ዋልት ዊትማን እና ልማታዊ መንግስት

ልማትዊየሁለተኛው የዓለም ጦርነትን መገባደድ ተከትሎ አሜሪካ የማርሻል የኢኮኖሚ ማገገቢያ እና የክላሲካል ሊበራሊዝም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ግንባታ ድጋፍ ለአውሮፓዊያኑ ስትነድፍ ያዩት ኢኮኖሚስቶች ትኩረታቸውን ሶስተኛው ዓለም በሚባለው ወይም በኦፊሴል ያላደጉ ሃገራት በሚባሉት የኤዥያ፣ አፍሪካ እና ደቡብ አሜሪካ ሃገራት ላይ አደረጉ። እነዚህ ስፍራዎች ባብዛኛው ያልተማረ ህዝብ የሚኖርባቸው፣ ስራ አጥነት በከፍተኛ ደረጃ የተንሰራፋባቸው እና ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት የሚታይባቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ ኢኮኖሚያቸውም ከኋላ ቀር ግብርና ጋር የተሳሰረ ነው። የህዝብ ሃብትም በገሃድ ሲመዘበር እና ወደ ውጭ ሃገራት ሲሸሽ የሚታየው ከነዚህ አካባቢዎች ነው። በነዚህ ስፍራዎች የሚኖረው ህዝብ ኑሮም በከፍተኛ ግሽበት የተጎዳ፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት ሰለባ የሆነ እና ለጥቁር ገበያም የተጋለጠ ነው።

ዋልት ዊትማን የተባለ የማሳቹሴት ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጅ ኢኮኖሚስት ሁኔታውን ካጤነ በኋላ በ1960 ዓ/ም የፀረ ኮሚኒስት ማኒፌስቶ ነው ያለውን “የኢኮኖሚ እድገት ደረጃዎች፡-የሶስተኛው ዓለም እቅድ” ፃፈ። በዋልት ዊትማን የተነደፈው ይህ የመንግስት ቅርጽ እና የኢኮኖሚ ንድፈ ሃሳብ እቅድ ‘ልማታዊ መንግስት’ የሚል ስም አግኝቷል። ዋልት ዊትማን እንደሚለው ከሆነ ያላደጉ ሃገራት በድህነት አዙሪት ቀለበት የወደቁ ስለሆነ እድገት ከውስጥ ማመንጨት አይቻላቸውም። ስለዚህ መንግስት ይህን የድህነት ቀለበት ጥሶ እስኪወጣ ድረስ መጠነ ሰፊ ፕሮጄክቶች በመንግስት መከናወን አለባቸው ባይ ነው። እንደ ዊትማን ከሆነ ለነዚህ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክቶች የሚሆነውን ገንዘብ የዓለም ባንክ በብድር መልክ ሊሰጥ ይገባል። በርግጥ የዓለም ባንክም በዚሁ መሰረት ለሃገራት ብድር ሲያበድር ኖሯል።

በዚያን ወቅት ከወደ ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የሚጮኽውን ሰው ግን ለማድመጥ የወደደ አልነበረም። ይህ ድንቅ ኢኮኖሚስት ፒተር ባወር ነበር። “እባካችሁ! እርዳታ አገር ያሳድጋል ማለት እብደት ነው። በውጭ ኢንቨስትመንት እንጅ በውጭ እርዳታ ያደገ አንድም ሃገር የለም። መንግስት ኢኮኖሚውን በሚቆጣጠርበት ሃገር ውጤቱ እድገትና ብልፅግና ሳይሆን ጭቆና፣ ሙስና እና ሰቆቃ ብቻ ነው።” በማለት ድምፁን አሰማ። በመንግስት ተጠፍንጎ የተያዘ ኢኮኖሚ ማንም ያቅደው ማን ለገበያ ምቹ የሆነ ስርዓትን እስካልፈጠረ እና የነፃ ማህበረሰብ ተቋማት እስካልተገነቡ ድረስ ውጤቱ ከሶሻሊዝም ስርዓት የተለየ አይሆንም። በመሰረቱ መንግስት ለአንድ ሃገር ለሃብት መፈጠር ምክንያት የሚበጁ ፖሊሶዎችን እና ነጻ ተቋማትን በሕግ እንዲቋቋሙ ከማድረግ ባለፈ እና ሰዎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበትን በሕግ የበላይነት የሚመራ ስርዓት ከመጠበቅ ባለፈ በራሱ ሃብት ሊፈጥር አይችልም። መንግስት ሃብት ይፈጥራል ብሎ ማሰብ በራሱ መዥገር ወይም ቁንጫ ወይም ቅማል ደም በመምጠጥ ፋንታ ደም ይለግሳሉ እንደ ማለት ነው።

