ሞንት ፒለሪን፣ ሉድዊግ ኤርሃርድ፣ እና ኒዎ-ሊበራሊዝም

(By Kidus Mehalu)

⦿ ሞንት ፒለሪን – ስዊዘርላንድ 

ኦስትሪያዊው ፍሬደሪክ ሄይክ በ1938ዓ/ም በሉዊስ ሮጀር አማካይነት የተዘጋጀውን ዓይነት የምክክር መድረክ በስዊዘርላንድ አዘጋጀ። ከሚያዚያ አንድ ቀን አስራ ዘጠኝ አርባ ሰባት ዓ/ም እስከ ሚያዚያ አስር በሞንት ሚለሪን(ቫውድ) በተደረገው በዚህኛ የምክክር ስብሰባ ላይ ከአሌክሳንደር ሩስቶ በቀር በፓሪስ በተደረገው የዋልተር ሊፕማን ውይይት ታዳሚ የነበሩት ሰዎች እንዲሁም አዳዲሶቹ የምጣኔ ሃብት ሳይንስ ፈርጦች ሚልተን ፍሪድማን እና ጆርጅ ስቲግለር ተገኝተዋል። የኒዎ-ሊበራሊዝም አቀንቃኞች እና የጥንቱ ሊበራሊዝም ደጋፊዎች ቦታ ቦታቸውን ይዘው የያዙት አቋም ለምን እና እንዴት ትክክል እንደሆነ ለማሳመን ማሰላሰላቸውን ቀጥለዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ውጥናቸው የከሸፈባቸው መስለው የሚታዩት ኒዎ-ሊበራሎች በእልህ እና በቁጭት እየተብሰለሰሉ ሃሳባቸውን መሰንዘር ጀመሩ። የጥንቱ ሊበራሊዝም አራማጆችም ለዓለም የሚበጃት መፍትሄ የጥንቱን ሊበራሊዝም ክፍተት በመሙላት የሚገኝ መሆኑን ለማስረዳት ሞከሩ።

ሞንትተሰብሳቢዎቹ ልዩነታቸውን ለማስታረቅ እንዲረዳቸው በአንድ ማህበር ጥላ ስር ለመስራት ያቀረቡት ሃሳብ ተቀባይነት ቢያገኝም የሚቋቋመው አዲስ ማህበር ስም ግን አነታርኳቸዋል። ኒዎ-ሊበራሎቹ የማህበሩ ስም “የአዲሱ ሊበራሊዝም(ኒዎ- ሊበራሊዝም) ማህበር” እንዲባል ሲፈልጉ ሊበራሎቹ ደግሞ “የጥንቱ ሊበራሊዝም(ክላሲካል ሊበራሊዝም) ማህበር” መባል አለበት አሉ። ሁለቱም ቡድኖች በያዙት አቋም ስላልተስማሙ የማህበሩን ስም በተሰበሰቡበት አነስተኛ የስዊዘርላንድ መንደር ውስጥ በሚገኝ ተራራ ስም ለመጥራት ወሰኑ። በስዊዘርላንድ የቫውድ ግዛት የሚገኘው የዚህ ተራራ ስም ‘ሞንት ፒለሪን’ ይባላል። ስለዚህ ይህንኑ ስም እንዲይዝ ተደረገና የሞንት ፒለሪን ሶሳይቲ ሚያዚያ ስምንት ቀን አስራ ዘጠኝ አርባ ሰባት ዓ/ም ተቋቋመ።

ማህበሩ ከተቋቋመ በኋላ የኒዎ-ሊበራሊዝም ሃሳብ አመንጭ አሌክሳንደር ሩስቶ እና የወቅቱ የምዕራብ ጀርመን ኢኮኖሚ ካውንስል ዳይሬክተር የነበረው ጓደኛው ሉድዊግ ኤርሃርድ በአባልነት ተቀላቅለውታል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደድ በኋላ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ጦር በተቆጣጠረው የምዕራብ ጀርመን ክፍል የኢኮኖሚ ካውንስል ዳይሬክተር ሆኖ የተሾመው ኢኮኖሚስቱ ዶ/ር ሉድዊግ ኤርሃርድ አጋጣሚውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፅንሰ ሃሳቦችን በከፊል ተግባራዊ ለማድረግ ተጠቀመበት።

