የሃገራት ብልፅግና እና ፖለቲካል ኢኮኖሚ  

(By Kidus Mehalu)

ባንዲራ⦿ ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ 

ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ አንድ ዓይነት ባሕል እና ቋንቋ የነበራቸው አንድ ህዝብ ነበሩ። ሁለቱ ሃገራት ተለያይተው የቀሩት የተባበሩት መንግስታት ኮሪያን በቅኝ ግዛት ይዛ የነበረችውን ጃፓን በጦርነት ለማስለቀቅ በተደረገ ጦርነት ነበር። በአስራ ዘጠኝ አምሳ ሶስት ዓ/ም የኮሪያ ጦርነት በጃፓን ሽንፈት ሲጠናቀቅ በደቡብ በኩል አሜሪካ በሰሜን በኩል ደግሞ የቀድሞዋ ሶቬት ህብረት ሃገሪቱን ለሁለት ቆረጧት።

ኮሪያዎች በሚለያዩበት ወቅት በሁለቱም ስፍራ የነበረው የህዝብ ቁጥር ተቀራራቢ ነበር። እነዚህ አንድ ዓይነት ባህል፣ ቋንቋ እና ልማድ የነበራቸው ህዝቦች ከዚያን ቀን ጀምሮ በሚከተሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት ተለያዩ። ደቡብ ኮሪያ የአሜሪካን ካፒታሊዝም ስትመርጥ ሰሜን ኮሪያ ደግሞ የሶቬትን ሶሻሊዝም መንገዷ አደረገች።

ዛሬ የሚታየው የሁለቱ ሃገራት ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ይራራቃል። በሁለት ሽህ አስራ አራት ዓ/ም በወጣው የሄሪቴጅ ፋውንዴሽን የኢኮኖሚ ነፃነት የሚዳስስ ሪፖርት ላይየደቡብኮሪያ ዜጎችአማካኝአመታዊገቢከሰላሳሁለትሽህየአሜሪካዶላርበላይ ሲሆን በዓለምም አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ናት። የጎረቤት ሰሜን ኮሪያ ዜጎች በሁለት ሽህ አስራ አንድ ዓ/ም አንድ ሽህ ስምንት መቶ የአሜሪካ ዶላር ያህል ገቢ እንደነበራቸው ሲአይኤ በድረ ገፁ ላይ ያሰፈረ ሲሆን ከዚያ ወዲህ የወጣ ግን ምንም ተጨባጭ መረጃ የለም። በሁለት ሽህ አስራ አራት ዓ/ም የተባበሩት መንግስታት ባወጣው ሪፖርት የሰሜን ኮሪያዊያን ድህነት ‘ከድህነት ወለል በታች’ የሚለው ቃል አይገልጸውም። የሰሜን ኮሪያ ዜጎች አይጥ፣ ውሻ እና ተመሳሳይ አውሬዎች ሳይቀር ቅንጦት ሆነውባቸዋል።

