እኔ እርሳስ [በሊዮናርድ ሬድ]

እኔ እርሳስ“እኔ እርሳስ” ነኝ። ያውም ተራ የእንጨት እርሳስ። ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉ ልጆች፣ ወንዶች፣ ሴቶች፣ወጣቶች፣ጎልማሶች፣መምህራኖች እንዲሁም ገበሬዎች ሁሉ ያውቁኛል። የእኔ ሙያ መፃፍ ነው። መሳል እና መሞነጫጭርም ነው። ግን ደግሞ ሙያየም አይደለም። በቃ የእኔ ስራ እንዲህ ነው። ስለዘር ሐረግ እጽፋለሁ። ለምን እንደምጽፍ ሊገርማችሁ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ታሪኬ መሳጭ ስለመሆኑ ልንገራችሁ። በመቀጠል ደግሞ ከዛፍ ወይም ከፀሐይ ግባት ወይም ደግሞ ከመብረቅ ብልጭታ የምበልጥ እንቆቅልሽ መሆኔን እተርካለሁ። ይሁን እንጂ የሚጠቀሙኝ ሰዎች ሁሉ እኔን ከቁብ እንደማይቆጥሩኝ፣ የተራ ስራ ውጤት እንደሆንኩ፣ መሠረት የለሽ ነገር እና ከሌሎች ነገሮች አንፃር እኔን ሲመዝኑኝ ከመጤፍ አለመቁጠራቸው ያሳዝናል። ሰዎች አንዱን ነገር ከሌላው አሳንሰው በማየት አባዜያቸው የተነሣ እኔን ከተራነት ጎራ መድበውኛል። የሰው ልጅ እየፈጸመ ያለው ይህ ከፍተኛ ስህተት ራሱን ከክፉ አደጋ ውስጥ አውጥቶ ረጅም ዘመን መኖር እንዳይችል አድርጎታል። ጂኬ ቼስተረቶን ትዝብቱን ሲገልጽ “ዕጹቦችን ትተን ዕጹብን ፍለጋ ስንባዝን እንጠፋለን፡፡” ብሏል፡፡

እኔ እርሳስ ቀላል እና ተራ መስዬ ብታይም፣አድናቆት እና አክብሮት ትቸሩኝ ዘንድ  ስለራሴ ዕውነታውን እወዳለሁ። በርግጥ ይህ የሚሆነው ልትረዱኝ ከቻላችሁ ነው፡፡ እሽ እሱ ይቅር። ምናልባት እንድትረዱኝ መጠየቄ ብዙ ማስቸገር ይሆንብኛል።  ከዚያ ይልቅ በተአምራዊነቴ የምወክለውን ተምሳሌት መገንዘብ ከቻላችሁ ይበቃል። ያኔ የሰው ዘር በመከፋት እያጣ ያለውን ደስታ መልሶ እንዲያገኝ እና ነጻነቱን እንዲጎናጸፍ አጋሩ ትሆናላችሁ፡፡ እናም የማስተምረው ታላቅ ትምህርት አለኝ። ይህን ትምህርት ሳስተምር መኪና  ወይም አውሮፕላን ወይም ኮምፒውተር ማስተማር ከሚችለው በላይ አስበልጨ ነው። አዎ! ምክንያቱም ለሰዎች በጣም ቀላል እመስላለሁና። ይህን ስል ግን የዕውነት ቀላል አልምሰላችሁ!

እኔ እንዴት እንደምሠራ በብቸኝነት ሊያውቅ የሚችል ሰው በምድር ላይ ቢፈለግ ፈፅሞ ሊገኝ አይችልም። ይህን ስላችሁ የማይታመን ተአምር ይመስላችኋል አይደል? በተለይ ደግሞ በየአመቱ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን የሚሆኑ አምሳያዎቼ ማለትም እርሳስ በሃገረ አሜሪካ እንደሚመረቱ ስትሰሙ ይደንቃችኋል።

እስቲ በእጃችሁ ብድግ አድርጉኝና ሁለመናዬን ተመልክቱ። ምን አያችሁ? እርግጠኛ ነኝ ያያችሁት ዓይን የማይሞላ ነገር ነው፡፡ የሆነ እንጨት፣ ደረቅ የቀለም ቅብ፣ የግራፋይት ሊድ፣ ብልጭልጭ መናኛ ብረት እና ላጲስ አያችሁ?

የትየለሌ ቅድመ ዘሮቼን እወቁ!