⦿ ጀርመንን ከትቢያ ያነሳት ሉድዊግ ኤርሃርድ  እና ኒዎ-ሊበራሊዝም

ሰኔ 21 ቀን 1948 ዓ/ም ሿሚዎቹን ሳያስፈቅድና ሳያማክር ናዚ ሲተገብረው የቆየውን የዋጋ ቁጥጥር፣ የሰራተኞች ዝቅተኛ ደሞዝ ጣሪያ፣ የዋጋ ቁጥጥር እና አምራቾች መንግስት የሚፈልገውን ምርት ብቻ እንዲያመርቱ ሲደረጉበት የነበረውን የምርት ቁጥጥር እንዲሁም የምግብ ዕደላ(ሬሽን) ፕሮግራም እንዲቀር መወሰኑን በሬዲዮ ያወጀው ሉድዊግ ኤርሃርድ ናዚ በጦርነቱ ምክንያት እያተመ ወደ ኢኮኖሚው ያስገባው እና የምዕራብ ጀርመን ኢኮኖሚ ሊሸከመው ከሚችለው አምስት እጥፍ የሚበልጥ ገንዘብ ከኢኮኖሚው ውስጥ የማስወጣት ስራም ሲሰራ ቆይቷል። በዚያው ዕለት በሬዲዮ ባደረገው ንግግር ከቀጣዩ ቀን ጀምሮ ይጠቀሙበት የነበረውን የድሮው ገንዘብ ‘ሪች ማርክ’ በአዲሱ ‘ደች ማርክ’ እንደሚተካና አስር ሪች ማርክ በአንድ ደች ማርክ እንዲመነዘር መወሰኑን ለህዝብ አሳወቀ።

ሉድዊግ ኤርሃርድ በብቸኝነት ባሳለፈው ውሳኔ ምክንያት በጀርመን የአሜሪካ ጦር አዛዥ በነበሩት ጄነራል ሉዊስ ክሌይ ፊት ተይዞ እንዲቀርብ ተደረገ። ጄነራል ክሌይም ኤርሃርድን “አማካሪዎቼ እንደነገሩኝ ከሆነ የፈፀምከው ትልቅ ስህተት ነው። ስለዚያ ምን ትላለህ?” በማለት ጠየቁት።

ኤርሃርድ በበኩሉ ለጄነራል ክሌይ “አማካሪዎችዎን አይስሟቸው። የእርሶ አማካሪዎች የነገሩዎትን ዓይነት ምክር የእኔም አማካሪዎች ነግረውኛል።” በማለት መልስ ከሰጣቸው በኋላ ወዲያውኑ ቢለቀቅም ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ በድጋሚ አሜሪካዊው ኮሎኔል ኦብረስት ፊት እንዲቀርብ ተደረገ። ኮሎኔል ኦብረስትም “ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ባለበት በዚህ ወቅት የዋጋ ቁጥጥር እንዲላላ ማድረግህ እና የምግብ እደላ ፕሮግራማችን እንዲስተጓጎል ማድረግህ ተገቢ ነውን? ዓላማህስ ምንድ ነው?” ብለው ጠየቁት። ludwig erhard

