የሆንግ ኮንግ ተዓምራዊ እድገት ሚስጥር!

ሆቴየግለስብ ነጻነት!

“ዴሞክራሲያዊ” የሚል መጠሪያ ያላቸው እና ስለ ዴሞክራሲ የሚያወሩ መንግስታት ሁሉ ዴሞክራሲያዊ እንዳልሆኑት ሁሉ የሆነ ሃገር የሚከተለውን ስርዓት እንዲህ ነው ከማለት በፊት የሚተገብሩትን ስርዓት እንጅ የስርዓቱን ስም ማየት ስህተት ላይ ይጥላል።ለምሳሌ ስም ብቻ ለሚመለከቱ ሰዎች አውሮፓ በሶሻሊዝም ስርዓት ስር ያለች ሊመስላቸው ሁሉ ይችላል።ምክንያቱም በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ካለው 751 ወንበር ውስጥ ከ450 በላይ የሚሆነውን የያዙት ስማቸው ‘ሶሻሊስታዊ’ ከሚል ፓርቲዎች ተመርጠው የገቡ ሰዎች ናቸው።እውነታው ግን ሶሻሊስታዊ አሰራሮችን ከጤና(በየሃገሩ ያሉት በሽታወች ስለሚለያዩ)፣ድጎማ(ዌልፌር) እና ከአካባቢ ፖሊሲዎች( በየሃገሩ ያሉ የኢንቫይሮንመንት ችግሮች ስለሚለያዩ) በቀር በአውሮፓ ሕብረት አገራት ውስጥ ሶሻሊዝም ጋር ቁርኝት ያላቸውን አሰራሮች መተግበር በሕግ ክልክል ነው። ይህ ብዙዎች ሶሻሊስት የሚመስሏቸውን ግን በተግባር ካፒታሊዝምን ከብዙ ሃገራት በተሻለ መንገድ በሚተገብሩት የስካንዲኒቪያ ሃገሮች ጭምር የሚተገበር ደረቅ እውነታ(ፋክት) ነው።ዴንማርክ ይህ ሕግ ባይመለከታትም ካፒታሊዝምን በመተግበር ግን ከሁሉም የስካንዲኒቪያ ሃገሮች ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካም ትበልጣለች።

“የኤዥያ ተዓምራት” የሚባሉት ሃገራት ያደጉት በምን ዓይነት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት እንደሆን ለመረዳት ይህን ጽሁፍ ካነበቡ በኋላ ፍርዱን ለራስዎ ይስጡ።እኔም “ነገር ከስሩ•••” እንዲሉ ከስረ መሰረቱ ለማሳየት ሆንግ ኮንግን መነሻ ማድረግ ፈለግሁ። እኤአ በ1960ዎቹ ቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ እንደ አንዲት አነስተኛ የአሳ ማስገሪያ መንደር ነበር የምታያት-ሆንግ ኮንግን! በዚያን ጊዜ ሆንግ ኮንግ ዘጠኝ መቶ ሽህ (900,000) ያህል ህዝብ ነበራት። እኤአ ከ1961ዓ/ም በኋላ ለሆንግ ኮንግ አለቃ ሆኖ በእንግሊዝ የተሾመው ሰር ጆን ጀምስ ከሃገሩ እንግሊዝ የሚተላለፉለትን ህዝብን አደህይቶ እና አቆርቁዞ የመግዥያ መመሪያዎች በመጣስ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎችን የሰቆቃ ታሪክ ለመቀየር መስራት ጀመረ። እንግሊዝ ከፍተኛ ግብር እየጣለች ስትበዘብዛቸው የኖሩት የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች በሰር ጆን ጀምስ ነጻ ወጡ። ከጥቂት የግብር ስርዓት በስተቀር አብዛኛውን የግብር ስርዓት እንዳትከፍሉ ብሎ ወሰነ። ሆንግ ኮንግ ከግዙፍ ኩባንያዎች ገቢ ላይ 15በመቶ ግብር ትሰበስባለች።

