ካፒታሊዝም እና ኢኮኖሚክስ 

ሉድዊግካፒታሊዝም ለሰው ልጅ እንደ ግለሰብ እውቅና እና ነጻነት የሚሰጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት ስርዓት ነው። የካፒታሊዝም ዋና መገለጫው ጠንካራ የህግ ስርዓት፣ የፖለቲካ ነጻነት፣ የኢኮኖሚ ነጻነት፣ የሚዲያ ነጻነት፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት ነጻነት ናቸው። ካፒታሊዝም በግለሰቦች መብት እውቅና፣ በህግ የበላይነት እና በኢኮኖሚ ነፃነት ላይ የሚቆም ፍትሃዊ እና ሞራላዊ ስርዓት ነው። ካፒታሊዝም ማህበራዊ ትብብርን እና የህብረት ስራን በመፍጠር ረገድ እስከ ዛሬ ከነበሩት ስርዓቶች ሁሉ የላቀ ድንቅ መሳሪያ ነው፡፡ በካፒታሊዝም ስርዓት ውስጥ የሰዎችን የልፋት ውጤት፣ ጉልበት እና ንብረት ወዘተ ከፈቃዳቸው ውጭ በጉልበት መንጠቅ ፈፅሞ አይቻልም። ለካፒታሊዝም ስርዓት አማራጭ ሆነው የሚቀርቡት ሶሻሊዝም፣ ኮምዩኒዝም፣ ክሮኒ ካፒታሊዝም፣ ኦኪንክላቱራ ካፒታሊዝም፣ ኢምቤድድ መርካንቲሊዝም፣ ዴሞክራቲክ ሶሻሊዝም፣ ኒዎ ሊበራሊዝም፣ ኮርፖሬቲዝም፣ ፋሽዝም፣ ናዚዝም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፥ ልማታዊ መንግስት ወዘተ ናቸው።

ካፒታሊዝም የሰዎች ሕይዎት፣ ነፃነት እና ንብረት መብት መከበር ላይ የሚቆም ስርዓት ነው። ካፒታሊዝም ለሰዎች አኩል መወዳደሪያ ሜዳን የሚፈጥር ስርዓት ነው። በኢኮኖሚው ረገድ ያየን አንደሁ ካፒታሊዝም የገበያ ውድድር የሚተገበርበት ስርዓት ነው። የካፒታሊዝም ስርዓት በሕግ የበላይነት ይመራል። በካፒታሊዝም ስርዓት ሰዎች የተቸገሩ ሰዎችን እና ድርጅቶችን የሚረዱት በራሳቸው ተነሳሽነት ብቻ ነው። ካፒታሊዝም ለግለሰቦች የማሰብ ነፃነትን ስለሚፈቅድ ስርዓቱ የድንቅ ፈጠራዎች፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጅዎች እና የአዳዲስ ግኝቶች ምንጭ ነው። ኢንተርኔት፣ ስልኮች፣ ኮምፒውተሮች፣ ካሜራዎች፣ መኪናዎች፣ አውሮፕላኖች ወዘተ ሁሉ የካፒታሊዝም ስርዓት ከፈጠረው ማህበረሰብ ውስጥ የወጡ በነፃነት የሚያስቡ ግለሰቦች የፈጠራ ውጤቶች መሆናቸውን አትዘንጉ። ሁሉም በግለሰቦች እንጅ በመንግስት እቅድ፣ ገንዘብ ወይም አስገዳጅነት የተገኙ አይደሉም።

ካፒታሊዝም ሰዎችን ከድህነት በማውጣት ይበልጥ እንዲበለፅጉ የሚያደርግ እና ሐብት እንዲያፈሩ የሚያደርግ የእሴት ምንጭ ነው። ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በቻይና እና በሕንድ ከድህነት ተላቀዋል። ይህ የሆነው ሃገራቱ ካፒታሊዝምን ይበልጥ ተግባራዊ በማድረጋቸው ነው። የካፒታሊዝም ዋነኛ መዳረሻ ግብ የሰው ልጅ ብልፅግና እና ነፃነት ነው። በዓለም ላይ የሚታየው ትልቁ ክፍተት ካፒታሊዝምን ተግብረው ሃብታም በሆኑ እና ባለመቀበላቸው ምክንያት ድህነት ውስጥ ሰጥመው በቀሩት መሃል ያለው ነው።

