የእኩልነት እና የልዩነት የሞራል መሰረቶች

እንደሚታወቀው ገበያ የግድ እኩል ሐብትን መፍጠር እንደማያስችለው ሁሉ በአንጻሩ የግድ እኩል መነሻ ሐብትንም አይጠይቅም፡፡ ይህ መሆኑ ገበያ ለምን ኖረ ሊያስብለን አይችልም፡፡ ልዩነት(inequality) በገበያ ላይ በሚደረግ ልውውጥ የሚፈጠር እንግዳ ያልሆነ ውጤት ሲሆን ይልቁንም ለልውውጥ መኖርም አስፈላጊ የሆነ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ አለልዩነት የሚካሔድ ልውውጥ ትርጉም ያለው አይሆንም፡፡ ሐብት በገበያ አማካኝነት ለማህበረሰብ እንዲዳረስ በሚደረግበት ሁኔታ ውስጥ የገበያ ልውውጥ እኩልነትን እንዲፈጥር ተስፋ ማድረግ ቂልነት ነው፡፡ ለነፃ ገበያ ተግባራዊነት፣ መለዋወጥ የሚያስችል እኩል ነፃነትን ጨምሮ የእኩል መሰረታዊ መብቶች መኖር ያስፈልጋል፡፡ ነፃ ገበያ ከሕጋዊ መብቶች መረጋገጥ በስተቀር እኩል ሐብት እንዲያስገኝ ተስፋ ማድረግም ሆነ የሁኔታዎች እኩልነት ላይ እንዲመሰረት መጠበቅ ተገቢ አይደለም።

እኩልነትን እንደ ሞራል ጉዳይ ማየቱ ፍፁም አስቸጋሪ የሚሆን ነገር ነው፡፡ እኩልነትን ማምጣት ዋነኛ ጉዳያቸው ባደረጉና ባላደረጉ ጎራዎች መካከል ያሉትን የአተያይ ልዩነቶች መመልከት እንችላለን፡፡ በዚህም መሰረት ወደ እኩልነት መሔድን ዋነኛ ጉዳያቸው ያደረጉት የኢጋሊታሪያን አተያይ (Egalitarian Perspectives) ያላቸው ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ይህን አተያይ የማይጋሩት ኢ-ኢጋሊታሪያኖች ናቨው። የኢ-ኢጋሊቴሪያን አተያይ (nonegalitarian perspectives) ያላቸው የእኩልነት አስፈላጊነት ላይ ትኩረት አይሰጡም። ልዩነት ወይም ኢ – እኩልነትም (inequality) የግድ መኖር አለበትም አይሉም፡፡ ሆኖም ግን እኩልነትን ብቻ እንደ ግብ የሚያነሱትን የኢጋሊታሪያኖች ዋነኛ ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡ በተለይ ሊካተቱ የሚገቡ ሌሎች ግቦችን አለማካተታቸውንና በቁሳዊ ሐብት እኩልነት መረጋገጥ ላይ ብቻ ማትኮራቸውን ይነቅፋሉ፡፡ የክላሲካል ሊብራል (ወይም ሊበሪታሪያን) ኢ-ኢጋሊታሪያኖች የመሰረታዊ መብቶች እኩልነት አስፈላጊ ነው ይላሉ። በመሆኑም የኢጋሊቴሪያውያኖች አተያይ ከኢ-ኢጋሊቴሪያዉያኖች አተያይ ይለያል፡፡ (የመብቶች እኩልነት የዘመናዊውና የነፃው ማህበረሰብ ሕዝቦች የደረሱበት የሕግ ፣ የንብረት እና የመቻቻል ተሞክሮ ዋነኛ መሰረት ነው፡፡) ኢ-ኢጋሊቴሪያን ሊበርታሪያኖችና ክላሲካል ሊበራሎች አመለካከታቸው እጅጉን የጠራ ፣ የማይሻር ዕውነታ ወይም ዘላቂነት ያለው ስለመሆኑ ይመሰክራሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የሐብት “ክፍፍል” እኩልነት በአጠቃላይ ተግባራዊ መሆን የማይችል ነገር ግን ቅርፃዊ የሆነና በቃላት ብቻ የሚገለፅ እኩልነት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የመነሻ ሐብትች እኩልነት ወይም የልውውጥ ውጤት በሆነ የሐብት እኩልነት ላይ ከማተኮር ይልቅ አንድ ግለሰብ ከሌሎች ጋር የሚኖሩትን ግንኙነቶች (በገበያ ላይ የሚደረጉ ልውውጦችን ጨምሮ) ለመገምገም እንደመሰረት የሚጠቅመው የግለሰቡ የሞራል ደረጃ እኩልነት ወይም ኢ-እኩልነት(ልዩነት) ላይ ማትኮሩ የተሻለ ትርጉም ይሰጣል፡፡ በዚህም መሰረት ማንም ሰው ከማንኛውም ሰው የሚልቅ (ወይም የሚያንስ) የሞራል ደረጃ አይኖረውም ወይም በአማራጭነት አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች በሞራል የላቁ (ወይም ያነሱ) ናቸው፡፡ አሁን ይህን መሰረት አድርጎ አንድ ሰው የመነሻ ሐብት ወይም ከልውውጥ ሒደቶች ውጤት የተገኘ ሐብት እኩል የመሆን አስፈላጊነት ወይም አላስፈላጊነት ላይ መከራከር ይችላል፡፡