ሉድዊግ ኤርሃርድም “እኔ ያደረግሁት የዋጋ ቁጥጥር እንዲላላ ሳይሆን ፈፅሞ እንዲቀር ነው። የምግብ ዕደላ ፕሮግራምም ጭራሽ እንዲቀር እንጅ እንዲስተጓጎል አላደረግሁም። በጀርመን የምግብ ዕደላ ፕሮግራም የተጀመረው በዋጋ ቁጥጥር ምክንያት የምግብ አቅርቦት ችግር መከሰቱን ተከትሎ ነበር። ዓላማየ የዋጋ ቁጥጥር እንዲቀር በማድረግ ከገበያ የጠፉትን ምርቶች ወደ ገበያ እንዲመለሱ ማድረግ ነው። ምግብ ለማግኘት የሚያስፈልገው ብቸኛ ቲኬት ‘ደች ማርክ’ ነው። ይህን ‘ደች ማርክ’ ለማግኘት ደግሞ የግድ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል። የዚህን ውጤት ከጥቂት ጊዜ በኋላ አብረን እናይዋለን።” በማለት ለኮሎኔሉ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል። ጀርመን የአውሮፓ የጋራ መገበያያ የሆነውን ዩሮ ገንዘቧ ከማድረጓ በፊት ስትጠቀምበት የቆየችው ብር ‘ደች ማርክ’ ይባላል።

ይህ የኤርሃርድ ውሳኔ ቆይቶ ትክክል የነበረ እና ውጤቱም አስደናቂ ሆኖ ታይቷል። የዋጋ ቁጥጥር መነሳቱ የምርት አቅርቦት ችግርን የፈታ ሲሆን የገንዘብ ለውጡ ደግሞ የጀርመናዊያንን እህል ውሃ ሲፈታተን የነበረውን ግሽበት አቁሞታል። የዋጋ ቁጥጥር እና ተመን አለመኖር ገበያ የገዥዎችን ፍላጎት በትክክል ለሻጮች/ለነጋዴዎች እንዲደርስ ያደርጋል። የመንግስት የምግብ እድላ እና የድጎማ ፕሮግራም እንዲቀር መደረጉ ለሻጮች/ነጋዴዎች ምግብ ቢያቀርቡ ጥሩ ትርፍ እንደሚያገኙ መልክት ስለሚሰጣቸው ተፈላጊውን ምርት በበቂ ሁኔታ ለገበያ ለማቅረብ ይነሳሳሉ።

ሉድዊግ ኤርሃርድ በተከታዮቹ ወራት ተጨማሪ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ታሪፍን ከማስወገድ ጀምሮ ከግለሰቦች የሚሰበሰብ የገቢ ግብር ከሰማኒያ አምስት በመቶ ወደ አስራ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲል የተደረገ ሲሆን ከኩባንያዎች ላይ የሚሰበሰበው የገቢ ግብር ደግሞ ከስልሳ አምስት በመቶ ወደ ሃምሳ በመቶ እንዲወርድ አድርጓል። ሰዎች ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ ከፍተኛ ወለድ በማስተዋወቅ የምዕራብ ጀርመን የገንዘብ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ እና ኢኮኖሚዋም በከፍተኛ ፍጥነት እንዲመነደግ አደረገ።

አሜሪካ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለደቀቁ የምዕራብ አውሮፓ ሃገራት በነደፈችው የማርሻል የኢኮኖሚ ማገገሚያ እና ሌሎች እርዳታዎች ጋር ተደማምሮ ምዕራብ ጀርመን እስከ ጥቅምት ወር አስራ ዘጠኝ ሃምሳ አራት ዓ/ም ድረስ ሁለት ቢሊዮን ያህል ዶላር አግኝታለች። ሆኖም ግን ከዚህ የሚበልጥ ብዙ የማርሻል ፕሮግራም የማገገሚያ ገንዘብ ከደረሳቸው የምዕራብ አውሮፓ ሃገራት አንፃር ሲታይ የጀርመን የኢኮኖሚ እድገት ከሁሉም ፈጣን እና አስደናቂ ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ይህ ነው የማይባል የሞራል ውድቀት የደረሰባቸው፣ ኑሮአቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተናጋባቸው እና ተስፋ በማጣት የተጎሳቆሉት ጀርመናዊያን ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት አስር ዓመታት ውስጥ ብቻ አንገታቸውን ቀና ማድረግ ችለዋል። በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ምዕራብ ጀርመን ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ቀጥሎ በዓለም ትልቁን ግዙፍ ኢኮኖሚ ገነባች።

