የኢኮኖሚ ነጻነት ቁልቁለት በኢትዮጵያ

(በቅዱስ መሐሉ) የካናዳው ፍሬዘር ተቋም እና የዓለም የኢኮኖሚ ነጻነት መረብ በየአመቱ የሚያወጣውን ሪፖርት ከሰዓታት በፊት ይፋ አድርጓል።  ሪፖርቱ የ157 ሃገራትን ያካተተ ሲሆን ኢትዮጵያም አምና ከነበረችበት የ141ኛ ደረጃ አራት ደረጃ ዝቅ በማለት የ145ኛ ደረጃን አግኝታለች።  ሆንግ ኮንግ እንደ ሁሌውም የአንደኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ሲንጋፖር፣ ኒውዚላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ካናዳ፣ ጆርጂያ፣ አየርላንድ፣ሞሪሽየስ፣እና ዱባይ ከሁለተኛ እስከ ዘጠነኛ ደረጃን የተቀዳጁ ሲሆን አውስትራሊያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብ የ10ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የሪፖርቱ መመዘኛዎች በሆኑት አምስት የኢኮኖሚ ነጻነት አውታሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ከሁለቱ መመዘኛዎች በስተቀር በሌሎቹ ደረጃዋ አሽቆልቁሏል።  የሪፖርቱ ሚዛን ሆነው ከ1 እስከ 10 በሆነ ነጥብ በሚሰጥ ነጥብ የሃገራትን የኢኮኖሚ ነጻነት ደረጃ በሚዳስሰው ሪፖርት የመጀመሪያ መመዘኛ መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ እና የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት፣ የመንግስት ገንዘብ አጠቃቀም እና ወጭ እንዲሁም የኩባንያ ግብር ተመንን በመቃኘት ኢትዮጵያ አምና ከነበራት የ6ነጥብ 71 ውጤት ዛሬ በወጣው ሪፖርት ወደ 6ነጥብ 11 ዝቅ ብላለች። ሁለተኛው የኢኮኖሚ ነጻነት ሚዛን ዳሰሰ መህልቁን የሚጥለው በሕግ ስርዓት እና በንብረት ባለቤትነት መብት ላይ ሲሆን በዚህኛውም ሃገሪቱ አምና ካስመዘገበችው የ4ነጥብ 97 ውጤት ወደ 4ነጥብ 96 ወርዳለች። ይህኛው መመዘኛው የፍትሕ ስርዓቱ እና የዳኞች ገለልተኛነት፣ የሕግ ስርዓቱ ተዓማኒነት፣የፖሊስ ታማኝነት፣ የወታደራዊ ተቋሙ በሕግ የበላይነት እና በፖለቲካው ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት፣የሕጋዊ ውል ጥንካሬ እና ተፈጻሚነት እንዲሁም ወንጀል በቢዝነስ ላይ ያለውን ተጽእኖ ስፋት እና ልክ በመዳሰስ በተጠቀሱት ዘርፎች ኢትዮጵያ ቁልቁለት ላይ መሆኗን ይጠቁማል። ሶስተኛው ሚዛን የገንዘብ ፍሰት መጨመር እና ግሽበትን የሚመለከት ሲሆን በዚህ ዘርፍ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ አምና ከነበረችበት የ 5.16 ነጥብ ወደ 5ነጥብ 47 ነጥብ ከፍ ማለቷን ያሳያል።