ሁለት በሞራል እኩል ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ጠዋት ጠዋት የሚጠጡት ቡና በመጠን ፣ በጥራትና በዋጋ ግድ ተመሳሳይ ለሆን ይገባልን? በማለት እንጠይቃለን። ወይም አንድ ገንዘብ በመለገስ የሚታወቅ ሰውና ገንዘብ የማይሰጠው ጎረቤቱ ፣ ሁለቱም እኩል የሞራል ደረጃ ያላቸው፣እኩል ዋጋ የሚያወጡ ፍራፍሬዎችን በእኩል መጠን የሚያፈሩ ማሳዎች ግድ ሊኖራቸው ይገባልን? በሞራል ደረጃ እኩል መሆን ለመነሻ ሐብት ፣ ለፍጆታ ቁሳቁሶች ወይም ለይዞታዎች እኩልነት የሚያበረክተው ፋይዳ የለም፡፡ እኩል ጠቀሜታ ያለው የሞራል ደረጃ ያላቸውን የሁለት ቼዝ ተጫዋቾችን የግንኙነት ሁኔታ እንመልከት፡፡ በሞራል እኩል ከመሆናቸው የሚገኝ ጠቀሜታቸው ፣ የተጫዎቾቹን ችሎታዎች ግድ ተመሳሳይ መሆን ይጠይቃልን? ወይም እያንዳንዱ ግጥሚያ ባለመሸናነፍ መጠናቀቅ ይገባልን? ወይም ሁለቱም ተመሳሳይ የአጨዋወት ሕጎችን እንዲከተሉ ይጠይቃቸዋልን? በግጥሚያዎቻቸው ሁሉ ሳይረታቱ ይለያዩ ዘንድ የተለመደውን የጨዋታ ሕግ እንዳይከተሉ የሚያስገድዳቸው የትኛው ሐቅ ነው? በእኩል የሞራል ደረጃ፣ በመነሻ ሐብት እንዲሁም የሥራ ውጤት በሆነ ሐብት መካከል አንዳችም ቀጥተኛ ትስስር የለም፡፡

