አሌክሳንደር ሩስቶ እና ኒዎ-ሊበራሊዝም

book(By Kidus Mehalu) ⦿ አሌክሳንደር ሩስቶ እና ኒዎ-ሊበራሊዝም 

የሶሻሊስቶች መፈንጫ የነበረው የዕውቁ የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ምሁራን የዓለምን ኢኮኖሚ ያተራመሰው መቅሰፍት መንስዔው የአሜሪካ መንግስት በኢኮኖሚው ላይ እጁን አለቅጥ መክተቱ እና የተንሸዋረረ ሶሻሊስታዊ ፖሊሲ መከተሉ መሆኑን በማስታወቅ በአንድ ጊዜ ግልብጥ ብለው ከሶሻሊዝም ጎራ መነጠላቸውን አሳወቁ። የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ሶሻሊስት ምሁራን በበኩላቸው “የዓለምን ኢኮኖሚ ያናጋው የአሜሪካ ካፒታሊዝም ነው።” ብለው ታቃውሟቸውን አሰሙ። የላይኛወቹ ‘ዘ ያንግ ቱርክስ’ እና ‘የካምብሪጅ ሰርከስ’ በመባል የሚታወቁት ሶሻሊስቶች በለንደን ታይምስ ላይ ለኢኮኖሚው የእንግሊዝ ምሁራን ሃሳባቸውን እንዲህ በነፃነት ሲያስተጋቡ በጀርመን ደግሞ ሶሻሊስታዊ ብሄርተኝነት ያሰከራቸው ዘረኞች(ናዚዎች) “መኖር የሚፈልግ ሁሉ መዋጋት አለበት። በያዝነው ዘላለማዊ ትግል ውስጥ አሻራውን የማያሳርፍ ሁሉ የመኖር መብት የለውም። ከዚህ በተጨማሪ አናሳ ቁጥር ያላቸው የሰው ልጆች ወይም ንፁህ ዘር የሌላቸው ሰዎች ወይም ክልሶች ሁሉ መጥፋት አለባቸው።” የሚለውን ሰይጣናዊ መመሪያቸውን ይፋ ያደረጉበት ወቅት ነበር። ስለዚህ ለሃገራቸው መፍትሄ ፍለጋ የተነሱ የጀርመን ምሁራን በነፃነት የሚወያዩበት እና ሃሳብ የሚለዋወጡበት መንገድ አልነበረም።

የጀርመን ምሁራን ለኢኮኖሚ ምስቅልቅል ዳርጎናል ያሉትን ‘ሊበራሊዝም’ በሌላ አዲስ ሥርዓት መተካት እንዳለበት እና ሃገራቸው አዲስ አቅጣጫ መከተል እንዳለባት ስላመኑ ውስጥ ውስጡን በድብቅ እየተገናኙ ለወቅቱ የኢኮኖሚ ምስቅልቅል መፍትሄ ያፈላልጉ ነበር። የዚህ ምክክር ቡድን አባል የነበረውና ኢኮኖሚክስ፣ ፊዚክስ፣ ሳይኮሎጅ እና ፍልስፍና በማጥናት በአስራ ዘጠኝ ዜሮ ስምንት ከኤርላንገን ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪውን ያገኘው አሌክሳንደር ሩስቶ በ1932ዓ/ም የጀርመን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ንግግር እንዲያደርግ ተጋበዘ። ሩስቶ በማህበሩ ፕሬዝዳንት ወርነር ሶምባርት ተጋብዞ “ነፃ ኢኮኖሚ፤ጠንካራ መንግስት” በሚል ርዕስ ያቀረበው ንግግር እስከ ዛሬ ድረስ የኒዎ-ሊበራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ አስኳል ተደርጎ ይቆጠራል። ይህንን ንግግሩን ተከትሎ አሌክሳንደር ሩስቶ እና ጓደኞቹ ጌስታፖ በተባለው የናዚ ነጭ ለባሽ ቡድን የክትትል መረብ ስር ወደቁ።

በ1933 ዓ/ም ቤቱ በጌስታፖ የተበረበረው ሩስቶ ለሕይዎቱ በመስጋት ወደ ቱርክ ሲሰደድ ጥቂት ጓደኞቹ ደግሞ ስዊዘርላንድ የመግባት እድል አገኙ። ይህን ማድረግ ያልቻሉት ደግሞ በዚያው በጀርመን ድምፃቸውን አጥፍተው በየቤተክርስቲያኑ እየተሰበሰቡ ለሃገራቸው የሚበጅ መፍትሄ ፍለጋ ሃሳብ መለዋወጥ ቀጠሉ። አሌክሳንደር ሩስቶ በቱርክ ሳለ ከሌላ ሃገራት ሊቃውንቶች ጋር እየተገናኘ ለዓለም የሚበጅ አዲስ ስርዓት ፍለጋውን አላቆመም።

