ፔጌዳ – አዲሱ ናዚ በጀርመን!

ኮምኒዝም ወደ ሶሻሊዝም የሚወስድ ጽንፈኛ የሞት መንገድ ነው። የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት መገባደድ ተከትሎ ሶሻሊስታዊ ብሄርተኝነትን ስታራምድ የቆየችው እና ድፍን አውሮፓን አሳሯን ስታሳያት የቆየችው ጀርመን ለ41 ዓመታት ያህል ለሁለት ተከፍላ ቆይታለች። እነዚያ ሁለት ሃገራት ምስራቅ እና ምዕራብ ጀርመን በመባል ይታወቃሉ። በሁለቱ ጀርመኖች የተዘራው ዘር ሁለት ዓይነት ነበር። የምስራቁን ዛሬ የሌለችው የያኔዋ የምስራቁ ዓለም ‘ሱፐር ፓወር’ ሶቬት ህብረት ኮምኒዝምን ዘርታ ተንከባክባ አሳደገችበት። ምዕራቡን ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ተረክበው የሰው ስርዓት ዘሩበት። የሰው ስርዓት የተዘራበትን አገር አገሬው እራሱ ይበጀኛል ብሎ ስለሚንከባከበው ስርዓቱ ቶሎ ስር ሰዶ ያብባል። የዛሬ 25ዓመት የበርሊን ግምብ ሲፈርስ የታየው ይሄው ነው። ሰው የዘራውን ያጭዳል እንደሚባለው ኮምኒዝምን የዘሩት ፍሬዎቹን ማለትም ውርደትን፣ድህነትን፣ተስፋ ማጣትን፣ ሰው የመሆንን ትርጉም ሁሉ እስከማጣት ደረሱ። ድሮ ሃገራቸው የነበረውን የምዕራቡን ግዛት ልክ ዛሬ ሶሪያውያን እና የሌሎች ሃገር ዜጎች ወደ ጀርመን በገባን ብለው እንደሚመኙት የምስራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ምዕራብ ጀርመን ለመግባት በየቀኑ የአረመኔ ኮምኒስቶች ጥይት ሰለባ ይሆኑ ነበር።
ሶሻሊዝም ያለ ጭካኔ እና ኢሞራላዊነት የሚቆም ስርዓት አይደለም። ጀርመን በሶሻሊዝም ስርዓት ያሳለፈችውን ዓመታት “የጀርመን ጥቁር ዓመታት! በጀርመን የሰይጣኖች መነሳት!” በሚል ይገልጹታል።የት እና እንዴት ባለ ቦታ ላይ እንደሚገልጹት ሳሳያችሁ ጀርመን በሶሻሊዝም ምን ያህል እንደምታፍር ታያላችሁ። ጀርመናውያን ሶሻሊስቶች ከስህተታቸው ታርመው ቢያንስ የሚመጣው አዲስ ትውልድ ሶሻሊዝም ማለት 11ምን ማለት እንደሆን እንዲረዳ በግልጽ ምልክት አስቀምጠዋል። ዛሬም ድረስ “ሶሻሊዝም ወይም ሞት” ለሚሉ የኔ አገር ሰዎች ተመልሸ አሳያቸዋለሁ። በጥላቻ የተጋረደ ዓይምሮ በምክንያት እንደማያምን ግን ሁሌም እረዳለሁ። ስለዚህ ያን የማደርገው አቋማቸውን ይፈትሻሉ ብየ ሳልሆን የሶሻሊዝምን ክፋት ለመሸፋፈን ሲውተረተሩ እና ሌላውን ለማደናገር ሲሞክሩ በማየቴ ነው።በነገራችን ላይ ሶሻሊዝም ወረቀት ላይ እጹብ ድንቅ የሆነ ፍልስፍና ነው። በወረቀቱ ላይ ከሰፈሩት ጥሩ እና በጎ ምኞቶች ውስጥ ግን አንዱም ያለ ግዴታ እና ጠብ መንጃ የሚተገበር አይደለም።