⦿ ቻይና እና ሆንግ ኮንግ
ከአስራ ዘጠኝ ዘጠና ሁለት ዓ/ም በፊት በዋናዋ የቻይና ምድር እና በሆንግ ኮንግ መካከል የነበረው ልዩነት የሰማይና ምድር ያህል ይራራቃል። አሁንም እነዚህ አንድ አይነት ሕዝብ እና አንድ ዓይነት ባሕል የነበራቸው እንደነበሩ መዘንጋት የለብንም። በሰሜን ኮሪያ እና በምስራቅ ጀርመን የታየው የኢኮኖሚ ቀውስ በቻይናም ነበር። ከአስራ ዘጠኝ ዘጠና ሁለት ዓ/ም ጀምሮ ባደረገችው እጅግ ሥር ነቀል የሆነ የነፃ ገበያ ስርዓት ግንባታ ቻይና ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት ችላለች። በቻይና የሚተገበረው ኮምዩኒዝም ግን የግለሰብ ነፃነት አይሰጥም። የካፒታሊዝም ስርዓት ዋና ማጠንጠኛው የግለሰብ ነፃነት መሆኑን ልብ ይሏል። ይህም የኢኮኖሚ ነፃነት ዋነኛ ግብዓት ሲሆን ከፖለቲካ ነፃነት ጋርም የተቆራኘ ነው፡፡ በቻይና የመሰብሰብ ነፃነት ብሎ ነገር የለም። የመምረጥ ነፃነት ቀርቶ ምርጫ ሚባል ነገርም የለም። የኮምዩኒስት ፓርቲው የቻይናን ፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ ከቻይናዊያን እጅ ቀምቷል። የግለሰቦች ነጻነት ስፋት የፈጠረው ልዩነት በሆንግ ኮንግ እና በቻይና ዜጎች ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ መሃል የሃያ አምስት ሽህ ዶላር ልዩነት ሊፈጥር ችሏል። የቻይናዊያን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ ዘጠኝ ሽህ ዶላር ይጠጋል። ሶሻሊዝም እና ሌሎች መጠሪያ ብራንዶቹ ኮምኒዝምም ሆነ ልማታዊ መንግስት የሚባሉት ለቡድን እንጅ ቡድኑን ለሚፈጥሩት ግለሰቦች እውቅናና ነጻነት አይሰጡም።

⦿ ምዕራብ ጀርመን እና ምስራቅ ጀርመን 

በኮሪያ ጦርነት ወቅት ኮሪያ ሁለት እንደሆነችው ሁሉ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ጀርመን ሽንፈት ሲገባደድ ጀርመንም ለሁለት ተከፈለች። ምዕራቡን አሜሪካ እና ሶቬት ህብረት ጀርመንን ለሁለት ተካፈሏት። ምዕራቡ የአሜሪካ ካፒታሊዝም ሲሳይ ሲደርሳት ምስራቅ ጀርመን ደግሞ የሶቬት ሶሻሊዝም ሰለባ መሆኗ ግድ ሆነ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለሁለት ከመከፈላቸው በፊት የምስራቅ እና የምዕራብ ጀርመን ሰዎች አንድ ዓይነት ባህል፣ወግ እና ልማድ የነበራቸው አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ሕዝብ ነበሩ።

ለአርባ ዓመታት ያህል የሶሻሊዝም የጡት አባት በነበረችው ሶቬት ህብረት ታንኮች ታጥረው ኮምኒዝም እንደ ዓይጥ የተሞከረባቸው የምስራቅ ጀርመን ነዋሪዎች የባርነት፣ የድህነት እና የውርደት ኑሮ በቃን አሉ። ህዳር ዘጠኝ ቀን አስራ ዘጠኝ ሰማንያ ዘጠኝ ዓ/ም በርሊን የዓለምን ታሪክ የቀየረ አመጽ ለማስተናገድ ተገደደች። ይህ አመፅ ተከትሎ በሶቬት ህብረት የተገነባውና ለሃያ ስምንት ዓመታት ያህል በርሊንን ለሁለት የከፈላት የበርሊን ግምብ ፈረሰ።

የበርሊን ግምብ ከመፍረሱ በፊት ምዕራብ ጀርመን ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ የነበራት ሃገር ስትሆን ምስራቅ ጀርመን ደግሞ በተመሳሳይ ወቅት አሰቃቂ የኢኮኖሚ ቀጠና ነበረች። ጀርመን ለሁለት ከተከፈለች ከ41ዓመታት በኋላ የበርሊን ግምብ ከፈረሰ ከአንድ ዓመት በኋላ ጥቅምት ሶስት ቀን አስራ ዘጠኝ ዘጠና ዓ/ም በኦፊሴል ተዋህዳ እንደዱሮው አንድ ትልቅ ሃገር ሆናለች። ዛሬ የጀርመናዊያን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ አርባ ሽህ የአሜሪካ ዶላር ገደማ ነው።

