አዳም ስሚዝ እና ክላሲካል ኢኮኖሚክስ 

አዳም ስሚዝ⦿ አዳም ስሚዝ–የኢኮኖሚክስ ሳይንስ አባት

እኤአ በአስራ ሰባት ሃያ ሶስት ዓ/ም ስኮትላንዳዊው የኢኮኖሚ ሳይንስ ጠበብት እና ፈላስፋ በኤደንበርግ አቅራቢያ በምትገኝ ኪርካልዲ በምትባል የምስራቅ ስኮትላንድ መንደር ውስጥ ተወለደ። በዘመናዊ የኢኮኖሚክስ ሳይንስ ውስጥ የሱን ያህል አሻራውን የተወ ሰው የለም። ይህ ሰው ባለስልጣናትን ተናግሮ ማሳመን ባለመቻሉ እነሱን ለማሳመን በማለት ተንትኖ እና አብራርቶ የፃፈው መፅሃፍ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ የኢኮኖሚክስ ሳይንስ መሰረት ሆኖ ዘልቋል። እኤአ በአስራ ሰባት ስልሳ አራት ዓ/ም ቻርለስ ታውንሴድ የተባለ የእንግሊዝ ፓርላማ አባል የእንጀራ ልጁን ፈረንሳይ ሄዶ የሚያስጠናለት ከሆነ የእድሜ ዘመኑን ሁሉ ክፍያ ሳያቋርጥ እንደሚጦረው ለአዳም ስሚዝ ይነግረዋል። ማስተማር እና መናገር የማይሆንለት የግላስጎ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር አዳም ስሚዝም ሳያቅማማ ወደ ፈረረንሳይ ተጓዘ። እዛም ብዙ ሳይቆይ ማስጠናት ያስጠላዋል። አዳም ስሚዝ በፈረንሳይ ከነ ቮልቴር፣ ቱርጎት እና ሌሎች የፈረንሳይ ዝነኛ ሰዎች ጋርም ተገናኘ። በዚህ ጊዜ ነበር አለኝ የሚለውን እና የእንግሊዝ ባለስልጣናትን ድሮ ተናግሮ ማሳመን ያልቻለውን አዲስ የኢኮኖሚ ንድፍ በፅሁፍ ለማሰናዳት በመወሰን ፅሁፉን የጀመረው። አዳም ስሚዝ የእንግሊዝ ባለስልጣናትን እና መኳንንትን ለማሳመን በማለት የፃፈው መፅሃፍ ‘አን ኢንኳየሪ ኢን ቱ ዘ ኔቸር ኤንድ ኮዝስ ኦፍ ዘ ዌልዝ ኦፍ ኔሽን’ በመባል ይታወቃል። መጋቢት ዘጠኝ ቀን አስራ ሰባት ሰባ ስድስት ዓ/ም ስትራህን እና ካዴል በሚባልና ለንደን የሚገኝ አሳታሚ ድርጅት ያሳተመው ይህ መፅሃፍ በአንድ ሽሕ ገፅ ብዛት የተዘጋጀ ሁለት ጥራዞች ነበር። ሁለቱ ጥራዞችም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የተፈጥሮአዊ አሰራር ቅንጅት፣ የሃገር እድገት መሰረቶችን እና የሰው ልጅ ያለውን ድርሻ በሚገባ አካተው የቀረቡ ስራዎች ናቸው። አዳም ስሚዝ ለዚህ ስራው ከአሳታሚው አምስት መቶ ፓውንድ ተከፍሎታል።

የአዳም ስሚዝን ጥራዞች ያነበበው የሃገሩ ልጅ እና ስመ ጥሩው ፈላስፋ ዴቪድ ሂውም “አስገራሚ ችሎታ፥ ድንቅ ተፈጥሮ፥ ምርጥ ስራ” ብሎ አወድሶለታል። ፈረንሳዊው ድንቅ የጥበብ ሰው ቮልቴርም “ሃገሬ ፈረንሳይ ከሱ ጋር የምታነፃፅረው ሰው የላትም!” በማለት አዳም ስሚዝን ከፍ አድርጎታል። አዳም ስሚዝ በጣም አስቀያሚ ስለነበር ሴቶች አይቀርቡትም ነበር። በዚያ ላይ ንግግሩ ሸካራ እና የማይጥም እንደነበር ይነገራል። በግንቦት ወር አስራ ሰባት ስልሳ ስድስት ዓ/ም አዳም ስሚዝን በፓሪስ ያገኘችው ፈረንሳዊቷ ደራሲ ማዳሜ ሪኮኒ “ዝንጉ ቢሆንም ተወዳጅ ነው።” ስትል ስለ አዳም ስሚዝ ተናግራለች።

