የኖቤል ሽልማት እና የኢኮኖሚክስ ሳይንስ ትውውቅ

የችካጎ ዩኒቨርስቲ ኖቤል ተሸላሚ ኢኮኖሚስቶች በከፊል

የችካጎ ዩኒቨርስቲ ኖቤል ተሸላሚ ኢኮኖሚስቶች በከፊል

በህዳር ወር 1895ዓ/ም ቱጃሩ አልፍሬድ ኖቤል ለዓለም በጎ ላበረከቱ ሰዎች በስሙ ሽልማት እንዲሰጥ ተናዞ ሞተ። ያም ሆኖ እስከ 1969 ዓ/ም ድረስ አንድም የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ በኖቤል ሽልማት ውስጥ እንዲካተት አልተደረገም ነበር። በ1968ዓ/ም ስዊድናዊው ኢኮኖሚስት ገነር ሚራድ ኢኮኖሚክስን ከሌላው ማህበራዊ ሳይንስ ጋር መወዳደር የሌለበት እንዲሁም በየጊዜው ለሚደረጉ ጥልቅ የምጣኔ ሃብት ቀመሮች እና ምርምሮች ወደፊት መጓዝ ማበረታቻ የሚያሻው ሳይንስ መሆኑን በመግለፅ በኖቤል የሽልማት ዝርዝር ውስጥ ኢኮኖሚክስ እንዲካተት 260 አባላት ያሉትን የስዊድን ሮያል አካዳሚ አሳመነ። ይሄን ተከትሎ የስዊድን ብሄራዊ ባንክ በኢኮኖሚክስ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ለሆኑ ሰዎች የሚሆነውን ገንዘብ ከ1969ዓ/ም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ሲሸልም ቆይቷል። ለተቀሩት የኖቤል ሽልማት ዘርፎች ማለትም ለኬሚስትሪ፥ፊዚክስ፥ ሰላም፥ስነ ፅሁፍ እና የህክምና ሳይንስ የሚሰጠው ገንዘብ የሚሸፈነው ግን በአልፍሬድ ኖቤል ሃብት ነው።

የኖቤል ሽልማት በርካታ ስራ ሰርተው በድህነት፥በብቸኝነት እና በኑሮ ተመችቷቸው ያልነበሩ ሰዎችን እንዲህ ካለው አዙሪት አውጥቷቸዋል። ከነዚህ መሃል ፍሬደሪክ ሄይክ በበሽታና በብስጭት የአልጋ ቁራኛ የነበረ ሲሆን በወርሃ ህዳር 1974ዓ/ም አንዲት ማለዳ የጮኸች ስልክ ለማንሳት ከአልጋው ወረደ። ከስቶክሆልም የተደወለችው ስልክ  “የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆነሃል!” የምትል መልዕክት የያዘች ነበረች። ፍሬደሪክ ሄይክ ከዚች የስልክ ጥሪ በኋላ ተነቃቃ፥አሜሪካንም ለቆ ወደ ሃገሩ ጀርመን በመመለስ 18 የደስታ ዓመታት ኑሮ ወደማይቀረው ዓለም ሄደ። ጆን ናሽም እንዲሁ በድህነት እና በብቸኝነት ሲሰቃይ ቆይቶ በስተመጨረሻ የኖቤል ሽልማት በማግኘቱ ከድህነት ወጥቶ ይመኘው የነበረውን አይነት ኑሮ ሲኖር የቆየ ሲሆን ግንቦት 24 ቀን  2015ዓ/ም ኒውጀርሲ ውስጥ በደረሰበት የሚኪና አደጋ ህይወቱ አልፏል። ሩሰል ክሮው ‘ኤ ቢውቲፍል ማይንድ’ ፊልም ላይ ስብዕናውን ተክቶ የሚተውንበት፣የማቲማቲካል ኢኮኖሚክስ ሊቅ እና የጌም ቲወሪ ቀማሪ የሆነው ጆን የ86ዓመት አዛውንት የነበረ ሲሆን በደረሰበት የመኪና አደጋ አብራ ህይዎቷ ያለፈው ሚስቱ አሊካ ናሽ ደግሞ የ82 ዓመት ባልቴት ነበረች። ሁለቱ ባልና ሚስቶች አደጋው የደረሰባቸው ከኖርዌይ ንጉስ ሄራልድ 5ኛ እጅ የ400ሽሕ ዶላር ሽልማት ተቀብሎ ወደ ሃገሩ አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ ከኒዋርክ አየር ማረፊያ በታክሲ ወደ ቤታቸው በማምራት ላይ ሳሉ ነበር።