የበርሊን ግምብ መፍረሱን ተከትሎ በሶቬት ህብረት አነሳሽነት የተቋቋሙት የምስራቁ ዓለም ግዙፍ ተቋማት መንገዳገድ ጀመሩ። ሰኔ ሃያ ስምንት ቀን አስራ ዘጠኝ ዘጠና አንድ ዓ/ም ‘ኮምኮን’ ፈረሰ። ሌላኛው ግዙፍ የኮምኒስቱ ዓለም ተቋም የነበረው የዋርሶው ፓክት ደግሞ ከሶስት ቀናት በኋላ ሃምሌ አንድ ቀን አስራ ዘጠኝ ዘጠና አንድ ዓ/ ም ግብዓተ መሬቱ ተፈፀመ። በዚሁ ዓመት ከአስራ ዘጠኝ አስራ ሰባት ዓ/ም ጀምሮ ሶሻሊዝምን ያሳደገችው እና በታንኳቿ ጠብቃ ያቆየችው እና በመላው ዓለም ያዳረሰችው ትልቋ ሶቬት ህብረት ፈራረሰችና ከታሪክ መድረክ ላይ ወረደች።

⦿ ቬንዙዌላ እና ቺሊ ቺሌ

የደቡብ አሜሪካዊቷ ቦሊቫሪያን ሪፐብሊክ ቬንዙዌላ እንደ ቺሊ የተፈጥሮ ሃብት ችግር የለባትም። ሃገሪቱ በቀን ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ ታመርታለች። ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉን ለዓለም ገበያ ስታቀርስብ ከተቀረው ግማሽ ላይ ሲሶ ያህሉን ከቻይና የተበደረችውን ገንዘብ ለመክፈል ወደ ቤይጅንግ ትልካለች። በየቀኑ ስድስት መቶ ሺ በርሚል ነዳጅ ለሃገሪቱ የነዳጅ ፍላጎት ጥቅም ላይ ሲውል መቶ ሺ ነዳጅ በርሚል ደግሞ በየቀኑ ወደ ኩባ ትልካለች። የተቀረው በአካባቢው ለሚገኙ የደቡብ አሜሪካ ሃገራት ይቸበቸባል።

ቬንዙዌላ ሶስት መቶ ቢሊዮን በርሚል ያህል የነዳጅ ዘይት ክምችት እንዳላት የተረጋገጠ ቢሆንም ሌላዋ የደቡብ አሜሪካ ሃገር ቺሊ ደግሞ ከመዳብ በቀር ይህ ነው የሚባል የተፈጥሮ ሃብት የላትም። በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ መጀመሪያ ላይ በቺሊ የነበረውን ሶሾሳሊስታዊ አሰራሮች ተከትሎ የቺሊያዊያን ሕይወት ተናጋ። የቺሊ ዜጎች ኑሮ በድህነት እና በርሃብ ተመሳቀለ። ይህ ቀረሽ የማይባለው የዋጋ ቁጥጥር ከፍተኛ የሆነ የምርት አቅርቦት ችግር እንዲከሰት ምክንያት ሆነ። ቅጣም ባሩ የጠፋበት ግሽበት የችሊያዊያንን ህልውና ተፈታተነ። ይህን ተከትሎ በመስከርም ወር አስራ ዘጠኝ ሰባ ሶስት ዓ/ም የኮምኒስቱ ሳልቫዶር አሌንዴ መንግስት በጄነራል ኦግስቶ ፒኖቼ በሚመሩ ወታደሮች ተገለበጠ።

ጄነራል ፒኖቼ ስልጣን እንደያዘ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ቺካጎ የሚገኙ ቺሊያዊያን ስመ- ጥር ኢኮኖሚስቶች ቺሊን ከገባችበት አዘቅት እንዲታደጉዋት ጥሪ አቀረበላቸው። ቺካጎ ቦይስ በመባል የሚታወቁት ኢኮኖሚስቶች ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ወደዚያው አመሩ። ቺካጎ ቦይስ ለቺሊ ይበጃል የተባለውን መፍትሄ አቀረቡ። እነሱም፡-

