ሉላዊነት ፣የንብረት ባለቤትነት መብት እና የሃብት ትስስር (በጁን አሩንጋ)

June Arunga

[በዚህ ጽሑፍ ኬንያዊቷ ጁን አሩንጋ በነጻ ንግድ አማካይነት የአፍሪካውያንን በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የመሳተፍ አስፈላጊነት ትተነትናለች። ለውጭ ኢንቨስተሮች ልዩ የጥቅም መብቶችን የሚሰጥን፣ የዜጎችን የንብረት መብቶች የሚጥስን፣የሀገር ውስጥ ልሂቃንን የልዩ ጥቅም ባለመብት የሚያደርግን፣የሌሎችን በእኩል ደረጃ የመነገድ እና ኢንቨስት የማድረግ ነጻነትን የሚነፍግን መሰናክሎች ትተቻለች። አመለካከትዋ በስልታዊ ኣካሔድ ነጻ ንግድን የሚደግፍ ነው፡፡ በልዩ የጥቅም መብቶችና በሞኖፖሊ ኃይሎች የነጻ ገበያ ካፒታሊዝም እንዳይፋለስና የአፍሪካ ህዝብ የንብረት መብቶች ይከበሩለት ዘንድ ድምፅዋን ታሰማለች።]

ከተሞክሮዬ እንዳየሁት በጣም ብዙዎች – ምናልባትም 90 በመቶ የሚያህሉ አለመግባባቶች መንስኤ የሚሆነው የሌላውን ወገን መረጃ አለማግኘት ነው፡፡ ሰዎች ከአንድ ባህል ወደ ሌላ ባህል ሲንቀሳቀሱ የሌላው ወገን መረጃ ያስፈልጋቸዋል። በባህል ጥበቃ ሰበብ በሚደረግ ተከላካይነት ፣ በብሔርተኝነትና አንዱ ሌላውን መረዳት ባለመቻል ተከስቶ ከነበረው የረጅም ዘመናት ከየእርስ በርስ መገለል በኋላ በአፍሪካ ምድር ላይ በአፍሪካውያኑ መካከል በጣም ሰፊ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት መጀመርን ልናበረታታና ልናከብር የሚገባ ይመስለኛል፡፡ የንግድ መስፋፋት አንዳንዶችን ያስፈራቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች መረጃ ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ብዬ አስባለሁ።

ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ዕውን እየሆነ ነው ፤ እናም ልንቀበለው የሚገባን ይመስለኛል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የእውቀት መስፋፋትንና ሌሎች በርካታ ነገሮችን በዓለም ዙሪያ ፈጥሯል፡፡ እንዲህም ሆኖ ብዙዎች ራሳቸውን ያገልላሉ፡፡ ጥያቄው ለምንድን ነው ነው? In defence of global capitalism በሚል ርዕስ በ2002 የታተመ ዓይን ገላጭ መጽሐፍ ደራሲ የሆነውን ስዊድናዊ ኢኮኖሚስት ጀሐን ኖርበርግን አገኘሁት፡፡ የመረጃ አጠቃቀም ዘዴው ግርምት ፈጠረብኝ፡፡

