እኔ እርሳስ [የመጨረሻ ክፍል]

እኔ እርሳስ ስለ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት አሰራር፣ ስለሚጠይቀው ሁሉን አቀፍ የሙያ ትስስር፣ የተለያየ ዓይነት ሙያ ያላቸው የማይተዋወቁ ሰዎች ሳይመካከሩ የሚያደርጉት ድንበር ዘለል ትብብር እና ገበያ ያለውን ሃገራትን የማስተሳሰር አቅም በደንብ ያስረዳል። በተለይም ‘መርፌ መስራት እንኳን የማንችል!’ እያልን ለምንቆጭ ሰዎች ብዙ ትምህርት ትሰጠናለች።ከሃምሳ ዓመታት በፊት በእውቁ ኢኮኖሚስት እና የፖለቲካ ጠበብት ሊዮናርድ ሬድ የተፃፈችው ‘እኔ እርሳስ” ወደ አማርኛ የተቀዳችው የፅሁፉ ኮፒራይት ባለቤት በሆነው የኢኮኖሚክ ትምህርት ፋውንዴሽን የፅሁፍ ፈቃድ ነው። መልካም ንባብ!

የእውቀት ውስንነት!

ቀደም ብዬ “እኔ እርሳስ” እንዴት እንደምሠራ ሊያውቅ የሚችል በዚህ ምድር ላይ ቢፈለግ አንድም ሰው ሊገኝ አይችልም በማለት ያስቀመጥኩትን ሀሳቤን በመቃወም አሁን ሊሞግተኝ የሚፈልግ ይኖር ይሆን?  እርግጥ ነው በእኔ አፈጣጠር ሂደት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እጆች ይሳተፋሉ። የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ሰዎች እርስ በርሳቸው አለመተዋወቃቸው ነው፡፡ አንድ ሰው በአቅራቢያው ከጥቂቶች በስተቀር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎችን  አያውቃቸውም፡፡ ይህን ዕውነታ ከተገነዘባችሁ፣ እናንተ ደግሞ እጅግ እርቃችሁ በመሔድ ፍጥረቴን ከብራዚል ቡና ለቃሚዎች እና በየሥፍራው ከሚገኙ የምግብ ሰብል አምራቾች ጋር አገናኝታችሁ ልትናገሩ ትችላላችሁ፡፡ ይህ የፍጥረቴን ዝምድና ስፋት ያሳያል። ከእነዚህ ሚሊዮኖች መካከል የእርሳስ ማምረቻ ፋብሪካውን ስራ አስኪያጅ ጨምሮ እያንዳንዱ ግለሰብ እኔን ለመስራት በሚከወን የምርት ሂደት ውስጥ ውስን ከሆነው ዕውቀቱ በዘለለ የሚያበረክተው የተለየ ነገር አይኖርም። በሥራ ላይ ሊያውሉት ከሚችሉት ዕውቀት እና ችሎታ አንፃር ስንመለከት በስሪላንካ በሚገኘው የሴይሎን የማዕድን ስፍራ ሠራተኞችና በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ባሉት የእንጨት ሠራተኞች መካከል ያለው ልዩነት የሙያቸው ዓይነት መለያየት ብቻ ነው፡፡ የማዕድን ሠራተኛውም ሆነ የእንጨት ሠራተኛው፣የፋብሪካው ኬሚስት ወይም የፓራፊን አምራች የሆነው የነዳጅ ዘይት ማምረቻ ሠራተኛ በሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከሚፈጥረው እሴት ውጭ እሱን በተለይ ተአምረኛ ሊያስብለው የሚችል ምንም ነገር የለም።