ለምሳሌ በእንትና ኪስ ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ አለ ማለትና የገንዘቡስ መጠን ጎረቤቱ ከሆነው ሰው ኪስ ውስጥ ከሚገኘው ጠቅላላ ገንዘብ ስለመብለጡ ወይም ስለማነሱ በጉዳይነት ማንሳት በራሱ ለሰው ልጅ ሕይወት ሞራላዊ ፋይዳ ያለው ነገር አይደለም፡፡ መሆን ያለበት ግን ገንዘቡ እዚያ ኪስ ውስጥ በምን መንገድ ገባ የሚለው ነው፡፡ አንድን ታክሲ ሾፌርና አንድን ታታሪ ነጋዴ ወስደን ድርጊቶቻቸውን ከሁለንተናዊ የሞራል ደረጃዎች ጋር የመጣጣሙን ሁኔታ መሰረት በማድረግ ለምሳሌ የፍትህ ስርዓቶችን እንዲሁም በራሳቸውና በሌሎች ሰዎች ህሊና ውስጥ ያለውን የሞራል ብይን ማክበር አለማክበራቸውን በመንተራስ ፍትኃዊ ወይም ኢ-ፍትኃዊ ብለን ልንፈርጃቸው እንችላለን፡፡ ይህ ግን የሁለቱን ሰዎች ባሕርይ እንጂ ሐብት ወይም ከገበያ ልውውጥ ውጤት ያገኙትን ሐብት መጠን አይወስንም፡፡ ለብልፅግናም ሆነ ለድህነት ወሳኝ የሆነው የሰዎች ድርጊት (ተግባራዊ እንቅስቃሴ) እንጂ ሙገሳና ወቀሳ አይደለም፡፡

የሐብትንና የእኩልነትን ተዛምዶ ወደ መመልከቱ እንመለስ፡፡ የሐብት ይዞታዎች የፍትኃዊ ባሕርይ ወይም የአስገዳጅ ኃይል ውጤቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ የሚካሄዱ ልውውጦች የበለጠ ልዩነትን ወይም እኩልነትን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ የመንግስት ጣልቃ ገብነትና የሐብት መልሶ ስርጭትም የበለጠ ልዩነትን ወይም የበለጠ እኩልነትን መፍጠር የሚችል ነው፡፡ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር በየትኛውም ዓይነት መስተጋብር የግድ እኩል የሆነ ወይም የግድ እኩል ያልሆነ ነገር የለም፡፡ አንተርፕርነር ሐብት መፍጠር በመቻሉ ከሌላው ሰው የበለጠ ሐብት ይኖረዋል፡፡ ሐብት ፈጣሪው ሌላውንም ጭምር መጥቀሙ እንዳለ ሆኖ፡፡ በነፃ ገበያ ውስጥ የሚከናወኑ ልውውጦች ከቀድሞ ሥርዓቶች በውርስ የተወራረዱትን ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ የጉልበተኞችን የጥቅም መብቶች በመሸርሸር ብልፅግናን አስፋፍቶ የበለጠ እኩልነትንም ሊፈጥር ይችላል፡፡ ዘራፊ አንድን ሰው ዘርፎ የዝርፊ ሰለባ ከሆነው ሰው የበለጠ ሐብት በመያዝ የበለጠ ኢ-እኩልነትን ይፈጥራል ፣ ወይም የተዘራፊውን ሰው ያህል ሐብት በመያዝ የበለጠ እኩልነት ሊፈጥር ይችላል፡፡ በተመሳሳይም መንገድ በስልጣን ኃይል የተደራጀ የመንግስት ጣልቃ ገብነት በገበያ ተዋናዮች ምርጫዎች (ፍላጎቶች) ላይ በመረማመድ (ገበያ ጥበቃን ፣ ድጎማንና “ኪራይ ሰብሳቢነት”ን ምክንያት በማድረግ) ወይ ደግሞ በኮምዪኒስት አገዛዝ ስር በነበሩ አገሮች ውስጥ ሲደረግ እንደነበረው አረመኔያዊ የኃይል እርምጃና ጥቃት ብቻ እጅግ የሰፋ የሀብት ኢ-እኩልነትን ሊከሰት ይችላል፡፡

ሕጋዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት የላቀ ወይም ያነሰ የገቢ እኩልነት ስለመፍጠሩ መለኪያ የሚሆነው ፅንሰ ሐሳባዊ ነገር ሳይሆን ተግባራዊ / ሙከራዊ ነገር ነው፡፡ የዓለም የኢኮኖሚ ነፃነት ሪፖርት (www.freetheworld.com) የአገራትን የኢኮኖሚ ነፃነት ደረጃዎችን በመለካት ከተለያዩ የኢኮኖሚ ማመላከቻዎች (ከመኖሪያ ዕድሜ ፣ ከትምህርት ሽፋን ፣ ከሙስና መንሰራፋት ፣ ከነፍስ ወከፍ ገቢ ወዘተ… ) ጋር ያነጻጽራል፡፡ መረጃው እጅግ ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች ነዋሪዎች ኢኮኖሚያቸው ነጻ ካልሆኑ ሃገራት ዜጎች አንጻር እጅግ ይበልጥ በሐብት የበለፀጉ መሆናቸውን ከማመላከቱም በላይ በነዚያ ሃገራት ያለው የገቢ ልዩነት በፖሊሲዎች ልዩነት ምክንያት አለመምጣቱን ይጠቁማል።

ሆኖም ግን ኢኮኖሚያቸው ነጻ በልሆኑ ሃገራት ዜጎች መካከል ያለው የገቢ መጠን ልዩነት ግን የፖሊሲዎች ልዩነት ውጤት መሆኑን አሳይቷል፡፡ የዓለም አገራትን በአራት ቡድን የከፋፈለው ሪፖርት(እያንዳንዱ ቡድን 25%(በመቶ) የሚሆነውን የዓለም አገራት ያካትታል)፣ ነጻ በመሆን ደረጃ ከቡድኖቹ የመጨረሻ ወይም አራተኛ ተርታ ላይ በተቀመጠው ቡድን ውስጥ ያሉ የመጨረሻ ድሃ የሆኑት የ10%ቱ (በመቶ) ሕዝብ አማካይ የብሔራዊ ገቢ ድርሻ እኤአ በ2008 ዓ/ም 2.47%(በመቶ) የነበረ ሲሆን ፣ ቀጥሎ ነፃ በመሆን ደረጃ በሶስተኝነት ላይ የተቀመጠው ድርሻ 2.19%(በመቶ) ነበር። በሁለተኛነት ነፃ የተባለው ደግሞ 2.27%(በመቶ) ሲሆን አንደኛ (እጅግ) ነፃ የሆነው ቡድን ደግሞ 2.58%(በመቶ) ነበር፡፡

በእነዚህ ቡድኖች መካከል ጎልቶ የሚታል (ወሳኝ) ልዩነት የለም፡፡ ይህም ማለት እንደዚህ ዓይነቱ ልዩነት በኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያዎች ከሚከሰት ተፅዕኖ ነፃ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ሲታይ አስር በመቶ (10%) የሚሆኑት የመጨረሻ ድሆች የሚያገኙት የገቢ መጠን በሰፊው ይለያያል፡፡ የልዩነቱ ትክክለኛ ምክንያት ከኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ተፅዕኖ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ከአራተኛው ወይም የመጨረሻ ዝቅተኛ ነፃ አገራት ከሆኑት አስር በመቶ (10%) ያህሉ የመጨረሻ ድሆች ውስጥ መሆን ማለት ግን ዘጠኝ መቶ አስር ($910) የአሜሪካ ዶላር አማካይ ዓመታዊ ገቢ ማግኘት ማለት ነው። እጅግ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ካላቸው አስር በመቶ (10%) የመጨረሻ ድሆች ውስጥ መሆን ማለት ደግሞ ስምንት ሽህ አራት መቶ ሰባ አራት ($8474) የአሜሪካ ዶላር አማካይ ዓመታዊ ገቢ ማግኘት ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በአራተኛው ምድብ ሃገራት ውስጥ ለምሳሌ በኢትዮጵያ፣ዚምቧቢዬ፣ እና ሶሪያ የሚገኙት ድሆች ከሃገራቸው ይልቅ በአንደኛውም ምድብ ሃገራት ውስጥ ለምሳሌ በስዊዘርላንድ ወይም በሆንግ ኮንግ ድሃ መሆን እጅጉን ይሻላቸዋል ማለት ነው።