⦿ ካፒታሊዝም እና ሞራላዊነት

በካፒታሊዝም ስርዓት የሰዎች ገቢ የሚወሰነው በሃይማኖታቸው፣ በፖለቲካ አቋማቸው፣ በመልካቸው ጥቁር ወይም ነጭ መሆን ሳይሆን በስራ ውድድር በሚያሳዩት ችሎታ፣ ጥረት እና ብቃት ልክ ነው። የእኛው ሃገር ሶሻሊስቶች አገር ቤት መኖር ባልቻሉበት ወቅት እንኳ የተሰደዱት ‘ኢምፔሪያሊስት’ እያሉ ሲያወግዟቸው ወደነበሩት የካፒታሊስት ሃገሮች መሆኑን ልብ ይሏል። ይህ ስለምን ሆነ ቢባል መልሱ አጭር እና ግልፅ ነው። እሱም በካፒታሊስቶቹ ሃገራት ለስደተኛው የሚተርፍ እና ካፒታልን በጥረት መፍጠር የሚያስችል የካፒታሊዝም ስርዓት መርሆዎች ተግባራዊ ይደረግ ስለነበር ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ ካፒታሊዝም እንደ ሌሎቹ ስርዓቶች ዘረኛ እና አድሎአዊ አለመሆኑ ነው። ካፒታሊዝም በሃገራቸው ሰርተው መኖር ያልቻሉ ሰዎችን ከሃገራቸው ውጭ ባገኙት የኢኮኖሚ ነጻነት ተወዳዳሪ ሆነው የሃብት ማማ ላይ መውጣት አስችሏቸዋል። ካፒታሊዝም ጥቂት ለማይባሉ ኢትዮጵያዊያንም ትላላቅ ቦታዎች ላይ እንዲሰሩ ዕድሉን ፈጥሮላቸዋል።

ከየትኛውም የዓለም ክፍል የበለጠ ለድሆች ርዳታ የሚጎርፈውም የካፒታሊዝም ስርዓት ከሚተገበርባቸው የካፒታሊስት ሃገራት መሆኑን ለማወቅ ንፁህ ህሊና ብቻ በቂ ነው። ሶሻሊስቶች ‘ስግብግብ’ የሚሉት የካፒታሊስት ማህበረሰብ በወሬ እና በመፈክር ሳይሆን ሳይሆን በተግባር በተሰደዱ ጊዜ በሩን ከፍቶ ተቀብሏቸዋል። ያለውን በማካፈል በዚያ እንዲቋቋሙ ረድቷቸዋል። ከሁሉም በላይ ነፃነትን እንዲያጣጥሙ እና በርግጥ ነፃነት ማለት ምን እንደሆን በተግባር አሳይቷቸዋል። ይህ የካፒታሊዝም ሞራላዊነት ማሳያ ነው።