የሚያስደንቅ ዕውነታ እነሆ!የነዳጅ ዘይት አምራች ሠራተኛው፣ ኬሚስቱ፣ የግራፋይት ማዕድን አውጪው፣ ሸክላ አፈር ቆፋሪው፣ የባቡሮች ወይም የመርከቦች ወይም የጭነት መኪኖች ማምረቻ ሠራተኞች፣ መናኛ ብልጭልጭ ብረቴን የሚያበጀው ማሽን ሰራተኛ እና የእርሳስ ማምረቻ ፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ጭምር ሁሉም የሚሠሩት የየራሣቸውን የሥራ ድርሻ ለመወጣት እንጅ እኔን ፈልገውኝ አይደለም። ምናልባትም እያንዳንዳቸው ለእኔ የሚኖራቸው ፍላጎት አንድ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ከሚኖረው ፍላጎት ያንስ ይሆናል። በእርግጥ ከእነዚህ ብዙሃን መካከል እኔን ከነጭራሹ አይተው የማያውቁም ይኖራሉ። ወይም እኔን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የማያውቁ ሞልተዋል።  የእነዚህ ሰዎች ፍላጎት ከእኔ ውጪ ላለ ነገር ነው፡፡ ምናልባትም እንዲህ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ሚሊዮኖች እያንዳንዳቸው ባላቸው ውስን ዕውቀት ሠርተው በሚያገኙት ገቢ የሚፈልጉትን ወይም የሚያስፈልጓቸውን ሸቀጦችና አገልግሎቶች ገበያ ላይ በልውውጥ መልክ ማግኘት መቻላቸውን ተገንዝበው ይሆናል። እኔ ደግሞ ከእነዚህ ሸቀጦች መካከል ልኖርም ላልኖርም እችላለሁ።

ሁሉን የሚያውቅ አይምሮ ይኖራልን? 

አሁንም ይበልጥ አስደናቂ ዕውነታ እንካችሁ። ይኸውም እኔን ወደ ህልውና ለማምጣት አስፈላጊ በሆኑት የትየለሌ የሥራ ሒደቶች ላይ መወሰን የሚችል ወይም እነዚህን ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን የሥራ ሒደቶችን በኃይል ተቆጣጥሮ ማስፈፀም የሚችል ሁሉን የሚያውቅ አይምሮ ያለው አንድም ሰው ያለመኖሩ ነው። የዚህ ዓይነት አይምሮ ሊኖረው የሚችል ሰው ስታስሱ ብትኖሩ ከቶ አይገኝም። ይልቁንም ስውሩ እጅ (ዘ ኢንቪዝብል ሃንድ) ይኽን ሥራ ሲያከናውን እናያለን። ይህንን ነው ቀደም ብዬ እንቆቅልሽ በማለት ያመላከትኳችሁ።

“ዛፍን የሚፈጥር እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡” ይባላል። በዚህ ሐሳብ የምንስማማው ለምንድ ነው?እኛ አንዲት ዛፍ እንኳ መፍጠር እንደማንችል ስለምንገነዘብ አይደለምን? ሌላው ቀርቶ እስቲ ዛፍን በአግባቡ መግለፅ እንችላለን? ላይ ላዩን ካልሆነ በቀር ጨርሶ አንችልም፡፡ ለምሳሌ-የሆኑ ሞለክዩላዊ ቅንብሮሾችን በመጠቃቀስ የዛፍ መገለጫ ይህ ነው ልንል እንችላለን፡፡ እስቲ በትንሹ ከሰዎች መካከል ምን ዓይነት አይምሮ ያለው ሰው ነው በአንድ ዛፍ የሕይወት ዘመን ውስጥ የሚካሔዱትን ሞለክዩላዊ ለውጦች በነቂስ መመዝገብ የሚችል? ይህ ፈጽሞ ሊታሰብና ሊሆን የማይችል ነገር ነው፡፡

“እኔ እርሳስ” የውስብስብ ተዓምራት ቅንብሮሽ ውጤት ነኝ፡፡ የዛፍ፣ የዚንክ፣ የመዳብ፣ የግራፋይት እና የሌሎችም፡፡ እነዚህ በተፈጥሮ የሚገኙ ተዓምራት ናቸው፡፡ ይበልጥ ትንግርት የሆነ ሌላም ተዓምር አለ። ይኸውም እኔ የሰው ልጅ አይምሮአዊ(መስተሃልያዊ) የፈጠራ ጥረቶች ቅንብር ውጤት መሆኔ ነው፡፡ ሁሉን የሚያውቅ  አይምሮ ያለው አንድም ሰው ያለመኖሩ ሐቅ በገሃድ እየታየ ባለበት ሁኔታ፣ ለሰው ልጅ መሠረታዊ ነገሮች እና ፍላጎቶች ምላሽ ይሰጡ ዘንድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ውስን የሰው ልጅ መስተሃልያዊ የፈጠራ እና ጥረት ውጤቶች በተፈጥሮአዊ እና በራሳቸው አካሔድ ይቀነባበራሉ፡፡ ዛፍን መፍጠር የሚችለው እግዚኣብሔር ብቻ በመሆኑ፣ እኔንም መፍጠር የሚችለው እግዚኣብሔር ብቻ እንደሆነ አበክሬ እናገራለሁ፡፡ ሰው ዛፍን ለመፍጠር ሞለክዩሎችን በአንድነት ማቀነባበር ከሚከብደው ሁኔታ ባልተናነሰ እኔንም ወደ ህላዌነት ለማምጣት እነዚህን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ውስን ዕውቀቶች አቀናጅቶ መምራት ይከብደዋል፡፡