የልማታዊ መንግስትን ንድፈ ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀምሮ ያቀረበው ኢኮኖሚስቱ ዋልት ዊትማን በ1990ዎቹ ባደረገው ቃለ ምልልስ “ልማታዊ መንግስት” የሚባለው ስርዓት እንደማይሰራ በአንደበቱ ተናግሯል። የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ምሁር የሆነውን ፒተር ባወር አቋም በማንፀባረቅ የተናገረው ዋልት ዊትማን “ስራየ ብየ ፒተር ባወርን ባደምጠው ኖሮ የእኔ አቋም ስህተት እንደነበር ለማወቅ ሶቬት ህብረት እስክትፈራርስ መጠበቅ ባላስፈለገኝ ነበር።” ብሏል። የዓለም ባንክም በ1996ዓ/ም ባወጣው ‘ፍሮም ፕላን ቱ ማርኬት’ [ከማዕከላዊ የመንግስት ዕቅድ ወደ ገበያ] በሚለው ሪፖርቱ ላይ የዋልት ዊትማንን መንገድ መከተሉ ስህተት ላይ እንደጣለው በመግለፅ አቋሙን ከፒተር ባወር ጋር አንድ አድርጓል።

የልማታዊ መንግስትን ንድፈ ሃሳብ በቀመረው ሰው ሳይቀር የልማታዊ መንግስት ስርዓት በቅርብ ሩቅ  የድህነት፣ የስደት እና የጠኔ ምንጭ መሆኑ ተረጋግጧል። እንዲህ ያለ ስርዓት ባለበት ሃገር የገንዘብና የሃብት ምንጭ ሁሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ስለሚወድቅ ለስርዓቱ ታማኝ ከሆኑና ከሚያጎበድዱት በቀር ብዙሃኑ እንዲበለፅግ አይፈቀድለትም። በእንደዚህ አይነት ስርዓት ውስጥ ሆኖ በጥረት ሃብት ለማግኘት መሞከር እጅግ አድካሚ እና ፈታኝ ከመሆኑም በላይ መንግስት የሚሰሩ ሰዎችን በማያባሩ ‘ልማታዊ’ የመዋጮ አይነቶች ድካማቸውን ፍሬ አልባ በማድረግ ጥሪታቸውን ሁሉ ያራቁትባቸዋል። በልማታዊ መንግስት አሰራር መሰረት ሃብታም የሚሆኑት የሚሰሩ ሰዎች ሳይሆን መንግስት ሃብታም እንዲሆኑ የሚመርጣቸው እና የሚፈቅድላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። በእንዲህ አይነት ስርዓት ውስጥ ጥቂቶች በብዙዎች ኪሳራ የማይገባቸውን ሃብት እንዲያጋብሱ “የማሪያም መንገድ” ይከፈትላቸዋል።

ልማታዊ መንግስት የሚባለው የሚያወጣው ሕግ ተፈፃሚ የሚሆነው በዜጎች ላይ ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት የልማታዊ መንግስት ስርዓት የፍትህ መሰረት የሕግ የበላይነት(ሩል ኦፍ ሎው) ሳይሆን በሕግ የበላይነትን (ሩል ባይ ሎው) ማስጠበቅ ነው። ይህንኑ የበላይነት ለማስጠበቅም የፍትህ ስርዓቱ መንግስት እንዳሻው ጣልቃ የሚገባበት እና ባለስልጣናት ለዳኞች ቀኝን ትዕዛዝ በማሳለፍ የሚፈልጉትን የፍርድ ትዕዛዝ የሚሰጡበት ጭምር ነው። በልማታዊ መንግስት ስርዓት ስር የሚኖሩ ዜጎች ኢኮኖሚያዊ እጣፈንታ የሚወሰነው ለመንግስት ባላቸው ፖለቲካዊ ወገንተኝነት እና ታማኝነት ነው። ልማታዊ መንግስት የሚያሳልፈውን ውሳኔ እና እቅድ ዜጎች ወጥ በሆነ መንገድ እንዲያምኑ እና በተመሳሳይ ቃላት እንዲያስተጋቡ የሚደረግበት ስርዓት ነው። ይህ ዓይነት ስርዓት ሙስና መገለጫው ከመሆኑ ባሻገር የነፃ ማህበረሰብ ተቋማት አስፈላጊነትንም አይቀበለም።