የሶሻሊዝም አስርቱ ቃላት እና የ’ሆሞ ማርክሲስት’ ጅማሬ!

እራሱን የሰራተኛው መደብ (የላባደሩ) ቻርለስ ዳርዊን ወይም ፈጣሪ አድርጎ የሚያየው ካርል ማርክስ እኤአ በአስራ ስምንት ስልሳ ሰባት ዓ/ም በጀርመንኛ ቋንቋ ያሳተመውን ዳስ ካፒታል የተባለ መጽሃፉን የሰራተኛው መደብ ‘መጽሃፍ ቅዱስ’ እያለ ያንቆለጳጵሰው ነበር። የዳስ ካፒታል የእንግሊዝኛ ቅጅ ካፒታል በመባል ይታወቃል። ካርል ማርክስ ያለ ደም አፋሳሽ አመጽ ተምኔታዊ ፍልስፍናው ሊሳካ እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቃል። ይህም ይሳካ ዘንድ ዘ ኮምዩኒስት ማኒፌስቶ ላይ አስር የአፈጻጸም መመሪያዎችን ለተከታዮቹ ጽፏል። መመሪያዎቹ ዛሬ ድረስ በአምባገነን መንግስታት ጥቅም ላይ ሲውሉ እና ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቃት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።

ሶሻሊ ፊት

ዘ ኮምኒስት ማኒፌስቶ ላይ የተዘረዘሩት የማርክሲዝም ሶሻሊስታዊ አቢዮት ማስፈፀሚያ አስሩ መመሪያዎች የሚከተሉት ናቸው።

አንደኛ ❒ የንብረት ባለቤትነት መብት የሚባል ነገር እንዳይኖር ማድረግ እና መሬት ሁሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆን ማድረግ፣

ሁለተኛ ❒ ከፍተኛ የሆነ የገቢ ግብር በሰራተኛው ላይ መጫን፣

ሶስተኛ ❒ የውርስ መብት የሚባል እንዳይኖር ማድረግ፣

አራተኛ ❒ የተቃዋሚዎችን እና የስደተኛ/የመጤ ሰዎችን ንብረት መንጠቅ፣

አምስተኛ ❒ የባንክ ብድር እና ገንዘብ አቅርቦቱን ለማን፣ መቼ እና የት እንደሚደርስ በብሄራዊ ባንክ አማካይነት የማእከላዊ ዕዝ ቁጥጥር አካል እንዲሆን ማድረግ፣

ስድስተኛ ❒ የትራንስፖርት እና የመገናኛ ብዙሃን ከአብዮታዊው ሶሻሊስቱ ቡድን እጅ እንዳይወጣ በማእከላዊ ዕዝ ቁጥጥር ስር እንዲሆን፣

ሰባተኛ ❒የመንግስትፋብሪካዎችእናወታደራዊኢንዱስትሪዎችንማስፋፋት፣

ስምንተኛ ❒ ለግብርና የሚያገለግሉ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማምረት ይቻል ዘንድ ሁሉም ሰው ላይ የስራ ግዴታ መጣል፣

ዘጠነኛ ❒ የግብርናእናአምራችኢንዱስትሪዎችንማቀናጀት፣በከተማእናበገጠር መካከል ያለውን ልዩነት ቀስ በቀስ ተመጣጣኝ ቁጥር ያለው ህዝብ እንዲሰፍር በማድረግ ማጥፋት፣ እና

አስረኛ ❒ በመንግስትትምህርትቤቶችህጻናትበነጻእንዲማሩእናበማርክሲዝም ሶሻሊስታዊ መመሪያ ተኮትኩተው እንዲያድጉ በማድረግ ለጉልበት ብዝበዛ የሚዳርገውን ነባሩን የቤተሰብ አወቃቀር ስርዓት ማጥፋት የሚሉት ናቸው።

ማርክስ የሰራተኛውን የበላይነት (አምባገነንነት) በአሰሪው ላይ በመጫን እና የግለሰቦችን ንብረት በመንጠቅ የመደብ ትግልን እና ባርነትን ማጥፋት ይገባል ብሎ ያምናል። በዳስ ካፒታል ላይም ገንዘብ መጥፋት ያለበት ነገር መሆኑን ፅፏል። አብዮታዊ ሶሻሊዝም ገነትን በምድር እንደሚገነባ ከዚያ በኋላም የሰው ልጅ ኑሮ በተድላ እና በሃሴት የተሞላ እንደሚሆን ካርል ማርክስ አትቷል። የሰራተኛው/የላባደሩ የበላይነት እና ህብረት ወደ መደብ አልባ እና ዓለም ዓቀፋዊ ማህበረሰብ ይሸጋገራል። የዚህ ማህበረሰብ አዲስ ሰው ጅማሬም ‘ሆሞ ማርክሲስት’[ሆሞ ሳፒያንስ እንደሚባለው መሆኑ ነው ] ይባላል በማለት ካርል ማርክስ ተምኔቱን አስፍሯል።

የማርክሲዝም መፈክሮች፣ ዓርማዎቹ፣ ቀያይ ማስታወቂያወቹ፣ ሰማዕታቱ፣ ደቀመዛሙርቶቹ እና መዝሙሩ ጭምር በብዙዎች ዘንድ እንደ ሃይማኖት ሲቆጠሩ ኖረዋል። ብዙዎች የሰው ልጅን ከበዝባዥ እና ከጨቋኝ ስርዓት ማውጣት ይቻለዋል ያሉትን የማርክስን ሶሻሊስታዊ አብዮት ከዳር እዳር አቀጣጥለዋል። በመላው ዓለም በዝባዥ እና ጨቋኝ የተባሉ ብዙ ዘውዳዊ ስርዓቶች ደም አፋሳሽ በሆነ አብዮት ተወግደው ማርክሲዝም ቦታ ይዞ ቆይቷል። ይሄው ፍልስፍና በሃገራችንም ከዳር ዳር ተራግቦ ዘውዳዊውን ስርዓት በመገርሰስ ደርግን ወልዷል።

የካርል ማርክስ አስተምህሮች ሙሉ ለሙሉ ተምኔታዊ በመሆናቸው ምክንያት አንድም እንኳ ቲወሪው ስኬታማ ሊሆን አልቻለም። የሶሻሊዝም ስርዓት የተተገበረባቸው ሃገራት ሁሉ በታሪካቸው አይተው የማያውቁት ዓይነት ቸነፈር፣ ስደት፣ ተስፋ መቁረጥና እልቂትን አይተዋል። ሶሻሊዝም ማርክስ እንደተረከልን ያሳየን ገነትን ሳይሆን የምድር ሲዖልን ነበር። የፀሃይ ብርሃን ተክሎች የፎቶሴንተሲስ ስርዓት ያከናውኑ ዘንድ አስፈላጊ የሆነውን ያህል ሶሻሊዝም እና ቅጥያ ብራንዶቹን ተግባራዊ ለማድረግ ዜጎችን ማሸበር፣ ማዋርድ፣ ንብረታቸውን መቀማት፣ማሸማቀቅ፣ ለስደት መዳረግ፣ ተስፋ ማሳጣት እና መግደል የስርዓቱ እስትንፋስ ናቸው።