ቀደም ሲል እኔ በተዓምራዊነቴ የምወክለውን ተምሳሌት መገንዘብ ከቻላችሁ፣ የሰው ልጅ በመከፋት እያጣ ያለውን ነፃነቱን መታደግ እንዲችል ትረዱታላችሁ፡፡ በማለት የገለፅኩት ይህንኑ ነው፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ያሉትን ውስን እውቀቶች እና ችሎታወች “ተፈጥሮኣዊ አካሔድን ይዘው መጓዝ ይኖርባቸዋል!” የሚለውን ከተቀበለ፣ ውስኖቹ ዕውቀቶች ለሰው ልጅ መሠረታዊ ነገሮችና ፍላጎቶች ምላሽ ይሰጡ ዘንድ አውቶማቲክ በሆነ አኳኃን ራሳቸውን ወደ ተቀነባበሩ ፈጠራዊና ለውጥ ከሳች ወደሆኑ ንድፎች ይለወጣሉ። ይህም ማለት ምንም ዓይነት የመንግስትም ሆነ የሌላ ሁሉን-አውቅ ባይ ጫና እና ተፅዕኖ አይኖርም ማለት ነው፡፡ ይህ ከተተገበረ የሰው ልጅ የነፃነቱን ፍፁም መሠረታዊ ግብዓት ያገኛል፡፡ እሱም የነፃ ሕዝብ ህላዌነት ዕምነት ነው፡፡ ያለዚህ ዕምነት ነፃነት ከቶውንም ሊኖር አይችልም።

ሰዎች ነፃ ሲሆኑ•••

ሰዎች ነፃነት ሲያገኙ ምን እንደሚያከናውኑ ማስረጃ (ምስክርነት) መስጠት የሚችል ዕቃ ‘እኔ እርሳስ’ ብቻ በሆንኩና ሰዎች ማስረጃውን ባይቀበሉ ተገቢ በተባለ ነበር። ነገር ግን ብዙ ማስረጃ ሰጪዎች አሉ፡፡ ማስረጃዎቹም በእያንዳንዱ ዘንድ ይገኛሉ፡፡ ሁሉም እኛኑ የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ለምሣሌ ፖስታ የማደል ሥራ አውቶሞቢልን ወይም የሒሳብ ማሽንን ወይም ሰብል ሰብስቦ የሚወቃ ኮምባይነርን ወይም ወፍጮን ወይም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ነገሮችን ከመፍጠርና ከመገንባት አንፃር ሲታይ እጅግ ቀላል ተግባር ነው፡፡

ልብ ብላችኋል! ፖስታ ማደል?! ሆኖም ከሁሉን አውቅ መንግስት ብቻ ወደታች በሚወርድ የማዕከላዊ እቅድ እና በነፃ ሕዝብ የማመን ዕምነት በሌለበት አሰራር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ውስን ዕውቀቶች በተፈጥሮኣዊ፣በፈቃደኝነት እና ተኣምራዊ አኳኋን ሊቀናጁ ስለማይችሉ ሕብረት ፈጥረው ለመሠረታዊ ፍላጎቶች አመርቂ ምላሽ መስጠት አይቻላቸውም። እንደ ፖስታ ማደል የመሳሰሉት ሥራዎች ከመንግስት ሞኖፖሊ ወጥተው በግለሰቦች እንዲከናወኑ ቢደረግ ብዙ ሰዎች ፖስታን በብቃት የማደል ችሎታ ይኖራቸዋል የሚል እምነት አይኖቸውም። ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው በፖስታ ማደል ሥራ ውስጥ የሚከናወነውን እያንዳንዱን ተግባር እንዴት እንደሚከናወን ስለማያውቅ እና ይህን ስራ ከመንግስት ውጭ ያሉ ሌሎች ግለሰቦች ሊሰሩት የሚችሉት ስራ መሆኑን አስበውት ስለማያውቁ ነው።