Screen Shot 2015-10-21 at 21.52.22ሶሻሊዝም ከዚህም አልፎ የማህበረሰብን የምግባር እና የሞራል ደረጃ ያዘቅጣል። ሃይማኖታዊ አስተምሮህዎች ጋር የሚጋጭ ብቻ ሳይሆን ለሃይማኖትም እውቅና የሚሰጥ ስርዓት አይደለም። ፈጣሪ የማይወደው የሚመስለን እና ህሊናችን የማይቀበለው ድርጊቶች በሶሻሊዝም የተሞገሱ እና እንዲደረጉ የሚመከሩ ናቸው። ስደተኛን ንብረቱን መቀማት እና ማባረር ካርል ማርክስ የሶሻሊዝም ማስፈጸሚያ ብሎ ከዘረዘራቸው አስር ህግጋት ውስጥ አንዱ ነው። ዝርዝሩን የሶሻሊዝም አስርቱ ቃላት በሚል ቀደም ብየ የጻፍኩትን ሊያነቡ ይችላሉ። በጀርመን አሁን ስደተኞች ላይ የሚደረገው ጥላቻ እና ጥቃት 99በመቶ በቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን ግዛቶች ውስጥ የሚደረጉ ናቸው።ፔጌዳ ሰኞ ዕለት በቀድሞዋ የምስራቅ ጀርመን ግዛት ድሬስደን ውስጥ ባደረገው የዘረኝንነት ሰልፍ ላይ በመሪው አማካይነት “የጀርመን መንግስት ከመካከለኛው ምስራቅ የሚፈልሱ እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ለሆኑ ስደተኞች መጠለያ የሚሰጥ ከሆነ እኛ እራሳችን መፍትሄ አለን። ጀርመንን ከወራሪዎች እንታደጋለን።  በመጨረሻም እናሸንፋለን።” በማለት ለጀርመን መንግስት ማስጠንቀቂያ አዘል መልክቱን አስተላልፏል። ሰልፉ ወዲያውኑ በጀርመናዊያን ተቃውሞ ቢገጥመውም ስጋቱ ግን እያየለ ዘረኝነቱም በግልጽ እየተዛመተ መሆኑ ይታያል።

የፔጊዳ ማለትም ‘ፓትሪኦቲክ ዩሮፒያንስ አጌንስት ዘ ኢስላሚፊኬሽን ኦፍ ዘ ዌስት’ የጀርመን መንግስት ስደተኞችን እንዳይቀበል ከፍተኛ የጥላቻ እና የዘረኝነት ዘመቻ እያካሄደ ሲሆን በተለያዩ የጀርመን ከተሞችም በተለይም ከመካከለኛው ምስራቅ የመጡ ስደተኞች የሚገኙበትን መጠለያ ጣቢያዎችን ከማቃጠል ጀሞሮ አባላቱ እስካሁን ከ200በላይ ጥቃቶችን በስደተኞች ላይ ፈጽመዋል።ባለፈው ወር የሰድተኞችን ካምፕ ለማቃጠል ሶስት ቀንና ለሊት ከፖሊስ ጋር የተፋጠጠው ፔጌዳ ውጥኑን ያሰበውን ያህል ማሳካት ስላልቻለ 33 ፖሊሶችን አቁስሏል።የጀርመን መንግስት በተደጋጋሚ ለእንዲህ ያለ ዘረኝንነት ትግስት የለኝም ሲል ቢደመጥም ፔጌዳ ግን ጥቃቱን ከስደተኞች ጋር አብረው በሚሰሩ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ጭምር መፈጸም ጀምሯል።

ከሶስት ቀን በፊት ቅዳሜ ዕለት ደግሞ አንድ የ44ዓመት ዘረኛ ኮምኒስት እና የፔጌዳ አባል ህዝቡ ስደተኞችን እንዲቀበል በመቀስቀስ የታወቃች እና በምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ የነበረች የጀርመን ፖለቲከኛ በቢላዋ አርዷታል። ሰውየው ይህን በሚያደርግብበት ወቅት “ይሄን የማደርገው ለልጆሽ  ብየ ነው።” እያለ ይጮህ እንደነበር የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል። ኮሎኝ በጀርመን ተቻችሎ መኖር እና መረዳዳት ይታይባቸዋል ከሚባሉ ከተሞች አንድኛው ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ ከተማዋ 10ሽህ የሶሪያ ስደተኞችን ተቀብላለች። የ58 ዓመቷ ሄነሪት ሬከር ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እነዚህን ስደተኞች በማስተባበር እና ቦታ እንዲያገኙ ስትሯሯጥ የቆየች ሃላፊ ነበረች።

የታረደችው ሴት-ሄነሪት ሬከር ምስል በምርጫ ፖስተር  ላይ

የታረደችው ሴት-ሄነሪት ሬከር ምስል በምርጫ ፖስተር ላይ

ሴትየዋ በማግስቱ እሁድ በተደረገው ምርጫ 52 በመቶ ምርጫውን በማሸነፍ በጀርመን በትልቅነቷ 4ኛ የሆነችው የኮሎኝ ከተማ የመጀመሪያዋ ሴት ከንቲባ በመሆን ተመርጣለች። ሄነሪት ሬከር ግን በአሁኑ ሰዓት በኮሎኝ ሆስፒታል ራሷን ስታ በአርቲፊሻል መንገድ ትንፋሽ/ኦክስጅን እንድታገኝ እየተደረገ ነው። ዶክተሮች በቅርቡ እንደምታገግም አስታውቀዋል።