ሆንግ ኮንግ ከወደብ በስተቀር ምንም ዓይነት የተፈጥሮ ሃብት የሌላት ሃገር መሆኗንም አትርሱ። እንግሊዛዊው ሰር ጆን ጀምስ የሆንግ ኮንግ ሰዎች ሰርተው መብላት ይችሉ ዘንድ ከማንኛውም ዓይነት የቡድን ሰንሰለት ነጻ አድርጎ ለቀቃቸው። ሰር ጆን ጀምስ ከነጻነት በስተቀር ሌላ ምንም ነገር ሊሰጣቸው እንደማይችል እንዲሁም ከእንግሊዝ የሚሰፈርላቸው የእህል ርዳታም ከዚህ ጊዜ በኋላ እንደማይኖር ለሆንግ ኮንግ ሰዎች በግልጽ ነገራቸው። ማንም ሰው ያለፍቃዱ በቡድን መደራጀት የለበትም አለ። የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ህዝብን ረግጦ ለመግዛት ከሚያመቸው ቡድናዊ የመንጋ አስተሳሰብ ወደ ‘ሰው’ ነት ተሸጋገሩ። በሆንግ ኮንግ የሰው ልጅ ጭንቅላት ስራውን መስራት ጀመረ።ከዚያ በፊት ማንም ማሰብ አይችልም ወይም ቢያስብም ተፈጻሚ የሚሆነው የቡድን እንጅ የግለሰብ አሳብ አልነበረም።

እኤአ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ማለትም ሆንኮንጋዊያን እንደ ግለሰብ ማሰብ፣ መስራት፣ መነገድ እንደሚችሉ እና ያለ ፍላጎታቸው የማንም ሰው ቡድናዊ ዓላማ ተፈጻሚ እንደማይሆንባቸው ከተረጋገጠ ከ30አመታት በኋላ የሆንግ ኮንግ ሰዎች አመታዊ ገቢ ከቅኝ ገዥያቸው እንግሊዝ ዜጎች በ25 በመቶ ብልጫ አሳየ። ቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ ብርክ ያዛት። ደነበረች። ሃብታም ህዝብን በርግጥም ረግጦ በግድ መግዛት አይቻልም። ይህን ጠንቅቃ የተረዳችው እንግሊዝ እኤአ ሃምሌ 1 ቀን 1997ዓ/ም ሆንግ ኮንግን ከመቶ ሃምሳ(150) የግዞት ዓመታት በኋላ ለቻይና ጥላት ሄደች። ይህን ክፍል አንድ ጹፍ ከመዝጋቴ በፊት ለግለሰብ ነጻነት እውቅና የሚሰጥ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት ካፒታሊዝም ብቻ መሆኑን ማስታወስ እወዳለሁ።

የሚዲያ፣የፍትህ እና የፋይናንስ ተቋማት ነጻነት Screen Shot 2015-10-31 at 22.00.39

ሆንግ ኮንግ የቻይና ኮምኒዝም ስርዓት የማይተገበርባት ልዩ ግዛት ናት። እንግሊዝ ሆንግ ኮንግን ለቻይና በምትመልስበት ወቅት ለሆንግ ኮንግ መተዳደሪያ የሚሆን እና ለ50 ዓመታት የሚሰራ የራሷ መሰረታዊ ሕግ እንዲኖራት አድርጋለች።ይህ መሰረታዊ ሕግ ሆንግ ኮንግን የንግድ እና የንብረት ባለቤትነት መብት፣የመናገር እና የሚዲያ ነጻነት፣የፍትህ እና የዳኝነት ነጻነት፣የግለሰብ፣የፋይናንስ ተቋማት ነጻነት እንዲኖራት አስችሏታል። ከሆንግ ኮንግ አንጻር እነዚህ ነጻነቶች በዋናዋ የቻይና ምድር የሉም ማለት ይቻላል።

ሆንግ ኮንግ 70አባላት ያሉት የሕግ አውጭ ም/ቤት ያላት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 35 ያህሉ በቀጥታ በህዝብ ምርጫ ይመረጣሉ። ከንግዱ ማህበረሰብ፣ከሲቪል ማህበረሰብ፣ከአሰሪዎች  እና ሰራተኞች፣ ከወጣቶች፣ከሴቶች፣ከጤና ባለሙያዎች ወዘተ የሚመረጡ ወኪሎች ደግሞ 30 ወንበር ይይዛሉ። የተቀረውን 5 ወንበር ደግሞ የሆንግ ኮንግ 18 አውራጃወች በቅድሚያ ከመረጧቸው ሰዎች ውስጥ ለህዝብ ምርጫ በማቅረብ ያስመርጣሉ። በቀጥታ በህዝብ የሚመረጠው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ እና ህዝቡ ለቻይና ያጎበድዳሉ የሚላቸውን ፖለቲከኞችን እንደማይመርጥ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ቻይና የሆንግ ኮንግን መሰረታዊ ሕግ[ቤዚክ ሎው] ‘የመጨረሻው ተርጓሚ አካል ነኝ’ በሚል በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት በተደጋጋሚ እንደታየው የሆንግ ኮንግን ገዥ በእጅ አዙር ትሾማለች።

