አዳም ስሚዝ፣ ክላሲካል ኢኮኖሚክስ እና ካፒታሊዝም

ኣዳም ስሚዝየአዳም ስሚዝ ሃሳቦች የፈጠሩት የአስተሳሰብ ለውጥ እንግሊዝ በነገስታቷ እና ከነገስታቷ ጋር በተቆራኘችው ቤተክርስቲያን ላይ የሕግ ልጓም ታበጅ ዘንድ አስገድዷታል። የአዳም ስሚዝ የኢኮኖሚ ሞዴል እና አስተምህሮ የኢንዱስትሪ አቢዮትን ይቀጣጠል ዘንድ ትልቅ ድርሻ ነበረው። የፖለቲካ ነፃነት ትግልን አፋፍሟል። የእሱን መፅሃፍ ያነበቡት ዣን ባፕቲስት ሴይ እና ፍሬደሪክ ባስቲያ ሃሳቡ ለሃገራችን ይበጃል ብለው ስራዎቹን በፈረንሳይ አሰራጭተዋል። በአሜሪካ ደግሞ ከመስራቾቹ አንዱ እና ኋላም ፕሬዝዳንት የነበረው ቶማስ ጀፈርሰን የስኮትላንዳዊውን ሃሳብ “ለውጥ ከሳች እና ሃብት ፈጣሪ ነው።” በማለት እንዲስፋፋ አድርጓል። እነዚህን ሃሳቦችም እራሱ ባረቀቀው የአሜሪካ ሕገ-መንግስት ውስጥ አካቷቸዋል። ከነዚህ መሃል የአሜሪካ መሰረቶች ተብለው የሚታወቁት “ላይፍ፣ ሊበርቲ እና ዘ ፐርሱይት ኦፍ ሃፒነስ” የአሜሪካ ሕገ-መንግስት የማዕዘን ዲንጋይ ናቸው። አዳም ስሚዝ መፅሃፉን ባሳተመበት ዓመት ዓመት ሃምሌ አራት ቀን አስራ ሰባት ሰባ ስድስት ዓ/ም አሜሪካዊያን ከእንግሊዝ ጋር ያደረጉትን መራራ የነፃነት ትግል ድል አድርገው ነፃነታቸውን ያወጁበት ቀን ነበር። ጆርጅ ዋሽንግተን የአዲሲቷ ሃገር አሜሪካ አባት ሲባል አዳም ስሚዝም ወዲህ የአዲስ ሳይንስ አባት ተባለ። ቶማስ ጀፈርሰን የአዳም ስሚዝን የምጣኔ ሃብት አስተምህሮ የሃብት ሳይንስ (ዘ ሳይንስ ኦፍ ዌልዝ) ሲል ያልቆለጳጵሰው ነበር።

የአዳም ስሚዝ ሃሳቦችን የተገበሩት ሃገራት አጀብ ድንቅ በሚያሰኝ ሁኔታ የአዳዲስ ፈጠራዎች እና ቴክኖሎጅ ባለቤቶች መሆን ጀመሩ። ይህም ከቻይናዊያን እና ከአረቦች ኋላ ሲንቀረፈፉ የነበሩትን ምዕራባዊያንን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀድመው እንዲታዩ በሩን ከፈተላቸው። በእንፋሎት የሚሰራ ሞተር፣ አውቶማቲክ የጨርቅ መስሪያ ማሽን ፣ የመገጣጠሚያ ማሽኖት ፣ ሲምፎኒ ኦርኬስትራ፣ በእንፋሎት የሚሰራ የሕትመት ማሽን ፣ በዝቅተኛ ዋጋ ሊገኝ የሚችል ወረቀት፣ ብረትና መስታወት ፣ የመፃፍና የማንበብ ዕውቀት መስፋፋት፣ የዘመናዊ ዩኒቨርስቲ መስፋፋት … ወዘተርፈ።