የዘር ሐረጋችሁን ወደኋላ ርቃችሁ መቁጠር እንደምትቸገሩት ሁሉ እኔም የዘር ሐረጌን ወደኋላ ርቄ ሁሉን መጥራትና መዘርዘር ያዳግተኛል። ቢሆንም ግን እናንተ ላይ ግርምት መጫር የሚያስችለኝን ያህል የስረ መሠረቴን ስፋት እና ውስብስብነት በበቂ ሁኔታ መግለፅ እችላለሁ፡፡

የዘር ሐረጌ በአሜሪካ ሰሜናዊ ካሊፎርኒያ ግዛቶች ውስጥ ቀጥ ብሎ ከሚበቅል ሴዳር (Cedar) የተባለ መዓዛማ ዛፍ ይጀምራል። እስቲ የሴዳርን ዛፎች ከመቁረጥ አንስቶ ግንዶቹን ሰብስቦ በባቡር ወደሚጫንበት የባቡር ሃዲድ ዳርቻ እስከማጓጓዝ ድረስ ላሉት ሒደቶች የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ ለአንድ አፍታ ለማስታወስ ሞክሩ፡፡ በዚህ ሥራ በርካታ መጋዞች፣ የጭነት መኪኖች፣ ገመዶችና ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ማሽኖች ይሳተፋሉ። እነዚህን ቁሳቁሶች ለማምረት የሚሳተፉትን የሰዎች ብዛት እንዲሁም የሚያስፈልጉትን አያሌ የሙያ ክህሎት እና የችሎታ ዓይነቶችን አስቡ፡፡ ከከርሰ ምድር የብረት ማእድን ከማውጣት ሥራ ጀምሮ ማእድኑን ወደ ብረት እስከ መቀየር፣ ከብረቱ መጋዞችን፣ መጥረቢያዎችን እና ሞተሮችን እስከ መሥራት፣ ወፍራም እና ጠንካራ ገመድ ለማግኘት ደግሞ ለገመዱ መሥሪያ ግብዓት የሚሆነውን ዛፍ ከማብቀል አንስቶ ገመድ ሆኖ እስኪመጣ ያሉትን የምርት ሂደቶች፣ በእንጨት ማቅረቢያ ካምፕ ውስጥ የሚያስፈልጉ ነገሮች ማለትም የሠራተኞች መኝታ፣ የዕቃ መጋዘኖች፣ የምግብ ማዘጋጃ ቤቶች፣ የምግብ ዕቃዎች፣ የምግብ ዝግጅት  ወዘተ…ያሉትን  ሁሉ ያካትታል። ይህን ሁሉ ስታስቡ እያንዳንዱ የእንጨት ሠራተኛ ከሚጠጣው የአንዲት ስኒ ቡና ዝግጅት በስተጀርባ በሽዎች የሚቆጠሩ የሰው እጆች ስለመኖራቸውም አስተውሉ።

የሴዳር ግንዶቹ በሳን ሊንደሮ ካሊፎርኒያ ወደሚገኘው የእንጨት ፋብሪካ ይጓጓዛሉ። ለማጓጓዙ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ መኪኖችን፣ ሃዲዶችን፣ የባቡር ሞተሮችን የሚያመርቱ እና የመገናኛ አውታሮችን የሚዘረጉ ግለሰቦችን ልብ ይበሉ። እነዚህ ሁሉ የቅድመ ፍጥረቴ ሠራዊቶች ናቸው፡፡

በሳን ሊንደሮ የሚገኘውን የእንጨት ፋብሪካ ለማሽን እና ለህንጻው ግንባታ ያዋለውን ገንዘብ እንዳትረሱ በማሳሰብ ወደ አፈጣጠሬ ልመልሳችሁ። የሴዳር እንጨት በትናንሹ ተቆራርጦ በእርሳስ ቁመት ልክ ይሆንና ውፍረቱ ከአንድ ኢንች አንድ አራተኛ በሚያንስ መጠን ትናንሽ ቦርዶች ይዘጋጃሉ። ቦርዶቹ ወደ ማድረቂያ ምድጃ ይከተቱና እንዲደርቁ ይደረጋል።ከዚያም ቀለም ይቀባሉ። ቀለም የሚቀቡት ሲታዩ እንዲያምሩ እና ውበታቸው እንዲጨምር ነው። ከዚያም የእንጨት ቦርዶቹ ሰም ይቀቡና ዳግም እንዲደርቁ ይደረጋል። ቀለሙን እና የማድረቂያ ምድጃውን ለማምረት ስንት ሰዎች ተሳትፈዋል? ሞተሮች፣በሞተር ላይ የሚገጠሙ ቺንጊያዎችን እና የሚንቀሳቅሳቸው ሃይል እንዲሁም  ለማሽኑ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ቁሶችን ሁሉ ለማቅረብ ስንት አይነት ሙያዊ ክህሎት እና የዕውቀት ስብጥር ጠይቆ ይሆን?