ይህ ሹመት የሚከናዎነው ግን ከሆንግ ኮንግ 18አውራጃዎች በጥንቃቄ ቀድመው በሚምረጡ 1200 ያህል አባላት ያሉት እና ለቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ቅርብ በሆኑ ሆንግ ኮንጋዊያን በተቋቋመ የምርጫ ኮሚቴ ነው። ቻይና ከዚህ ባለፈ የብዙ ክፍለ ዘመናት የማናቆር፣ የተንኮል እና የአገዛዝ ጥበብ ባለቤት የሆነችው እንግሊዝ ያልገዛቻትን ሆንግ ኮንግ እንደ ህጻን ልጅ አባብላ ይዛታለች። አንዳንዴ ታስፈራራታለች እንጅ የተቀረውን በቢሊዮን የሚቆጠር ህዝቧን ቀስፋ በያዘችበት ኮምኒስታዊ መንገድ በጉልበት ልርገጥሽ አላለቻትም። ሆንኮንጋዊያን በበኩላቸው “ቻይናዊያን አይደለንም፤ቻይና በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባቷን ታቁም!” ማለቱን አጠናክረው ገፍተውበታል። ይህን ርዕስ ከመቋጨቴ በፊት አንባቢዎች ለሚዲያ፣ለፍትህ እና ለፋይናንስ ተቋማት ነጻነት የሚሰጠውን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት እንዲያስታውሱ እና ለራሳቸው መልሱን እንዲሰጡ አሳስባለሁ።

ሆሊየኢኮኖሚ ነጻነት!

በዓለም ላይ እጅግ በጣም ሃብታም ህዝብ ከሚኖርባቸው ሃገራት ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትሰለፈው ሆንግ ኮንግ ከትላልቅ የዓለም የፋይናስ መገበያያ ሃገራትም ዋነኛዋ ናት። የኢኮኖሚ ነፃነት የነገሰባት ሆንግ ኮንግ የዜጎቿ አማካይ የመኖሪያ እድሜ ከ80ዓመት በላይ ነው። የኢኮኖሚ ነፃነት የሰውን ልጅ ከችጋር እና ሰቀቀን ነፃ ስለሚያደርገው ሰዎች ያለ እድሜያቸው እንዳይሞቱ ትልቅ አስተዋፆ ያደርጋል። ሰባት ሚሊዮን ያህል ሃብታም ህዝብ ያላት ሃገር ሆንግ ኮንግ አመታዊ የኢኮኖሚ ጠቅላላ ምርቷ(ጂዲፒ) 369.4ቢሊዮን ዶላር ነው። የሆንግ ኮንግ ዜጎች ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ51 ሽሕ የአሜሪካ ዶላር በላይ ሲሆን በዓለም ላይ ዜጎቻቸው የተሻለ ገቢ ያገኛሉ ከሚባሉ ሃገራት በተለይም ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሃብታም ናቸው ብለው ከሚያስቧቸው ሃገራት ዜጎች አንፃር ሲታይ የሆንግ ኮንግ ሰዎች ዓመታዊ ገቢ በአማካይ 264%(በመቶ) ይበልጣል።