የካፒታሊዝምን ሞራላዊነት ለማሳየት ሌላ ምሳሌ ልጨምር። ማይክሮ ሶፍት ኩባንያ አፍሪካዊያን እና ሌሎች ድሃ ሃገራት ሶፍትዌሮቹን እያባዙ ሲጠቀሙ ዝም የሚለው እንዳይጠቀሙ ማድረግ ስለማይችል ሳይሆን የመክፈል አቅም እንደሌላቸው በመረዳቱ ነው። ሰዎች ሁልጊዜ ራሳቼውን ከኢንተርኔት ካላራቁ በቀር ህገወጥ ሶፍትዌሮችን መቆጣጠር በጣም ቀላል ነው። በአዲስ አበባ በአስራ አምስት ብር ወይም ሃያ ብር የምንገዛው ሁሉንም ያቀፈው የማይክሮሶፍት ኦፊስ ሶፍትዌር (ወርድ፣ ኤክሰል፣ አክሰስ፣ ፓወር ፖይንት ወዘተ) በአሜሪካ የኦፊስ ሶፍትዌሮች ዋጋ ማለትም ወርድ ብቻውን፣ ኤክሰል ብቻውን፣ አክሰስ ብቻውን፣ ፓወር ፖይንት ብቻውን ወዘተ እያንዳንዳቸው የሚሸጡት በሰላሳ አራት ዶላር ነው። እስኪ አስቡት አዲስ አበባ ከሶፍትዌር ሱቆች ከሃያ ብር ባልበለጠ ዋጋ ሁሉንም የማይክሮ ሶፍት ኦፊስ ፕሮግራሞች ማግኘት የቻልነውን ያህል በአሜሪካ እነዚህኑ ፕሮግራሞች ለማግኘት አንድ ሰው ሰባት ሲባዛ ሰላሳ አራት ዶላር ማለትም ሁለት መቶ ሰላሳ ስምንት ዶላር ወይም አራት ሽህ ሰባት መቶ ስልሳ ብር ገደማ ይከፍላል ማለት ነው። ማይክሮሶፍት ይህን ያህል ገንዘብ እኛን ክፈሉ ቢለን ለመክፈል የሚያስችል አቅም ስለሌለን ኮምፒውተር መጠቀማችን ይቀራል። አሊያም ደግሞ ያን መክፈል ከሚችሉ ሰዎች ላይ እንደ ኢንተርኔት ሁሉ ኮምፒውተርም በደቂቃ እየከፈልን መጠቀም እንጀምራለን ማለት ነው። ማይክሮሶፍት ለድሃ ሃገራት ምርቱን በነፃ እንዲጠቀሙ የፈቀደው በራሱ ተነሳሽነት እንጅ በማንም አስገዳጅነት አይደለም። ማይክሮ ሶፍት ይህን ለመረዳት የሚያስችል ሞራል ያገኘው ካፒታሊዝም የፈጠረው የካፒታሊስት ማህበረሰብ አስተሳሰብ ውጤት በመሆኑ ነው።

ፕሮ⦿ የካፒታሊዝም እድሜው ስንት ነው

ይህን ለመመለስ እስቲ በምናብ ወደ ኋላ ልውሰዳችሁና መነሻችንን የማደን ችሎታ የነበረውን ጥንታዊው ሰው እናድርግ። አዎ! የአደን መሳሪያ የመስራት ጥበብ ያልነበረውን የዋሻ ሰው በዓይነ ህሊናችሁ ተመልከቱት፡፡ የዋሻው ሰው ልክ እንደኛ በጉልበት፣ በፅናት፣ እና በችሎታ ወዘተ በተፈጥሮ የተለያየ ነው። የተሻለ ጉልበት ያለው ታዳኙን እንስሳ ለምሳሌ አጋዘን ከሌሎች ይበልጥ ያሯሩጣል። የመያዝ እድሉም ጉልበት ከሌላቸው ሰዎች ይሻላል። ጉልበት የሌላቸው ደግሞ አቅም በፈቀደ የሚችሉትን ያህል ጥረት በማድረግ በልተው ያድራሉ። በሂደትም ከሚታደኑት እንስሳ የቆዳ ልብስ በመስራት ብርድን ለመከላከል ጥረት ያደርጋሉ። ጉልበት ያለው ሰው አድኖ በልቶ የሚተርፈውን ስጋ በልዋጭ ለማግኘት ለእርሱ የቆዳ ልብስ ይሰጡታል። በምትኩ የሚበሉትን ስጋ ያገኛሉ። ከዚያ ደግሞ “ከድንጋይ የሚሻል የአደን መሳሪያ ለምን አንሰራም?” ብለው ያስባሉ። ለምሳሌ መጥረቢያ ሊሆን ይችላል። እዚህ ላይ በአደን ፋንታ መጥረቢያ ለመስራት ከወሰኑ በዚህ ላይ የሚያጠፉትን ጊዜ ‘ኦፖርቹኒቲ ኮስት’ ብለን እንጠራዋለን።

