ነገሮችን ይበልጥ ስለሚያወሳስብ ነው። የመንግስት ወጭ ማብዛትን እና የግብር ጫናን በማስመልከት ታሪክን፣የሃገራት ነባራዊ ሁናቴ እና የምጣኔ ሃብትን ሳይንሳዊ ሃቅ በሌላ ጽሁፍ በጥልቀት ለመዳሰስ እመለስበታለሁ።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.