ፔጌዳ ለወትሮውም ዘረኝነት ካልጠፋበት በቀድሞዋ የኮምኒስት ምስራቅ ጀርመን ግዛቶች ውስጥ ስር እየሰደደ ሲሆን ስደተኞች ላይ የሚዘራው ጥላቻም ወደ ምዕራብ ጀርመን በመዛመት የአንጌላ ሜርክልን ጥምር መንግስት  እየተፈታተነ ነው። የህዝብ ድጋፍ እየከዳቸው መሆኑን የተመለከተው የአንጌላ መርክል ክርስቲያን ዴሞክራቲክ ዩኒየን ፓርቲም አቋማቸውን እንደማይደግፍ እና የፓርቲው ፖሊሲ ጋር እንደሚጋጭ በይፋ ተናግሯል። ጥምሩ የባቫሪያን ክርስቲያን ሶሻል ዩኒየንም ቻንስለሯ አቋማቸውን እንዲቀይሩ አሳስቧል። ዛሬ የጀርመን የንግድ ተቋማት እና ግዙፍ ኩባንያዎች ሃላፊዎች ለቻንስለሯ ባስተላለፉት መልክት “ጀርመን በዓመት ከአምስት መቶ ሽህ በላይ ስደተኞችን የመቀበል አቅም የላትም።የስደተኛው ቁጥር ብዛት ስደተኞችን ለመርዳት የምናደርገው ጥረት ሊደናቀፍ ይችላል። ቻንስለሯ በጎ ምኞታቸው መሬት ያለውን እውነታ መመርኮዝ አለበት። ይህ ካልሆነ ለጀርመን አደጋ እየጋበዙ ነው።”በማለት አቋማቸውን እንዲቀይሩ አሳስበዋል።  የጀርመን መንግስት እስካሁን የህዝብ ቁጣ በመፍራት በሚስጥር ቢይዘውም በዚህ ዓመት ብቻ  1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች ወደ ሃገሪቱ  ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።ከዚህ በተጨማሪ ስደተኞችን ለመርዳት በጀርመን ግብር ከፋዮች ላይ መጠነኛ የግብር ጭማሪ ይደረግ የሚለው ሃሳብ በጀርመናዊያን ፈጽሞ ተቀባይነት ያላገኘ  መንግስት ያን የሚያደርግበት የሕግ መሰረትም እንደሌለው ታውቋል።

በ2015ዓ/ም የመጀመሪያው ስድስት ወራት ከቀረቡት 170ሽህ ማመልከቻቸዎች ውስጥ 42ሽህ ያክሉን የጥገኝነት ማመልከቻቸው ውድቅ ቢደረግም እስካሁን ከጀርመን የተባረሩት ግን 8200ሰዎች ብቻ ናቸው። የዚህ ምክንያቱ የሰዎቹ ማንነታቸውን የሚገልጸውን ዶክመንቶች በማጥፋታቸው ሲሆን እነዚህኑ ወረቀቶች ለመተካት ከሃገሮቻቸው ጋር የሚደረገው ድርድር  አጥጋቢ ምላሽ አልተገኘም። ያም ሆኖ የናይጀሪያ እና የግብጽ መንግስታት በመጨረሻ ላይ ለዜጎቻቸው ምትክ ዶክመንት ለጀርመን መንግስት በመስጠታቸው በቅርቡ ይመለሳሉ ተብሏል። የአፍጋኒስታን እና የፓኪስታን መንግስታት ግን ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የስሜን አፍሪካ መንግስታትም እስካሁን ፈቃደኛ አልሆኑም።

አንጌላ መርክል ከራሷ ፓርቲ አመራሮች እና ባለስልጣናት እስከ ደህንነት ቢሮ እና መከላከያ እንዲሁም የትላልቅ ኢንዱስትሪዎች እና ቢዝነሶች ከህዝቡ ጋር በመሆን የሚያደርጉትን ግፊት ለማርገብ በማለት የጥገኝነት ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞችን ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ በአፋጣኝ ወደ ሃገሮቻቸው መመለስ መጀመሩን አስታውቋል። ከኦስትሪያ ጋር ድንበር የሚጋራው ሃብታሙ የደቡባዊ ጀርመን ባቫሪያ ግዛት ግን እስካሁን ወደ መጡበት ያባረራቸው ስደተኞች ቁጥር ጠቅላላ ጀርመን ካባረረቻቸው ይበልጣል። ባቫሪያ ባለፈው ወር የጀርመን መንግስት ስደተኞችን መግታት ካልቻለ ግዛቱን እራሱ እንደሚጠብቅ ማስታወቁ ይታወቃል። በጀርመን ያለውን የደተኞች ሕግም ባለፈው ሳምንት በጣም ጥብቅ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን በአዲሱ ሕግ ማንኛውም ስደተኛ ከጀርመን ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ እና ልማድ ጋር በፍጥነት መዋህድ ይኖርበታል። ጀርመንኛ ቋንቋ መማርም ይጠበቅበታል።