አሌክሳንደር ሩስቶ በነሃሴ ወር 1938ዓ/ም ‘ሊበራሊዝምን ከወደቀበት እናንሳው’ በሚል ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሉዊስ ሮጀር በፓሪስ ባዘጋጀውና ‘የዋልተር ሊፕማን የፓሪስ ውይይት’ በመባል የሚታወቀው መድረክ ላይ እንዲሳተፉ ከተመረጡት ሃያ አምስት ሰዎችም አንዱ ነበር። ፈረንሳዊው ፈላስፋ ራይሞንድ አሮን፣ አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዋልተር ሊፕማን፣ ኦስትሪያዊው የፖለቲካ ጠበብት እና ፈላስፋ ኋላም የኖቤል ተሸላሚ የሆነው ፍሬደሪክ ሄይክ፣ ኦስትሪያዊው የፍሬደሪክ ሄይክ መምህር እና የሃያኛው ክ/ዘመን የምጣኔ ሃብት ሊቀ ሊቃውንት ሉድዊግ ቮን ሜስስ፣ የሃንጋሪ ተወላጅ የሆነው እንግሊዛዊው ፈላስፋ ሚካኤል ፓላኒ፣ እና ጀርመናዊያው ኢኮኖሚስት ዊልሄልም ሮፕኬ በውይይቱ ላይ እንዲታደሙ ከተጋበዙት ሰዎች መሃል ይገኙበታል።

“ሊበራሊዝምን ከወደቀበት እናንሳው” በሚል ዓላማ የተዘጋጀው የፓሪሱ ስብሰባ እንደተጀመረ አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዋልተር ሊፕማን በወቅቱ ለነበረው የኢኮኖሚ ምስቅልቅል እና የፖለቲካ ውጥንቅጥ ‘ተጠያቂ ነው’ ያለውን ሊበራሊዝም “ሰውኛ ባህሪ ካልተላበሰው ሶሻሊዝም ለይቼ አላየው።” በማለት አፅንኦት ሰጥቶ ተናግሯል። ጀርመናዊው አሌክሳንደር ሩስቶ በበኩሉ “የሞተ ነገር እንዴት ይነሳል? ሊበራሊዝም አብቅቶለታል።” በማለት ሊበራሊዝም የወደቀበትን የስነ ልቦና፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ርዕዮት ዓለማዊ ምክንያቶችን በመዘርዘር ዲስኩር አሰማ። አሌክሳንደር ሩስቶው ሊበራሊዝም መንግስት በኢኮኖሚው ላይ በሚያደርገው ጣልቃ ገብነት እና ይሄው መንግስት መጀመሪያውኑ ጣልቃ እየገባ ከመስመር እንዲወጣ ያደረገውን ኢኮኖሚ ለማስተካከል ሲሞክር በሚፈጥራቸው ተጨማሪ ስህተቶች መውደቁን ካተተ በኋላ ለሊበራሊዝም እንደ አማራጭ ሲቀርቡ የነበሩትን ሶሻሊዝም እና ኮምኒዝምን “ከዴሞክራሲ፣ ከነጻነት እና ከሰው ልጆች ጋር የማይሄዱ የኢኮኖሚ ስርዓት ቅርፅ እና ይዘት የሌላቸው ደመነፍሳዊ መንገዶች” ብሎ በመወረፍ ለዓለም ይበጃል ያለውን አዲስ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓት ይፋ አደረገ።

የአዲሱን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጽንሰ-ሃሳብ ስምም ኒዎ-ሊበራሊዝም ብሎ ሰየመው። በነገራችን ላይ ካርል ማርክስ ‘ካፒታሊዝም’ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተጠቀመው እና ቃሉንም እንደፈጠረው ሁሉ ኒዎ-ሊበራሊዝም የሚለውን ቃልም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው እና ቃሉንም የፈጠረው ዶ/ር አሌክሳንደር ሩስቶ ነው። የኒዎ-ሊበራሊዝም ፅንሰ ሃሳብ ዋና ዋና አስተምህሮዎች እና መርሆዎች የሚባሉትም የሚከተሉት ናቸው።

✲ መንግስት በመጠኑ ጣልቃ የሚገባበት ነጻ የገበያ ስርዓት ያስፈልጋል። ምክንያቱም የገበያ ሃይል እንደ ፖለቲካ ሃይል መጥፎ ስለሆነ መንግስት የገበያን መጥፎ ውጤት ለማስቀረት ጣልቃ መግባት ይኖርበታል። ለዚህም ሲባል በመንግስት የሚቋቋም ገበያን የሚጠብቅ እና የሚቆጣጠር ፖሊስ (ማርኬት ፖሊስ) አስፈላጊ ነው። የፖሊሶቹ ስራም አላስፈላጊ የገበያ ውድድርን እና የገበያ ህግን ማስከበር ይሆናል።

