⦿ ሶሻሊዝም፣ ሽብር እና አክራሪነት 

ሶሻሊዝም ለሰው ልጅ እንደ ግለሰብ እውቅና የማይሰጥ፣ የንብረት ባለቤትነት መብትን የሚከለክል፣ የሰዎችን የልፋት እና የድካም ፍሬ በጉልበት የሚነጥቅ ኢ-ፍትሃዊ እና ኢ- ሞራላዊ ስርዓት ነው። ሶሻሊዝም የሰዎችን ነፃነት በመገደብ እና መህልቁን ዕጣ ፈንታቸውን በመቆጣጠር ላይ የሚጥል በውሸት የሰለጠነ አዋራጅ ስርዓት ነው። ሶሻሊዝም እና ቅጥያ ብራንዶቹ ከስማቸው እና አካሄዳቸው መለያየት በቀር ሳይሰሩ ነፃ ማግኘትን፣ የሚሰሩ ሰዎችን መቀማት እና ማሸማቀቅን ጨምሮ ጥገኝነትን የሚያበረታቱ ናቸው። የስርዓቱ ፖሊሲዎች የግለሰቦችን የፈጠራ ተነሳሽነት እና ሐብት የማፍራት ተስፋን ያጨልማሉ። በሶሻሊዝም እና በተቀጥያ ብራንዶቹ ስር የሚኖር ህዝብ ሁልጊዜ መዋጮ የሚጠየቅ ሲሆን ይኸው መዋጮ የሚሰበሰበውም በግለሰቦች ውዴታ ሳይሆን በመንግስት አስገዳጅነት ነው። የዚህ ዓይነት መዋጮ ትክክለኛ ስም ንጥቂያ ይባላል።

የሶሻሊዝም ስርዓት ዋና መገለጫው የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሚዲያ ፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት ነጻነት እጦት እና የሕግ ስርዓት አልባነት ናቸው። ከኢኮኖሚው አንፃር ያየን እንደሁ ሶሻሊዝም እና ብራንዶቹ ኢኮኖሚን በብቸኝነት እንዲሁም ገበያን ያለተወዳዳሪ በመቆጣጠር የሚተገበሩ ሲሆን የሚመሩትም በሕግ የበላይነት ሳይሆን በገዥ ፓርቲ ፍላጎት ነው። ሶሻሊዝም በሰዎች ሕይዎት፣ ነፃነት እና ንብረት መብት ንጥቂያ ላይ የሚቆም የሽብር፣ የሰቆቃ፣ የድህነት፣ የውርደት፣ የባርነት እና የስደት ምንጭ የሆነ ስርዓት ነው።

የሃያኛው ክ/ዘመን አሰቃቂ፣ ደም አፋሳሽ እና አውዳሚ የነበረው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተከሰተው ሶሻሊዝም በወለደው ሌሎችን የመናቅ እና የጥላቻ ብሄርተኝነት እንደነበር የማይታበል ሃቅ ነው። ሶሻሊዝም የጦረኝነት እና የጀብደኝነት አይዲዮሎጅ ነው። በዓለም ዙሪያ በመካሄድ ላይ ያሉት እና ሃይማኖትን እንደ ሽፋን የሚጠቀሙት የሽብርተኝነት እና የፅንፈኝነት ንቅናቄዎች መዳረሻ ግብ ከሶሻሊዝም ግብ ጋር ልዩነቱ ውጫዊ ልባሱ ወይም ሽፋኑ ብቻ ነው። የሽብር እና አክራሪነት ንቅናቄዎች ‘ሶሻሊዝም’ በሚለው ስም ምትክ ሃይማኖትን መጠቀሚያ ለማድረግ ከመሞከራቸው ባለፈ ዋነኛ መዳረሻ ግባቸው እንደ ሶሻሊዝም ሁሉ የሰው ልጅን ተፈጥሮአዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች በመበጣጠስ እንደ እንስሳ አንድ አይነት እና ወጥ በማድረግ ‘እኩል’ ማድረግ ነው። በኔ እምነት በዓለም ላይ አሁን በመካሄድ ላይ ላሉ የሽብርተኝነት ንቅናቄዎች ምንጩ ሶሻሊዝም እና ከፍልስፍናው የሚመነጨው አስተሳሰብ እንጅ ሃይማኖት አይደለም።