✲ መንግስትበከፍተኛሁኔታወጭዎቹንእንዲቀንስ፣

✲ የግብርስርዓትማሻሻያእንዲደረግእናሁሉምየግብርተመንዝቅእንዲደረግ፣

✲ መንግስት እንዳሻው ገንዘብ እያተመ እንዳያጋሽብ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት አሰራር እንዲዘረጋ ፣

✲ መንግስት ከኢኮኖሚው ውስጥ እጁን እንዲያወጣ እና የመንግስት የሆኑ ተቋማትን ለግለሰብ ነጋዴዎች እንዲሸጥ የሚሉ ነበሩ።

የቺሊመንግስትይህን ተግባራዊማድረግከጀመረበኋላየነበረውግሽበትበከፍተኛ ሁኔታ ከመቀነሱም በላይ ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ ሃገሪቱ ተአምራዊ የኢኮኖሚ እድገት አስመዘገበች። በሁለት ሽህ አስራ አራት ዓ/ም ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን ባወጣው የኢኮኖሚ ነፃነት ሪፖርት ቺሊ ከደቡብ አሜሪካ ሃገራት አንደኛ ስትሆን በሪፖርቱ ከተካተቱ መቶ ሰባ ሁለት ሃገራት ውስጥም የአስረኛ ደረጃን ይዛለች። የዜጎቿ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢም ከአስራ ስምንት ሽህ አራት መቶ ዶላር በላይ ሆኖል። በኢኮኖሚ ነፃነቷ የሚያህላት ሃገር የለም። አስራ ሰባት ሚሊዮን ህዝብ ያላት ቺሊ ዜጎቿ ከደቡብ አሜሪካ የተሻለ የኢኮኖሚ እና የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በአንፃሩ በዓለም ላይ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ሃብት ካላቸው ሃገራት አንዷ የሆነችው ቬንዙዌላ ጤናማ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓት እጦት መንገዳገድ ይዛለች። የዜጎቿም ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል። የተፈጥሮ ሃብቷ ከሃያ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ከሆነው ህዝቧ ውስጥ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩትን ሃያ ስምንት በመቶ ቬንዙዌላዊያን ሊታደጋቸው አልቻለም። የ“ዲሞክራሲያዊ ሶሻሊዝም” እንጅ “የሶሻሊዝም ስርዓት አራማጅ አይደለሁም።”ሲል በተደጋጋሚ የሚደመጠው የቬንዙዌላ መንግስት “ቬንዙዌላን የላቲን አሜሪካ ገነት አደርጋለሁ!” ብሎ ከፎከረ አመታት ተቆጥረዋል። በርግጥ ቆይቶም ቢሆን ይህ የሶሻሊስቶች መፈክር ለቬንዙዌላዊያን የምድር ሲዖል መግቢያ ትኬት ሆኖባቸዋል።

ከአስራ ዘጠኝ ዘጠና ዘጠኝ ዓ/ም እስከ ሁለት ሽህ አስራ ሁለት ዓ/ም ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ ብቻ የቬንዙዌላ መንግስት የባለሃብቶችን ንብረት ከመውረስ አንስቶ በገበያው ላይ በሚያደርገው ጣልቃ ገብነት፣ አምራቾች መንግስት የሚፈልገውን ምርት እንዲያመርቱ የሚገደዱበት ቁጥጥር መስፋት፣ መንግስት በሸቀጦች ላይ የሚጥለው የዋጋ ተመን እንዲሁም የገንዘብን ዋጋ ዝቅ ማድረግ ጨምሮ እያተመ ወደ ኢኮኖሚው የሚያስገባው የገንዘብ ፍሰት መጨመር የቬንዙዌላን ኢኮኖሚ በአምስት መቶ ፐርሰንት እንዲጋሽብ አድርጓል። የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ሁጎ ቻቬዝ ሞት ተከትሎ በሚያዚያ ወር ሁለት ሽህ አስራ ሶስት ዓ/ም ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሰዎችን ሃብት በመውረስ እና ሃብታም ያሏቸውን ሰዎች ንብረት በመቀማት ተጠምደው ቢኖሩም ውጤት የከፋ ችግር አስከትሏል። እስካሁን ድረስ ቬንዙዌላ ውስጥ ሶስት መቶ ሃምሳ ሰባት ሽሕ የንግድ እና የቢዝነስ ተቋማት ስራቸውን ለማቆም የተገደዱ ሲሆን በዚህ ምክንያት አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሽሕ የሃገሪቱ ዜጎች ስራ አጥ ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪም ‘ዴሞክራሲያዊ’ ሶሻሊስቱ የቬንዙዌላ መንግስት መቶ ሃምሳ ሽሕ የንግድ እና የቢዝነስ ተቋማትን ወርሷል።