የዓለም ባንክ በየዓመቱ በሚያወጣው ለቢዝነስ ምቹ የሆኑ ሃገራትን የሚዳስስበት ሪፖርት ላይ ሆንግ ኮንግ ቀዳሚ ስትሆን የካናዳው ፍሬዘር ኢንስቲትዩት ሲያወጣው በኖረው የኢኮኖሚ ነፃነት ሪፖርት ላይም እስካሁን የሚገዳደራት ሌላ ሃገር አልተገኘም። ሆንግ ኮንግ ላለፉት 21 ዓመታት የሄሪቴጅ ፋውንዴሽን እና ዋል ስትሪት ጆርናል በጋራ ሲያወጡት በኖረው እና የሃገራትን የኢኮኖሚ ነጻነት የሚዳስስ ሪፖርት ላይም ለተከታታይ 21 ዓመታት አንደኛ መሆን ችላለች። ሆንግ ኮንግ በሪፖርቱ ከተካተቱ 172 የዓለም ሃገራት ውስጥ የካፒታሊዝምን ኢኮኖሚያዊ ንድፈ ሃሳቦች በተግባር በማዋል የሚስተካከላት ሃገር የለም። ሆንግ ኮንግን አንደኛ ያሰኟት መስፈርቶች ነጻነትን ለሚወዱ የሰው ልጆች ሁሉ እንደ ምርጥ ሙዚቃ ይደጋገማል። ስለዚህ እኔም ደግሜ ደጋግሜ ስለዚያች ሚጢጢ የኤዥያ ምድር እፅፍላችኋለሁ። አዎ! ስለዚያች ትንሽ የድሆች የአሳ ማስገሪያ መንደር ስለነበረችው ምድር እከትባለሁ። ከሃገሯ መሬት አንዳችም ማዕድን የማይወጣባት፥ የግብርና ምርቷ ዜሮ በመቶ (0%) የሆነባት እና ከወደብ በቀር ምንም ዓይነት የተፈጥሮ ሃብት ስለሌላት ሆንግ ኮንግ ስኬት እተርካለሁ። ምክንያቱም ሆንግ ኮንግ አገር በወሬ፣ በስብሰባ፣ በመፈክር እና በፕሮፖጋንዳ እንደማያድግ ጥሩ ማሳያ ትሆናለች።

የሆንግ ኮንግ የኢኮኖሚ እድገት፥ በሃብት የመመንደጓ እና የብልፅግናዋ ቁልፎች ከሌሎች ሃገራት ሁሉ ልቆ የተገኘው የኢኮኖሚ ነጻነቷ የአምበሳውን ድርሻ ይይዛል።ሆንግ ኮንግ ከሌሎቹ ሃገራት ሁሉ በኢኮኖሚ ነጻነቷ በልጣ የተገኘችው:-1ኛ፡ በአንጻራዊነት ምንም ሙስና የሌለባት ምድር መሆኗ፣ 2ኛ: ብቃት ያለው እና ገለልተኛ የፍትህ ሥርዓት ስላላት፣ 3ኛ፡ለግለሰቦች ሃብት እና ጥረት ህጋዊ ከለላ የምትሰጥ እና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት ምድር መሆኗ፣ 4ኛ፡ ያልተወሳሰበ፣ ግልጽ፣ እና አነስተኛ የግብር ስርዓት ተግባራዊ ማድረጓ፣ 5ኛ፡ በሆንግኮንግ ውስጥ የሽያጭ ታክስ(ግብር) እና ተጨማሪ እሴት ታክስ ከነጭራሹ አለመኖሩ፣ 6ኛ፡ የሆንግኮንግ ዜጎች ከቋሚ ንብረታቸው ላይ ከሚያገኙት ጥቅም ምንም አይነት ግብር አለመክፈላቸው(ለምሳሌ ቤት ሲሸጡም ሆነ ሲያከራዩ ለመንግስት የሚከፍሉት ግብር የለም) እና በውርስ ከሚገኝ ሃብት ላይም ምንም አይነት ግብር አለመከፈሉ፣ 7ኛ፡ በአንጻራዊነት ሆንግኮንግ ምንም አይነት የውጭ ሃገር እዳ ወይም ብድር የሌለባት ሃገር በመሆኗ እና 8ኛ፡ በሆንግኮንግ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ወደሃገር ቤት የሚገቡም ሆነ ከሃገር የሚወጡ ሸቀጦች እና ሌሎች እቃዎች ላይ ቀረጥ የሚባል ነገር ባለመኖሩ ነው። የሆንግ ኮንግ ተዓምራዊ ዕድገት ሚስጥራት ተብሎ ከላይ ጀምሮ የተዘረዘሩት ምክንያቶች ሁሉም ከካፒታሊዝም ስርዓት ውጭ የሚሰሩ አይደሉም። ስለዚህ ሆንግ ኮንግን ጨምሮ የአራቱም የኤዥያ ነብሮች ተዓምራት የኢኮኖሚ ዕድገት ሚስጥር ካፒታሊዝም መሆኑን ጠቅሼ ጽሁፌን መቋጨት ወደድኩ። ምናልባት ይህ የማይዋጥለት ሊኖር ስለሚችል ስለ አራቱ የኤዥያ ነብሮች የኢኮኖሚ እድገት ሚስጥር ይበልጥ መረዳት እንዲችል እኤአ በ1993ዓ/ም የወጣውን “ዘ ኤዥያን ሚራክልስ” የሚለውን የዓለም ባንክ ሪፖርት እንዲያነብ ጋብዥዋለሁ።