669 ሕፃናትን ከሒትለር የሞት ድግስ ያወጣ ጀግና!!

ሰር ኒኮላስ ዊንተን /Sir Nicholas Wintonእኤአ ከ1938ዓ/ም – 1939ዓ/ም በአውሮፓ ላይ የጦርነት ደመና ያንዣበበበት ወቅት ነበር። ሰር ኒኮላስ ዊንተን በሎንዶን አክስዮን ሻጭ ሆኖ ይሰራ በነበረበት በዚያ ጊዜ ጓደኛው ገፋፋውና የገናን በዓልን ለማክበር ወደ ስዊዘርላንድ ሊያደርግ የነበረውን ጉዞ ሰርዞ ወደ ቼኮዝላቫኪያ ያመራል፡፡ እኤአ ታህሳስ 1938ዓ/ም በቼኮዝላቫኪያ መዲና ፕራግ ከተማ አቅራቢያ ማመን የሚያቅት እንግዳ ነገር በአይኑ አየ። እየታደኑ በማቆያ ካምፖች ውስጥ የታሰሩ የአይሁድ ስደተኞችን የተመለከተው ኒኮላስ ዊንተን በድንጋጤ ተሸማቀቀ፡፡ ሰዎቹ በመስከረም ወር በሒትለር እጅ ከወደቀችው የቼክዝሎቫኪያዋ ‘ሱደንትላንድ’ ከየመኖሪያ ቤቶቻቸው በኃይል ተጎትተው የተሰበሰቡ ነበሩ፡፡ ኒኮላስ ዊንተን የሰረዘውን እና ወደ ሰዊዘርላንድ ሊያደርግ የነበረውን የገና በዓል ከበር ቻቻ እና የዕረፍት ጊዜውን ቀደም ብሎ ባቀደው መንገድ ሊያደርግ ይችል ነበር። ሆኖም አውሮፓ ወደ ጦርነት እየገባች እንደሆነ እና እነዚያ ቀቢፀ – ተስፋ ውስጥ ያሉ ታጋቾች ሊተርፉ የሚችሉበት ጊዜ እያጠረ ያለ መሆኑን ዊንተን ተገንዝቧል። ግን ደግሞ እነዚያን ሁሉ ታጋቾች አንድ የውጭ አገር ዜጋ ምን በማድረግ ሊታደጋቸው እንደሚችል እንቆቅልሽ ይሆንበታል።

ወላጆች ይመጣል ብለው ከፈሩት የጦርነት መቅሰፍት ልጆቻቸውን ለማዳን ስደት ወቅቱ የሚጠይቀው መፍትሄ እንደሆን ቢረዱም እንዴት እና ወዴት የሚለው ጉዳይ ተጨማሪ እራስ ምታት ሆኖባቸው ነበር። ይህን የተረዳው ኒኮላስ ዊንተን አንዲት ደቂቃ እንኳ ሳያባክን ቀን የጨለመባቸውን ታጋች ስደተኞች የተፈራው ከባድ ወቅት እና የተደራጀ የናዚ ሰራዊት በስፍራው ከመድረሱ በፊት ወደ ሌላ ሃገር ለማሸጋገር ወሰነ። ይህን ውጥኑን ለማሳካት ታጋቾቹን ተቀብለው መጠለያ ለመስጠት ፍቃደኛ የሆኑ ሃገራትን ለማግኘት መዳከር ያዘ። ሃገራት ለነዚህ ቀን ለተደፋባቸው ሰዎች በራቸውን ክፍት ያደርጉ ዘንድ የተማፅኖ ደብዳቤ በዓለም ላይ ላሉ መንግስታት ፃፈ፡፡ ከስዊድን እና ከራሱ ሃገር እንግሊዝ በስተቀር ሁሉም ማለት ይቻላል ተማፅኖውን ሳይቀበሉ ቀሩ፡፡