በ1860ዓ/ም እንግሊዝ የዓለምን ንግድ ሃያ ሶስት በመቶ ያህል ብቻወን ታሾር ነበር። ሁለተኛዋ ፈረንሳይ ደግሞ አስራ አንድ በመቶ የዓለም ንግድን ስታጋብስ የነበር ሲሆን አሜሪካ ሶስተኛ ሆና ዘጠኝ በመቶውን ተቋድሳለች። በ1870 ዓ/ም እንግሊዝ በፋብሪካ ውጤቶች እና ምርት ሰላሳ አንድ ነጥብ ስምንት በመቶ የነበረ ሲሆን ሁለተኛ የነበረችው አሜሪካ ደግሞ ሃያ ሶስት ነጥብ ሶስት በመቶ፣ ጀርመን አስራ ሶስት ነጥብ ሁለት በመቶ እንዲሁም ፈረንሳይ አስር ነጥብ ሶስት በመቶ ድርሻ ነበራቸው። በአስራ ስምንት ሰማንያ ዓ/ም እንግሊዝ ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን ሸቀጦችን እና ምርቶችን ለዓለም ገበያ ያቀረበች ሲሆን በወቅቱ ተቀራራቢ ተፎካካሪዋ አሜሪካ ደግሞ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን ሸቀጥ ለገበያ አቅርባለች። ከእንግሊዝ ነፃ ከወጡ በኋላ የሚሲሲፒ ሸለቆን ምርታማ ያደረጉት፣ በትራስፖርት በኩል ሰፊዋን ሃገር በባቡር ሃዲድ ግንባታ ከዳር እዳር ያገናኙት፣ ዜጎች በሰላማዊ ኑሮአቸው በህግ አግባብ እና በፍቃዳቸው በሚያደርጉት ግንኙነት ውስጥ መንግስት ጣልቃ እንዳይገባ በሕግ ልጓም ያበጁለት፣ በዘመናዊ ጥበብ ባሸበረቁ ህንፃዎቿ እና ነፃነት ባላቸው ሰዎች በሚፈለፈሉ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ብዛት ለእንግሊዛዊያኑ ሳይቀር ትንግርት የሆኑት አሜሪካዊያን በሃያኛው ክ/ዘመን መግቢያ ላይ ሃያልነቱን ከእንግሊዝ ተረከቡ። እንግሊዛዊያን ለአዝማናት ረግጠው የገዟት ሃገር ከመቶ ዓመታት ባነሰ የነፃነት ጊዜ ውስጥ የዓለም ልዕለ ሃያል መሆኗ ማመን ቢያቅታቸውም የሚታይ የሚዳሰስ ሃቅ በመሆኑ ሊክዱት አልተቻላቸውም። ሃይልነቱን ተነጠቁ!

የአዳም ስሚዝን ክላሲካል የኢኮኖሚ ሞዴል ተግባር ላይ የዋሉ ሃገራት ሁሉ ለሁለት መቶ አመታት ያህል ከዚያ በፊት አይተውት በማያውቁት ተዓምራዊ የኢኮኖሚ እድገት ባለፀጋ ሆነዋል። በአንፃሩ የኢኮኖሚ ነፃነት፣ የገበያ ውድድር እና የግለሰብ ነፃነትን የሚጣረስ የኢኮኖሚ ስርዓት የሚተገብሩት ሃገራት ደግሞ የድሮውን ጥሩምባ እየነፉ ባሉበት እየረገጡ ይገኛሉ።

መፅሃፍአዳም ስሚዝ በዘመናዊ መንገድ የኢኮኖሚክስ ሳይንስን ለመጀመሪያ ጊዜ እኤአ መጋቢት ዘጠኝ ቀን 1776 ዓ/ም ‘አን ኢንኳየሪ ኢን ቱ ዘ ኔቸር ኤንድ ኮዝስ ኦፍ ዘ ዌልዝ ኦፍ ኔሽን’ በሚል ትልቅ መጽሃፍ አሰናድቶ እስካቀረበበት ጊዜ ድረስ ስለ ምጣኔ ሃብት የተፃፈ ዝርዝር መረጃ አልነበረም። ለዚህም ነው በስራዎቹ ከታዩት ከነብዙ ህጸጾቹ አዳም ስሚዝ የኢኮኖሚክስ ሳይንስ አባት የሚባለው። አዳም ስሚዝ ይህንኑ ስራውን ያቀረበው የሰው ልጅ ሲያደርግ የነበረውን የንግድ፣ የስራ፣ የአስተዳደር እና ማህበራዊ መስተጋብርን በደንብ ካጤነ በኋላ ነበር። አዳም ስሚዝ በሁሉም ስራዎቹ ላይ ካፒታሊዝም የሚል ቃል አንድም ቦታ ቢፈለግ አይገኝም። አዳም ስሚዝ በሁሉም ስራዎቹ ውስጥ ካፒታልን የሚገልጸው ‘ስቶክ’ እያለ ነው።

በርካታ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ፈላስፎች ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ያለተቀናቃኝ የዘለቀውን የአዳም ስሚዝ የክላሲካል ኢኮኖሚክስ ሞዴል በርካታ ጉድለቶች አሉበት በሚል ትችት እና ነቀፋ ሲያቀርቡበት ቢቆዩም እንደ ካርል ማርክስ ግን ትልቅ ፈተና የደቀነበት ሰው አልነበረም። ካርል ማርክስ ለአዳም ስሚዝ ስራዎች ምላሽ ይሆን ዘንድ ‘ዳስ ካፒታል’ የተባለውን መጽሃፍ በጀርመንኛ ቋንቋ ጽፎ አቀረበ። በፍሬደሪክ ኤንግልስ አማካይነት ለህትመት የበቃው ‘ዳስ ካፒታል’ ነባሩን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፍልስፍና ቢያንስ ለመቶ ያህል አመታት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የከተተ ነበር። ካርል ማርክስ በዳስ ካፒታል ከዚያ በፊት ያልነበሩ በርካታ ቃላትን የተጠቀመ ሲሆን ከነዚያ ቃላቶች ውስጥ አምርሮ የሚኮንነውን ካፒታሊዝም ሳይቀር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው እና ቃሉንም የፈጠረው እራሱ ነው። ይሁን እንጅ ካፒታሊዝም ከአዳም ስሚዝ “ዘ ዌልዝ ኦፍ ኔሽን”ጋር እንዳልተወለደው ሁሉ በካርል ማርክስ “ዳስ ካፒታል”ም ሊሞት አልቻለም።