እርሱ የነፃ ገበያ ተቃዋሚዎችን እንዲሁ በቀላሉ የሚያልፋቸው ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይልቁንም ጆሮውን ሰጥቶ ያዳምጣቸዋል፡፡ አመለካከቶቻቸውን ግምት ውስጥ አስገብቶ ይመረምራል፡፡ ከእነርሱ የሚያገኘውንም መረጃ ይተነትናል፡፡ እርሱን ራሱን መጀመሪያ ላይ ካፒታሊዝምን ወደ መቀበል ያስኬደው ለተጨባጭ መረጃ የነበረው ፍላጎት ነው፡፡
እጅግ የተጎዱ ሰዎችን (ድሆችን) አስተያየቶች የሚሰበሰብበት አካሔድም ጭምር አስገርሞኛል፡፡ ኖርበርግ ጥያቄዎችን እየጠየቀ በዓለም ላይ ተዘዋውሯል፡፡ ሰዎች ምን ማሰብ እንዳለባቸው አይነግራቸውም፡፡ ነገር ግን የሚያስቡት ምን እንደሆነ ይጠይቃቸዋል፡፡ በነጋዴነትም ሆነ በዓለም አቀፍ ንግድ ድርጅቶች ውስጥ በቀጣሪነት የንግድ ስራ ተሳታፊ የመሆን እድል ያገኙትን ድሆች በመጠየቅ – የበላይ ኃላፊዎች (ባለስልጣናት) ማየት የተሳናቸውን ሐቆች ገሀድ ያወጣል፡፡ በአዲሱ ፋብሪካ መስራትዎ ፣ ኑሮዎን አሻሻለው ወይም ችግርዎን አባባሰው? ለመጀመሪያ ጊዜ የያዙት ተንቀሳቃሽ ስልክዎ ሕይወትዎን አሻሻለው ወይም ጉስቁልናዎን ከፍ አረገው? ገቢዎ ጨመረ ወይስ ቀነሰ? በምንድን ነው የሚጓጓዙት? በእግር ፣ በቤስክሌት ፣ በሞተር ሳይክል ወይስ በመኪና? በእግርዎ ከመጓዝ ይልቅ ሞተር ሳይክል መጠቀምን ይመርጣሉን? እያለ በመጠየቅ ኖርበርግ እታች (መሬት ላይ) ያሉ ተጨባጭ ሐቆች እንዲወጡ ይገፋፋል፡፡
ተጠያቄዎቹ ምን እንደሚያስቡና ነጻ ገበያው ሕይወታቸውን ማሻሻል አለማሻሻሉን ይጠይቃቸዋል፡፡ የእያንዳንዱ ግለሰብ ሐሳብ ይሰማል።

እንደርሱ አመለካከት መሪዎቻችን ምን እያደረጉልን ሳይሆን ምን እያደረጉብን እንዳሉ መጠየቅ ይገባናል፡፡ መሪዎቻችን እየጎዱን ነው ያሉት፡፡ ይሰርቁናል ፣ ንግድ ሥራ ላይ እንዳንሰማራ ይከለክሉናል ፤ ድሆችን ወደታች ይጫናሉ፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ውስጥ የሕግ የበላይነት ባለመኖሩ ምክንያት የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አይፈቀድላቸውም፡፡ የእነዚህ አገራት ገቢ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያትም ይኸው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም መሪዎች ለሕዝቦቻቸው አክብሮት የላቸውምና!
ብዙዎቹ የድሃ አገራት መንግስታት ትኩረት “የውጭ ኢንቨስተሮችን” መሳብ ላይ ነው እንጂ የገዛ ሕዝቦቻቸውን ወደ ንግድ እንዲገቡ መፍቀድ ላይ አይደለም፡፡ የሀገሮቻቸው ሕዝቦች ተወዳዳሪ መሆን ይችሉ ዘንድ ገበያውን ክፍት የማድረግ ስራ በአጀንዳዎቻቸው ላይ አያሰፍሩም፡፡ የሀገሬው ሕዝብ ከሌላው ይበልጥ የሚታየውና የሚረዳው “ሀገረኛ የሆነ ዕውቀት” አለው፡፡ ይሁን እንጂ የአፍሪካ መንግስታት ለመረጧቸው የውጭ ኢንቨስተሮችና በጥቅም ትስስር ለተደራጁ የራሳቸው ቡድኖች እየፈቀዱ ገዛ ሕዝባቸውን ከገበያ ውጭ ያደርጉታል፡፡