የፅዳት ሰራተኞችስ ከቅድመ ዘር ሐረጎቼ የሚካተቱ አይደሉምን? ናቸው እንጅ! ለእንጨት ፋብሪካው ጋዝ የሚያቀርበው ድርጅት ሰራተኞች፣ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያቀርበው ኩባንያ ሰራተኞች እና የሃይል ማመንጫው በተገነባበት ወቅት የተሳተፉ ሰራተኞች ሁሉ የቅድመ ዘር ሐረጎቼ ናቸው። ቦርዶችን ጭነው የሚጓዙ መኪኖችም ዘሬን ስቆጥር የምዘነጋቸው አይደሉም።

በአንድ ወቅት ወላጆቼ ለእርሳስ ፋብሪካው ካጠራቀሙት ገንዘብ ውስጥ አራት ሚሊዮን ያህሉን ዶላር ለፋብሪካው ግንባታ እና ለማሽን ግዥ እንዳዋሉት አሳስቤአችሁ ትረካየን ልቀጥል። በእያንዳንዱ የሴዳር ቦርድ ላይ ወላጆቼ በገዙት የተወሳሰበ ማሽን አማካይነት ስምንት ቦዮች ይበጅባቸዋል። ቀጥሎ በሌላ ማሽን አማካይነት በእያንዳንዱ ቦይ ውስጥ ሊድ ይከተትና ማጣበቂያ (ኮላ) ተቀብቶ ሌላ ተመሳሳይ ቦርድ ይከደንበታል። አሁን ሊዱ ሳንዱዊች ሆነ ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያም አንድ ላይ ከተዋደደው የእንጨት ሳንዱዊች  እኔና ሰባት ወንድሞቼ በእርሳስ ቅርጽ ተጠርበን እንወጣለን።

የኔ ‘ሊድ’ ራሱ የውስብስብ ሥራዎች ውጤት ነው። ባይሆን ኖሮ ሊዱም ባልተገኘ ነበር።  እስቲ ተመልከቱ፡፡ የግራፋይት (graphite) ማእድኑ የሚወጣው ሲሪላንካ ውስጥ ሴይሎን በመባል ከሚጠራው ስፍራ ነው። ማእድን አውጪ ሠራተኞች እና የሚገለገሉባቸው የትየለሌ መሳሪያዎች፣ ማእድኑ የሚከተትበትን የወረቀት ከረጢቶች የሚያመርቱ ሠራተኞች፣ ለከረጢቶቹ መስፊያ የሚሆኑ ክሮችን የሚያመርቱ ሰዎች፣ መርከብ ላይ ጫኞች፣ መርከቦችን የሚሠሩ ሰዎች፣ በጥንቃቄ የሚያጓጉዙ መርከብ ነጅዎች(ካፒቴኖች)፣ መርከቡ በጉዞ ላይ ሳለ ባሕር ውስጥ ከሚገኙ ዓለቶች ጋር እንዳይላተም የመርከቡ ማማ ላይ ሆነው የመጠቆሚያ መብራት የሚቆጣጠሩ ሠራተኞች ሳይቀሩ ለኔ ውልደት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው።

ግራፋይቱ ከሚሲሲፒ ከመጣ የሸክላ አፈር ጋር ይቀላቀላል። ከዚያም የማጣራት ሂደቱን ለማቀላጠፍ አሞኒየም ሃድሮክሳይድ (Ammonium Hydroxide) ይጨመርበታል፡፡ እንደ ሰልፎኔትድ ታሎው (Sulphonated Tallow) ያለ ከእንስሳት ተዋጽኦ የተመረተ ስብ ለማርጠቢያነት ሲጨመርበት ከሰልፈሪክ አሲድ (sulphuric acid) ጋር ኬሚካላዊ ሂደት ያካሂዳል፡፡ በበርካታ ማሽኖች ውስጥ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ ቅልቅሉ (mixture) ልክ በማሽን እንደተፈጨ ስጋ እየተግተለተለ ይወጣል፡፡ ከዚያም በተፈለገው መጠንና ቅርፅ ተከፋፍሎ ይጋገርና በ1000ሽ  ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ የሊዶችን ጥንካሬ እና ልስላሴ ለመጨመር ከሜክሲኮ በመጣ ሙቅ ውህድ የካንደሊላ ሰም (candelilla wax) ፣የቅባት ሰም (paraffin wax) እና ሃይድሮጅኔትድ በሆኑ ተፈጥሮአዊ ስቦች (hydrogenated natural wax) ይታከማል፡፡