ሰዎች ነፃ ሲሆኑ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሰዎችን ድምፅ ሃዘንም ሆነ ደስታ በዓለም ዙሪያ ያሰራጫሉ። አንድ ድርጊት እየተከናወነ ባለበት ቅፅበት ሁሉም ሰው በየቤቱ ሆኖ እንዲከታተለው ምስላዊ እንቅስቃሴውን ከነድምፁ በቀጥታ ያስተላልፋሉ። ከአራት ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 150 መንገደኞችን ከሲያትል ወደ ባልቲሞር ያጓጉዛሉ።  ያለአንዳች ድጎማ ሊታመን በማይችል ዋጋ ነዳጅ ዘይት ከቴክሳስ ግዛት ወደ አንዱ የአገሪቱ ጥግ ወይም ኒውዮርክ ወደሚገኝ የብረት ማቅለጫ (Furnace) ያደርሳሉ። መንግስት አንድ 28ግራም ያህል ክብደት ያለውን ደብዳቤ በአንድ የከተማ ጎዳና ባሉ መዳረሻዎች ለማድረስ ከሚያስከፍለው ዋጋ ባነሰ ክፍያ አራት 2 ሊትር ገደማ  የነዳጅ ዘይት ዓለምን ለመዞር የግማሽ ያህል ከሚሆን ርቀት ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ በመጫን በምሥራቅ በኩል ከሚገኘው የባሕር ጠረፋችን ያመጣሉ።

እኔ ማስተማር ያለብኝ ትምህርት ይህ ነው፡፡ የሰው ልጅ አእምሮአዊ የፈጠራ ችሎታው እና ንቃተ ህሊናው እንዳይገታ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ። የእርስዎ ድርሻ ማህበረሰቡ ከዚህ ትምህርት ጋር ተጣጥሞ እንዲንቀሳቀስ ማደራጀት ብቻ ይሁን፡፡ የማህበረሰቡ የሕግ ማዕቀፍ በተቻለው መጠን ዕንቅፋቶችን ሁሉ እንዲከላ እና እንዲያስወግድ ያድርጉ፡፡ እነዚህ ፈጠራ-ነክ ዕውቀቶች፣ጥያቄዎች እና ችሎታዎች በነፃነት የሚሰራጩበትን እንዲሁም ለክርክር የሚቀርቡበትን ሁኔታዎች ያመቻቹ፡፡ የተቀረውን ለሥውሩ እጅ (ዘ ኢንቭዝብል ሃንድ) ይተው።ምንም እንኳ ‘እኔ እርሳስ’ ስታይ ቀላል ብመስልም የእኔን ያህል ስለ ስውሩ እጅ (ዘ ኢንቭዝብል ሃንድ) ያስረዳችሁ ኢኮኖሚስት እንደሌለ ግን መወራረድ እችላለሁ። የአፈጣጠሬን ተዓምራዊነት እንደማስረጃ ያቀረብኩላችሁ “እኔ እርሳስ”ን ለመስራት በገበያ ውስጥ ማለፍን፣ ሁሉን አቀፍ የሙያ ትስስር ማስፈለጉን፣ የተለያየ ዓይነት ሙያ ያላቸው ምናልባትም የማይተዋወቁ ሰዎች ትብብር መጠየቁን፣ ድንበር ዘለል ንግድ ግዴታ መሆኑን እና እኔን ለመስራት ሃገራት መተባበር እንዳለባቸውም ጭምር በተግባር ላሳያችሁ ብየ ነው። የዚህ እውነታ ተግባራዊነት ደግሞ የፀሐይ፣ የዝናብ፣ የሴዳር ዛፍ እና የመልካም ምድር ያህል ተፈጥሮአዊ ነው፡፡

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.