ለምሳሌ እንደ ባንክ፣ ቴሌ፣ውኃና የሃይል አቅርቦት ያሉ አገልግሎቶችን የመስጠት ስራ ላይ የሀገር ውስጥ ተወዳዳሪዎች እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ጠንካራ ገደቦች በመጣል ሕዝባችን ቴክኖሎጂን ፣ አማራጮችንና መሠረተ ልማትን የተመለከቱ ሀገራዊ እውቀቱንና ችሎታዎቹን እንዳይጠቀም ትኩረት ይነፍጉታል፡፡ ለ “ውጭ ኢንቨስተሮች” ልዩ እድል በመስጠት የራስን ዜጎች መግፋትና እንዳይወዳዳሩ ማድረግ “ሉላዊት” (“ግሎባላይዜሽን”) አይደለም፡፡ መሪዎቻችን የ“ውጭ ኢንቨስተሮች”ን ለመሳብ “ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች”ን ማዘጋጀታቸው ጥሩ ሐሳብ ከሆነ ፣ ለምንድንስ ነው ሰፊው ሕዝባችን ከእነርሱ ተጠቃሚ መሆን የማይችለው? የንግድን ነፃነት ለእያንዳንዱ ዜጋ ከማጋራት ይልቅ ለምንድነው የልዩ ጥቅማጥቅም መስጫ ልዩ ዞኖችን የሚያዘጋጁት? የንግድ ነፃነት ሕዝብ የሚገለገልበትን ነፃ የውድድር መድረክ መፍጠር ይገባዋል እንጂ የውድድር ፍላጎት ለሌላቸው የሀገሪቱ ልሂቃን (elites) ወይም ከሚኒስትሮች ጋር የተለየ ግንኙነት ላላቸው የውጭ ኢንቨስተሮች ልዩ ጥቅማጥቅም መስጫ መሆን የለበትም፡፡

ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በመሪዎች ፈቃድ የልዩ ጥቅማጥቅም መብት የሚያገኙበት አካሔድ “ነፃ ንግድ” ሊባል አይችልም፡፡ የሀገር ውስጥ ተቋማት በገዛ መሪዎቻቸው ከገበያ (ንግድ ስራ) የሚወገዱበት ስርዓት “ነፃ ንግድ” አይደለም፡፡ ነፃ ንግድ የሕግ በላይነት ለሁሉ መሆንንና በተፈጥሮኣዊ አካሔዶች ሁሉም የቻለው ድረስ – ፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ በንግድ ስራው (በልውውጡ) እንዲሳተፍ ማድረግ የሚያስችለን ነጻነት ነው።

እንደ አፍሪካዊነታችን ብልፅግናችን በውጭ ዕርዳታ ወይም በቀላል መንገድ በሚገኝ ገንዘብ የሚመጣ አይደለም፡፡ እሱን ብዙ አግኝተናል፡፡ ግና በድሆች ሕይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ አላመጣም፡፡ የዚህ ዓይነት ዕርዳታ ሙስናን ይፈጥራል። የሕግ በላይነትን ይጣረሳል ፤ ለጋሽ አገራት ውስጥ ካሉ የተለዩ ሰዎች (ድርጅቶች) ላይ አገልግሎቶችን የመግዛት እስራትን ይፈጥራል፡፡ ይህ የንግድ ግንኙነቶችን ያጎድፋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ “ዕርዳታ” መሪዎችን ከገዛ ሕዝቡ ያቆራርጣል፡፡

የንግድ ሥራ የሚኒስትሮችን ጆሮ ባገኙ የሀገር ውስጥ ልሂቃን ሊበላሽና ነጻ እንዳይሆን ሊደረግ ይችላል፡፡ እንዴት የሚለውን ራሳችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ የሀገር ውስጥንና የውጭን ተወዳዳሪዎች የማያካትት የሞኖፖሊ መብቶችን መስጠት ንግድን ያበላሻል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መሪዎቻችን ለውጭ ልሂቃን የሞኖፖል መብት ሲሰጡ የንግድ ስርዓት ይጎድፋል ፤ ነፃም ንግድ ሊኖር አይችልም፡፡ ይህ የሚሆነው የውጭ ልሂቃን ከራሳቸው መንግስታት ጋር በመነጋጋር በሚሰጡት ዕርዳታ ፣ ከመሪዎቻችን ጋር የራሳቸውን ጥቅም የሚያስከበር ድርድር በማድረግ የውል እስራት ውስጥ ስለሚከታቸው ነው። ድርድሩም የሀገር ውስጥና ሌሎች የውጭ ተፎካካሪዎች እንዳይካተቱ በውል የሚያስር ነው። እነዚህ ሁሉ ውሎች ነፃነታችንንና ገበያችንን የሚገድቡ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የጥራት ጉድለት የሚታይባቸውን ሽቀጣሸቀጦችና አገልግሎቶች እንድንገዛ እንገዳዳለን ፤ ወይም አዋጭ ያልሆነ ዋጋ የመክፈል ግዴታ ውስጥ ይከተናል። ምክንያቱም የምርጫ ነፃነት አይኖረንምና፡፡ የዚህ ዓይነቱ የነጻነት እጦት ቁልቁል የሚጫነንና ድህነታችን እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው፡፡