የሽብር ቡድኖች እና የአክራሪነት ንቅናቄዎች ልክ እንደ ሶሻሊዝም ሁሉ ያለ ሰዎች ፍላጎትና ፍቃድ በግድ የሚተገበሩ ናቸው። ስለዚህም የእንዲህ ዓይነት የሽብር ቡድን አባላት እና ተከታዮቻቸው በምክንያት እና አመክንዮ ሊያምኑ የሚችሉ ሰዎች እንዲሆኑ አይጠበቅም። አይደሉምም! ይህ ደግሞ ሰዎቹን ይበልጥ ጨካኝ እና ፍፁም አረመኔ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ለሰው ልጆች ሁሉ የተሻለ ነገር ለማምጣት እየታገልን ነው ብለው ስለሚያስቡም በሚፈፅሙት ዘግናኝ ግድያዎች ሁሉ አይፀፀቱም።

ሌኒን ዘ ኮምዩኒስት ማኒፌስቶ የተባለውን የካርል ማርክስ ስራ አንስቶ መሬት ላይ ለመተግበር ባይሞክር እና ባያራግበው ኑሮ ካርል ማርክስ ባልታወቀ ነበር። ግን ያ አልሆነም። ሌኒን ተምኔታዊ የሆነውን ሶሻሊዝም ለመተግበር በመጀመሪያ በቁም ቅዠት መስከር እና ቀጥሎም አውሬአዊ ባህሪ መላበስ ነበረበት። ሌኒን እንደ አይሲስ ያሉ የሽብር ቡድኖች እና የአክራሪነት ንቅናቄዎች ከሚያደርጉት ዘግናኝ፣ ኢ-ሞራላዊ፣ ኢ- ምክንያታዊ እና ኢ-ሃይማኖታዊ ግድያ እጅግ በሚያስከነዳ መልኩ ብዙ ሚሊዮኖችን ፈጅቷል። የሰው ልጆችን በቁማቸው ቆዳቸው እየተገፈፈ የብረት ማቅለጫ እቶን እሳት ውስጥ እንዲነከሩ አድርጓል። ማኦ ሌላኛውን የሶሻሊዝም ብራንድ ኮምዩኒዝምን ለመተግበር በተከተለው አውሬአዊ መንገድ ከሃምሳ ሚሊዮን በላይ ቻይናዊያን በጠኔ እንዲያልቁ አድርጓል። በካምቦዲያ ይህንኑ ተምኔታዊ ፍልስፍና ለመተግበር ሲባል ግማሽ ያህል የሃገሪቱ ህዝብ በርሃብና በጥይት አልቋል። የሽብር ቡድኖች እና የአክራሪነት ንቅናቄዎችም እንደ ሶሻሊዝም ሁሉ ዕውን ሊሆን የማይችል ፍልስፍናቸውን ለማሳካት ጉልበት ይጠቀማሉ። ዓላማቸውን ለመቀበል የሚያመነታውን እና አብሯቸው ለመጓዝ የማይፈልገውን ሰው ክርስቲያንም ሆነ እስላም ወይም የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ወይም ጭራሹኑ ሃይማኖት የሌለው ሁሉንም ይገድላሉ። እነዚህ ቡድኖች ሆን ብለው ዘግናኝ ግድያ የሚፈፅሙ ሲሆን ይህን የሚያደርጉትም ሌሎች በፍርሃት ርደው የቁም ቅዠታቸው ተካፋይ እና የተምኔታዊ ፍልስፍናቸው ተከታይ ይሆናል ብለው ስለሚያምኑ ነው።

በሶሻሊዝም አይዲዮሎጅ የተማረኩ፣ ፍቅር የወደቁ እና የሞቱለትም ጭምር እንደነበሩ ሁሉ በሽብር ቡድኖች እና የአክራሪነት ንቅናቄዎች ፍቅር የተማረኩ እና የሚሞቱም ብዙዎች ይኖራሉ። የሶሻሊዝም ቀይ ማዕበል ግማሽ የሚሆነውን የዓለም ክፍል በመቶ ሃምሳ ሚሊዮን የንፁሃን ደም አጨቅይቷል። ሶሻሊስቶቹ በከናቲራዎቻቸው ላይ የቼ-ጉቬራን ፎቶ ከማንጠልጠል ውጭ ከሶሻሊዝም ያተረፉት ምንም ነገር አልነበረም። እንደ አይሲስ ያሉ የሽብር ቡድኖች እና የአክራሪነት ንቅናቄዎችም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሰውን አንገት እንደ ሽንኩርት መከታተፋቸው ሲያከትም ምናልባት ደጋፊዎቻቸው የጂሃዲ ጆንን ወይም የአል ባግዳዲን ፎቶ በከናቲራዎቻቸው ላይ ሲያንጠለጥሉ ከማየት ውጭ ምንም የሚያተርፉት ነገር አይኖርም።