የኢኮኖሚ ዕድገት እና የፖሊሲዎች ሚና

ቬርኖን ስሚዝ (በኢኮኖሚክስ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ)

ቬርኖን ስሚዝ (በኢኮኖሚክስ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ)

የኢኮኖሚ ዕድገት በሕግ የበላይነት እና በግል ንብረት ባለቤትነት መብቶች ከሚደግፉ ነፃ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓቶች ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ኢኮኖሚያቸው በጠንካራ ማዕከላዊ እዝ ስር ወድቆ የነበሩ ሃገራትን በምናይበት ወቅት በነዚህ  ስፍራዎች ሁሉ ሸቀጦችን በስኬታማነት ማቅረብ እንዳልቻሉና እንዲያውም የመሰረታዊ ምግቦች ከፍተኛ እጥረት መታየቱን ታሪክ መዝግቦ የያዘው ሃቅ ነው። ሆኖም ግን ከቻይና እስከ ኒውዚላንድ እና አየርላንድ ድረስ መንግስታቶች በወሰዱት አንዳንድ የኢኮኖሚ ነፃነት ዕንቅፋቶችን የማስወገድ እርምጃ ለበርካቶች ተምሳሌት ይሆናል። እነዚህ አገራት ሰዎች ለራሳቸው የኢኮኖሚ መሻሻል እንዲተጉ በመፍቃድ ብቻ ጉልህ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት መቻላቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል፡፡

ቻይና በኢኮኖሚ ነፃነት አቅጣጫ ብዙ ተጉዛለች፡፡ ከዓመት በፊት ቻይናዊያን ንብረቶችን በባለቤትነት መያዝ ፣ መግዛት እና መሸጥ ይችሉ ዘንድ ሕገ – መንግስትዋን አሻሽላለች።  ለምን? እኔ እንዳየሁት ፣ ይህ ሕገ – መንግስታዊ ለውጥ በስፋት የተንሰራፋውን እና ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ያለውን መንግስታዊ ሙስናን እንዲሁም በልማት ውስጥ የፖለቲካውን ጣልቃ ገብነት ለማጥበብ የተቀመረ ስልት ነው፡፡የቻይናዊያን በህግ የተከለከሉ ንብረቶችን መሬትን ጨምሮ መሸጥ መለወጥ ያለማቆማቸው የቻይናን መንግስት ከገጠሙት ችግሮች መካከል ዋነኛው ነው። በዚህም የተነሳ በየአካባቢው ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት ይህን ሕግ እየጣሱ ከሚገኙት ሰዎች መካከል የተወሰኑትን ሰብስበው አናገሯቸው። በንግግራቸውም የንብረት ባለቤትነት መብቶችን ነፍጎ በማዕከላዊነት ለመምራት እና ለመቆጣጠር ሲባል በጣም አደገኛ ቢሮክራሲያዊ እና ለሙስና በር ከፋች የሆነ አስተዳደር በየአካባቢው መንሰራፋቱን ተገነዘቡ። ሌላው ከግምት ውስጥ የገባው የንብረት ባለቤትነት መብትን መገደብ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የማሄድ መሆኑ ነው። ከሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ጋር የሚጋጭ ህግ ለሰው ልጅ ማውጣት ቀለም እና ወረቀት ከማባከን ውጭ ጥቅም የለውም።

ምንም እንኳ ይህ ለውጥ ለነፃነት ሲባል ከሚደረጉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የተገኘ ውጤት ባይሆንም ነፃ ማህበረሰብን ለመፍጠር ለሚደረገው ጉዞ በሚገባ  ጥርጊያ መንገድ ሊከፍት የሚችል ነው፡፡ ፈጣን የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችም ተገኝተዋል፡፡ ይኸውም በአሁኑ ጊዜ ከ276 በላይ ግዙፍ ኩባንያዎች ከቻይና መንግስት ባገኙት የ50 አመት የመሬት ሊዝ ውል  ሐብታቸውን በቤይጂንግ አቅራቢያ አር እና ዲ ፓርክ (R & D park ) ላይ ኢንቨስት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

በአየርላንድ ያለው ክስተት በሐብት ለመበልፀግ የተፈጥሮ ሃብት መኖር እና ትልቅ ሀገር መሆን የግድ አስፈላጊ  እንዳልሆነ ያሳየናል፡፡  ባለፉት ዘመናት አየርላንዳዊያን ሀገራቸው ውስጥ የነበረውን አስከፊ ሕይወት በመሸሽ የተሰደዱ ሲሆን በዚህም አሜሪካ እና ታላቋ ብሪታንያ ተጠቃሚ ሆነዋል።  አየርላንድ ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት የሶስተኛው ዓለም አሁን ያለበት ዓይነት የድህነት ዝቅጠት ውስጥ ነበረች፡፡ ዛሬ በአውሮጳ ውስጥ ዋና ተዋናይ ስትሆን በዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ የቀድሞ ቅኝ ገዥ አለቃዋን አልፋት ሔዳለች፡፡ እንደ ዓለም ባንክ ስታቲስቲካዊ ዘገባ የአየርላንድ ጠቅላላ አመታዊ  ምርት (GDP) የዕድገት ፍጥነት በ1980ዎቹ ከነበረበት 3.2 ፐርሰንት በ1990ዎቹ ዓመታት ወደ 7.8 ፐርሰንት ማደግ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በነፍስ ወከፍ ገቢ አየርላንድ ከዓለም በስምንተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን እንግሊዝ ደግሞ በአስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ አየርላንድ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች ገንዘብ ፈሰስ (ኢንቨስት) ማድረግን ጨምሮ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶችን እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በማስፋፋት መልሶ ለማግኘት አዳጋች የሆነውን ስደተኛ ምሁራኖቿን ወደ ሀገራቸው የመመለስ የተሳካ ተሞክሮ አሳይታለች፡፡ የአየርላንድ ወጣቶች ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ናቸው፡፡

የእነዚህ ወጣቶች የመመለስ ምክንያት በእናት ሀገራቸው ላይ ያለውን የኢኮኖሚ ነፃነት ይበልጥ በማስፋፋት አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ነው፡፡ እነዚህ በዕውቀት የታነፁ ኢንተርፕርነሮች ቁሳዊ ሐብትን በመፈጠር ላይ ብቻ ሳይሆን ለሃገር ልጅም የ “ይቻላል” አርአያዎች ሆነው  ለሃገር እድገት እና ብልፅግና የራሳቸውን አሻራ አስቀምጠዋል። የአየርላንድ ታሪክ መጥፎ የመንግስት ፖሊሲዎችን በመቀየር የሀገሪቱን የምሁራን ፍልሰት ሙሉ በሙሉ መቀልበስ ወደሚያስችል አዲስ ኢኮኖሚያዊ የሥራ ዕድሎች እንዴት መለወጥ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው፡፡

(ይህ ጽሁፍ Human Betterment through Globalization በሚል ርዕስ ቬርኖን ስሚዝ እኤአ በ2005ዓ/ም የጻፈው ነው። ቬርኖን ስሚዝ ካሊፎርኒያ በሚገኘው ቻፕማን ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ ሲሆን እኤአ በ2002 የኖቤል ሽልማት አግኝቷል።ጽሁፉ ወደ አማርኛ የተመለሰው በአሳታሚው ፈቃድ ነው።)

***የጽሁፉን  የመጀመሪያ ክፍል በዚህኛው>> http://bit.ly/1fhalvO ሊንክ አማካይነት ያገኙታል።

Thank you for your comments

Please log in using one of these methods to post your comment:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.