ግለሰቦችን ያለ አገልግሎት ክፍያ እንዲሰሩ በማድረግ የአንድን ማህበረሰብ ሞራል መገንባት ይቻላልን?

ሌይ ፌንግ የሕይወት ታሪክና ሥራዎቹ በሃገረ ቻይና በሰፊው ናኝተውለት ነበር። ሌይ ፌንግ የጥገና ሥራው ፋታ አልነበረውም። ሰዎች የተበሳሱና የተሸነቋቆሩ የማብሰያ ቁሳቁሶችን ይዘው ከፊት ለፊቱ ረጅም ሰልፍ በመስራት ሲጠባበቁ ምስሉ በቴሌቪዥን ተደጋግሞ ይያይ ነበር። በምስሉ ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ሕብረተሰቡ የሌይ ፌንግን አርአያነት እና የሥራ ጥረት በቀናነት አይቶ ለተመሳሳይ የሥራ ጥረት እንዲበረታታ ነበር፡፡ በምስሉ የሚታየው የሰዎች ሠልፍ ረጅም ባይሆን ኖሮ ፕሮፖጋንዳው የማሳመን ኃይል ሊኖረው እንደማይችል ልብ ማለት ያሻል፡፡

ማንቆርቆሪያዎቻቸውንና ድስቶቻቸውን ለማስጠገን እዚያ ተኮልኩለው የነበሩ ሰዎችም ከሌይ ፌንግ ለመማር እዚያ ስፍራ ባልተገኙ ነበር፡፡ ሆኖም የዚህ ዓይነቱ ፕሮፖጋንዳ አንዳንድ መልካም ስራዎችን ለሌሎች ማስተማር የሚያስችል ሲሆን በዚያውም ጎን ለጎን በግል ደረጃ ሰዎች ከሌሎች ሥራዎች እንዴት ይበልጥ መጠቀም እንደሚችሉ የሚያስተምር ነው፡፡ በአንጻሩ ባለፉት ዘመናት ሰዎች ሌሎችን ያለምንም ክፍያ እንዲያገለግሉ የሚያነሳሱ ፕሮፓጋንዳዎች ማህበረሰባዊ ሞራልን ለመገንባት በሚል ሰበብ ይካሄዱ ነበር። [ይሁን እንጂ ከግለሰቦች ጥቅም እና ውስጣዊ መሻት ጋር ቁርኝት የሌለው ፕሮፖጋንዳ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር ስለማይጣጣም ስኬታማ አይሆንም። ግለሰቦች ለራሳቸው የሚያስቡትን እና ማድረግ የሚፈልጉትን ማድረግ ካልቻሉ ሞራል አይኖራቸውም። ሞራል የሌላቸው ግለሰቦች ሌሎችን እንዴት ማገልገል እንደሚችሉም አያውቁም። ሞራል ያለው ማህበረሰብ ሞራል በሌላቸው ግለሰቦች ይገነባል እንዴ?]

ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ከማግኘት አንፃር ስንመለከት ፣ ሌሎችን ለማገልገል የምንገባው ሁለንተናዊ ግዴታ እርባና የለሽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ነፃ የጥገና አገልግሎቶችን የማግኘት ሱስ ያደረባቸው ሰዎች ጥቅም የለሽ የተበላሹ ዕቃዎችን ምናልባትም የተጣሉ ዕቃዎችን ሳይቀር ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ዕቃዎችንም ለማስጠገን የሚፈለግባቸው ክፍያ ባለመኖሩ ምክንያት የጥገና ሥራው በሌሎች ትከሻ ላይ የሥራ ጫናን ይፈጥራል። እቃው በነጻ የሚጠገንለት የእያንዳንዱ ሰው አማካይ ወጭ በሰልፉ የሚያባክነው ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡ በጥቅሉ ከማህበረሰባዊ ጠቀሜታ አንፃር ሲታይ በተበላሹ እቃዎች ላይ የባከነው ጊዜ፣ የተደረገው ጥረት እና ለመጠገን የዋለው ቁስ ሁሉ የማያገለግሉ ወይም እምብዛም የማይጠቅሙ ዕቃዎችን የሚያስገኝ ሆኖ እናገኛለን። ነገር ግን የባከነው ጊዜና ቁሳቁስ ይበልጥ ምርታማ ለሆኑ ተግባራት ውሎ ቢሆን ኖሮ በእርግጠኝነት ለማህበረሰቡ የላቀ እሴት ይፈጥር ነበር፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ብቃትና አጠቃላይ ደህንነት አኳያ ይህ ክፍያ አልባ የጥገና ሥራ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ሌይ ፌንግ የሌሎችን ቁሳቁሶች በነጻ የሚጠግኑ ሰዎች መስፋፋት ቀደም ብለው በቁሳቁስ ጥገና ንግድ ላይ ተሰማርተው የነበሩትን ሰዎች እያዳከመ ስለሚሄድ ብዙ ሰዎች ከሥራቸው ይፈናቀላሉ። ይህ ደግሞ ለችግር ይዳርጋቸዋል። ችግረኛ የማህበረሰቡ አባላትን በመርዳቱ የሌይ ፌንግ ትምህርት አዎንታዊ ነውና አልቃወመውም፡፡ ነገር ግን ሌሎችን በነጻ የማገልገሉ ግፊት ትርምስንና ቀውስን ይፈጥራል፡፡ የሌይ ፌንግንም የመልካምነት ተግባር እና መንፈስ እንከናማ ያደርጋል።

በርግጥ ማህበረሰባችን ለእንዲህ አይነቱ አስተያየት በጎ ምላሽ የለውም። ይሄውም የሚመነጨው በእነርሱ ግምት ሌላው ከምንም በላይ ገንዘብን ሰለሚያስበልጥ ይመስላቸዋል፡፡ እንደነርሱ አስተሳሰብ ነጋዴዎች ወይም ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ምንም ዓይነት ችግር የማይደርስባቸው ይመስላቸዋል። ሐብታሞችንም ከቀሪው ማህበረሰብ በላይ የሆኑ አድርገው ያስባሉ። ድሆች ብቻ ለሰብዓዊነት ሥራ የሚታትሩ ነገር ግን የችግር ኑሮ የሚገፉ ይመስላቸዋል። ገንዘብ በሰዎች ግንኙነት ውስጥ ከተለመደው ሚናው ውጭ የተሻለ ነገር አይፈጥርም የሚል እምነት አላቸው። በዚህም የተነሳ ስለገንዘብ፣ ስለሸቀጦችና አገልግሎቶች እንዲሁም የዋጋ ተመን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች አይነጋገሩም። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በመረዳዳት እና በመተሳሰብ ላይ የሚቆምን ማህበረሰብ መፍጠር ይፈልጋሉ። ይህ ማለት ደግሞ ገበሬዎች ያለ አንዳች ክፍያ የመብል ሰብሎችን ያምርቱ፣ሸማኔዎች ያለክፍያ ለዜጎች ሁሉ አልባሳት ይሸምኑ፣ ፀጉር አስተካካዮች የማንኛውንም ሰው ፀጉር ይቁረጡ የሚባልበትን ማህበረሰብ መፍጠር ማለት ነው። ግና የዚህ ዓይነት ማህበረሰብን እውን መፍጠር ይቻላልን?