በአስራ ዘጠኝ ስልሳ ሶስት ዓ/ም የምዕራብ ጀርመን ቻንስለር(ጠ/ሚንስትር) የሆነው ሉድዊግ ኤርሃርድ የኒዎ-ሊበራሊዝም ፅንሰ ሃሳቦችን ይበልጥ እና በስፋት ለመተግበር ዕድሉን አገኘ። የአሌክሳንደር ሩስቶ ጓደኛ እና የሉድዊግ ኤርሃርድ አማካሪ የነበረው አልፍሬድ ሙለር ኒዎ-ሊበራሊዝም የሚለው ስም ከሊበራሊዝም ጋር ተቀራራቢ ስለነበር ጀርመናዊያን በጥርጣሬ እንዳያዩት እና ይህም ፍልስፍናውን ለማስፋፋት እንቅፋት እንዳይሆን በማለት ኒዎ-ሊበራሊዝምን ‘ሶሻል ማርኬት ኢኮኖሚ’[ማህበረሰብ መር ኢኮኖሚ] የሚል አዲስ ስም አወጣለት። የኒዎ-ሊበራሊዝም አቀንቃኞች ደግሞ ‘ኦርዶ ሊበራሊዝም’ እያሉ ሲግባቡበት ቆይተዋል። ኦርዶ የኒዎሊበራሎች መፅሄት ስም ነው።

የሉድዊግ ኤርሃርድ መንግስት “መንግስት በመጠኑ ጣልቃ የሚገባበት•••” የሚለውን የኒዎ-ሊበራሊዝም ፍልስፍና ክፍተት ተጠቅሞ የማህበረስብ ማሻሻያ እና የድጎማ/እርጥባን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ትልልቅ ንግድ ተቋማት እና ኩባንያዎች በቢዝነሱ ላይ የመወሰን ስልጣን ያላቸው የንግድ/የሰራተኛ ማህበራት በግዴታ እንዲያቋቁሙ የሚያስገድድ ሕግ አጸደቀ። የኩባንያዎች የማስፋፊያ እና የመልሶ ኢንቨስትመንት እቅድ ውሳኔ ሰጭ ባለንብረቶቹ ኩባንያዎች መሆኑ ቀርቶ መንግስት እንዲሆን የሚደነግግ አዋጅ ወጣ። ይህ የማህበረስብ ድጎማ እቅድ የመንግስት ጥገኛ የሆኑ ሰዎች እንዲበዙ በር ከፈተ። ድጎማ ከሚሹ ሰዎቹ አንፃር የመንግስት አቅም በቂ ስላልነበር መንግስት ሰራተኛው ክፍል ላይ ግብር ጨመረ። የሃገር ቤት ኩባንያዎችን ከውጭ ተፎካካሪዎቻቸው መጠበቅ በሚል ኩባንያዎቹ የኢንዱስትሪ ማህበር እንዲያቋቁሙ ተደረጎ ፍላጎታቸውን በፖለቲከኞች አማካይነት ማስጠበቅ እና የውጭ ተፎካካሪዎች በሃገሪቱ የነበራቸው ድርሻ እንዲመነምን ሆነ። ሉድዊግ ኤርሃርድ ቻንስለር ከመሆኑ በፊት ባደረገው ስር ነቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰው የጀርመን ኢኮኖሚ ወደኋላ መንሸራተት ጀመረ። የማህበረስብ መር ኢኮኖሚ የሚል አዲስ መጠሪያ ያገኘው ኒዎ-ሊበራሊዝም ቀስ በቀስ ጸረ ማህበረሰብ እና መንግስት እንዳሻው የሚፈነጭበት የውሸት ገበያ መር ኢኮኖሚ ስርዓት መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጣ።