✲ የገበያ ውድድርን ውጤታማ እና ተመጣጣኝ ለማድረግ ሲባል በጋዜጣ፣ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ወዘተ የማስታወቂያ አገልግሎት መፈቀድ የለበትም። ምክንያቱም ማስታወቂያ ማሰራት የሚችሉት ትልልቆቹ የንግድ ተቋማት ብቻ ስለሚሆኑ ትንንሾቹ ይጎዳሉ።

✲ የፓተንት መብት ባለቤት የሆኑ ትላልቅ ኩባንያዎችን በማስገደድ ለትናንሾቹ ተወዳዳሪዎቻቸው ‘ላይሰንስ’ ማለትም ተመሳሳይ ዓይነት ምርት እንዲሰሩ የሚያስችል ፍቃድ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው።

✲ መንግስት ለሰራተኞች የሚያወጣው ዝቅተኛ የደሞዝ ጣራ (ሚኒመም ዌጂ) ተገቢ አይደለም። እንደዚያ ከማድረግ መንግስት አነስተኛ ደሞዝ ላላቸው ሰዎች ድጎማ ቢሰጥ ይቀላል። ለዚህ ድጎማ የሚውል ገንዘብ ደግሞ ኢኮኖሚ በሚያድግበት ወቅት ከፍተኛ ደሞዝ ከሚከፈላቸው ሰዎች ላይ በግብር መልክ መሰብሰብ ይቻላል።

✲ የማህበረሰብ ድጎማ እና አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ የሃገር ቤት ኩባንያዎችን ከውጭ ተፎካካሪዎቻቸው መጠበቅ እና የተረጋጋ የገንዘብ ፖሊሲ አስፈላጊ ናቸው።

የአዲሱ ሊበራሊዝም (ኒዎ-ሊበራሊዝም) ፅንሰ ሃሳቦች በዚህ መልኩ ከቀረቡ በኋላ አሌክሳንደር ሩስቶ ቀጣዩ የስብሰባ አጀንዳ “ኒዎ-ሊበራሊዝምን እንዴት እንስፋፋው?” እንዲሆን ሃሳብ አቀረበ። የአዲሱ ሊበራሊዝም ውልደት ዓለም ዓቀፍ ማዕከል ዋና መቀመጫውን ፓሪስ አድርጎ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ እና ስዊዘርላንድ ቅርንጫፎችን ከፍቶ እንዲሰራ ተወሰነ። በመላው ዓለም ማስፋፋት የሚለውም በረጅም ጊዜ ዕቅድ ውስጥ ተካተተ። የዋልተር ሊፕማኑ የፓሪስ ውይይት ለነባሩ ሊበራሊዝም የመሸኛ ድግስ ተደርጎ የተቆጠረ ቢሆንም በስብሰባው ላይ ከታደሙት መሃል ፍሬደሪክ ሄይክ እና ሉድዊግ ቮን ሜስስ የአዲሱ ሊበራሊዝም ፅንሰ ሃሳብ አራማጅ ለመሆን ድጋፋቸውን ሳይሰጡ ቀርቷል።

የአሌክሳንደር ሩስቶ ጓደኛ በነበረውና ቆይቶም የጀርመን ፕሬዝዳንት የሆነው ዓለም ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ አስጨንቆት በሚራወጥበት በዚህ ወቅት በአውሮፓ የሃያኛው ክ/ ዘመን ትልቅ ጦርነት እሳት ተጫረ። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት! በዋልተር ሊፕማን የውይይት መድረክ ላይ በፓሪስ ተላልፎ የነበረው ‘የአዲሱ ሊበራሊዝም ውልደት ዓለም ዓቀፍ ማዕከል’ ቢሮም ከመከፈቱ በፊት በዚሁ ምክንያት ተጨናገፈ። ይህ በወቅቱ ኒዎ- ሊበራሊዝም ከጥቂት ሰዎች አጀንዳነት እንዳያልፍ እና እንዳይስፋፋ እንቅፋት ሆኖታል።

በሃምሌ ወር አስራ ዘጠኝ አርባ አራት ዓ/ም አዶልፍ ሂትለርን ለመግደል የተደረገው ሙከራ ከከሸፈ በኋላ “የኒዎ-ሊበራሎች እጅ አለበት” በሚል የአሌክሳንደር ሩስቶ ጓደኞች የነበሩት ፍራንዝ ቦም እና ዋልተር ዩኮን ወደ እስር ቤት ተጋዙ። ጀርመን ከሂትለር በኋላ ሊኖራት የሚገባትን ፖሊሲ ቀርጾ የተገኘው ፍሬደሪክ ፔሬልስ ግን ወዲያውኑ ተረሸነ። በፍሪቡርግ የሚገኙ የፕሮቴስታንት ፓስተሮች “አቢያተ ክርስቲያናት የኒዎ-ሊበራሊዝም አስፋፊዎች መገናኛ እንዲሆኑ አድርጋችኋል።” ተብለው በናዚ ቁም ስቅላቸውን አዩ። በጥያቄ እየተፋጠጡ ተገረፉ። ጥቂት የማይባሉትም ተገደሉ።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.