ኢትዮጵያ ከውጩ ዓለም ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር አስመልክቶ ደግሞ ሪፖርቱ ሃገሪቱ አምና ከነበራት የ5 ነጥብ 28ዓ/ም ውጤት ወደ 4ነጥብ 97 መንሸራተቷን ይገልጣል።በዚህኛው የኢኮኖሚ ነጻነት መለኪያ ሚዛን ኢትዮጵያ ወደ ሃገርቤት በሚገቡ ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ የምትጥለው ታሪፍ፣ የንግድ ማነቆ የሆኑ መመሪያዎች እና ደምቦች፣ በጥቁር ገበያ ላይ የሚደረግ የውጭ ገንዘቦች ግብይት ነጻነት እንዲሁም በሃገሪቱ ያለውን የገንዘብ ፍሰት ነጻነት እና የውጭ ኢንቨስትመንት ገደቦች ጥልቀት ይዳስሳል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ  የገበያ ተዋናዮች እና ውድድር ደካማ ከሆኑት የሃገሪቱ ተቋማት በተጨማሪ ግልጽነት እና ነጻነት የሌለበት መሆኑ ሃገሪቱ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ያላትን ሕልም እስከዛሬ እውን እንዳይሆን ካደረጉት እንቅፋቶች መሃል አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ውጭ በምትልከው ቡና፣ወርቅ፣የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም የቅባት እህሎች እና ሌሎች የግብርና ምርቶች አማካይነት ከዓለም ገበያ ጋር  የተቆራኘ ቢሆንም መንግስት በሚከተለው የፖለቲካ አይዲዮሎጅ ምክንያት በሃገሪቱ የባንክ ሲስተም፣የካፒታል ገበያ እና የቢዝነስ ስራዎች ላይ የማያሰራ ከፍተኛ ቁጥጥር መኖር ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ተጠቅማ ወደተሻለ የኢኮኖሚ እና የማህበረስብ ዕድገት ምዕራፍ እንዳትደርስ አንቆ ይዟታል። በሪፖርቱ የመጨረሻው የኢኮኖሚ ነጻነት ዳሰሳ ውጤት ማንጠሪያ የሆነው በሃገሪቱ ያሉት የቢዝነስ ሕግጋት እና ደምቦች ናቸው።በዚህ ማዕቀፍ ለንግድ የሚውል የብድር አገልግሎት እና የወለድ ተመን ቁጥጥር፣ የስራ ቅጥር ውል እና የቅጥር ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ወለል ነጻነት መኖር አለመኖር፣ የቢዝነስ ድርጅት እና ነጋዲዎችን ገዳቢ ሕግ መኖር አለመኖር፣ ለንግድ ምዝገባ የሚወስደው ቀናት እና የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ስፋት፣ የንግድ ፍቃድ አሰጣጥ ሂደት እና በዚያ ዙሪያ ያሉ ቢሮክራሲዎችን ለማለፍ የሚደረጉ ሕገወጥ የገንዘብ ክፍያዎችን ሁሉ ይዳስሳል። በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያ ከአምናው ነጥብ በ0ነጥብ 23 ውጤት አሻሽላለች።

በአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛ በሆነችው ሃገር ኢትዮጵያዊያን የሚያገኙት ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከምስራቅ አፍሪካ (በቂ መረጃ ያለም በሚል በሪፖርቱ ያልተካተተችውን ኤርትራ እና ሶማሊያን  ሳይጨምር) የመጨረሻ ዝቅተኛው ነው። በዓለም የመጨረሻ ድሃ በሆነችው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት ማሽቆልቆሉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቁልቁል እየሄደ እና ድህነትም ይበልጥ እየተንሰራፋ መሆኑን ይናገራል።  የኢኮኖሚ ነጻነት ቁልቁል መውረድ የሕግ የበላይነት እና የፍትህ ተቋማት ነጻነት፣የሃይማኖት ነጻነት፣የሰው ሃይል ዕድገት ነጻነት፣ የሞላዊነት እና የማህበረሰብ ብልጽግና ውድቀት አመላካች መንገድም ነው። የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ነጻነት አይኖርም።ነጻነት የሌላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ደግሞ ደካማ ናቸው። በምስራቅ አፍሪካ ደካማ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት የሚገኙትም በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ባሉበት ሃገር ጠንካራ የመንግስት ተቋማት እንደሚኖሩ ከጎረቤት ኬንያ ማየት እንችላለን። በጥቅሉ ሲታይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የስትራክቸራል ችግር እንዳለበት ዓይኑን የገለጠ ሁሉ ሊያየው በሚችል ደረጃ ገዝፎ ይታያል። ይሄ የኢኮኖሚ መዛነፍም በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ የፖለቲካ አምዱን ሲነቀንቀው ዓለም እየተመለከተ ነው።