ከአስራ ዘጠኝ ሰላሳ ሁለት ዓ/ም ጀምሮ ጸረ ካፒታሊስት፣ ጸረ ሶሻሊስት እና ጸረ ኮምኒስት ሆኖ መንገድ ሲፈልግ የኖረው ኒዎ-ሊበራሊዝም ገበያ መር ኢኮኖሚን የሚያራምድ መንግስት የሚዘውረው የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ስርዓት ሆኖ ብቅ አለ።ታላቁ የምጣኔ ሃብት ጠበብት ሉድዊግ ቮን ሜስስ ሂውማን አክሽን በተባለው ድንቅ መፅሃፉ ላይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደድ በኋላ አፈር ልሶ የተነሳውን ኒዎ-ሊበራሊዝም “መሃል ቤት የቀረ፣ ፅንፈኛ ሶሻሊዝም እና የፍፁማዊ አምባገነንነት ምንጭ ነው።”ሲል ገልፆታል። ኒዎ-ሊበራሊዝም በተግባር የሕግ የበላይነት(ሩል ኦፍ ሎው) የሚከበርበት እና በንብረት ባለቤትነት መብት አስፈላጊነት የሚያምን ፣ መንግስት በፍትህ አካላት ላይ እንዳሻው የማያዝበት እና የፍርድ ትዕዛዝ የማይሰጥበት፣ የዜጎች ኢኮኖሚያዊ እጣፈንታ ለመንግስት ባላቸው ፖለቲካዊ ወገንተኝነት እና ታማኝነት የማይወሰንበት፣ በመንግስት የሚወሰን ውሳኔ እና እቅድን ሁሉም ዜጎች በተመሳሳይ ቃላት እንዲያነበንቡ የማይገደዱበት እንዲሁም ሙስናን የማያበረታታ ስርዓት ነው።

ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት በእንግሊዝ ‘ኬይኒሽያኒዝም’ እንዲወለድ ምክንያት እንደሆነው ሁሉ በጀርመንም ‘ኒዎ-ሊበራሊዝም’ እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል። ሁለቱም ስርዓቶች ከሶሻሊዝም ፅንሰ ሃሳቦች ጋር ብዙም አለመራራቃቸው ደግሞ ለሶሻሊም ስርዓት መፋፋት እና ማንሰራራት ትልቅ ድርሻ እንዲኖራቸው አድርጓል። ከአስራ ዘጠኝ ሰላሳዎቹ እስከ አስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ ዓመታት ያንሰራራው ኒዎ-ሊበራሊዝም በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ እና ሰማኒያዎቹ ዓመታት ራሱን ሊገልጥ ከማይችልበት አዘቅት ወድቋል። ሆኖም ግን ዛሬ ዛሬ ይህንኑ ኒዎ-ሊበራሊዝም ትርጉሙ እንኳ በቅጡ ያልገባቸው አምባገነኖች የሚቃወሟቸውን ሊበራሎች ለማጥቃት የስድብ ምንጭ በማድረግ ከወደቀበት አንስተውታል። ዓለም ዛሬም የምትፈልገው ጡንቻቸውን ያደለቡ አምባገነኖችን ሳይሆን እንደ ኒዎ- ሊበራሊዝም አይነት አዳዲስ ሃሳቦችን እና ውጥኖችን የሚያመነጩ ግለሰቦችን መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። የግለሰቦች ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ከቀረ ልክ እንደ ኒዎ- ሊበራሊዝም ወድቆ ሊቀር ይችላል እንጅ በጉልበት እንደሰለጠኑት አምባገነኖች በግዴታ በህዝብ ጫንቃ ላይ የሚሰለጥንበት መንገድ የለም።

Advertisement

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.