የኔ አካል የሆነው እንጨት (ሴዳር) ስድስት የቀለም ኮቶችን ይለብሳል፡፡ ስድስት ዙር ቀለም ይቀባል ማለት ነው፡፡ የቀለሙን ግብኣቶች (ingredients) በሙሉ ታውቁአችኋላቸውን? እስቲ ማነው የጉሎ ዛፍ አብቃዮችና የጉሎ ዘይት ጨማቂዎች በቀለሙ ውስጥ ድርሻ እንዳላቸው የሚያውቅ? አዎ እነሱም ድርሻ አላቸው! ሌላው ቀርቶ ያማረ ቢጫማ መልክ እንዲኖረኝ የማድረግ ሂደቶች እንኳ አንድ ሰው መጥቀስ ከሚችለው ቁጥር በላይ የተለያዩ ችሎታዎችን የሚጠይቅ መሆኑን ብታውቁ ይገርማችኋል፡፡ መለያ ጽሁፌንም ተመልከቱ፡፡ ካርቦን ብላክ (carbon black) ከሙጫ (resin) ጋር በሙቀት ኃይል በመቀላቀል የሚፈጠር ስስ ሽፋን (film) ነው፡፡ ሙጫ እንዴት ይመረታል? ካርቦን ብላክስ ምንድን ነው?

እላዬ ላይ የሚገኘው መናኛው የብረት ጥምጣሜ ጅንፎ ነሃስ (brass) ነው፡፡ የዚንክ (zink) እና የመዳብ (copper) ማእድን አውጪ ሠራተኞችንና ከእነዚህ ተፈጥሮኣዊ ምርቶች አብረቅራቂ የብራስ ንጣፎችን የሚሠሩ ጥበበኞችን አስተውሉ፡፡ በብረቴ ላይ የሚገኙት ጥቁር ቀለበቶች ከጥቁር ኒኬል የተሠሩ ናቸው። ጥቁር ኒኬል ምንድን ነው? እንዴትስ ነው ቀለበቱ ብረቱ ላይ የሚታተመው? የብረቴ መሐል ስፍራ ጥቁር ኒኬል የለውም፡፡ ለምን እንደሌለው በጽሁፍ እንድገልጽ ብጠየቅ ተጨማሪ ብዙ ገጾች ያስፈልጉኛል።

አናቴ ላይ የሚገጠም ሞገስ አጎናፃፊ ዘውድም አለኝ። ላጲስ ይሰኛል። ሰዎች በሚጠቀሙኝ ጊዜ የሚፈጽሙትን ግድፈቶች ፈግፍገው የሚያጠፉበት ነው። ሲፈገፈግበት የማጥፋቱን ተግባር የሚያከናውነው ፋክታይስ (factice) የተባለ የላጲስ መሥሪያ ግብአት ነው፡፡ ፋክታይስ ከኢንዶኔዥያ ከሚመጣ ‘ሬስ’ ከሚባል ቅባታማ ሰብል ፍሬ ተጨምቆ በተገኘ ዘይት (race-seed oil) እና ሰልፈር ክሎራይድ (sulfur chloride) መካከል በሚካሄድ ኬሚካላዊ ሂደት የሚፈጠር ጎማ መሰል ምርት ነው፡፡ የላጲሱ አካል የሆነው ጎማ ከእርሳስ ጋ ባለው አገልግሎቱ፣ ሰዎች ከሚያስቡት በተጻራሪ በማጣበቂያነት ከማገልገል የዘለለ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ ጎማውን ጠንካራ የማድረግ ሂደቶችን የሚያቀላጥፉ ግብኣቶች እጅግ ብዙ ናቸው። ከግብዓቶቹ መካከል ፑማይስ (pumice) የሚመጣው ከጣሊያን ነው፡፡ የላጲሱን ቀለም የሚወስነው ደግሞ ካድሚየም ሰልፋይድ (cadmium sulfide) የተባለ ኬሚካል ነው፡፡ [ክፍል 2 ይቀጥላል።]

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.