መንግስት በገበያ ላይ የሚፈፅመው ከፍተኛ የሆነ ጣልቃ ገብነት ነጋዴዎች የንግድ ፍቃዳቸውን እንዲመልሱ ስላስገደዳቸው በሃገሪቱ የተከሰተው የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች እጥረት እጅግ ተባብሶ ቀጥሏል። የመሰረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ማለትም ስኳር፣ ጨው፣ ቅቤ፣ የልጆች ወተት፣ ዱቄት፣ ቡና ወዘተ በቬንዙዌላ ምድር ቅንጦት ሆነዋል። መንግስት ያወጣው የዋጋ ተመን የነበረውን የምርት እጥረት እና የአቅርቦት ችግር እጅግ በማባባሱ ምክንያት የመፀዳጃ ቤት ወረቀት እና የገላ ሳሙና ጭምር ከገበያ ላይ እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል።ይህን ተከትሎ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በሃፍረት ያሸማቀቀ መግለጫ የሰጡ የቬንዙዌላ ሶሻሊስቶች ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ቱሪስቶች እና የሆቴል እንግዶች የመፀዳጃ ቤት ወረቀት እና የገላ ሳሙና መያዝ እንዳይዘነጉ አሳስበዋል።

ኒኮላስ ማዱሮ በሚያዚያ ወር ሁለት ሽህ አስራ ሶስት ዓ/ም ስልጣን በያዙበት ወቅት አንድ የአሜሪካን ዶላር በስምንት የቬንዙዌላ ብር(ቦሊቫር ፉርቴ) ሲመነዘር የነበረ ቢሆንም በየካቲት ወር ሁለት ሽህ አስራ አምስት ዓ/ም በጥቁር ገበያ ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር መቶ ዘጠና ሁለት ቦሊቫር ፉርቴ(የቬንዙዌላ ብር) ሲመነዘር ተስተውሏል። በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የምንዛሬው መጠን ሁለት መቶ ሰባ ዘጠኝ ቦሊቫር ፉርቴ ደርሷል። በነሃሴ ወር መጀመሪያ ላይ ግን አንዱ የአሜሪካ ዶላር አራት መቶ ሃያ ሶስት ቦሊቫር ፉርቴ ተመንዝሯል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እየጋሸበ የመጣው የቬንዙዌላ ገንዘብ ተፈላጊነቱ እየቀነሰ በመሄዱ ቬንዙዌላዊያን ድሮ ገንዘብ ከመፈጠሩ በፊት ወደ ነበረው ዓይነት የእቃን በቃ ግብይት(ባርተር ንግድ) እየገቡ ነው። ኢኮኖሚዋ ሙሉ ለሙሉ በሚያስችል ሁኔታ ወደ ጥቁር ገበያነት እየተቀየረ በሄደችው ቬንዙዌላ ገበያዎች ላይ ለመገበያየት አሁን እቃ ወይም ዶላር መያዝ ግድ እየሆነ ነው።