ለዚህ ጥያቄ ከርዕሰ ጉዳያችን ትንሽ ወጣ በማለት ቀላል መልስ እንፈልግለት። አንድን ፀጉር አስተካካይ እንውሰድ፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት ወንዶች ከሦስት እስከ አራት ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ፀጉራችን አንዴ ይቆረጣሉ፡፡ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ወንዶች ከሶስት እስከ አራት ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ፀጉራቸውን አንዴ ይቆረጣሉ። ይሁንና ፀጉርን በነጻ የሚቆረጡ ሰዎች ቢኖሩ ወንዶቹ ፀጉራቸውን ለመስተካከል ወደ ፀጉር ቤት የሚሄዱት በየሳምንቱ ይሆን ነበር። ለፀጉር ቆረጣ ሥራ ገንዘብ ማስከፈሉ በሥራው ላይ የሚሰማራውን የሰው ኃይል በተሻለ መንገድ መጠቀም ያስችላል፡፡ ለፀጉር አስተካካዮች የሚከፈለው የአገልግሎት ዋጋም ወደዚህ ሥራ የሚሰማሩትን የማህበረሰቡ አባላት ቁጥር ይወስናል፡፡ የሚከፈለውን የአገልግሎት ዋጋ መጠን መንግስት ዝቅ ቢያደርግ ፀጉር መቆረጥ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ስለሚጨምር የፀጉር ቆራጮችም ቁጥር መጨመር ግድ ይላል፡፡ የዋጋ ተመን በማውጣት የባለሙያንም ሆነ የምርትን መጠን መጨመር አይቻልም።በመሆኑም የፀጉር ቆረጮችን የአገልግሎት ክፍያ መቀነስ ፀጉር መቆረጥ የሚፈልጉ ሰዎችን የሚያበዛውን ያህል ውስን ቁጥር ያላቸውን ፀጉር አስተካካይ ባለሙያዎች በመጨመር ረገድ የሚኖረው ትርጉም አይኖርም። ይህ የፀጉር ቆረጣ ሥራን የተመለከተው እውነታ ፣ በሌሎችም የሥራ መስኮች ላይ የሚሠራ እውነታ ነው፡፡

በብዙዎቹ የቻይና ገጠራማ አካባቢዎች ነፃ አገልግሎቶችን የመሰጣጣቱ ስራ በሰፊው የተለመደ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ አዲስ ቤት መገንባት ቢፈልግ ፣ የግንባታውን ስራ ለማገዝ ዘመዶቹና ጓደኞቹ ሁሉ ይሰባሰባሉ፡፡ በግንባታው ሥራ ላይ ለተሳተፉት ሰዎች ትልቅ የምግብ ግብዣ ከማድረግ ውጭ በስተቀር አንዳችም የገንዘብ ክፍያ አይሰጥም፡፡ ሥራው ላይ ከተሳተፉት ሰዎች መካከል በሌላ ጊዜ እንዱ አዲስ ቤት መገንባት ቢፈልግ ፣ ቀደም ብሎ እገዛ የተደረገለት ሰው ውለታ ከፋይ ነውና ለዚህኛው ሰው እሱም የግንባታ እገዛ ያዳርጋል፡፡ ዘወትር የኤሌክትሪክ መስመሮችን ዘወትር ያለምንም ክፍያ ለሚዘረጉ የጥገና ሰራተኞችም ክፍያ አይፈጸምም። ሰራተኞቹም አዲስ ዓመት በመጣ ጊዜ ብቻ ከባለቤቱ የማካካሻ ስጦታ እንዲሰጣቸው ይጠብቃሉ፡፡ ይህን የመሳሰለ ገንዘብ ነክ ያልሆነ ልውውጥ ፣ለሰጡት አገልግሎት ወይም ለተመሳሳይ አገልግሎት ሊከፈል የሚገባው የዋጋ መጠን ምን ያህል እንደሆነ በትክክል መለካት አያስችልም፡፡ በዚህም የተነሳ የሰራተኛው የጉልበት ዋጋ በበቂ ደረጃ አያድግም፤ በማህበረቡ ውስጥ የስራ ክፍፍልም አይኖርም፡፡ በገንዘብ የተገለጹ ዋጋዎችን ወይም የሥራ ክፍያ መጠቀም ለማህበረሰባዊ ልማት ወሳኝ ሚናን የሚጫወተውን ያህል ከሐብት ክፍፍልም እጅግ የላቁ ጠቀሜታዎችን ማግኘት የሚያስችል ወሳኝ ዘዴ ነው፡፡

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.