የምንዘረፈው በአዋጭ (በዝቅተኛ) ዋጋ መግዛት ባለመቻላችንና ጥራት የጎደላቸውን ሸቀጣሸቀጦችንና አገልግሎቶችን መግዛት በመገደዳችን ብቻ አይደለም፡፡ ሥራን የመፍጠር እድሎች ጭምር እናጣለን። አእምሮኣችንን እንዳንጠቀም እንደረጋለን፡፡ እምቅ ኃይላችንና እውቀታችን ጭምር ይመክናል፡፡ ይህ እየቀጠለ ሲሄድ በህዝብ ላይ የሚፈጸም ታላቅ ወንጀል ይሆናል፡፡ የተከላካይነትና የልዩ ጥቅማጥቅም መብቶች መኖር የኢኮኖሚን ክስረት የሚያስቀጥል ብቻ ሳይሆን እውቅትን ፣ አቅምን ፣ መልካም ባሕርይን ፣ ፈቃደኝነትን ፣ ቁርጠኝነትንና በራስ የመተማመን ዕምነትን ሁሉ ያጠፋል፡፡
እኛ የምንፈልገው መረጃ ነው፡፡ መሬት ወርደን ከሰዎች ጋር መነጋገር እንፈልጋለን፡፡ ተመሳሳይ ሐቆችን ማረጋገጥ እንሻለን፡፡ አብዛኞቹ ምስጢራት እይደሉም ፤ እንዲያውም ሚስጢር የሚመስሉት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የነፃ ገበያ ካፒታሊዝም ፣ የንግድ ነጻነትና በሕግ የበላይነት ስር የእኩል መብቶች መኖር ለሰፊው ሕዝብ ብልጽግናን መፍጠር ስለማስቻላቸው የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡

እኛ የምንፈልገው እምቅ ኃይላችንን መገንዘብና መጠቀም እንድንችል መድረክ የሚፈጥርልንን የነጻ ገበያ ካፒታሊዝምን ነው፡፡ ሔርናንዶ ዲ ሶቶ የተባለው ፔሩያዊ ኢኮኖሚስት ሰዎች ኑሮኣቸውን ለማሻሻል “ሙት ካፒታልን” እንዴት ወደ “ሕያው ካፒታል” መቀየር እንደሚችሉ ግልጽ አድርጎ ጽፏል። የካፒታል አጥረት ወይም እጦት የሚገታን አይደለም፡፡ እኛ አፍሪካ ውስጥ የሚንገኝ ብዙ ብዙ ካፒታል አለን፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛው ካፒታል ሕይወታችንን ማሻሻል በሚችልበት ሁኔታ ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ በቃ “ሙት” ነው፡፡ የተትረፈረፈው ካፒታላችን ሕይወት የሚፈጥር “ሕያው ካፒታል“ እንዲሆን ለማድረግ የንብረት ባለቤትነት መብቶቻችን እንዲሻሻሉ እንፈልጋለን፡፡ ንብረት እንፈልጋለን፡፡ ይህም ማለት መብቶቻችን እንዲከበሩ እንፈልጋለን ማለት ነው፡፡ በሕግ ፊት እኩልነትን እንፈልጋለን።የነጻ ገበያ ካፒታሊዝምን እንፈልጋልን፡፡

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.