ዊሊያም ቬከሪም እንዲሁ የኖቤል ሽልማት ተዘፍቆበት ከነበረው ድህነት ገላግሎታል። በዘርፉ ከስዊድን የተሸለመው ብቸኛ ሰው የኢኮኖሚክስ ሳይንስ በኖቤል ሽልማት ዝርዝር ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ገነር ሚራድ ሲሆን ሽልማቱን ከፍሬደሪክ ሄይክ ጋር ለመጋራት አንገራግሮ ነበር። ፍሬዴሪክ ሄይክም “ድሮውንም ለሶሻሊስቶች መሬት በማይነካ፥ልብ አንጠልጥል ፍልስፍናቸው በስነፅሁፍ እንጅ በኢኮኖሚክስ ሽልማት መስጠት ተገቢ አልነበረም።ኢኮኖሚክስና ሶሻሊስቶች አይተዋወቁምና” ብሎ ነቁሮቷል። በዚህ የተበሳጨው ገነር ሚራድ ኋላ ላይ ሽልማቱን መቀበሉ ሲያበሳጨው የኖረ ሲሆን “የኢኮኖሚክስ ሳይንስ በኖቤል ሽልማት ውስጥ እንዲካተት ጥረት ማድረጌም ስህተት ነበር።”ብሏል። ሽልማቱ በተጀመረበት ወቅት የኖቤል ሽልማት የገንዘብ መጠን 77ሽህ የአሜሪካ ዶላር የነበረ ሲሆን ከጊዜ ወደጊዜ ከፍ እያለ መጥቶ 1ሚሊዮን 600ሽህ ዶላር ሊደርስ ችሏል።

በኢኮኖሚክስ ሳይንስ የኖቤል ሽልማት መሰጠት ከተጀመረ ከ1969ዓ/ም ወዲህ አንድም ኮሚኒስት የኖቤልን ሽልማት አላገኘም። ኢኮኖሚስት ሆና በኢኮኖሚክስ ሳይንስ እስከዛሬ ኖቤል የተሸለመች ሴት የለችም። ሆኖም ግን የፖለቲካ ጠበብቷ ኢሊኖር ኦስትሮም በኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚ ሆናለች። የፕሪንስተን ዩኒቨርስቲው አርተር ሉዊስ በዘርፉ ኖቤል የተሸለመ ብቸኛው ጥቁር ሰው ነው። የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲው አማርታያ ሴን በኢኮኖሚክስ የኖቤል ሽልማት ያገኘ ብቸኛ የኤዥያ ሰው ነው። ኢኮኖሚስት ሆኖ የሰላም የኖቤል ሽልማት ያገኘው ብቸኛ ሰው ደግሞ የአንስተኛ ብድር ልዩ አቅርቦት የጀመረውና የግራሚን ባንክ መስራቹ ባንግላዴሻዊው መሃመድ ዩኑስ ነው። የኖቤል ሽልማት ገንዘቡን በመጠቀም እጅግ በጣም ሃብታም ኢንቨስተር ለመሆን የቻለው ደግሞ ጣሊያናዊው ፍራንኮ ሞዲግሊያኒ ሲሆን የኖቤል ሽልማት ያገኘው በ1985ዓ/ም ነበር።

በኢኮኖሚክስ የኖቤል ሽልማት ካገኙት ሰዎች ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት በዩኒቨርስቲ ኦፍ ችካጎ የተማሩ ወይም ያስተማሩ ሰዎች ናቸው። ከነዚህም መካከል ፍሬደሪክ ሄይክ፥ሚልተን ፍሪድማን፥ጋሪ ቤከር እና ሮበርት ሉቃስ(ጁኒየር)  ይገኙበታል።  ሮበርት ሉቃስ(ጁኒየር) በ1989ዓ/ም ከሚስቱ ጋር ሲለያይ “ልብሽ የወደደውን ንብረት ሁሉ ውሰጅ። ከምትወስጅው ንብረት በተጨማሪም በሚቀጥሉት 5 አመታት የኖቤል ሽልማት የማገኝ ከሆነ የሽልማቱን ገንዘብ አካፍልሻለሁ” ብሎ ቃል ይገባላታል። አምስተኛው ዓመት ሊጠናቀቅ ቀናቶች እንደቀሩ በአንድኛው ማለዳ ጢርርርርርርር አለች የሮበርት ስልክ ከወደ ስቶክሆልም። አዎ ይህች የስልክ ጥሪ ሮበርት ሉቃስ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆኑን ነገረችው። ሮበርት ደስ ብሎት ወደ ቀድሞ ሚስቱ ደወለ። “የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆኔ ተነግሮኛል። ደስ ብሎኛል። የዛሬ አምስት አመት የገባሁልሽን ቃሌን አከብራለሁ።” ብሎ አስፈነጥዛት። በቃሉም መሰረት የሽልማቱን ማለትም የ1ሚሊዮን 600ሽህ ዶላር ግማሽ ሰጣት። ስምንት መቶ ሽህ ዶላር!!!

***ዘመኖቹ በሙሉ እንደ ኤሮፓዊያን አቆጣጠር(እኤአ) ናቸው።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.