እኔና እናንተ ነፃ ልውውጥ ከማካሔዳችን በፊት እኩል መነሻ ሐብት ኖረንም አልኖረንም ወይም ነፃ ልውውጥ ካደረግን በኃላ እኩል ሐብት አፈራን አላፈራን ይህ በራሱ የሞራል ችግር አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይበልጥ እኩል የሆኑ የልውውጥ ትሩፋቶች ይፈጠሩ ዘንድ በምናደርጋቸው ጥረቶች ሁሉ (እንደዚህ ያሉ ውጤቶችን መፍጠር ቀላል እንዳለመሆኑ ፣ ይህን ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ማድረግ የሚቻል አይመስልም) በሞራል እኩል የሆኑ ሰዎችን በእኩል ሁኔታ ማስተናገድንና እኩል ሕጎችን በእነርሱ ላይ መተግበርን አለመፍቀድ በእርግጥም የሞራል ችግር ነው፡፡ ይህም ማለት በዋነኝነት አስፈላጊ የሆነውን የሞራል እኩልነት መጣስ ማለት ነው፡፡

የሐብት ኢ-እኩልነትን (ልዩነትን) አስመልክቶ በዓለም ላይ እየተነገረ ያለው መጥፎ ዜና ነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት ባላቸው ማህበረሰቦች ውስጥ ስለሚገኙ ሐብታሞችና ድሆች መካከል ስላለው የሐብት ልዩነት ሳይሆን ነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት በሚከተሉ እና ነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓት በማይከተሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ስላለው የሰዎች ሐብት ልዩነት መግዘፍ ነው፡፡ በመበልጸግና በመደህየት መካከል ያለው ይህ ክፍተት በኢኮኖሚያቸው ላይ ያወጧቸውን የማያሰሩ ገዳቢ ሕጎች እና አላስፈላጊ ቁጥጥሮች በማንሳት መቀየር ይችላሉ። በሌላ አነጋገር ነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት የማይከተሉት ደሃ ሀገራት በኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ለውጥ በማድረግ በእርግጠኝነት ነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት ከሚከተሉት ሀገራት ዜጎች ጋር ያላቸውን ትልቅ የሃብት ልዩነት ማጥበብ ይችላሉ። ነፃ ያልሆነ የኢኮኖሚ ስርኣት ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን ነፃ በማውጣት ለዓለም መጠነ ሰፊ ሃብት እንዲፈጠር ማድረግ ይቻላል። በዓለም ዙሪያ የሚታየውን ስር የሰደደ ድህነትም መቀነስ ይቻላል። ለዚህ እውን መሆን ደግሞ ሁላችንም ለፍትህ መረጋገጥ ህዝብን ማንቃት ይገባናል። ንቃት አዎንታዊ ቅጥያን የሚያመጣ በመሆኑ ከአምባገነኖች መዳፍ ፤ በሙስና ከተዘፈቀ ሥርዓት፣ ከጠብመንጃ አገዛዝ እንዲሁም ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር ፈጽሞ ተዛምዶ ከሌላቸው የሶሻሊዝም እና ክሮኒዝም ኢፍትሃዊ እና አድሎ የሞላበት የጭቆና ቀንበር ያላቅቃቸዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ማለት የፍትህ መስፈርቶች እኩል መሆን ፣ የማምረትና የመለዋወጥ መብቶች ለሁሉ በእኩል ደረጃ መከበር ማለት ሲሆን ይህ ሞራል ያላቸው ፍጡራን የፍትሃዊነት ትክክለኛ መመዘኛ ነው፡፡

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.