እነዚህ ሰዎች መጥረቢያ የሚሰሩት ጉልበት ካለው አዳኝ ጋር በስጋ ለመቀያየር ባላቸው ተነሳሽነት(ኢንሰንቲቭስ) ነው። ይህን በማድረጋቸው ደግሞ ጉልበት ላለው ሰው አደኑን ያቀሉለታል። እነርሱም በልዋጩ ሞያቸውን በመጠቀም በልተው ያድራሉ ማለት ነው። ይህም መጥረቢያ የሚሰሩትን ኢንተርፕርነሮች ይበልጥ ስለሚያበረታታ ዘወትር መጥረቢያ በመስራት፣ በማሻሻል እና በማዘመን የማህበረሰቡን የአደን ስራ ያቀሉለታል። በዚህም ምክንያት የማህበረሰቡ አባላት ይበልጥ ብቃት ያለው የአደን መሳሪያ ስለሚጠቀሙ በርካታ ሚዳቆ፣ ሰስ፣ እና አጋዘን ወዘተ ማደን ያስችላቸዋል። በደንብ ጠግበው በልተው ማደርም ይጀምራሉ። መጥረቢያ በመስራታቸው ጥቅም ያገኙት ኢንተርፕርነሮች ይቀጥሉና “ለምን ጦር አንሰራም?” ይላሉ። ለጦር መስሪያ የሚውሉ ጥሬ እቃዎችን የሚያቀርቡ ኢንተርፕርነሮችም ይፈጠራሉ።እንዲህ እንዲህ እያለ እነሱም ሆነ የሚኖሩበት ማህበረሰብ ይበለፅጋል።

እንግዲህ ከላይ ባየነው ምሳሌ መሰረት የግለሰብ ነፃነት ለፈጠራ ስራ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ፣ የፈጠራው የባለቤትነት መብት መከበር ወሳኝ መሆኑን እና ሰላማዊ የልውውጥ ስርዓት(ገበያ) ከጥንት ጀምሮ ከሰው ልጅ ጋር የነበረ ተፈጥሯዊ መሆኑን ማየት እንችላለን። መህልቁን በነፃነት መጠበቅ፥ በንብረት ባለቤትነት መብት መከበር እና በሰላማዊ ግብይት ላይ የሚጥለው ስርዓት ደግሞ ካፒታሊዝም ብቻ ነው።

እነዚህን መጥረቢያ የሚሰሩ ኢንተርፕርነሮች ጉልበተኛ ነጣቂ ወይም መንግስት ስጋ ሳይሰጣቸው ወይም የድካማቸውን ዋጋ ሳይከፍል መጥረቢያቸውን በጉልበት የሚቀማቸው ከሆነ መጥረቢያ በመስራታቸው የሚያገኙት ጥቅም ስለሌለ ለመስራት የሚያነሳሳቸው ምክንያት (ኢንሰቲቭስ) አይኖርም። ስለዚህ መስራቱን ይተውታል። በዚህም ምክንያት ሁሉም ተያይዘው ወደ አድካሚው የህይዎት ውጣውረድ እና ኋላቀርነት ተመልሰው ይገባሉ። ሶሻሊዝም እና ተቀጽላ ብራንዶቹ ሁሉንም ሰው ደሃ የሚያደርጉት የሰዎችን የመስራት እና የመጣር ተነሳሽነት በተመሳሳይ መንገድ ስለሚያመክኑት ነው።

ካፒታዝሊም በአዳም ስሚዝ ዘ ዌልዝ ኦፍ ኔሽን ጋር የተወለደ ፍልስፍና ሳይሆን ከሰው ልጅ ጋር ከጥንት ጀምሮ አብሮ የኖረ ተፈጥሮአዊ ስርዓት ነው ማለት ይቻላል። ተፈጥሮአዊ ባይሆን ኖሮ በጠብ መንጃም ቢሆን ሶሻሊዝም ግማሽ በሚሆነው የዓለም ክፍል ቦታ ይዞ በቆየባቸው 72 ያህል ዓመታት ሊሞት የሚችል ፍልስፍና ነበር። እውነታው ግን ተቃራኒው ሆኖ ሶሻሊስቶቹን ጨምሮ የተቀረው ዓለም በዓይኑ ተመልክቷል።