አዳም ስሚዝ ከልጅነቱ ጀምሮ ብቻውን ማውራት የሚወድ፣ ማታ ማታ ብቻውን እያወራ ሳያውቀው ሌላ ከተማ ድረስ የሚጓዝ ሰው ነበር። በሶስት ዓመት እድሜው ጅፕሲዎች ሰርቀውት የነበረ ቢሆንም ከወራት ፍለጋ በኋላ አጎቱ አግኝቶት ወደ እናቱ ተመልሷል። የአዳም ስሚዝ አባት የሞተው እሱ የተወለደ ዕለት ነው። ባንድ ወቅት ጓደኛውን በቤቱ ጋብዞት በሻይ ኩባያ ቅቤ ሰፍሮ አቅርቦለታል። በሱ ቤት ሻይ መቅዳቱ ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ አንዲት ሴት በቤቱ ጋብዟት ከምግቡም ከወይኑንም ከተቋደሱ በኋላ ወደ ምኝታ ክፍል ይገባሉ። አጅሬ ወዲያውኑ ብቻውን እያወራ የመጓዝ አመሉ ትዝ ይለውና የሌት ልብሱን እንደለበሰ ውልቅ ይላል። ቆንጅት አልጋ ላይ ጋደም ብላ ካሁን አሁን ይመጣል ብላ ስጠብቅ አደረች። እሱ እንደሁ እረስቷት ከራሱ ጋር እያወራ ሲጓዝ ሌላ ከተማ ደርሶ ነጋበት። ብዙዎች ብዙ ዝንጉ ሰው ቢያውቁም በዚያ ዘመን ግን የአዳም ስሚዝን ያህል ዝንጉ ነበረ ማለት ያስቸግራል። የአዳም ስሚዝ የክላሲካል ኢኮኖሚክስ ሞዴል መሰረቶች የሚከተሉት ናቸው።

አንደኛ ❒ ነፃነት (ግለሰቦች፣ኢንተርፕርነሮች፣ነጋዴዎች እና ሰራተኞች በፈቃዳቸው ምርት፣ሸቀጥ፣ ገንዘብ እና ጉልበታቸውን የሚለዋወጡበት ስርዓት)፣

ሁለተኛ ❒ የገበያ ውድድር (ግለሰቦች፣ ኢንተርፕርነሮች፣ ነጋዴዎች እና ሰራተኞች በፈቃዳቸው አንዱን ካንዱ እያማረጡ የወደዱትን እየገዙ እና ያልፈለጉትን እየተው፣የምርቱን ዋጋ እና ጥራት በማወዳደር የሚገበዩበት እና የሚለዋወጡበት ስርዓት)፣

ሶስተኛ ❒ ፍትህ (ግለሰቦች፣ኢንተርፕርነሮች፣ነጋዴዎች እና ሰራተኞች በፈቃዳቸው ምርት፣ሸቀጥ፣ ገንዘብ እና ጉልበታቸውን በሚለዋወጡበት ወቅት አጭበርባሪዎችን፣ ነጣቂዎችን፣ ከሃዲዎችን የሚቀጣ እና የህግ የበላይነትን የሚያስጠብቅ ስርዓት) እጅግ አስፈላጊ ናቸው ይላል። ለነዚህ መሳካት ሲባል መንግስት እጁን ኢኮኖሚው ውስጥ ማስገባት እንደሌለበትም ይመክራል። መንግስት እጁን የሚያስገባ ከሆነ እንደ ግለሰቦች እና ነጋዴዎች ለጥቅም መሯሯጥ ይጀምራል። በዚህ ምክንያትም ዜጎች ይበደላሉ፤ ፍትህም ይጓደላል በማለት ያስረዳል።

የአዳም ስሚዝ ሃሳቦች የፈጠሩት የአስተሳሰብ ለውጥ እንግሊዝ በነገስታቷ እና ከነገስታቷ ጋር በተቆራኘችው ቤተክርስቲያን ላይ የሕግ ልጓም ታበጅ ዘንድ አስገድዷታል። የአዳም ስሚዝ የኢኮኖሚ ሞዴል እና አስተምህሮ የኢንዱስትሪ አቢዮትን ይቀጣጠል ዘንድ ትልቅ ድርሻ ነበረው። የፖለቲካ ነፃነት ትግልን አፋፍሟል። የእሱን መፅሃፍ ያነበቡት ዣን ባፕቲስት ሴይ እና ፍሬደሪክ ባስቲያ ሃሳቡ ለሃገራችን ይበጃል ብለው ስራዎቹን በፈረንሳይ አሰራጭተዋል። በአሜሪካ ደግሞ ከመስራቾቹ አንዱ እና ኋላም ፕሬዝዳንት የነበረው ቶማስ ጀፈርሰን የስኮትላንዳዊውን ሃሳብ “ለውጥ ከሳች እና ሃብት ፈጣሪ ነው።” በማለት እንዲስፋፋ አድርጓል። እነዚህን ሃሳቦችም እራሱ ባረቀቀው የአሜሪካ ሕገ-መንግስት ውስጥ አካቷቸዋል። ከነዚህ መሃል የአሜሪካ መሰረቶች ተብለው የሚታወቁት “ላይፍ፣ ሊበርቲ እና ዘ ፐርሱይት ኦፍ ሃፒነስ” የአሜሪካ ሕገ-መንግስት የማዕዘን ዲንጋይ ናቸው። አዳም ስሚዝ መፅሃፉን ባሳተመበት ዓመት ዓመት ሃምሌ አራት ቀን አስራ ሰባት ሰባ ስድስት ዓ/ም አሜሪካዊያን ከእንግሊዝ ጋር ያደረጉትን መራራ የነፃነት ትግል ድል አድርገው ነፃነታቸውን ያወጁበት ቀን ነበር። ጆርጅ ዋሽንግተን የአዲሲቷ ሃገር አሜሪካ አባት ሲባል አዳም ስሚዝም ወዲህ የአዲስ ሳይንስ አባት ተባለ። ቶማስ ጀፈርሰን የአዳም ስሚዝን የምጣኔ ሃብት አስተምህሮ የሃብት ሳይንስ (ዘ ሳይንስ ኦፍ ዌልዝ) ሲል ያልቆለጳጵሰው ነበር።