ሰር ኒኮላስ ዊንተን የሁለቱን ሃገራት ይሁንታ ካገኘ በኋላ የእርሱን ጥረት የሚያግዙ ወላጅ እናቱ ጭምር የተካተቱበት ጥቂት በጎ-ፈቃደኞችን በቡድን አደራጀ፡፡ ለግድያ ታጭተው በር ከተቆለፈባቸው ሰዎች መሃል አምስት ሺህ ያህል ሕፃናትን መዝግቦ በመያዝ በሃገረ-እንግሊዝ ሕፃናቱን በሞግዚትነት የሚቀበሉ እንግሊዛዊያንን ካደራጃቸው በጎ-ፈቃደኞች ጋር ሆኖ ማሰሱን ተያያዘው። “ሞግዚት ወላጆች በአፋጣኝ ይፈለጋሉ!” የሚለውን የዊንተንን ማስታወቂያ የእንግሊዝ ጋዜጦች ጠቅለል አድርገው በማብራራት በየገፆቻቸው ላይ አወጡለት፡፡ ይህ በሆነ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ለተወሰኑ ሕፃናቶች ያህል ሞግዚቶችን ለማግኘት ቻለ። ይህን ተከትሎ ሕፃናቱ በአፋጣኝ ወደ እንግሊዝ የሚገቡበትን አስፈላጊ የባቡር እና የመርከብ ትራንስፖርት በማደራጀት ላይ ያሉትን የበጎ ፈቃደኞች ቡድን የተቀላቀለው ዊንተን ለዚህ ቅዱስ ስራ ማስፈፀሚያ የሚውል የገንዘብ መዋጮ በማድረግም ግንባር ቀደም ሆነ።

እኤአ መጋቢት 14 ቀን 1939ዓ/ም የመጀመሪያዎቹ ሃያ “የዊንተን ልጆች” የፕራግን ከተማ ለቀቁ፡፡ በቀጣዩ ቀን የሒትለር ወታደሮች ቼኮዝሎቫኪያን ሙሉ በሙሉ ወረሩ፡፡ ይሁን እንጂ ዊንተን እና የበጎ-ፈቃደኞቹ ቡድን ስራውን አላቆመም። ባገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ሕፃናቱን ከሒትለር ለማስመለጥ የሐሰት ሠነዶችን ጭምር እያዘጋጀ ተጠቀመ፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስከ ተጀመረበት መስከረም አንድ ቀን ድረስ ሕፃናቱን ከአደጋ ለመታደግ እየሰራ የነበረው ቡድን 669 ሕፃናትን በተለያዩ ስምንት ምድቦች በባቡር ከአገሪቱ ማውጣት ቻለ። የጦርነቱ መስፋፋት በቀጣይነት አንድም ሕፃን እንዳይወሰድ ናዚን ባያግዘው ኖሮ በመጨረሻው ሙከራ 250 የሚሆኑ ሕፃናትን መውሰድ በተቻለ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ነገር በናዚ ካምፖች ውስጥ ከቀሩት ሕፃናት ከስድስት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከናዚ ጋር ሲፋለም የነበረው የተባበረውን ኃይል ድል ለማየት አንዳቸውም እንኳ በሕይወት አልተረፉም፡፡ ወላጆቻቸውም ጭምር እንደዚያው፡፡

እኤአ በ2006ዓ/ም ዶ/ር ላውረንስ ሪድ እንግሊዝ ውስጥ ሜይድን ላንድ በሚገኘው የኒኮላስ ዊንተን መኖሪያ ቤት ተገኝቶ ሁሉም ሰው ትኩረት ነፍጎት የነበረውን አደጋ ለምን እንደተጋፈጠ በጠየቀው ጊዜ “ምክንያቱም መደረግ የነበረበት ነገር ስለሆነ ነው ፤ እኔ ልረዳቸው እንደምችል አስቤ ነበር ያንን ያደረኩት፡፡” ብሎ ነግሮታል፡፡ ዛሬ “የዊንተን ልጆች” ከነልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው ሲደማመሩ ቁጥራቸው ወደ ስድስት ሺህ ይደርሳል፡፡

ይህ የዊንተን አርአያነት የሚያስተምረው ምግባር ሕይወትን የሚያበለፅግ ብቻ ሳይሆን ሕይወትን የሚታደግ መሆኑን ጭምር ነው፡፡

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.