የኢኮኖሚ ውጥንቅጥ መባባስ፣ ስር የሰደደ ማህበራዊ ምስቅልቅል እና በተምኔታዊው ሶሻሊዝም የተዋጀው ፖለቲካ ቬንዙዌላ ካለባት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ብድር እና ከዓለም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሽቆልቆል ጋር ተደማምሮ በሃገሪቱ ችጋር፣ ፍርሃትና እና ተስፋ ቢስነት ነግሷል። ቬንዙዌላ በላቲን አሜሪካ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ነፃነት ካለባቸው ሃገራት ቀንደኛዋ ስትሆን የሄሪቴጅ ፋውንዴሽን በሁለት ሽህ አስራ አራት ባወጣው የኢኮኖሚ ነፃነት ሪፖርት ላይም ከመቶ ሰባ ስምንት ሃገራት የመቶ ሰባ አምስተኛ ደረጃን ይዛለች። የሃገሪቱ ዜጎች አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከአስራ ሶስት ሽህ ዶላር በላይ ቢሆንም ጣራ ከነካው የገንዘብ ግሽበት እና የዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ የቬንዙዌላዊያን ችግርም ጣራ ነክቷል።

የፕላኔታችን እጅግ በጣም አደገኛ ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ ከሚባሉ አገሮች ውስጥ አንዷ በሆነችው ቬንዙዌላ በሁለት ሽህ አስራ አራት ዓ/ም ብቻ ሃያ አራት ሽህ ሰባት መቶ ያህል ሰዎች በወንበዴዎች ተገድለዋል። ይህም በዓመቱ ከተመዘገበው ጠቅላላ የሞት ቁጥር አስራ ሁለት በመቶ የሚሸፍን ሲሆን ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በቬንዙዌላ በየሃያ አንድ ደቂቃው አንድ ሰው ይገደላል። የሙስና ጥበብ ‘ፐርፌክት’ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሰባት፣ የሕግየበላይነትየጨነገፈባትእና ስርዓትአልባነትየነገሰባትቬንዙዌላበሃያአንደኛው ክ/ዘመን ሶሻሊዝም ሰውኛ ስርዓት አለመሆኑን እና አይቀሬ ውድቀቱን በማሳየት ላይ ያለች ህያው ምሳሌ ሆናለች። ቬንዙዌላ እና መንግስቷ የሶሻሊዝም ስርዓት የመጨረሻው የውድቀት አፋፍ ላይ ቆመው እያጣጣሩ ነው።

ኢትዮጵያ በውሃ ሃብቷ ከአፍሪካ አንደኛ ብትሆንም አንዴ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ’ ሌላ ጊዜ ‘ልማታዊ መንግስት’ በሌላ ወቅት ደግሞ ‘ልማታዊ ዴሞክራሲ መንግስት’ ነኝ የሚለው የኢትዮጵያ መንግስት “የዴሞክራሲያዊ ሶሻሊዝም እንጅ የሶሻሊዝም’ ስርዓት አራማጅ አይደለሁም።” ሲል ከኖረው ግን ከስም ባለፈ የሶሻሊስታዊ ፖሊሲዎችን ውጤት መቀየርም ሆነ ማስቀረት ካልቻለው የቬንዙዌላ መንግስት ውድቀት መማር ይኖርበታል። የኢትዮጵያ መንግስትም የስርዓት ስም ከመቀያየር ባለፈ ተግባራዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ነፃነትን ማስፋት እና የኢኮኖሚ ነፃነት መሰረቶችን ማክበር ካልቻለ ከፉከራ ባለፈ ኢትዮጵያዊያንን ከውሃ ጥም መታደግ እንደማይችል ከብዥታ በላይ ጥርት ብሎ ይታያል። የመንግስት ፖሊሲ ነጸብራቅ የሆኑ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ምስቅልቅሎች የሚቀየሩት ዜጎች በራሳቸው ፈቃድ የሚንቀሳቀሱበት እና በሕግ የበላይነት የሚዳኝ ነጻ የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ሲቻል ብቻ ነው።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.